>
5:13 pm - Monday April 19, 1897

"እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይያዝም!" (ታደለ ጥበቡ)

ጠቅላያችን አብይ አህመድ የአፍ ወለምታ ይሁን አስበዎበት የወልቃይትን ጥያቄ የመብራትና የውሐ ነው በማለት ማሳረጊያውን ነግረውናል።ብዙዎችንም  አብይ አህመድን መጠራጠር ጀምረዋል።
ለመሆኑ የወልቃይት ጥያቄ የመብራትና የውሐ ነውን? ከሚለው ለመነሳት ትንሽ ታሪካዊ ዳሰሳ ማድረጉ ሳያስፈልግ አይቀርም።
ወልቃይት በትግራዋይ ሥር እንዳልነበረች ብዙ ጽሐፍት የተስማሙበት የአካባቢው ህዝብ ያረጋገጠው ሐገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።በ14ኛው መክዘ በአጼ ዘርዓያዕቆብ  ዘመነ መንግሥት ከተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ “ዜና አክሱም” በማጣቀስ “ኢትዮጵያ መሬቱ፤ህዝቧ፤ታሪክና ባህል” በሚለው መጽሐፉ የተነተነው ዮሐንስ መኮንን  የትግራይ ወሰን “ተምቤን፣ሽሬ፣ሰራይ፣ሀማሴን፣ቡር፣ሳማ፣አጋሜ፣አምባ ሰነይት፣ገራልታ፣እንደርታ፣ሰሃርትና አበርገሌ”መሆናቸውን በዝርዝር ያስረዳል።
በተመሳሳይ መልኩ John R.short  የተባለው ሰው በ15ኛው መክዘ “the world through maps: a history of cartography” በተሰኘ መጽሐፉ በገጽ 352 ወልቃይትና ጠገዴ የአማራ ክልል ርስቶች እንደነበሩ በማያሻማ መልኩ አስቀምጦታል።
ሌላኘው የፖርቹጋል ሰው ኤሌዛቤል ፊሉል በ1634 አ.ም በጻፈው “tractatus tres historico-Geographical account of tigray,Ethiopia (athiopistische forschungen) 1934″በተሰኘ መጽሐፉ ምእራፍ አራት ላይ የትግራዋይ ወሰን ከተከዜ ማዶ ተሻግሮ እንደማያውቅ ይልቁንስ ወልቃይት፣ጠገዴና ሌሎችም በበጌምድር ክፍለሀገር ስር እንደነበሩ  ያስረዳል።
“Among all the kingdoms that the emperor of Ethiopia possesses today one of the greatest if not the greatest and the most important is the kingdom the. Tigre.from north to south that is from the limits of the hamasen to enderta,it covers an areas of from the east,which one hundred leagues (3.2miles) and from the east,which is besides dancali,located at the entrance to the red sea to the southern end of the red sea,to the west bounded by the tekezze river beside the semen,it covers an area of similar size,so that the kingdom has an early circular shape” ሲል በማለት አስቀምጧል።
በዘመነ መሳፍንት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ስኮትላንዳዊው ጀምስ ብሩስም travel to discover source of the Nile volume 3 በገጽ 582 ላይ የአማራና የትግራዋይ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ወሰን ተከዜ መሆኑን አረጋግጧል።
“Tigre is bounded by the teritory of the bahiren egash that is by the river mereb on the east and taccazze upon the west.it is about on hundred and twenty miles broad from E.to W.and two hundred from N.to S.”
ጀምስ ብሩስ በዚሁ መጽሐፉ ገጽ 10 ላይ “geographical division of Abyssinia in to province”በሚለው አንቀጹ
“The first division is called tigre,between red sea and the river tekeze.between that river(tekeze) and the Nile west wards where it bounds the oromo,it is called Amahara” ካለ በኋላ ወረድ ብሎ
“Tekezze is the natural boundary between tigre and Amhara” ሲል እቅጩን አስቀምጦታል።
በዘመነ አፄ ቴዎድሮስም ወልቃይትና ጠገዴ የአማራ ክልል ጥሬ ሀብቶች እንጂ  በትግራዋይ ስር አልነበሩም።
የአፄ ቴዎድሮስ  ልእለ ሀያልነት በምድረ አውሮፓ ወሬው መናፈስ ሲጀምር    የእንግሊዝ መንግስት ፓርላማና የጸጥታው ሀይል ኢትዮጵያን በሚገባ ለማወቅ ጥናት እንዲደረግ ትእዛዝ  ሰጥቶ ነበር።የእንግሊዙ topographical and statistical department of the war office A.C.cook በተባለ እንግሊዛዊ ኮሎነል አማካኝነት ስለ ኢትዮጵያ ከ15ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ በተለያዩ አውሮፓውያን የተጻፉ መጻሕፍትን ባንድ ላይ እንዲጠረዝ አደረጉ።ይሄ ጥናታዊ ሰነድ  በ1867 እ.ኤ.አ  በእንግሊዝ ንግስት ጥያቄ  ለ”house of common lower house ይውል ዘንድ ሲታተም   የወቅቱ የኢትዮጵያ ዝርዝር ጉዳይ ስለተካተተ   የወልቃይት ና ጠገዴም ጉዳይ  ተዳሶበታል።
” the provinces of Amhara are is simen,weldiba,wolkait,wogera, chilga,kuara,belesa,fogerra,damot,Gojjam,begemidir,beshilo…..waldiba situated to the Nw of simen between the tekeze and the angereb,extends as far as the junction of the two rivers.welkaitis to the west of waldiba it is interested through its whole length by the two river tekuar and guang.it is more wooded than waldiba……ይላል(routes in Abyssinia (printed in 1867G.C) በዚህ ትንታኔ ውስጥ እንደምትመለከቱት ዋልድባ፣ወልቃይት በአማራ ክልል ውስጥ ናቸው።የትግራዋይ እና የአማራ ተፈጥሮአዊና ታሪካዊ ወሰንም ተከዜ ነው።
በገፅ 188 ላይ እንደገና በወቅቱ የነበረውንም የትግራይን ክፍለሀገር ድንበር እና ግዛት (ሲተረጎም) እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።
“የትግራይ ወሰን በምዕራብ ሽሬ፣በምዕራብ ደቡብ ተምቤን እና አዴት፣በደቡብ ገርአልታ፣በምስራቅ አጋሜ፣በሰሜን መረብና በለሳ ናቸው” ሲል ይገልጸዋል።ስለዚህ በአፄ ቴውድሮስ ዘመን በ18ኛው ክፍለዘመንም ወልቃይትና ጠገዴ በትግራይዋይ ስር እንዳልነበሩ እንረዳለን ማለት ነው።
አይደለም በአጼ ቴዎድሮስ በአፄ ዮሐንስ 4ኛም  ወልቃይት ጠገዴ በተአምር የትግራዋይ ግዛቶች አልነበሩም። እውቁ ፈረንሳዊ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰር ኤሊስ ሬክለስ (በዩንቨርስቲ ኦፍ ብረስልስ የኮምፓራቲቭ ጂኦግራፊ ፕሮፌሰርና የዲፓርትመንቱ ሀላፊ የነበሩ ናቸው) በ 1880 ጀምሮ በተጻፈው “the earth and its inhabitants”በሚለው መጽሐፋቸው ክፍል አራት በገጽ 443 ላይ የሰሜን እና የምስራቅ አፍርካን የወቅቱን ጂኦግራፊ በዝርዝር ይተነትናል።በአጼ ዮሐንስ ዘመን የነበረውንም የኢትዮያን ክፍላተ ሀገራት በዝርዝር ቁልጭ አድርጎ እንዲህ ጽፎታል ።
“the Amhara government provinces are dembia,chelga,yantang era,dagossa,kuarra,begemidir,guna,saint,wadla,delanta,woggera,simen,tselemt,armachiho,tsegede,kolla wogerra,waldiba and wolkait” ሲል አጼ ዮሃንስ ንጉስ በነበረበት ዘመን በ1880ወቹ ወልቃይት፣ጠለምት፣ዋልድባና አላማጣ በትግራይ ስር አልነበሩም።ይሄንን እወነታም በኃይለስላሴ የትግራይ ገዥ የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም የትግራይ ምዕራባዊ ድንበር መቼም ቢሆን ተከዜ እንደነበረ አረጋግጠዋል።
ጣሊያን ኢትየጵያን በወረረች ጊዜ አማራው አልበገርላት ሲል  በቋንቋና በዘር በትና  ለመግዛት እቅድ አውጥታ ነበር። የዚህ ተዋናይ የነበረው  baron roman prochazka አቢሲንያ ዘ-ፓውደር ባረል በሚል መጽሐፍ ላይ እንዳስቀመጠው ኢትየጵያን ለመግዛት ህውሐት ያስቀጠለችውን ዘርና የቋንቋ  መሰረት ባደረገ ኢትዮጵያን በ5 እንደከፈሏት ገልጿል።እነርሱም:-
አማራ፣ኤርትራ/ትግሬ/፣ሐረር፣ኦሮሞ- ሲዳማ፣ሸዋና ሶማሌ ብለው  ከፈሏት ።በዚህ የቋንቋ ሽንሸና መሰረት እንኳን ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይዋይ  አልተካተቱም።በጎንደር ስር ነበሩ።ጣልያኖች በ1928አ.ም የተሰራው ካርታም ሁነኛ ማስረጃ ነው።
በአፓርታይዱ ደርግም እ.ኤ.አ 1990 ህውሐት አዲስአበባን ከመያዙ አንድ አመት በፊት በካምብሪጅ ዩንቨርስቲ በአፍርካ ጉዳዮች ላይ እና የኢትዮጵያን ታሪክና ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉት ፕሮፌሰር ክሪስቶፈር ክላፓ ስለወልቃይትና ጠገዴ እንዲህ ሲል ፅፈዋል።
“the area concerned welkait-tsegede separated from tigray by impressive natural barrier of setit tekezz river has never been governed as part of tigray at any period in the past,but has come under Gonder and semen”(Christopher clapham: transformation and continuity in revolutirevolutionary Ethiopia (cambridge:cambridge university press 1988 ገፅ 259)
ስለዚህ በጣሊያን ጊዜም የትግራይ ወሰን በደቡብ እንዳምሆኒ፣በደቡብ ምስራቅ አበርገሌ፣በምዕራበ ሽሬና አዲያቦ ነበሩ እንጂ ወልቃይት፣ጠገዴ፣ዋጃ ኮረም በትግራይ ስር አልነበሩም።
/ጥቆማ:-የበለጠ ለመረዳት በኔ የተጻፈውን ደም ሲፈስ ደም ይፈላል(ሰቆቃው አማራ) የሚለውን መጽሐፍ ከገጽ 11-51 ይመልከቱ።/
ውነታው ከላይ የገጥነው ቢሆንም ህውሐት ጣሊያን የተገበረችውን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ መግዛትን በአለበት አስቀጥለዋለች በዚህ መሰረት ወልቃይት ጨምሮ ከአማራ ጥቂት የማይበሉ መሬቶችን በጉልበት ነጥቀው ወስደዋል።
ይሄም ለወልቃይት ህዝብ የመከራ ጊዜን አብሮ ያበሰረ ነበረ።ወደ ትግራዋይ ከተጠቃለሉ በኋላ የወልቃይት ማህበረሰብ
-ልጆቻቸው በቋንቋቸው እንዳይማሩና በግድ በትግርኛ እንዲማሩ ተገደዋል
-የአማራን ባህል ቀይረው የትግራዋይን ባህል እንዲቀበሉ ጫና ተደርጎባቸዋል
-የአካባቢው ጥንታዊ የሀገርና የአካባቢው ስሞች ተቀይረዋል።ለምሳሌ:-
1.ክባቦ የነበረው ህይወት
2-እምባጋላ የነበረው ማይጨው
3-ወይናት የነበረው ደደቢት
4-ማይሌሌ የነበረው ኃይሎም
5-ኩርባ ሎሚ የነበረው ናይሎሚ
6-ባናት የነበረው ህይዎት እርሻ መካናይዜሽን…ወዘተ እየተባሉ ተቀይረዋል።
-ወልቃይት-አማራዎች በትግራይ መስርያ ቤት 5% ከመቶው ብቻ ይቀጠራሉ
-ወንዶችን እያሰሩ የአካባቢው ባለሥልጣኖች ሴት ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በግድ ደፍረዋል
– በማንኛውም መድረክ እንዳይናገሩ ድምጻቸው ተፍኗል ከተናገሩም የግንቦት ሰባት አባል ፣የደርግ ናፋቂ እየተባሉ እንደመሸማቀቁ ሆነዋል።
-ትግራይ አይደለንም ያሉ ሁሉ ንብረታቸው እየተነጠቁ በደህንነት እየታፈኑ የደረሱበት ሳይታወቅ የውሐ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።በሚፈናቀሉበት ቦታ ላይ ህውሃት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የትግራዋይ ህዝቦችን አስፍሮበታል።
ይሄን ሲያደርጉ የወልቃይት-አማራ ሀብት ንብረት እየተወረሱ  ነው።ለዚህም ይረዳ ዘንድ የሰብአዊ መብት ጉባኤ 141ኛ መግለጫ መመልከቱ በቂ ማስረጃ ነው።አልያ በደም ሲፈስ ደም ይፈላል መጽሐፍ ውስጥ ከገጽ 119-162 ያለውን ይመልከቱ።
የወልቃይት አማራ የማንነት ጥያቄ በማንሳቱ ተሰዷል፣ተፈናቅሏል፣ተፍኖ ታስሯል፣ተገድሏል።የግድያውን ቁጥር ለማወቅ ቢያስቸግርም በተደረገው መለስተኛ ጥናት ከ300 በላይ ወልቃይት አማራዎች ተገድለዋል።ብዙዎች የሄዱበት የውሐ ሽታ ሆነው ቀርተዋል።ይሄን ውነታ ለመረዳት በ1984,94 እና 2007 ላይ የተደረገውን የህዝብ ቆጠራ እንመልከት
በ19764 አ.ም በደርግ ጊዜ በተደረገው የህዝብ ቆጠራ  የወልቃይት አማራ ህዝብ ብዛት
ወንድ:-40,689
ሴት:-42,355 ድምር 83,044 ነበረ
በ1994  አ.ም ማለትም ወያኔ ስልጣኑን ከአደላደለ በኋላ የህዝቡ ቁጥር ከ83,044 አሽቆልቁሎ 48,690 ቀንሷል።ይሄም ማለት ህውሐት 34,354 የወልቃይ አማራን ህዝብ ከቦታው አፈናቅሏል ማለት ነው።በአንጻሩ ከ13 አመታት በኋላ የ2007 አ.ም ቆጠራ እንደሚያመላክተው ከ48,690 የነበረው ህዝብ ህውሐት እያመጣ ከአሰፈረበት በኋላ ወደ 92,167 አድጓል።በጣም የሚያስገረም የህዝብ ቁጥር ተጨምሯል ማለት ነው።
ለምሳሌ ሰመጉ በአወጣው 141ኛ መግለጫ ብቻ በ12/07/2008 ብቻ ከ137 በላይ ሰዎች ቦታውን ለቀው ተሰደዋል።ህገወጥ ግድያው እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።
የሰመጉን 141ኛ መግለጫ በአጭሩ ሲቀመጥ
1-በጉልበት  መሳርያቸውን የተነጠቁ 8
2-   ንብረታቸውን የተነጠቁ 15
3-የአካባቢው ጥንታው ስም ተቀይሮ በአዲስ የተተካው 12
4-ታፍነው የተወሰዱት 47
5-በህገወጥ መንገድ የታሰሩት 17
6-የተፈናቀሉ 137
7-የተገደሉ 34 ብሎ አስቀምጧል።
ከላይ የጠቀስነውን ቁጥር  ከነስማቸው እና የተፈጸመባቸውን ግፍ በዝርዝር መግለጫው ያስረዳል።ውድ አንባቢያን ይሄ የ2008 141ኛ መግለጫ ላይ የተጠቀሱት ብቻ ናቸው።ሌላውን አያካትትም።
ውነታው ይሄ ከሆነ ጠቅላያችን አብይ አህመድ የወልቃይት ጥያቄ የመብራትና የውሐ ነው ማለቱ ድፍረትና ንቀትም ጭምር ነው።ነገሩን ወደ ዲያስፖራው መጎተት የሚያዛልቅ አይመስለኝም።የዲያስፖራውን እንተወውና በቅርቡ እንኳ 88 የኮሚቴ አባላት የ2253 የወልቃይት ማህበረሰብ ፊርማ የተሰባሰበበትን ደብዳቤ በጥር25/2008 አ.ም ለጠ/ሚኒስትሩ፣ለምክትል ጠ/ሚ፣ለሚኒስትሮች ም/ቤት፣ለኢፌዴሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ለፍትህ ሚኒስቴር፣ለኢሀዴግ ጽ/ቤት፣ለኢፌዴሪ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምና ለኢፌዴሪ ስብአዊ መብት ኮሚሽንና ለሌሎችም በአስገቡት ደብዳቤ የወልቃይት-አማራ ህዝብ ከትግራዋይ ጋር  በታሪክ፣በመልክዓምድር አቀማመጥ፣በባህልና በቋንቋ ከትግራዋይ ጋር እንደማይገናኙ በመግለጽ  የማንነት ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
ውነታው ይሄው ብቻ ነው።ስህተቱ እባብ ለምዷል ተብሎ ኪሳችን ውስጥ ማስገባታችን ነው።ኢሀዴግ በጠቅላያችን አብይ አህመድ “ኢትዮጵያ”በሚል ኑዛዜ ሁሉም ሀጢያቱን እንዲረሳለት ለማድረግ የተሄደበት እኩይ-ገጸ ባህሪ ነው።
ደራሲው፣ዳሬክተሩ፣ፕሮውዲሰሩ ህውሃት ነው።ኢዲቲጉም ህውሐት ነው።መሪ ተዋናዩ አብይ አሕመድ ሲሆን የህዝቡን  ቀልብና ልብ ለመግዛት ለዘመናት ሲጠሏት የኖሩትን እና የመቶ አመት እድሜ  ናት እያሉ ሲያናንቋት የነበረችውን የኢትዮጵያን  ገጸ-ባህሪ ለብሶ እንዲጫወት መድረኩ ተሰጥቶታል።
ለዚህም ነው በ2008 ያ ሁሉ (ፓርላማው እንኳን ባረጋገጠው ከመቶ በላይ) የአማራ ወጣቶች የሞቱበት አንኳር  ጉዳይ የወልቃይት ጉዳይ ሆኖ ሳለ የውሐ ጥያቄ ነው ብሎ ውሐ የቸለሰበት።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!!!
Filed in: Amharic