>

ጎንደርን በጨረፍታ አስጎበኝዎታለሁ! አማራ ክልልን ያዩበታል! (በጌታቸው ሽፈራው)

 ጎንደርን ያውቋታል ሲባል ሰምቻለሁ። እኔ ለአንድ ወር ያህል ጎንደር ቆይቻለሁ። እርስዎ ጎንደርን የሚያውቋት የየመከላከያ አመራር ወይንም ባለስልጣን ሆነው ነው።  የሚያውቁት የመከላከያ እና የባለስልጣናቱን ጎንደር ነው። የህዝቡን ጎንደር አያውቋትም። በእርግጥም የድሮዋ ጎንደር ከዛሬዋ ትለያለች። ዛሬ መንገድ ላይ እያለፉም ቢሆን ሀቁን በግልፅ ይረዱታል። መረዳት የሚፈልጉና የሚችሉ ከሆነ! ጎንደርን ሲጎበኙ ሆን ተብሎ የደቀቀውን አማራ ክልልን በአንድ ከተማ ላይ  ይመለከቱታል! በተለይ የሚከተሉትን ከልብ ከጎበኙ:_
1) መንገዶቹ
ምን ያህል በዘመናዊ መኪና ቢሄዱባቸው፣ ይህን ከአየር መንገድ እንደወጡ የሚረዱት ይሆናል። በአዘዞ በኩል ቢያሳልፉዎት እንዴት ደስ ባለኝ። መንገዶቹ ፈራርሰው አስፓልት የሚባል ነገር የሌለው መሆኑን ሲረዱ  “የመጣሁት ሌላ ቦታ ነው?” ማለትዎ አይቀርም። ድሮ የሚያውቁት አስፓልት እንኳን የለም! ከተማ ውስጥ ሳይሆን ቋጥኝ የሚወጡ ይመስልወታል። በታችኛው መንገድ ሲመጡም የሚያገኙት ተመሳሳይ ነው።  የሆስፒታሉን መንገድ ባስጎበኝዎት የማያምኑትን ይመለከታሉ!
  2)   የፋሲሊደስ ቤተ መንግስት
ጎንደር አለኝ ከምትላቸው ቅርሶች መካከል አንዱና ዋነኛው የፋሲለደስ ቤተ መንግስት ነው። በአሁኑ ወቅት የፋሲለደስ  ቤተ መንግስት ሰው ደስ ብሎት የሚጎበኘው ሳይሆን “እየፈረሰ ነው” ብሎ ከንፈር የሚመጥለት ቅርስ ሆኗል። በአመት በርካታ ሺህ ዶላሮችን እያስገኘ የወፍ ላባ እና ኩስ እንኳ የሚጠርግለት አልተገኘም። ውጭ ላይ የነበሩት አግዳሚ ወንበሮች ተሰባብረዋል። ግንቡ እየፈረሰ ነው፣ ወለሎቹ ፈራርሰዋል። ቅርሱ ውስጥ የሚፈፀሙትን መቆጣጠሪያ ድብቅ ካሜራ ስለሌለው ግድግዳዎቹ የገባው ሁሉ የተሰማውን የሚፅፍባቸው ሰሌዳዎች ሆነዋል። ከቅርሱ የሚገኘው ገቢ የሚውለው ለፌደራል መንግስቱ መሆኑንም እንዲያስታውሱልኝ!
3/ ጎንደር ሆስፒታል 
የጎንደር ሆስፒታል በኢትዮጵያ ቀዳሚ ከሚባሉት ተቋማት መካከል መሆኑን አይረሱትም። ከላይ እንደገለፅኩልዎት በአዘዞ በኩል ወደ ሆስፒታሉ ቢያቀኑ አይንዎትን ማመን ያቅትዎታል። እርስዎ ስለ እናትዎ ያለዎትን ፍቅር በፓርላማው ገልፀዋል። የጎንደር እናቶች  ለመውለድ ወደ ሆስፒታል ሲመጡ  መንገዱ ከመፈራረሱ የተነሳ ፅንሱ ተዛብቶ የሞቱ  እንደአጋጣሚ ሆኖም መንገድ ላይ የወለዱ እንዳሉ ይነግሩዎታል። ወደ ሆስፒታሉ ገባ ቢሉ እናቶች፣ ህፃናት ውጭ ላይ ተኝተው ያገኟቸዋል።  ምን አልባት አጠር ሲል በአንድና ሁለት ወር ውስጥ የሚደርሳቸውን አልጋ እየተጠባበቁ ነው።
ይህ ሆስፒታል በትንሹ እስከ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ለሚኖርበት አካባቢ ቅርበት ያለው ነው። ነገር ግን በመቶ የሚቆጠሩትን እንኳ በሚገባ እያገለገለ አይደለም። እስርን ካልፈሩ የዚህ ምክንያት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ባላቸው ግንኙነት ለሆስፒታሉ እርዳታ፣ ልምድና ባለሙያ በማምጣት ይሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች ተማርረው እንዲሰደዱ መደረጋቸው  የቀሩት ሰዎች ይነግሩዎታል። በተጨማሪም ጠንካራ ሰዎችን ከሆስፒታሉ በማራቅ ለመንግስትዎ  የሚመቸውን አቅመ ቢስ ሰራተኛ እንደቀጠሩበት ያጫውቱዎታል። ለአብነት ያህልም ከስር የተዘረዘሩት ባለሙያዎች በሰበብ ከዩኑቨርሲቲ ሆስፒታሉ እንዲርቁ ተደርገው አቅመ ቢስ ካድሬ እንደተተካበት ያጫውቱዎታል። ለምሳሌ ያህልም:_
1ኛ ዶ/ር መሰረት_ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል  የህፃናት ስፔሻሊስት  የነበሩ_   ወደጤና ጥበቃ ሚኒስትር
2ኛ ዶ/ር አበባው_  የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ውስጥ ይሰራ የነበረ  ወደ ክልሉ ጤና  ጥበቃ
3ኛ  ዶ/ር ዘኪ_  የጎንደር ሆስፒታል  የቀዶ ጥገና  ሀኪምና መምህር  በአሁኑ ሰዓት  ወደ አዲስ አበባ ጥቁር አንበዳ የተወሰደ
4ኛ  ዶ/ር ካሳሁን  የጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ሆስታፒል   የቆዳ ጥገና  ሀኪምና መምህር  በአሁኑ ሰዓት ወደ አሜሪካ ሀገር የተሰደደ
5ኛ ዶ/ር ተስፋዬ _  ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል_ ትምህርት ሚኒስትር የተዛወረ
6ኛ ዶ/ር አለም ሰገድ _የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህር ወደ ጤና ጥበቃ
7ኛ  ፕ/ር አፈወርቅ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የምርምርና የማህበረሰብ አገልህሎት ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩ ወደሳይንስና ቴክኖሎጅ ተዛውረዋል
8ኛ  ዶ/ር ኤባ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል  የማይክሮ ባዮሎጅ  ትምህርት ቤት  ክፍል ተመራማሪና  መምህር_ በአሁኑ ወቅት ወደ ፓስተር ኢንስትቲትዩት
9ኛ ዶ/ር ደሳለኝ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል  የህብረተሰብና ጤና ትምህርት ክፍል መምህርና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የነበረ፣ አሁን ወደ ጤና ጥበቃ  ሚኒስትር የተዛወረ
10ኛ ዶ/ር ማህሌት _  የጎንደር ሆስፒታል ስፔሻሊስት፣ ወደ ጳውሎስ የተዛወረች
11ኛ  ዶ/ር በየነ _ የጎንደር ሆስፒታል  የማክሮ ባዮሎጅ  መምህርና ተመራማሪ የነበረ ወደ ፓስተር የተዛወረ
12ኛ  ዶ/ር ኤርሚያስ ዲሮ  _የጎንደር ሆስፒታል  የውስጥ ደዌ  ትምህርት ክፍል መምህርና የአባላዘር በሽታ  ተመራማሪ ~ወደ አሜሪካ የተሰደደ
ከላይ ለምሳሌ የተዘረዘሩት ባለፈው አምስት አመት ብቻ ወደተለያየ ቦታ ተዛውረው፣ ተማርረው ተሰድደው ሆስፒታሉ ባዶ ሆኗል። አንድ አቅመ ቢስ ካድሬን ወደ ጎንደር ለማምጣት “አትውሰዱን” እየተባሉ የረባ ስራ ወደማይሰሩበት ተቋማት ተዛውተው ሆስፒታሉ ባዶ እንደቀረ ያጫውቱዎታል!
 3/ ጎንደርን በነፃ የሚጠቀሙባቸው ተቋማትን ይጎብኙ
መቼም የፓርቲዎ አጋር ከሆነው ዳሸን ቢራ ፋብሪካ ውጭ ጎንደር ውስጥ ሌላ ፋብሪካ እንደሌለ ይገነዘባሉ። አልፎ አልፎ በከተማው የሚያዩወቸው ግንባታዎች የወልቃይት ተወላጆች ንብረት ናቸው። መቀሌ ሄደው ቢገነቡ ብዙ ነገር እንደሚመቻችላቸው እየተነገራቸው “አንፈልግም” ብለው በጫና የሰሯቸው ናቸው።  አልፎ አልፎ ከሚታዩት ውጭ ቀሪዎቹ የቆዩ የህዝብ ህንፃዎች ናቸው። ህንፃዎቹ በወር ከ30 እስከ 100 ሺህ ብር መከራየት የሚችሉ ናቸው። ይሁንና የተለያዩ የመንግስትና የፓርቲ ድርጅቶች እነዚህን ህንፃዎች በነፃ ወይንም ነፃ በሚባል ዋጋ እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ጥቂቶቹን ልጥቀስልዎት:_
1)ቴሌ
2)መብራት ኃይል
3) ከፍተኛ ፍርድ ቤት
4)ዞን ፖሊስ
5) የከተማው ፖሊስ
6) ዞን አስተዳደር
7)ከንቲባ ፅ/ቤት
8  / ጤና ቢሮ
9)ትምህርት ቢሮ
10) ጉምሩክ
11)ኢንቨስትኘንት ቢሮ
12) የከተማው ፖሊስ ቢሮ
13)የከተማው ፋይናንስ
14) የከተማው ፋይናንስ
15)ባህልና ቱሪዝም ቢሮ
16) ቀበሌ 3 ፅ/ቤት
17) ቻምበር ፅ/ቤት
18)ብሔራዊ ሎተሪ
19)ፖስታ ቤት
20)ጅንአድ
21)አምበሳ ጫማ
22) ጅምላሸቀጣሸቀጥ
23) የሰነዶች ማረጋገጫ
24) የከተማው ሲኒማ ቤት
25) አልማ
26)  የወረዳ ፍርድ ቤት
27) ንግድ ባንክ
28) ሜጋ
እነዚህ ተቋማት በወር ከ30 እስከ 100 ሺህ ብር ኪራይ መክፈል ነበረባቸው። በአጠቃላይ ሲታይ የጎንደር ሕንፃዎች ለእነዚህ የመንግስት፣ የህወሓት የንግድ ድርጅቶች፣ የፓርቲ ድርጅቶች  በርካታ ሚሊዮን ብሮ ዋጋን በነፃ ሲሰጡ ቆይተዋል። እነዚህ ተቋማት ህንፃ ቢገነቡ ይኖር የነበረው ኢንቨስትመንት እንዲሁ ቀርቷል።  በነፃ የሚያገለግሉትን የጎንደር ተቋማት ሲጎበኙ  ፋና ሬድዮ ጣቢያ የሚጠቅምባቸውን የደሴው የንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስት፣ የደብረማርቆሱ የንጉስ ተክለሀይማኖት ቤተመንግስትና ሌሎች ቅርሶችም የንግድ ቤት እንደሆኑ አስታውስዎታለሁ!
4/ ውሃና መብራት
መንግስትዎት ያለ ባለሙያ ስንት ፕሮጀክቶችን ሰርቻለሁ ብሎ ከለፈለፈ በኋላ ፕሮጀክቶቹ መና ሆነው እንደሚቀሩ የጎንደር ውሃ ፕሮጀክት ቋሚ ምስክር ይሆንዎታል። እናቶች፣ ልጆች በጀርባቸው ጀሪካን ተሸክመው ወደ ቀሃ ወንዝ ሲጓዙ አስጎበኝዎታለሁ።  የመብራቱን ጉዳይ አንድ ቀን ብቻ በከተማዋ ቢያድሩ በደንብ የሚረዱት ይሆናል!
5/ ነጋዴዎች
አዲስ አበባ ላይ ነጋዴዎችን አነጋግረዋል። በየሱቁ ዞረው ማነጋገር አይችሉም እንጅ ዞረው ቢያነጋግሩ እውነታውን ያዩት ነበር።  አንድ ሁለት ነጋዴዎችን ቢጠይቁ ምሬቱን ይነግሩዎታል። ነጋዴዎች ለፌደራል ወይ ለክልሉ መንግስት ግብር የሚከፍሉበት መንገድ አለ። ለፌደራል መንግስቱ የሚከፍሉት “plc” ብለው ሲከፍቱ  ነው። ከዚህ በታች ያሉት የሚከፍሉት ለክልሉ መንግስት ነው።  ሆኖም ግን የክልሉን ገቢ ፌደራል መንግስቱ (ህወሓት ማለቴ ነው) ሆን ብሎ ቀምቶታል። ለክልሉ የሚከፍሉት በጣም ከፍተኛ ግብር እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።  plc  ብሎ ያቋቋመ ለፌደራል መንግስት ስለሚከፍል ለክልሉ ከሚለፍሉት ጋር ሲነፃፀር በጣም ቅናሽ ግብር እንዲከፍል ይደረጋል። በዚህም ምክንያት የአማራ ክልል ገቢ እንዳይኖረው መደረጉን መፍትሄ ለማልሰጣቸው እኔ የነገሩኝን ለእርስዎማ በደንብ ይነግሩዎታል!
6/ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱ መኖርያ ቤት የነበረውን
ቀበሌ 18 የሚገኘውን ኮ/ል ደመቀ እስከ ሀምሌ 5 /2008 ዓም ይኖርበት የነበረውን ቤት ከፋሲለደስ ቤተ መንግስትም ቀድመው ቢጎበኙት ብየ እመክርዎታለሁ። 1ኛ እርስዎም የነበሩበት፣ አሁንም የሚመሩት መንግስት በሕዝብ ላይ የፈፀመው ጥቃት ነው። 2ኛ አንድ  መከላከል የሚችል ንፁህ ዜጋ ላይ የመንግስት ነኝ የሚል ጦር ይህን የመሰለ ጥቃት ከፈፀመ፣ ለመከላከል አቅም የሌለውን ምን ሊያደርገው እንደሚችል መገመት ይችላሉ።  ይህ ቤት መንግስት በአማራው ላይ ለፈፀመው፣ አማራውም በመንግስት መገፋቱ በቃኝ ያለበት ትልቅ ምልክት ነው! መንግስት ለሚፈፅመው አረመኔያዊ እርምጃ ምሳሌ ከመሆኑ ባሻገር ልብ ላለው ለወደፊት ቆም ብሎ ለማሰብ የሚያስችል ምልክት ነው!
ከላይ የተጠቀሱት የጎንደር ብቻ አይደሉም። ጎንደርን ለአማራ ክልል መነፀር አድርገው ይጠቀሙበት ዘንድ ነው። ይህ ስል እርስዎ ኢህአዴግ መሆንዎትን ረስቼ አይደለም! ኢህአዴግም ልቦና ይሰጠዋል ብየ አይደለም! ይህ ሁሉ መበደል፣ መበዝበዝ፣ መደህዬት ምን ሊያመጣ እንደሚችል ይገምታሉ ብየ ነው! የወልቃይት ጉዳይ ሌላ ነው! እኔ  ከምነግርዎት ይልቅ ስታዲዬም ላይ ይዘመርልዎታል!
Filed in: Amharic