>

ሰቲት ሑመራን፣ ቃፍታ ሑመራን፣ ወልቃይትን፣ ፀገዴን፣ ራያን፣ ከትግራይ ጋር ባንድ ላይ የሚጠቀልለውን የኢትዮጵያ ካርታ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረ ሰው!

— ሰቲት ሑመራን፣ ቃፍታ ሑመራን፣ ወልቃይትን፣ ፀገዴን፣ ራያን፣ ከትግራይ ጋር ባንድ ላይ የሚጠቀልለውን የኢትዮጵያ ካርታ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረ ሰው!

ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን (በቅጽል ስሙ ‹‹ጋሽ ሊበን ገብረ ኢትዮጵያ››) 
                                                  (በአሰፋ ሀይሉ)
— የቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ፣ የ1984 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢ!
— መንዝን አጥንቶ፣ አማርኛና ግዕዝን አጠናቆ፣ አማራው ሕዝብ ቅኝ-ገዢ ነው ብሎ ምርምሩን የደመደመ ቺካጎ ቡም!
ባለፈው ከመካከለኛው ዘመን ጀምሮ እስከ ቅድመ ኢጣልያ ወረራ በሃገራችን የመጡ የአውሮፓ ቅኝ ገዚዎች በአቢሲኒያውያንና በአፍሪካዊ ኢምፓየራቸው ላይ ስላደረባቸው ምኞት፣ ስላስተጋቧቸው ከእውነታው የራቁ አመለካከቶችና፣ ስላነገቡትም ዓይነተኛ ዓላማ በጥቂቱም ቢሆን ለመዳሰስ ሞክረን ነበር፡፡
አሁን ደግሞ – ያንኑ ትርክት በመቀጠል – ባለፈው ስሙን ያነሳነው — እና — ‹‹የአማሮች አጠቃላይ የሆነ ሥር የሰደደ ለውጥን-የመቋቋም ባህርይ!›› (‘Amhara’s typically rooted general resistance to change’) የሚለውን — በሰምና ወርቅ (‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ››) መጽሐፉ የከተበውን ከቺካጎ ዩኒቨርሲቲ በ 7 ዓመታት የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ማስተርሱን፣ ዶክትሬቱን – በተፋጠነ መርሃ ግብር ጥንቅቅ አድርጎ — መንዝን ለማጥናት የመጣውን — ዶ/ር ዶናልድ ኤን ሌቪን የሚሰኝ የውጭ ጎብኝ — በጥቂቱ — አንዳንድ አወዛጋቢ ሃሳቦቹን — እናነሣሣለን፡፡
ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን የተሰኙትን ሰው የማውቃቸው — ከ16 ዓመታት በፊት — በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ — ኢትዮጵያውያን እርስ-በርስ ቁርኝት ላይ ያላቸውን ጥልቅ ስነልቦናዊ አመለካከት ለማጥናት ያስችለኝ ዘንድ — በቤተመጻሕፍት ሄጄ መጽሐፍትን በማገላብጥበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የእርሳቸውን ሥራ ያገኘሁት፡፡ በዚያው ቤተ-መጻሕፍት በሚገኝ ያልታተመ ሥራዬም ላይ ጠቅሼያቸው እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ያን ጊዜ ባገኘሁት የእርሳቸው በዓለማቀፍ ጆርናል ላይ — የ66ቱ አብዮት ከመፈንዳቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ያሳተሙት ሥራቸው — ስለኢትዮጵያውያን የአብሮነት የሞራል ስብዕና የሚሰጠው ድምዳሜ እንዲህ የሚል ነበር፡—
‹‹ኢትዮጵያውያን በማህበር በተደራጁና በተሰባሰቡ ቁጥር – ከጥንት ጀምሮ –
ከባድ ቅጣትና የህይወት መቀጠፍ የሚደርስባቸው ሕዝቦች ስለሆኑ – እርስ
በርስ ተማምነው – በአንድ ላይ ተነጋግረውና ተደራጅተው – ማህበር መስርተው –
ለፖለቲካዊ መብቶቻቸው መታገልን – ፈጽሞ የሚፈሩ፣ ውስጠ-ወይራ፣
ተጠራጣሪ፣ እና ባለሥልጣንን እንደአምላክ የሚፈሩ – እናም ተማምኖ
በህብረት ለመጓዝ የማይሆንላቸው ህዝቦች ሆነዋል›› . . . የሚል ድምዳሜ ነበር የሰጡት፡፡
ይህን እንቀበለው ይባል፡፡ ግን ሌላ ያልተቀበልኩትና – አሁንም ድረስ – አምኜ ለመቀበል ያልቻልኩት – በህይወቴ ሁሉ ሲገርመኝ የሚኖር አንድ የዶናልድ ደምዳሜያቸው ነበር፡፡ ያኔ የገረመኝ ነገር – ዶናልድ ሌቪን – በዚያ ዓለማቀፍ ጥናታቸው ውስጥ — ለ19 ጊዜያት — ልብ እንበል — ለአስራ ዘጠኝ ጊዜያት ያህል — እየደጋገሙ የሚያጮኹት — አንድ ቃል ወይም አንድ ያው ሃሳብ ነበረ፡- ‹‹የአማራ ቅኝ ገዢነት››፣ ‹‹አምሃራ ኮሎኒያሊዝም››፣ ‹‹አምሃራ ዶሚኔሽን››፣ ‹‹አምሃራ ሰብጁጌሽን››፣ ‹‹አምሃራ ሩል››፣ ‹‹አምሃራ ዲክታተርሺፕ››፣ ‹‹አምሃራ ሱፒሪየሪቲ››፣ ‹‹አምሃራ አብሶሉቲስት ሞናርኪ››፣ ሌላ ቀርቶ ‹‹አምሃራ ባርባሪቲ›› የሚል ሁሉ ቃል ተጠቅመዋል፡፡ ያኔ ቆጠርኳቸው፡፡ 19 ጊዜያት ያህል እነዚያን ቃላት ተጠቅመዋል፡፡ አበስኩ ገበርኩ ብዬ ተለየሁዋቸው፡፡
ከብዙ ዓመታት በኋላ — ሁልጊዜ ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን በጠቀሷቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ውስጥ በተዘዋወርኩ ቁጥር — ሁልጊዜ ይገርመኝ የነበረው — ምን ያህል የተሳሳቱ ተመራማሪ እንደነበሩ እያሰብኩ ነበር፡፡ እንዴ! ምን ነክቷቸው ነበር እኚህ ሰው??? ያስብላልና ያ ጭፍን ድምዳሜያቸው፡፡
ወደመጨረሻቸው ዕድሜያቸው አካባቢ — ዶናልድ ሌቪን — ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት በመጡበት ወቅት — እጅጉን ከፍተኛ የጀግና የክብር አቀባበል ነበር በጣዩ መንግሥታችን የተደረገላቸው፡፡ ገረመኝ፡፡ በእርግጥ ትክቅ ሰው ናቸው፡፡ ብዙዎች ያከብሯቸዋል በሥራዎቻቸው፡፡ ለምን ተከበሩ አልልም፡፡ ግን ገረመኝ ነው ያልኩት፡፡ ምናልባት እኚህ ሰው ይሆኑ ለብዙዎቹ የብሔር ነፃ አውጭ ድርጅቶች — የአይዲዎሎጂ አባት የሆኑዋቸው?? የሚል ሃሳብ ግን ሁልጊዜ ይመጣብኛል፡፡ የኋላ አቀባበላቸው — በመጠኑ ያን ጥርጣሬዬን ያረጋገጠልኝ ይመስለኛል፡፡
ወጣቱ ዶናልድ ሌቪን — ድሮ በ1952 ገደማ — በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ — በማህበራዊ ሳይንስ (በሶሺዮሎጂ አጥኚነት፣ እና በቤተ መጻሕፍት አደራጅነት ተቀጥረው ወደ ሃገራችን የመጡ የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ አጥኚ ናቸው ሲባል ይሰማል ከብዙዎች፡፡ በመምህርነትም እንዳገለገሉ ከእርሳቸው መጽሐፍት የግል እማኝነት ማግኘት ይቻላል፡፡
የዶናልድ ሌቪን — የእግረመንገድ — ምናልባትም ዋነኛ — እዚህ ኢትዮጵያ ምድር ላይ መምጣት ምክንያት ግን — ለሁለተኛ ጊዜ ከመጣበትም የፋሺስት ሠራዊት ተርፎ መንግሥቱ ሳይፈርስ መኖር የቀጠለውን ይህን ጉደኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ — እና በኮሎኒያሊስቶቹና ፋሺስቶቹ እሳቤና ብዕር ‹‹በገዢነት›› የተሰየመውን — ‹‹የአማራን ሕዝብ›› በማጥናት — በፒ.ኤች.ዲ (በዶክትሬት ዲግሪ) ደረጃ በማጥናት — የሆነ ሶሺዮሎጂያዊ ግኝት ለማምጣት የተላኩ — አሜሪካዊ ተማሪ ወይም ተመራማሪ ነበሩ፡፡
እና ሌቪን – አልፎ አልፎ – ከአዲሳባ እየተነሳ ወደ መንዝ፣ ጎጃም፣ ጎንደር ዘልቋል፡፡ ሕዝቡም በከፍተኛ አክብሮትና እንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በሄደባቸው ጊዜ ሁሉ አስተናግዶ አብልቶ አጠጥቶ የሚፈልገውን ሰጥቶ በሠላም የሸኘው ህዝብ ነው፡፡ እርሱ ግን የጻፋቸውን ጥቂት ቃላት ብንመለከት የእነ ፕሮቻዝካ ልክፍት እንደክፉ መንፈስ ሆኖ አድሮበት ይሆን? ያሰኛል፡፡ ድሮ መንዝን የረገጠው – ጀርመናዊ ሚሲዮናዊ አሳሽ – ጆሃን ሉድዊግ ክራፍ – ስሜቱን ሳይደብቅ ሲናገር – ‹‹የሆነ ክፉ ሠይጣን ካላደረብኝ በቀር ይሰማኛል ብዬ የማልገምተው ዓይነት የጥላቻ ስሜት ነው በእነዚያ ሰዎች ላይ ያደረብኝ›› – ብሎ እንደጻፈ ባለፈው ጊዜ አስነብቤያለሁ፡፡ አሁን ይህኛውን ሌቪንንም ላየው – እንዲያ ብሎ አልጻፈውም እንጂ – የሚያንጸባርቀው ሁሉ ሃሳብ – ያን ዓይነት አስተሳሰቡን – ደግሞ ደጋግሞ ያሳብቅበታል፡፡
ለምሳሌ — ገና ያኔ በ1949 ዓመተ ምህረት በአፍላ ወጣትነት ባሳተመው ‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ›› የተሰኘ መጽሐፉ — ዶናልድ ሌቪን ስለ ናይጄሪያ እና ስለዩጋንዳ የብሔር ብሔረሰቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት ያነሳሳና — ስለኢትዮጵያ ሲመጣ ግን — አማራው ሌላውን የተቀረውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ መሬቱን ቀምቶ፣ ማንነቱን ረግጦ፣ ሁሉነገሩን በባርነት ያዋለ አስከፊ ቅኝ ገዢ ነው ይለዋል — እንዲህ በማለት፡- ‹‹Indeed, if any imperialism of modern times should be granted special consideration, it might be that of the Amhara.››፡፡ በመጨረሻም እንዲህ ይላል የመንዙ ተመራማሪ — ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን፡-
“In Ethiopia, Amhara rule has long provided a minima basis for national unity. While this rule has been secured by coercive means, it has accustomed the carious tribes in Ethiopia to live under a common sovereignty and to some extent has enabled their leaders to communicate with one another by means of a common native tongue.
… These drawbacks have been those of any imperialism. During great Amhara expansion under Menelik (1889-1913), many peoples were maltreated. Indepenedent tribesmen were reduced to slavery; unique cultrures were decimated; proud kings were dragged in the dust. Those who held the Amhara position in these occupied territories seixed land from the indigenous peoples and exploited them much as would any invader.”
እንግዲህ ይህን ምን ይሉታል??? ስለምንስ አላማ ተጻፈ?? ይህስ ከእነ ባሮን ሮማን ፕሮቻዝካም ሆነ ከእነ ጆሃን ሉድዊግ ክሮፍ በጥላቻ የተሞላ ድምዳሜና ትርክት በምን ይለያል?? — መልሱን ለራሳቸውን ልተወው፡፡ ግን መርሳት የማይቻለው ሃቅ — ይህ በ1949 — ከብዙ የተማሪዎችና ሀዝባዊ ብሔርና ርዕዮተ-ዓለም ወለድ ፖለቲካዊ ንቅናቄዎች አስቀድሞ የተጻፈ መጽሐፍ — እና ያቀነቀናቸው አስገራሚ ሃሳቦች ሁሉ — በብዙ ያገራችን የወቅቱ ምሁራንና ተማሪዎች ጽሑፎች ውስጥ — ቃልበቃል ተገልብጠው — ለፖለቲካና አመጽ፣ (ወይም ‹‹ለትግል››) መሣሪያ ሆነው የማገልገላቸውን ሃቅ ነው፡፡ ዶናልድ (ትራምፕ! አላልኩም) ዶናልድ ሌቪን — ሌላ ሌላውን ትተን — ከዚህ ጽሑፍ ጋር ከመጽሐፉ ላይ ፎቶ በማንሳት የተለጠፈውን ካርታ — በኢትዮጵያ ምድር በመሳል — ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመኝ ምሁር ነው — በበኩሌ!!! በ1949 በእኛ፡፡ በፈረንጆች በ1957 ነው ይህን ካርታ ያሳተመው፡፡ ካርታውን በሚስልበት ወቅት — ከተከዜ ወንዝ ወዲህ ያለው የወልቃይት ግዛትና ህዝብ — በበጌምድር መስተዳድር ሥር የነበረ ክፍለሃገር ነበር፡፡ በሰሜን ወሎ ያለው የራያም ግዛትና ሕዝብ እንዲሁ — በወሎ ገዢዎችና አስተዳዳሪዎች ሲተዳደር የኖረ ክልል ነበረ፡፡ እንግዲህ ይሄ ዶ/ር ዶናልድ ሌቪን — እንዴት ብሎ ሃሳቡ እንደመጣለት ባይታወቅም — ግን ይሄን ካርታ ስሎ — ከመጽሐፉ የሽፋን ገጽ ቀጥሎ በሙሉ ገጽ ላይ ገጭ አደረገው፡፡ ጉድ እኮ ነው፡፡
ካርታው የወቅቱን የጂኦግራፊያዊ አከላለል በማለፍ የራሱን አግድሞሽ መስመሮች በመቀነብ — ሌላ የራሱን የካርታ ክልል ያስቀምጣል፡፡ በካርታው መግለጫ ላይ ‹‹የትግርኛ ተናጋሪ የሆኑት›› በሚል — ከኤርትራ ለይቶ — ‹‹ትግሬን፣ ወልቃይትንና ራያን›› አንድ ላይ በመንደፍ ያስቀምጣል፡፡ ይቀጥልና አማርኛ ተናጋሪ ብሎ — የተሳለውን የኢትዮጵያ ካርታ በቋንቋ አከላለል በመሸንሸን — ‹‹በጌምድርን፣ ወሎን፣ ጎጃምን፣ ሸዋን›› ደግሞ — አንድ የካርታ ክልል ውስጥ አስፍሮ — ‹‹የአማርኛ ተናጋሪ የሆኑት›› በማለት — ይከፍለናል፡፡ ወቸ ጉድ!!!
እና ታዲያ — አሁን — በአሁኗ ‹‹አዲሲቷ›› ኢትዮጵያ የምናገኘው ካርታ — ከዚህ — ከዶናልድ ሌቪን የ1949 ዓመተ ምህረት ካርታ — ምን ይለየዋል??? — ምንም የሚለየው ነገር ያለ አልመሰለኝም፡፡ እስከማውቀው ድረስ — እደግመዋለሁ — እስከማውቀው ድረስ — ከጥንታዊ ነገሥታት ካርታዎች — እስከዘመኔ ካርታዎች — ገና ከእነመንግሥቱ ንዋይ መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ አስቀድሞ — የኢትዮጵያን የወደፊት ካርታ — ከመጽሐፍ ሙሉ ትንታኔ ጋር ያቀረበ — አንድም — እደግመዋለሁ አንድም — ምሁርም ሆነ ተንታኝ ወይም አሳሽ አሊያም ተጓዥ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ብዬ ብሰናበት መረጥኩ፡፡
በመጨረሻ ግን ሳልጠቅስ የማላልፈው የዶ/ር ዶናልድ ሌቪ ‹‹ሰምና ወርቅ›› ‹‹ዋክስ ኤንድ ጎልድ›› መጽሐፍ አወዛጋቢነትን በተመለከተ በምሁራን የተሰነዘረን የትዝብት ሂስ ወይም ሙያዊ የቅኝት አስተያየትን ነው፡፡ ያም ሂስ የእኔ የራሴም አስተያየት ነው፡፡ በሙሉ ልብ እጋራዋለሁ፡፡ አንባቢም አይቶት የራሱን አቋምና አስተያየት ይያዝበት፡፡ ሂሱ የሚለው እንዲህ ነው፡—
“Dr. Levine’s Wax & Gold is one of these. It has received a mixed reception ranging from unrestrained acclaim to mild praises and outright denunciations. These varied and heated reactions pinpoint the duality of the book: it is a serious and illuminating piece of work; it has at the same time, the maddening sting of a gadfly.”
የዶክተሩ ሰምና ወርቅ መጽሐፍ — አወዛጋቢ ነው ለብዙዎች — በአንድ በኩል የሚገርም አንፀባራቂና በትኩረት ሊጠና የሚገባ የምርምር ሥራ ነው — በተመሣሣይ መልኩ ደግሞ — መጽሐፉ — በንዴት አቅልን የሚያስት — የተርብ ንድፊያ ነው — ብለን መውሰድ ይቻለን ይመስለኛል!!! — ነው የሚለው ሂስ አድራጊው፡፡ አከበርኩት፡፡
በኢትዮጵያዊ ጨዋ አንደበት — ለዚሁ ዶ/ር — ዶናልድ ሌቪን — ነፍስ ይማር — እያልኩ ጽሑፌንና አስተያየቴን ደምድሜ አበቃሁ፡፡
በአንድነት ታላቅ ነን፡፡ ስንከፋፈል ኢምንት ነን፡፡ አንድነት ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያችን ለትውልዳችን ትለምልም!! አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!! ኢትዮጵያ በልጆቿ ፍጹም ፍቅርና የተባበረ ክንድ ለዘለዓለም በጸጋ በፍስሃ ትኑር፡፡ አሜን፡፡
“Kulu Amekeru Wezesenaye Atsneu,” “Test everything that is said. Hold on to what is good,” ‹‹ሁሉን መርምሩ፤ ሸጋ የሆውን ያዙ፡፡››
— ራሳቸው ዶ/ር ዶናልድ ኤን ሌቪ፤ በ1996 (2004 እ.ኤ.አ.) ከአአዩ የክብር ዶክትሬት ሲሰጣቸው በእንግሊዝኛና ግዕዝ የተናገሩት፡፡
መልካም ጊዜ፡፡
የካርታው እና በጽሑፉ የተጠቀሱ የሌሎች ሥራዎች ዋነኛ ማጣቀሻ ምንጮች (ከምስጋና ጋር)፡-
– Donald N. Levine, Wax & Gold: Tradition and Innovation in Ethiopian Culture (With a new preface by the author), fifth impression, 1972, The University of Chicago Press, Chicago and London, Printed in USA.
– Professor Ayele Bekerie, Mekele, Ethiopia, Article on Tadias, Tribute to Ethiopia Scholar Don Levine: Reflections & Photos, April 7, 2015፡
— Dr. Theodore M. Vestal, Professor Emeritus, Oklahoma State University, Article on Tadias, Tribute to Ethiopia Scholar Don Levine: Reflections & Photos, April 7, 2015
— Gedamu Abraha, Wax and Gold Commentary, Posted by Gedamu Abraha on November 2, 2005 by sevensecondsaway:
Filed in: Amharic