>

ቻይናና ኢትዮጵያ፣ ጃፓንና ኢጣልያ፣ ሚኒቲ እና ዛኖኒ የግራዚያኒ የመርዝ-ጋዝ ሰበቦች! (አሰፋ ሀይሉ)

— ብዙዎች ጦርነት ህግ የለውም ይላሉ፡፡ ጦርነት ግን ህግ አለው፡፡ ጦር መሣሪያ ማነገብህና መተኮስህ ከህግ አያስጥልህም፡፡ የጦርነትም ህግ አለው፡፡ 
— የጓነ ብሔራዊ የማንነት ስሜት — (Overdose Nationalism) — በሁለመናቸው ‹‹ያለልክ›› የተጸናወታቸው — በራስ ወዳድነት — የግሪኩን ናርሲሰስን የሚያስንቁ — እነዚያ ብሔረተኛ ፋሺስቶች…!!
— ኢትዮጵያም — ልክ እንደቀደመችው የጉልበተኛ ተስፋፊዎች ሰለባ — ልክ እንደ ቻይና — ለመንግሥታቱ ማህበር — አቤቱታዋን አሰማች — አስጥሉኝ! አንድ በሉልኝ! ስትል ጮኸች፡፡ ሰሚ ግን አልነበራትም፡፡
— አስከፊው የመርዝ ጋዝም — ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ላይርከፈከፍ ተርከፈከፈ፡፡  ግራዚያኒ የፎከረው እውነቱን ነበረ፡፡ በሕዝባችን ታይቶ የማይታወቅ ክፉ መቅሰፍት ነበር ከሠማይ ያዘነበብን፡፡ ሃገሩን ያለ ሕዝባችን ተቃጠለ፡፡ ሰሚም፣ አፅናኝም አልነበረውም፡፡
— የመንግሥታቱ ማህበር — በዓለም ሠላምንም ሣያመጣ፣ የደህንነት ዋስትናንም ለአባላቱ ሳይሰጥ፣ እኩልነትንም በሕዝቦች መካከል ሳያሰፍን፣ የተፈራውንም 2ኛውን የዓለም ጦርነትም መግታት ተስኖት — ሩቅ አልሞ ተነስቶ — ባጨር ታጥቆ — ባጭር ተሰነካክሎ ቀረ፡፡
— ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ — ስናልፍ አፈር — ስናልፍ ኢትዮጵያ ነን!››፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ትኑር፡፡
…… ከጽሑፉ የተወሰደ፤ መልካም ንባብ ………
የዓለም ሉዓላዊ ሃገራት አባል በሆኑበት የመንግሥታቱ ድርጅት (League of Nations) ኢትዮጵያ — የዛሬን አያድርገውና — ከአፍሪካ ብቸኛዋ ሉዓላዊት የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሃገር ነበረች፡፡ ያ እውነታ ግን ለኢጣልያ ፋሺስቶች ፈጽሞ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ ደሞ እኮ ይህች — ለምን ከእኛ ጋር ‹‹እኩል-ቤት›› እንዲጫወቱ እንፈቅድላቸዋለን? የምትል ንቀት-አዘል የፋሺስቶች አመለካከት እኮ  የተንጸባረቀችው — በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ እንዳይመስለን!!! ነገሩ የእኛ ነገር ብቻ እኮ አይደለም — ሌሎችም ‹‹ምንም አያመጡም!›› በሚል — ከኢትዮጵያም አስቀድሞ — የፋሺስቶችን ገፈት የቀመሱ — የአንዲት የሉዓላዊት ሃገር ሕዝቦች ነበሩ፡፡ ቻይናውያን፡፡
በ1900ዎቹ የመጀመሪያ አጋማሽ — ቻይናዎቹ — ከእነርሱም ደግሞ በተለይ ጥቅጥቅ ባለ ሰፊ መስክ በገጠር ኑሮ የሚተዳደሩት የማንቹሪያ ቻይናዎች — ጃፓኖቹ ብሔረተኛ ኢምፔሪያሊስቶች የተናቁ ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በተለይ ደግሞ — የቻይና ማንቹሪያ ግዛት ሕዝቦች፡፡ የተናቁበት ምክንያቱስ? ምክንያቱ ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ያው ነው፡፡ ገጠራማ ኑሮን ስለሚገፉ፣ ፋብሪካን ስላላስፋፉ፣ በአየር ስላልበረሩ፣ የጦር መሣሪያን ስላላመረቱ፣ አቅመ-ደካማ ናቸው ተብሎ ስለሚታሰብ!! — ያሳዝናል፡፡
የወቅቱ የጃፓን ኢምፔሪያሊስቶች — እንዲህ ባዮች ነበሩ፡— እኛን ለሚያህል ታላቅ ሥልጡን ሕዝብ — እንዴት ተብሎ እፍኝ የማይሞላ ቁራጭ መሬት ሃገር ተብሎ ይሰጠናል? እና ለሌሎች ደካማ ሕዝቦች (ለእነቻይና እና ሌሎች ኢንዶ-ቻይና ሃገራት ህዝቦች) ለምን የተንጣለለ ታላቅ ግዛት ይሰጣቸዋል? የጃፓን መሬት ለጃፓናውያን ጠቦናል! መተንፈሻ እንፈልጋለን! ስለዚህ ሰፊ መሬት ወዳለበት ሃገርና ሕዝብ ሄደን… በክርናችን መብታችንን እያስገበርን — ሰፊ መሬት ነጥቀን፣ ሕዝቡን ቀጥቅጠን — የሚገባንን ያህል መሬት እንወስዳለን! ያኔ — ማንነታችን — በዓለም ሁሉ ታውቆ — የሚገባን ክብር ይቸረናል!!! ታላቁን የጃፓን ኃያል ማንነት — ለዓለም ማሳየት አለብን!! — የሚል ፋሺስታዊ አመለካከት ይዘው — በመላው ኢንዶ-ቻይና ወረራ ላይ በመሰማራት — ከቬትናም እስከ ኮሪያ — ቅኝ ግዛት ላይ የተሰማሩ — የጃፓን ተስፋፊ ብሔረተኛ ኢምፔሪያሊስቶች ነበሩ — ቻይናዎችን የናቋቸው፡፡
እና የጃፓኖቹ ብሔረተኛ ፋሺስቶች — በ1924 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ1931) — በማንቹሪያ በኩል ወደ ኮሪያ የዘረጋነውን የባቡር ድልድይ — ቻይናውያኑ በደማሚት አፈነዱብን ብለው — የማንቹሪያን አውራጃዎች አንድ በአንድ ወረሩ፡፡ ቻይናም ወዲያውኑ ለመንግሥታቱ ድርጅት ‹‹ወረራ ተፈጸመብኝ — አስቁሙልኝ!›› ብላ አመለከተች፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ጥርስ የሌለው አንበሣ ሆነ፡፡ ቃላት ብቻ፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት — እንግሊዞችን ወረራውን አጣሩ ብሎ ሾማቸው፡፡ እንግሊዞቹ ግን — የእስያ ግዛቶቻቸው በጃፓኖቹ እንዳይጠቁባቸው ስለፈሩ — የቻይናን ጩኸት — ጆሮ ዳባ ልበስ አሉ!! እጅግ ሰፊው የማንቹሪያ ግዛት — ወደ ቻይና ተመልሶ አይቀላቀልም፣ ራሱን የቻለ የማንቹሪያኖች ሃገር ይሁን፣ ጃፓኖችም ከማንቹሪያ ይውጡ! — ሲሉ ፍርዳቸውን ሰጡ እንግሊዞቹ፡፡
ያን ውሳኔ ሲሰሙ — ቻይናዎቹ ምን ሲደረግ! አሉ፡፡ ጃፓኖቹ ደግሞ አይናቸውን በጨው አጥበው — በጉልበታችን የያዝነውን እናንተ በእስኪሪፕቶ ልትነጥቁን ትሻላችሁ እንዴ?! ብለው — የመንግሥታቱን ማህበር — አባልነቱንም አንፈልግም ብለው — ከመንግሥታቱ ማህበር ከነአካቴው ረግጠው ወጡ!! የመንግሥታቱ ማህበር አባል ሃገራት — አንዱ አባል በጉልበተኛ ሃገር ጥቃት ቢደርስበት — በጋራ ሆ! ብለው አቅመ-ደካማውን ለመከላከል፣ ጉልበተኛውን ለማቀብና ድባቅ ለመምታት የጋራ ቃልኪዳን ቢኖራቸውም — ሁሉም ምንተዳዬ! ብሎ — የጃፓኖችን የኃይል ወረራ — ከንፈራቸውን እየመጠጡ — አሳለፉት!!!
ያ ከሆነ አራት ዓመት ሳይሞላው ደግሞ — ልክ የእስያውያኑ ጃፓኖችን የመሠለ የቁጭትና ብስጭት ስሜት የተጋባባቸው — የኢጣልያ ፋሺስቶች — ተመሣሣይ ሐተታ ዘ ምክንያት አንግበው — ወደ አፍሪካ ምስራቃዊ ግዛቶች አቀኑ፡፡ ጥቂቶችንም በኃይል ለመያዝ ቻሉ፡፡ እና የኢጣልያ ብሔረተኛ ፋሺስት አስገባሪዎች — በ1920ዎቹ ሲያቆጠቁጡ — ራሳቸውን ከእነፈረንሣይና እንግሊዝ ጋር አስተያዩ፡፡ ያም የራሳቸውን ኢምንትነት አሳያቸው፡፡ እናም ያን ፈጽሞ አንቀበልም! የሚል መፈክር ያነገቡ የአውሮፓ ትምክህተኞች ሆኑ፡፡
የኢጣልያኖቹ ብሔረተኛ ፋሺስቶች እንዲህ ባዮች ነበሩ፡— ‹‹እኛን ያህል ሥልጡን ህዝቦች — እንዴት በዚህች ሙዳ መሬት ላይ ኑሩ እንባላለን? የኛ ቄሣሮች እኮ — የዛሬን አያድርገውና — መላውን ዓለም ያስገበሩ — ዓለምን ያንበረከኩ ኃያላን ነበሩ! እኛ እኮ የአውሮፓ ሥልጣኔ — የማዕዘን ራስ ነን! እና — ስንቱ ‹‹ኋላ-ቀር›› ሕዝብ — ምንም የማይጠቀምበትን፣ የማይገባውን፣ ስንትና ስንት ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ግዛት ይዞ ቁጭ ብሎ — እንዴት ብንናቅ ነው —እኛ ታላቆቹ የኢጣልያ ሕዝቦች — ይህቺን በውሃ የተከበበች ብጥስጣሽ መሬት — እስከ ዕድሜ ልካችሁ ይዛችሁ ቅሩ የምንባለው?!!!›› የሚሉ ነበሩ — የጓነ ብሔራዊ የማንነት ስሜት — (Overdose Nationalism) — በሁለመናቸው ‹‹ያለልክ›› የተጸናወታቸው — በራስ ወዳድነት — የግሪኩን ናርሲሰስን የሚያስንቁ — እነዚያ ብሔረተኛ ፋሺስቶች!!
እንግዲህ — ልክ እንደ ጃፓን ብሔረተኛ ኢምፔሪያሊስቶች — እኛም ላይ — በኦጋዴን የወልወል የውሃ ጉድጓዶች አሳብረው — ወደ ኢትዮጵያ ሠርገው ሊገቡ የሞከሩትን — የኢጣልያ ሹምባሾችና ወታደሮች — ድንበሬን አላስነካም፣ አታልፏትም ሃገሬን፣ ቀኝ ኋላ ዙር፣ ውርድ ከራስ! ብሎ የተፋለማቸውን የኢትዮጵያ ድንበር ታጣቂ — በሐሰት — ኢትዮጵያ በግዛቴና በዜጎቼ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍታብኛለነች፣ አደጋ ጥላብኛለች፣ ካሣ ልትክሰኝ፣ ይቅርታ ልትጠይቀኝ፣ እና ለባንዲራዬ ልትሰግድ ይገባታል — በማለት — ተነሱብን — እነዚያ በአድዋ ሽንፈት ‹‹የቆሰለ-ነብር›› ሆነው አርባ ዓመት ሙሉ እየተንገበገቡ ካራቸውን ሲስሉ የከረሙት — ተረኛዎቹ የአውሮፓ ፋሺስት ወራሪዎች፡፡
እናም — በ1928 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ1935) — ጃፓን ማንቹሪያን በወረረች በ4ኛ ዓመቱ — ፋሺስት ኢጣልያ ደግሞ — የመንግሥታቱን ማህበር ቃልኪዳን በመጣስ — በጥቁር አፍሪካዊቷ ሉዓላዊት የመንግሥታቱ ድርጅት አባል ሃገር — በኢትዮጵያ ላይ — የወረራ ተግባሯን (Act of Aggression) ፈጸመች፡፡ ኢትዮጵያም — ልክ እንደቀደመችው የጉልበተኛ ተስፋፊዎች ሰለባ — ልክ እንደ ቻይና — ለመንግሥታቱ ማህበር — አቤቱታዋን አሰማች — አስጥሉኝ! አንድ በሉልኝ! ስትል ጮኸች፡፡ ሰሚ ግን አልነበራትም፡፡ ጭራሽ — ጃንሆይ ራሳቸው — በመንግሥታቱ ማህበር አዳራሽ ልመናቸውንና ንግግራቸውን እያሰሙ ባሉባት ደቂቃ እንኳ — ‹‹አንሰማህም! ሂድልን ከዚህ! አናዳምጥም!›› የሚሉና ሌሎች በዘረኝነት የተሞሉ ዘለፋዎችንና አሳፋሪ ሁካታዎችን እያነሱባቸው ነበር — ፋሺስቶችና የፋሺስቶቹ ደጋፊ ሃገራት ተወካዮች፡፡
በመጨረሻም የኢጣልያ ፋሺስት መንግሥት — የቀደሙትን የጃፓን ኮሎኒያሊስቶች አርአያ በመከተል — እንዲያውም ወጥቼበታለሁ! የለሁበትም! አያገባችሁም! ብሎ — ከብሔረተኛ ሶሻሊስት (ከናዚ) ጀርመኒ መንግሥት ጋር — ከመንግሥታቱ ማህበር — ውልቅ ብሎ ወጣ!! የሚገርመው ግን — ያ የመንግሥታቱ ማህበር —አሁንም — የኃያላኑ ጥቅም አልተነካም ብሎ በማመን — ለአቅመ-ደካማዋ የወረራ ሰለባ ኢትዮጵያ — የሰጠው ምላሽ — ከከንፈር መምጠጥ ያልተናነሰ — ባዶ ወቀሳ ብቻ ነበር — መስሚያ የሌላቸውን የኢጣልያ ፋሺስቶች — ጥርስ የሌለው አንበሣ ሲወቅሳቸው — ምን ሊሰሙት? ምንስ ውጤት ሊያመጣ? — ምንም!!! ምንም ውጤት አላመጣም፡፡ ያሳዝናል፡፡ የመንግሥታቱ ማህበር ቻይናን ከጃፓን ብሔረተኛ ወራሪዎች አላስጣለም፡፡ ያኔ የመንግሥታቱ ማህበር ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ብሔረተኛ ወራሪዎች አላስጣለም አሁንም፡፡ ያሳዝናል ታሪክ ራሱን ሲደግም፡፡
ቸልተኝነት፣ ኢ-እኩልነት፣ እና አቅመ-ቢስነት ሲደራረብበት ግን — አንዱ ሃገር ተነስቶ እንዳሻው በሌላው ሃገር ላይ ኃይል እንዳይጠቀም፣ ከተጠቀመ ደግሞ ሁሉም የመንግሥታቱ ማህበር አባል በፅኑ እንዲያወግዘው፣ አውግዞም የማያዳግም የተባበረ እርምጃ እንዲወስድበት ለማስቻል ተብሎ — በመንግሥታቱ ቃልኪዳን ተገብቶ በ1ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት — ዳግመኛ የዓለም ጦርነት — ህግ በማይገዛው ጉልበተኛ ሃገር ቆስቋሽነት እንዳይነሳ ሲባል — ለዓለም ሠላም የተቋቋመው — ይህ የመንግሥታቱ ማህበር — በመጀመሪያ አቅመ-ቢስ የሆኑት ሃገራት በጉልበተኞቹ እየተበሉ አይቶ እንዳላየ ሲያልፍ — ኋላ ላይ ደግሞ — ጉልበተኞች ጉልበተኞችን እየቀደሙ በጉልበት ሲሰለቅጡ ለማስጣል ኃይልና ብርታት ርቆት ሲገኝ — የመንግሥታቱ ማህበር — በዓለም ሠላምንም ሣያመጣ፣ የደህንነት ዋስትናንም ለአባላቱ ሳይሰጥ፣ እኩልነትንም በሕዝቦች መካከል ሳያሰፍን፣ የተፈራውንም 2ኛውን የዓለም ጦርነትም መግታት ተስኖት — ሩቅ አልሞ ተነስቶ — ባጨር ታጥቆ — ባጭር ተሰነካክሎ ቀረ፡፡
ከጦርነቱ በኋላ — ራሳቸው በስልጣኔ ስም ባርነትን ለማስፋፋት ዓላማ የመጡትን ኢጣልያኖች — የሠለጠነው ዓለም ያለማውገዙን በትዝብት በማንሳት — ክቡር ደጃዝማች ከበደ ሚካኤል — ‹‹ኢትዮጵያና ምዕራባዊ ሥልጣኔ›› በሚል ርዕስ — በሶስት ቋንቋዎች ባሳተሙት መጽሐፋቸው — እንዲህ ያላሉ፡-
‹‹ኢትዮጵያ በኢጣልያ ስትወረር.. ለሌሎች የተገባው ጥበቃ አያስፈልጋትም፣
በኢጣልያ ስር ብትተዳደር ይበጃታል፣ ብለው ማሰባቸው እንግዲህ እኛ እንደ
ኢጣልያኖች ትልልቅ ፋብሪካዎችን ገንብተን በቀን በርካታ ቁጥር ያላቸውን
አውሮፕላኖች ካላመረቱ በቀር መብትና ክብር እንደሚገባው ሰብዓዊ ፍጡር
አንቆጥራቸውም ከሚል የፀረ-እኩልነት ሃሳብ የመነጨ ካልሆነ በቀር እኛ ለእነርሱ
የተገባው የማይገባን ምን ሰበብ ይገኝ ኖሯል?››
እውነት ነው ምንም ሰበብ የለም፡፡ ሰበቡ ጦርነትን መብት፣ ጦረኝነትን የበላይነት፣ ጉልበትን ሥልጣኔ አድርጎ የመቁጠር እውነታ ብቻ ነው፡፡ የመንግሥታቱ ማህበርም ነገር — ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ – ባረም ይመለሱ›› ሆኖበት—  ጨዋታው ፈረሰ — ዳቦው ተቆረሰ፡፡ በዓለምም — ህግ የሌለበት — ጉልበተኞች በጉልበታቸው ህልውናቸውን የሚያቆዩበት — ለራስህ ራስህ ታጥቀህ በተጠንቀቅ ቆመህ ራስህን የምትጠብቅበት — በግልህ ደመኛህን የምታደባይበት — መዋጋት መብትህ የሆነበት — የዱር ህግ — በዓለሙ ሁሉ ሰፈነ፡፡ እና ምን ተረፈ? — ጦርነት ብቻ፡፡ ጦርነት እና ጦርነት — ብቻ!!!!
ብዙዎች ጦርነት ህግ የለውም ይላሉ፡፡ ጦርነት ግን ህግ አለው፡፡ ጦር መሣሪያ ማነገብህና መተኮስህ ከህግ አያስጥልህም፡፡ የጦርነትም ህግ አለው፡፡ Laws of Armed Conflict፡፡ ህጉ መኖሩን አለ፡፡ ግን ብዙዎች የሚስማሙት — ህጉ ጥርስ አልባ መሆኑን ነው፡፡ ለምሳሌ በጦርነት ወቅት — ባላጋራህን የቱንም ያህል ብትጠላው፣ የቱንም ያህል ጉልበትህ እየላመ ቢመጣብህ — ለማሸነፍ ስትል — የተከለከሉ የመርዝ ጋዞችን — በጠላትህ ህዝብ ላይ አትዘራም!! ያ አንዱ የጦርነት ህግ ነው፡፡ የ1916ቱ የጄኔቫ የኬሚካል መሣሪያዎችን በጦርነት ያለማዋል ስምምነት ህግ፡፡ ህግ የይስሙላ ከሆነስ? ህግማ የይስሙላ ሲሆን — ያልተተገበረ ህግ — እንደሌለ ይቆጠራል፡፡ ህግ አለ፡፡ ግን ህግ የለም፡፡ ያ ነው የሆነው በጊዜው፡፡
በወቅቱ ኢጣልያኖች ‹‹ሙስታርድ ጋዝ›› የተባለውን አደገኛ ጅምላ ጨራሽ ኬሚካል መርዝ በከፍተኛ ቁጥር አምርተው አከማቹ፡፡ ክፋቱ ግን ያኔ ማከማቸት ገና አልተከለከለም፡፡ መጠቀም ነው የተከለከለው፡፡ እግዚያሃር ያሣይህ፡፡ እስክትጠቀምበት እኮ — ባላጋሮችህም ሆኑ ወዳጆችህ — እጃቸውን አጣምረው — አፍጠው ያዩሃል፣ በዓይነቁራኛ — እንደማለት እኮ ነው የሚመስለው፡፡ የኢጣልያ ፋሺስቶችም — መሬት ጠበበን አይደል ያሉት? እና ታዲያ መሬት ከፈለጉ — መሬቱ ላይ የሰፈረውን ህዝብ — ለባርነት የሚበቃቸውን ትተው — ጥርግ አርገው መጨረስ ሲያስቡ ይመስላል — የሙስታርድ መርዝ ጋዝ አምርተው ያከማቹት፡፡ ማከማቸትን የያኔው የጄኔቫ ዓለማቀፍ ስምምነት አልከለከለማ፡፡ ግን… ግን…. ካከማቹ በኋላስ?
ካከማቹማ በኋላ… ለመጠቀም… ሰበብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የመርዝ ጋዝ ስለረጨችብን — እኛም ረጨንባት›› የሚል — የመረጫጨት ምክንያት አጡ፡፡ ምክንቱም ያኔ እኛ — በእጃችን የነበረ — ከእንቆቆና ድኝ፣ ከከርቤና ቀበሪቾ የበለጠ — ጠላትን እግሩን ቄጠማ፣ ፀጉሩን ገለባ የምናደርግበት — ሌላ የተለየ — በሰው ላይ የምንበትነውም ሆነ — በምድር የምንዘራው አንዳችም አደገኛ ጭስ አልነበረንምና፡፡ እውነቱ ያ ነው፡፡ ያን ሁሉም ያውቃል፡፡ ስለዚህ ኢጣልያኖች ሌላ ምክንያት — ሌላ ሰበብ — ይፈልጉ ጀመር — የመርዝ ጢሳቸውን በኢትዮጵያውያን ላይ ለመንዛት፡፡ ያን ሰበብ ሲጠባበቁ — በድንገት — ሴጦ — ሠይጣን — አንድ መልካም ሰበብ የሚሆን — አንድ ጥሩ መርዶ አሰማቸው፡፡
ያ ሰበብ — የሁለት የኢጣልያ የውጊያ አውሮፕላን አብራሪዎች — የቲቶ ሚኒቲ እና የሲልቪዮ ዛኖኒ —  በኢትዮጵያውያን አርበኞች መገደል ነበረ፡፡ ዕለቷ — ወራሪዎቹ የኢጣልያ ፋሺስቶች — አዲሱ ዓመት — መልካም የወረራ ዓመት እንዲሆንላቸው — ‹‹መሬቱን ጨሌ፣ ሰዉን በሬ›› እንዲያደርግላቸው — ጭቦ የማያውቅ የመሠላቸውን የራሳቸውን እግዜር የሚማጠኑባት — ዓመታቸውን ‹‹ሀ›› ብለው የሚባርኩባት ዕለት ነበረች፡፡
በዚያች ዕለት ነው — በኢትዮጵያውያን ላይ ቦምብን ለማዝነብ ወደኢትዮጵያ የመጡትን —ሁለት ወጣት የኢጣልያ ወጣት አብራሪዎች አስከሬን ሳጥኖች — በነጭ የከፈን ጨርቅ ሸፍነው የተሸከሙ — የወቅቱን የኢጣልያን ቁምጣ የወታደር ዩኒፎርምና መለዮ የለበሱ — የኢጣልያ ወራሪ ሰራዊት አባላትን ከፊት ለፊቱ አስከትቶ — በልዑላዊ እርጋታና በቁጭት — ለዓለም የሚሠራጩ የፕሮፓጋንዳ ፎቶግራፎችን ሲነሣ የነበረው የፋሺስት ኢጣልያ የጦር ጄነራል — ጄነራል ሮዶልፎ ግራዚያኒ — እስካሁን ምህረትንና ትዕግስትን ስናሳይ ቆይተናል — ከአሁን በኋላ ግን — በእነዚህ ትዕግስታችንን እንደፍርሃት በቆጠሩት ኢትዮጵያውያን ላይ — አይተውት የማያውቁትን የሠማይ መቅሰፍት — እናወርድባቸዋለን — ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን — ከፊታችን ወድቀው ምህረታችንን የሚለምኑበት ሰዓት እስከሚመጣ ድረስ!!! — እያለ ይፎክር ነበር፡፡
ፉከራው የሙስታርድ ጋዝ — ሰበቡ ደግሞ — የቲቶ ሚኒቲ እና የሲልቪዮ ዛኖኒ — ሞት፡፡ ቲቶ ሚኒቲ እና ሲልቪዮ ዛኖኒ — ዳግም ላይመለሱ ሞቱ፡፡ አስከፊው የመርዝ ጋዝም — ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ላይርከፈከፍ ተርከፈከፈ፡፡  ግራዚያኒ የፎከረው እውነቱን ነበረ፡፡ በሕዝባችን ታይቶ የማይታወቅ ክፉ መቅሰፍት ነበር ከሠማይ ያዘነበብን፡፡ ሃገሩን ያለ ሕዝባችን ተቃጠለ፡፡ ሰሚም፣ አፅናኝም አልነበረውም፡፡ የኢጣልያ ፋሺስቶች በአክራሪ ብሔረተኛ ስሜት ተነሣሥተው — የወረሩትን ምስኪን አቅመ-ቢስ ህዝብ — በመርዝ ጋዝ ፈጁት፡፡ ቆዳ ሙልጭ ብሎ ከስጋ ተለዬ፡፡ ዓይኖች ተለበለቡ፡፡ የሰው አካል እንደብጉንጅ ፈነዳዳ፡፡ በመርዝ ተቦጫጨቀ፡፡ ፎቶዎቹ እስካሁን አሉ፡፡ ሃሳቡን እንጂ ፎቶዎቹን ማካፈል ምን ሊበጅ? ብለን ተውነው፡፡ መተው ነው፡፡ እነርሱ 40 ዓመት ሙሉ ስላልተዉ ነው ያን ዓይነት መቅሰፍት ሰንቀው የመጡት፡፡ እኛም እንዲያ ያልከፋነው ስለተውናቸው ይመስለኛል፡፡ “Forgive and Forget”፡፡ ይቅር ማለትና መርሣት፡፡ አበቃ፡፡
‹‹ለቀን የራሱ ክፋት ይበቃዋል››፡፡ ያለፈውን ቀን ክፋት — በዛሬው ቀናችን ላይ ዘርግፈን —የዛሬውን ቀናችንን — ከከፋው በላይ — ለምን እናከፋዋለን?? ብዬ ሣስብ — የጻፍኩትን ሁሉ ላጠፋው ወሰንኩ፡፡ እና . . . ላጲስ አማረኝ፡፡ ላጲስ፡፡ የእስኪሪፕቶ ላጲስ፡፡ ሁሉንም እንዳናስታውስ፣ ሁሉንም እንዳንረሳ — የአዕምሯችንን መጻፊያና ማጥፊያ አመጣጥኖ ለሰው ልጆች ለሰጠ ጠቢብ አምላክ — ክብር ምስጋና ይሁንለት — ብለን ከደንን መዝገባችንን፡፡ በዚህች ሃገር ለሞቱት ሁሉ ነፍሳቸውን እንዲምር፣ ለህያዋኑ ሁሉ በረከትን እንዲያበዛልን፣ ምህረትና ቸርነቱን እንዳያጓድልብን — ለፈጣሪ አምላካችን — ፀሎታችንን አሳረግን፡፡
‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ — ስናልፍ አፈር — ስናልፍ ኢትዮጵያ ነን!››፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያችን ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ቻው፡፡
ፎቶግራፎቹ (ለባለቤቶቹና በለጋስነት ላካፈሉን ከልብ ከመነጨ ምስጋና ጋር)፡-
1) Le_salme_di_Tito_Minniti_e_Silvio_Zannoni – The recovery of the bodies of Tito Minniti and Silvio Zannoni. The killing of the two airmen was the pretext for the use of gas – January 1, 1935,
2) inizio1 – graziani mass in ethiopia,
3) Il Duce Benito Mussolini, and
4) Abune Petros Memorial – North Star saved to Africa.
Filed in: Amharic