>

እውን የወያኔ የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› ችግር አንቀጽ 39 ብቻ ነው? [ከይኄይስ እውነቱ]

ለዛሬው አስተያየት መነሻ የሆነኝ የኅብር ሬዲዮው ጋዜጠኛ ሀብታሙ የአዲሱን ጠ/ሚኒስትር  በዓለ ሲመት ንግግር ተከትሎ በልዩ ልዩ የኅብረተሰባችን ክፍሎች የተፈጠረውን ተስፋና ሥጋት እንዲሁም ጠ/ሚኒስተሩ ሊገጥመው ያለውን ተግዳሮት በተመለከተ በአውሮጳ የሚኖሩ ሁለት ኢትዮጵያውያንን ያስተናገደበት ውይይት ነው፡፡ ውይይቱን እስከመጨረሻው ተከታትዬአለሁ፡፡ የተነሱት ጥያቄዎችና ተጋባዦቹ ያነሷቸው ነጥቦች ባጠቃላይ አነጋገር ገንቢና መልካም ተሐዝቦት እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ ሆኖም ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዱ አሁን ያለው የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ከአንቀጽ 39 በስተቀር ችግር እንደሌለበት ሲናገር ተደምጧል፡፡ ቃል በቃል ለማስቀመጥ ‹‹… የሕገ መንግሥት ችግር የለብንም እኛ፡፡ ሕጉ በጣም በጣም በጣም ኹሉን ነገር ያሟላ ሕግ ነው በሕገ መንግሥቱ ከአንቀጽ 39 በስተቀር…››

(https://youtu.be/NSACbuOldmA?t=1807 ከ29፡41 ደቂቃ ጀምሮ አዳምጠው ያመሳክሩ)

ይህንን ጉዳይ ነቅሼ ያወጣሁበት ምክንያት ለፀጉር ስንጠቃ ሳይሆን መሠረታዊና ወያኔን ወደ ታሪክ ቆሻሻ ቅርጫት ከወረወርን በኋላ በምንገነባው ኹሉን አሳታፊ መንግሥተ ሕዝብ ላይ አንደምታ ያለው በመሆኑ ነው፡፡ በየትኛውም ዐውድ ይነገር ላለፉት 26 የባርነት ዘመናት በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ ለደረሰው ምስቅልቅል – በተለይም አፓርታይዳዊ የክልል አጥር በማቆም – የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ይህ ወያኔ ለይስሙላ የተከለው ሰነድ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡

ከፍ ብሎ በተወያዩ የቀረበውን አባባል በተቃራኒው ማስቀመጥ ለይስሙላው ‹ሕገ መንግሥት› የሚመጥን ይመስለኛል፡፡ በተግባር መክነው/ጨንግፈው ከቀሩት የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ድንጋጌዎች በስተቀር የማስመሰያው ‹ሕገ መንግሥት› የተጻፈበትን ብራና ያህል ዋጋ የማያወጣ ሰነድ ነው፡፡ እንዴት የሚለውን ከጭንጋፉ ሰነድ አብነቶችን በመንቀስ የምመለስበት ሆኖ፣ መሠረታዊ ይዘቱ ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ ድንጋጌዎቻቸው ከወረቀት አልፈው በተግባር በድነው የቀሩ ‹ሕግጋተ መንግሥትን› በጥቂቱ ለማየት እንሞክራለን፡፡

 

  • ከተግባራዊ አፈጻጸም አኳያ

 

በዓለማችን ስለሚገኙ ሕግጋተ መንግሥት እጅግ የከፋ አፈጻጸም፣ በዚህ ረገድ የለየላቸው ጥፋተኞችን ወይም የይስሙላ/ዐባይ (ላልቶ የሚነበብ) ‹ሕገ መንግሥቶች›ን (Sham/façade Constitutions) በማስፈን ረገድ ስለሚታወቁ አገሮች በተዘጋጀና 3 ዓሥርታትን የሚሸፍን ጥናታዊ ጽሑፍ የይስሙላን ‹ሕገ መንግሥት› እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡

“Sometimes, constitutions lie. Anecdotal examples abound of “sham”2 or “façade”3 constitutions that fail to constrain or even describe the powers of the state. …. The constitution of Eritrea, for example, enshrines the “right to freedom of thought, conscience and belief,”5 the “freedom of speech and expression,”6 and the “freedom to practice any religion and to manifest such practice.”7 But the government of Eritrea is, in practice, one of the most repressive regimes on earth.8 In Equatorial Guinea, arbitrary arrests,9 executions,10 and rampant torture by government security forces11 make a mockery of constitutional guarantees of “[f]reedom of expression,”12 “[t]he right to speak,”13 and “respect” for every person’s “life, integrity and physical and moral dignity.”14 The North Korean constitution’s formal promises of “private property,”15 “freedom of speech, the press, assembly, demonstration, and association,”16 and “freedom of residence and travel”17 combine fantasy with farce.18  

These are not merely isolated examples of disrespect for explicit constitutional rights. The dilemma that constitutions may amount to nothing more than “parchment barriers” is as old as the practice of constitution-writing itself.19

There is more than one reason for which a constitution might be deemed a sham. A constitution that bears no relationship to reality could qualify. So too could a constitution that is descriptively accurate but has no effect on anyone’s behavior.74 The intentions behind a constitution may also be relevant. A distinction can be drawn between constitutions that are violated because they were never intended as anything more than window-dressing, and those that are violated because they prove genuinely difficult to uphold. Alternatively, constitutions can be evaluated on the basis of substantive criteria. It could be argued that a constitution that fails to embody certain substantive principles, such as limited government and the rule of law, does not deserve to be called a constitution at all.

…a constitution is classified as a sham if its provisions are not upheld in practice. We determine whether this definition has been met by looking solely to the magnitude of the gap between what a country promises in its constitution and what it delivers in practice: the larger the shortfall, the more strongly that the constitution is identified as a sham.”

(የጥናታዊ ጽሑፉ ምንጭ David S.Law and Mila Verstegg, Sham Constitutions, 101 CAL. L. REV. 863 (2013) or http//scholarship.law.berkeley.edu/californialawreview/vol 101/iss/4/ ሲሆን፣ በቀረበው የጥናቱ ክፍል ውስጥ የተጠቀሱ የግርጌ ማስታወሻዎችን ከምንጩ መመልከት ይቻላል፡፡)

ከፍ ብለን የጠቀስነው የጥናቱ ክፍል ጭምቅ አሳብና መንፈስ ባጭሩ ለመግለጽ፤ ለመንግሥት ሥልጣን ገደብ ማበጀትን፣ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥን የመሳሰሉ ቊልፍ ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎችን ያላካተተ፤ የያዛቸው ድንጋጌዎች÷ የገባቸው ቃሎች በተግባር የማይተረጐም ወይም በምድር ላይ ከሚታየው ፅድቅ ጋር አንዳች ግንኙነት የሌለው፤ ድንጋጌዎቹ ከመነሻውም ለታይታና ለማጭበርበሪያ ታቅደው የተቀረፁ በመሆናቸው አገዛዞች ያለአንዳች መሸማቀቅና ኀፍረት የሚጥሱት፤ ሰነድ፣ የተጻፈበትን ወረቀት ዋጋ የማያወጣ፣ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› (sham or façade constitution) ተብሎ የሚታወቅ ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግሥት ተብሎ ለመጠራትም ብቃት እንደሌለው ይናገራል፡፡

ጉልበት ወይም ወታደራዊ ኃይል የአገዛዛቸው መነሻና መድረሻ የሆነ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዞች ያለ ሕዝብ ፈቃድ በጫኗቸው፣ ያለምንም ተጠያቂነት እንደፈለጉ የሚጥሷቸው፣ የራሳቸው ዘባተሎና ጠባብ የቡድን አሳቦች የታጨቀባቸው፣ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች በተግባር ከሕግ በላይ ሆነው በሚፈነጩባቸው አገዛዞች በጓዳ ተዘጋጅተው በአደባባይ ለታይታ የሚቀርቡ ሰነዶች የቡድን ፖለቲካዊ መክሥት (መግለጫ) በመሆናቸው ሕገ መንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊነትን በእጅጉ የሚያራክሱ ናቸው፡፡ ሽብርተኛው የወያኔ አገዛዝ ‹ሕገ መንግሥት› እያለ የሚያደነቁረን አገርን ከፋፍሎ በጉልበት ለመያዝና ለመዝረፍ የተማማለበትን የቡድን መግለጫ ነው፡፡ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሰነድ ዋና አገልግሎት ዜጎችን ማታለል ነው በተለይም የውጭ ታዛቢዎችን ማታለልና ማማለል ነው፡፡ ሌላው የአገዛዞችን መረን የለቀቀ ሥልጣን መሸፈኛ ቅብ በመሆን ገጽታቸውን የተሻለ አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡  በእንዲህ ዓይነቱ ሰነድ የተካተቱ ድንጋጌዎችና መርሆዎች ተግባራዊነት ስለሌላቸው ሕጋዊ ተቀባይነታቸውን/ አቋማቸውን ያጡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን ዘረኛ አገዛዝ ጨምሮ አብዛኛው የአፍሪቃ አገዛዞች ለራሳቸው ድብቅ አጀንዳ የይስሙላ ‹ሕግጋተ መንግሥት› ቢያቆሙም እነዚህ አገዛዞች ከሕገመንግሥታዊነት (በሕገ መንግሥት መርሆዎች በተለይም በሕግ በተገደበ የፖለቲካ ሥልጣን የሚተዳደር ሥርዓት) ጋር ትውውቅ የላቸውም፡፡

የወያኔ አገዛዝ በ1987 ዓ.ም. ‹ሕገ መንግሥት› ብሎ ያወጀው ሰነድ ከቡድኑ መግለጫዎች ባሻገር ለማታለያነት ያካተታቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ተግባራዊ ባለመሆናቸው፣ በተለይም ላለፉት 27 የሰቆቃ ዓመታት በገሃድ በመጣሳቸው (ባስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ጭምር ተፈጻሚነታቸው በመቋረጡ) ሰነዱን የይስሙላ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ‹ያልነበራት›፣ አሁንም ‹የሌላት› አገር አድርጓታል፡፡

ይህንን የጽሑፌን ክፍል በጥብቅ ማሳሰቢያ መቋጨት አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ የጎሣ አቀንቃኝ ቡድኖችና ግለሰቦች (አብዛኞቹ በሥልጣን ተረኝነት ካልሆነ ከወያኔ የጎላ ልዩነት የሌላቸው) የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› ከአፈጻጸም ጉድለት በስተቀር እንከን የለውም የሚል አቋም አላቸው፡፡ ይሁን እንጂ የወያኔ የይስሙለ ‹ሕገ መንግሥት› በተግባር አልተፈጸመም ማለት ከሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አንፃር ከፍተኛ ጉድለት ቢሆንም የሰነዱ ዐበይት እንከኖች ግን ከመሠረታዊ ይዘቱ የመነጨ መሆኑን ላሠምርበት እፈልጋለኹ፡፡

ከመሠረታዊ ይዘት አኳያ

 

ይህንን ንዑስ ርእስ በሚመለከት ‹‹የወያኔ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› (façade constitution) ፤ በማር የተለወሰ ሬት››  በሚል  .አ.አ.በ29/11/2016 ያቀረብኩትን አስተያየት መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡https://www.ethioreference.com/amharic/Need%20for%20a%20New%20Constitution.pdf ለግንዛቤ እንዲረዳ በማሰብ የተወሰኑት ነጥቦችም ከዚሁ ጽሑፍ ቃል በቃል ተወስደዋል፡፡

 

  • ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውቅና አለመስጠት (የመግቢያው አንቀጽ)

 

ሕገ መንግሥት ሕዝብና መንግሥት ማኅበራዊ ውል አድርገው የሚተዳደሩበት የቃል ኪዳን መፈጣጠሚያ ሰነድ ወይም የአንድ አገር የበላይ ሕግ እንደመሆኑ የመተዳደሪያ ሰነዱ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ/ዜጋ በማያሻማ ሁኔታ መግለጹ የቃል ኪዳኑ ጽኑ መሠረት ነው፡፡ በዚህም መሠረት የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› በዓለም ላይ ከሚገኙ ሕግጋተ መንግሥት ባፈነገጠ መልኩ ቃል ኪዳን የተገባቡትን ወገኖች የገለጸው መያዣ መጨበጫ በሌለው፣ ግዑዝ በሆነ፣ ትርጕም በሌለው፣ የወያኔን መንደርተኝነት በሚያሳብቅ ኢምንትነት ነው፡፡ ይኸውም ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች››፡፡ በሚል በሰነዱ የመግቢያ አንቀጽ ተመልክቷል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ ያለው ሕዝብ ማነው? ሰነዱ ለሌሎች አገሮች ሕዝቦችም እንዲያገለግል የታሰበ ነው እንዴ?  ኢትዮጵያና ሕዝቧ በዓለም ታሪክ ውስጥ ህልው ሆነው ለዘመናት ከኖሩ፤ በነገድ፣ በጎሣ የሚገለጹ ልዩ ማኅበረሰቦች መኖራቸው የሕዝቡን አንድነት የሚያስቀር አይደለም፡፡ ወያኔ ግን ይህን ጌጥ የሆነ ሕብር አገርን ለመበተንና ኢትዮጵያውያንን ለማቃቃር በእጅጉ ተጠቅሞበታል፡፡ ሌሎች አገሮች ከኛም የሰፋ የጎሣ ስብጥር ሳይኖራቸው ቀርቶ አይደለም እኮ የናይጄሪያ ሕዝብ፣ የሕንድ ሕዝብ፣ የብራዚል ሕዝብ፣ የአሜሪካ ሕዝብ፣ የኬንያ ሕዝብ ወዘተ. እያሉ በሕግጋተ መንግሥታቸው ያስቀመጡት፡፡ ወያኔ የአገሩ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ በአጋጣሚ የተሰባሰበ፤ የታሪክ፣ የባህል፣ የትውፊት፣የአብሮነት የጋራ እሴቶች ዝምድና/ትስስር ወዘተ. የሌላቸው ማኅበረሰቦች ጥርቅም/ክምችት አድርጎ የቀረፀው አንድነትና ኅብረትን በማጥፋት መከፋፈልና መለያየት መሠረቱ ለሆነው የጎሣ ፖለቲካና የሐሰት ‹የጎሣ ፌዴራላዊ ሥርዓት› መደላድል ለመፍጠር መሆኑን ያሳለፍናቸው 27 የግፍ ዓመታት ምስክሮች ናቸው፡፡

ከዚሁ ንዑስ ርእስ ሳልወጣ በተያያዥነት ሊነሳ የሚገባው ስለ ሕዝብ ሉዓላዊነት በይስሙላው ‹ሕገ መንግሥት› የተቀመጠው አባባል ነው፡፡ በሺዎች በሚቆጠር የሀገረ መንግሥትነት ታሪካችን ውስጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ሆኖ አያውቅም፡፡ በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ላይ የሠለጠነው የወያኔ አገዛዝ የሕዝብ ሉዐላዊነትን በ‹ወረቀት› ላይ እንኳን ነፍጎታል፡፡ አሁንም ምዉት የሆነውን አባባል በመድገም፤ ‹‹…ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዐላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡››

የአገሩን ባለቤት የካደ ‹ወረቀት› እንዴት ሕገ መንግሥት ተብሎ እውቅና ይሰጠዋል?

 

  • ክልል የተባለውን የዜጎች ወህኒ ቤት መትከሉ (አናቅጽ 46፣47፣48)

 

በዓለማችን እጅግ ጨቋኝ ከሚባሉ አገዛዞች አንዱ ላለፉት 26 ዓመታት በኢትዮጵያ ላይ ተንሠራፍቶ የቆየው የጥቂት ዘረኞችና ወንበዴዎች ወያኔ አገዛዝ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪቃው የአፓርታይድ አገዛዝ አምሳል ‹ክልል› የሚባል ዘጠኝ የአትድረሱብኝ አጥር አበጅቶ ኢትዮጵያን የዜጎች ማጎሪያ ወህኒ ቤት አድርጓታል፡፡ ዜጎች የትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል አገሬ ነው ብለው የባለቤትነት ስሜት ተስምቷቸው ከቦታ ቦታ በመዘዋር ኑሮአቸውን በመረጡትና በፈለጉት አካባቢ እንዳይመሠርቱ የእሾኽ አጥር አበጅቷል፡፡ ይህም የተደረገው ዜጎች ላይ ካለ ፍላጎታቸው በተጫነው የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን ክፍላተ ሀገራት ሆን ብሎና ለራሱ አገዛዝ እንዲያመቸው በአመዛኙ በጎሣና ቋንቋ ከፋፍሎ የአገራችን ጌጥና መለያ የሆኑ ማኅበረሰቦችን በማጋጨት እስካሁን ያልበረደ ትልቅ አገራዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ በተለይም በታሪክ፣ በባህል፣ በመልክዐ ምድር አቀማመጥ የታወቁ ነባር ክፍላተ ሀገራትን መሬት በኃይል/በወረራ  መልክ (የበርካታ ዜጎችን ሕይወት በማጥፋት) በመያዝና እኔ ቆሜለታለኹ የሚለው ማኅበረሰብ ወደሚገኝበት ‹ክልል› በመቀላቀል ለረጅም ዘመናት በመተሳሰብ አብሮ የኖሩ ማኅበረሰቦች መካከል በቀላሉ የማይሽር ቁርሾ ተክሏል፡፡ ዛሬ ወያኔ ለሥልጣንና ለዝርፊያው አመቻችቶ በፈጠራቸው ‹ክልሎች› መካከል እንደቀድሞው በግጦሽ ሣርና ውኃ ሳይሆን አንዱ ሌላውን እንደ አጎራባች አገር በመቁጠር በድንበር ምክንያት (‹ዞን›፣ ‹ክልል› መሆን ይገባኛል በሚሉ፣ በማንነት እኔን ከማይመስሉ ጋር ተካለልኩ በሚሉ ጥያቄዎች) በሚነሱ ግጭቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለ፣ሌሎች ማኅበራዊ ቀውሶችም የተከተሉበት ጦርነት አከል ግጭቶችን መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በዚህም የአንድነት፣ የአብሮነት በተለይም የብሔራዊ (ኢትዮጵያዊ) ማንነት በእጅጉ እንዲዳከም አድርጓል፡፡ በርካታ የ‹ፖለቲካ ማኅበራት› በጎሣ መስመር መደራጀታቸው እንዲሁም የዜግነት መታወቂያ ተነፍጎን ያልፈቀድነውንና የማናምንበትን የጎሣ መታወቂያ እንድንይዝ መገደዳችን የዚሁ ‹ክልል› የተባለ የአገዛዝ መዋቅር መገለጫዎች ናቸው፡፡ በዚህም ወያኔ በኢትዮጵያ ምድር በዜግነት ላይ የሚመሠረት ሥልጡን ፖለቲካን አስወግዶ የማንነት ፖለቲካ እንዲሠለጥን ያልፈነቀለው ደንጊያ የለም፡፡ ታዲያ ይህንን በተግባር አጥፊነቱ የተረጋገጠ የይስሙላ ሰነድ ይዘን አዲሲቱን ኢትዮጵያ ማለም ይታሰባል?

 

  •  ለሥልጣን ገደብ/ልጓም የማያበጅ መሆኑ

 

እንደሚታወቀው  ሥልጣኑ የተገደበ መንግሥት መኖር የሕገ መንግሥት ተቀዳሚና ዋና ዓላማ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ መርህ ነው፡፡ ሕወሐት በ‹ፓርላሜንታዊ ሥርዓት› እና ‹ኢሕአዴግ›አዊ ሽፋን የዕድሜ ልክ ገዥ ለመሆን ያለመበትን ‹ሕገ መንግሥት› ተክሏል፡፡ በዚህም የአንድ ፓርቲን ፈላጭ ቆራጭነት በማንገሥ ሕጋዊ የሥልጣን ሽግግር እንዳይኖር በሩን ከመዝጋቱ በተጨማሪ የሕዝብን የሥልጣን ባለቤትነት በጽሑፍም በተግባርም እውቅና ነስቷል፡፡ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት ሕዝብ ለመሆኑ እውቅና ላልሰጠ፣ የሥልጣን ገደብ ላላበጀ እና ሕዝብ በፈለገ ጊዜ ሊቀይረው የማይችለው ሥርዓትን ያቋቋመ ‹ሕገ መንግሥት› በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

 

  • በሦስቱ የመንግሥት የሥልጣን ዘርፎች መካከል የሥልጣን ክፍፍል መርህ እና የርስ በርስ ቁጥጥርና ምዝዝን ሥርዓት አለመኖር

 

የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› በሕግ አውጭው፣ በሕግ ተርጓሚው እና በሕግ አስፈጻሚው አካላት መካከል ግልጽ ክፍፍል የማያደርግ ከመሆኑም በላይ የሶሻሊዝምን ሥርዓት ፍልስምና (ሕወሐታዊ ‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›) መሠረት በማድረግ ሕግ አውጪውን (ፓርላማውን/ ‹የተወካዮች ም/ቤት›) የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል መሆኑን በአንቀጽ 50/3 ደንግጓል፡፡ አንዱ የሥልጣን አካል ከሌላው የሚልቅበት ሁኔታ በመካከላቸው ሊኖረው የሚችለውን የርስ በርስ ቁጥጥርና ምዝዝን ሥርዓት የሚያፋልስ ይሆናል፡፡ (ለአብነት ተራ ቊጥር 2.5ን ይመልከቱ፡፡) በዚህም ‹ሕገ መንግሥቱ› የሥልጣን ክፍፍልን ሳይሆን የሥልጣን አንድነትን በማራመድ ለገዢዎቹ የ‹ኮሚዩኒስት ደቀመዛሙርት› አምባገነንነት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሕወሐት አገዛዝ በተግባር ሕግ አውጭው አካል የሚኒስትሮች ም/ቤት (ሕግ አስፈጻሚው) ሲሆን የፓርላማው መደበኛ ሥራ ያለቀለት የሕግ ሰነድ ላይ ማኅተም ማሳረፍ መሆኑን ላለፉት 26 ዓመታት የታዘብነው ሐቅ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹ሕገ መንግሥቱ› ከዳኝነት ነፃነት ጋር በተያያዘ ስለ ዳኞች አሰያየም፣ ስለሚነሱበት ሁኔታ፣ ዝውውር፣ ዲስፕሊናዊ ርምጃና የመሳሰሉትን በሚመለከት ዋስትና የሚሰጥ ሕገ መንግሥታዊ አካል አልደነገገም፡፡ በተግባር ስናይ ደግሞ   ሕግ አስፈጻሚው አካል በዳኝነት ሥርዓቱ (ሕግ ተርጓሚው) ውስጥ እንደፈለገ ጣልቃ በመግባት የአንድ መንግሥት ዓምድ የሆነውን የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ከሥሩ አናግቷል፡፡ በዚህም የሕግ የበላይነት አለመኖር የወንበዴው ሥርዓት ዓይነተኛ መገለጫ ሆኗል፡፡

 

  • ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄን የሚያይ የዳኝነት ሥርዓት አለመኖሩ (Absence of Judicial Review System of Constitutionality) (አንቀጽ 62/1)

 

በዓለም ሥራ ላይ ከዋሉ ሕግጋተ መንግሥት ባፈነገጠ መልኩ ሕግ አውጭው የሚያወጣቸው የበታች ሕጎች፣ ሕግ አስፈጻሚው የሚያከናውናቸው ተግባራትና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች፣ ሕግ ተርጓሚው የሚሰጠው ዳኝነት ከሕገ መንግሥት ጋር ያላቸውን መጣጣም/ሕገመንግሥታዊነትን መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው የአገሪቱ የመጨረሻው ፍርድ ቤት ወይም ለዚሁ ዓላማ የተቋቋመ ሕገ መንግሥታዊ ፍ/ቤት ሳይሆን ፓርላማው (ሕግ አውጭው) መሆኑ ማንም በራሱ ጉዳይ ዳኛ መሆን አይገባውም የሚለውን መሠረታዊ የሕግ መርህ የሚቃረን ነው፡፡ በመሆኑም በሕግ አውጭው፣ በሕግ ተርጓሚው እና በሕግ አስፈጻሚው መካከል ሊኖር የሚገባውን የርስ በርስ ቊጥጥር/ምዝዝን ሥርዓት አፋልሷል፡፡ በዚህም ብቸኛው ገዢ ፓርቲ የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን ትርጓሜ ለራሱ ፖለቲካ መጠቀሚያ አደርጎታል፡፡ ባለፉት 26  ዓመታት ወያኔ ያወጣቸው አፋኝ ሕጎች (እንደ ፕሬስ ፣ ፀረ ሽብር፣ ‹መያድ›ወዘተ. የመሳሰሉ ሕጎች) የሕገመንግሥታዊነትን ፈተና እንደማይለፉ እሙን ነው፡፡

 

  • የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ (አንቀጽ 40/3)

 

የመሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነትን ‹‹የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው›› በማለት በተግባር  ለሕወሐትና አገልጋዮቹ (አገሬውን በማፈናቀል ‹ለውጭ ባለሀብት› ተብዬዎች በመቸብቸብ ጭምር) ብቻ የሥልጣንና የሀብት ምንጭ እንዲሆን በማድረግ ሕዝብና አገዛዙ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ ካደረጉ ዐበይት ምክንያቶች አንዱ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል ተፈጽሟል፤ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ምክንያት ሆኗል፤በዚህ ረገድ በሚከተለውም ፖሊሲ የአካባቢና የተፈጥሮ ሚዛን እንዲዛባ ሆኗል፡፡ ይህ ድንጋጌ ጉድለቱ የተግባር ብቻ ሳይሆን ወያኔ ለራሱ ጥቅም ሲል የመሬት ሥሪት ሥርዓቱ ‹‹የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው›› የሚለው ለሕወሐትና ደጋፊዎቹ ሥልጣንና ሀብት ማደላደያ በመሆኑ ወያኔ በመቃብሬ ላይ ካልሆነ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም ቢልም (ይህ አባባል ወያኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዐላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ያለመቀበሉ ማስረጃ ነው) በወያኔ ግብአተ መሬት ላይ አዲስ የመሬት ሥሪት የሚያቆም ሕገ መንግሥት በሕዝብ ፍላጎት ይደነገጋል፡፡ በእኔ እምነት አዲሱ ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ዜጎች የመሬት ባለቤትነት መብት የሚያረጋግጥ/ዋስትና የሚሰጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ በተለይም ለዘመናት በስሙ ሲነገድበት ለኖረው አርሶ አደር፡፡ በእርግጥ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ከተቻለ መንግሥት ለጋራ ጥቅም የሚያስተዳድረውና በዜጎች ባለአደራነት የሚይዘው መሬት መኖሩ ተገቢና በሌሎችም ዴሞክራሲዎች የሚሠራበት ነው፡፡

ለማሳያ ያህል ከብዙ በጥቂቱ ነሳሳንለት እንጂ የይስሙላው ሰነድ መሠረታዊ የይዘት ችግር ከመግቢያው አንቀጽ እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ነው፡፡ የአገራችንን ልዩ ገጽታ ግምት ውስጥ በማስገባት በጥልቀት ተፈትሸው በሕዝብ ውሳኔ ሊያርፍባቸው ከሚገቡ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መካከል ስለ መንግሥት አወቃቀር ሥርዓት (አሐዳዊ ወይስ ፌዴራላዊ፤ ፌዴራላዊ ከሆነስ መሠረቶቹ ምን ሊሆኑ ይገባቸዋል?)፤ ቅርፀ መንግሥት (ፕሬዚዳንታዊ ወይስ ፓርላሜንታዊ)፤የኢትዮጵያ ግዛት ሉዐላዊነት፤ የአገር መከላከያና ደኅንነት ጉዳዮች፤ ማንነትን (ጎሣን) መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ማኅበር ስለማቋቋም፤ ስለ ርእሰ ከተማዋ አዲስ አበባ፤ ሰንደቅ ዓላማ፤ ብሔራዊ ቋንቋ፤ መንግሥትና ሃይማኖት ስለሚኖራቸው ግንኙነት ወዘተ. ይገኙበታል፡፡ እነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች በጥናት ላይ የተመሠረተ አዲስ ዕይታዎችን ይሻሉ፡፡

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ሕዝብ የወንበዴዎቹን የወያኔ አገዛዝ ሲያሰወግድ ‹ሕገ መንግሥት› ተብሎ ሊጠራ የማይገባውን ይህን መርዘኛ ሰነድ ባንድነት ማስወገዱን ለአፍታ መዘንጋት የለበትም፡፡

Filed in: Amharic