>
5:16 pm - Friday May 24, 5405

ዶክተር አብይ እና ጎንደር (ሀብታሙ አያሌው)

ጠቅላያችን ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ጎንደር አቅንተው ህዝብ እንደሚያወያዩ ዜናውን ማስነገራቸው  ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በሚል ከጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት፤  ከብሔራዊ ደህንነት ቢሮ  የሀገር ውስጥ ደህንነት ዲቪዚዬን፤ ከፌደራል ፖሊስ፤  ከመከላከያ ተወከልን ብለው ከኮማንድ ፓስቱ ጋር የተቀናጁ ጎንደር ገብተው  ከአቶ በለምነህ መኮንን አስተባባሪነት ከብአዴን  ጽ/ቤት  መመሪያ እየሰጡ  ወደ ስብሰባው የሚገቡ ሰዎችን በመለየት ላይ ናቸው።
አላማውም የወልቃይት ጥያቄ ፈፅሞ  እንዳይነሳ ለማድረግ እና ጠቅላዩ ላይ ምንም አይነት የተቃውሞ ድምፅ እንዳይሰማ ለማድረግ ያለመ ነው። ታስረው የነበሩ ሰዎችና ከእነሱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚገመቱ ሁሉ ዝር እንዳይሉ አቋም ተይዟል።  ጥብቅ ክትትል ከማድረግ ባሻገር  ጥያቄ ሊያነሱ ይችላሉ ተብለው የተጠረጠሩትን  ሁሉ አስቀድሞ ከማሽማቀቅ  ባሻገር የተወሰኑ ወጣቶችን በማሰር ለማደናገጥም መታቀዱ ታውቋል። የወልቃት የማንነት ጠያቂ  ያነሱ የኮሚቴው አባላት  ወደ ውይይት አደራሽ እንዳይገቡ ይደረግ መባሉን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ንጉሱ ጥላሁን በመቃወማቸው ውዝግብ መነሳቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ዋናውና አደገኛው ነገር የደህንነቱ ኃይል የቅማንት ማንነት ጥያቄ እንደገና ለአብይ እንዲቀርብ ወደ ሱዳን የሚያገናኙ 3 ቀበሌዎች ወደዛው ልዩ ወደሚሉት ዞን እንዲካተት ለማድረግ ጥያቄውን በይፋ እንዲያነሱ ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ   በጎንደር ቆይታው ለብቻቸው እንዲያናግራቸው ሁኔታው እያመቻቹ መሆኑም ተጠቁሟል።  አጠቃላይ ሴራው እንደተጠበቀ ሆኖ ጠቅላይ ሚንስተሩ ሺዎች የተሰውለትን የወልቃይት ጉዳይ በተራ የቃላት ጫወታ ለመሻገር እና ህወሓትን ለማስደሰት የሄደበት እርቀት ያስነሳውን ቁጣ ለመሸፈን፤ አዳራሽ ውስጥ የተመረጡ ካድሬዎች በማስገባት እንደ መቀሌው አይነት ጭብጨባ ለማሰማት በትጋት እየሰሩ መሆኑን የማያወላዳ ተጨባጭ የውስጥ መረጃ አመልክቷል።
ዶክተር አብይ ከጅምሩ እራስህን ጠልፈህ ላለመውደቅ ጉዞህ ከጭብጨባ ባሻገር ያለውን እንዲያይ እንለምናለን። የሚቃወምን አርቀው የሚያጨበጭብ ባዳራሽ ሞልቶ ማስመሰል የማይጠቅመው የመለስም የኃይለማርያምም መንገድ ነውና እባክህ ተወው። የወልቃይት (የጎንደርን) ህዝብ ጥያቄ በአዳራሽ ተመርጦ ከሚሰበሰብልህ  ካድሬ እንደ አዲስ አትፈልገው። ጥያቄውን የያዘ የ9 ዓመት ልጅ ሰውነቱ  በአምስት የአጋዚ ጥይት ሲነደል አይተሃል። ጎንደር ባህርዳር ወልዲያ ምንጃር በተቃውሞ ሲናጡ በአይንህ ብቻ አይደለም በልብህ አይተሃል። እናም የእናቶቻችን ሃዘን ከልባቸው ሳይሽር እንባቸው የሸረሸረው የጉንጫቸው ሸንተረር ሳይጠፋ የደቁት ደረታቸው ሳያገግም በመቀሌ የሰነዘርከውን የተሳሳተ ቃል ደግመህ ዳግመኛ እንዳታቆስላቸው ማሳሰብ ይገባ ይመስለኛል። እውነት እልሃለው ( መጥታስ ቢሆን ማን አያት  አናኛቱ) እያልን ስናነባ አማራ ኬኛ እያልን በሞታችን ትግል ስናቀና የጠዋት ታሪካችንን መስተጋብር  አስተውለህ የተዋህደነውን መደመር መልካም ነው ስላልክ የሆንነውን ወደህ ስለተቀበልክ በአንደበትህም ስለመሰከርህ ወደድንህ።
እናም ጌታው ፍቅርን መግፋት መልካም አይደለምና መምጣቱን ና ነገር ግን የካድሬን ጎዳና ትተህ በህዝብ ጎዳና ና የመንገድህ አሰናካይ ሌጊዎን ህወሓት እንዳለ እናውቃለን መደመር መልካም ነው ትል የለም ?  እናማ ከህዝብ ጋር ተደመር ወደ ከፍታው ያመጣህ እርሱ ብርቱ ነው እመነኝ ህዝብ አይሸነፍም። አየህ ጌታ የወልቃይት ጥያቄ ውሃ ነው የሚል ስህተት ዳግም እንዳያሰሩህ አደራ እውነት እውነት እልሃለሁ ለውሃ ችግር ወልቃይት አይወረድም ጎንደር ጎሮሮዋ ደርቆ ታገኛታለህ። የወልቃይት ጉዳይ ነባሮች ተነቅለው በተተከሉ አዲስ የህወሓት ትክሎች ብቻ አይወሰንም ህዝብ ማለት ያም ይሄም ነውና። “ዳያስፖራው መጥቶ እንዲያይ ምኞቴ ነው ስትል” በማርያም እምላለሁ አሳዘንከኝ።
ሃሳብህ ሸጋ ነው ነገር ግን ከጅምላ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋው በእድል እንደ ናቡቴ የአባቱ እርስት እንቅልፍ የሚነሳው  ወልቃይቴ ጎንደሬ አገሩን እኮ ተቀምቷል። ጌታው መቼም ቤተመንግስት አያድር ነገር ፍትህ በእናንተ ዘንድ እድል ፈንታ አግኝታ  ቀዬውን እትብቱ የተቀበረበትን አፈር ተራጭቶ ቦርቆ ያደገበትን የናፈቀውን ምድር አገሩን እንዲያይ ወልቃይትን ከህወሓት ሚሊሻ አላቀህ ትግሬውም አማራውም ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የሚኖሩበት ካላደረክ ና ብትለው ወዴት ይመጣል ? እናማ ጌታው  ወደ ትግሉ  እምብርት ሲሄዱ ጥንቃቄ ይሻል እና ያስቡበት።
Filed in: Amharic