>

ስለ ወልቃይት መቆም፣ መጠየቅ ብሔርተኝነት አይደለም! (ጌታቸው ሽፈራው)

ተወደደም ተጠላም የወልቃይት ጉዳይ ለሰው ህይወትና አካል የመቆም የሰብአዊ መብት ጥያቄ ነው። ወልቃይት የትግራይ ነች በማለቱ የተሸለመ እንጅ በደል የደረሰበት የለም። ወልቃይት አማራ ነው ብለው የተነሱት ላይ የሚደርሰው በደል ግን የከፋ ሆኗል።
“ወልቃይት የአማራ ነው” የሚል ሕጋዊ ጥያቄ ያነሱት ለምን ይበደላሉ? ወልቃይት የትግራይ ነው ብለው ከሚከራከሩት ጋር ለምን እኩል መብት የላቸውም? ወልቃይት የትግራይ ነው ከሚሉት ጋር በመከራከራቸው ይህን ያህል በደል እየደረሰባቸውስ  በዚህ ሁሉ መስዋዕትነት ለምን ጥያቄያቸውን ቀጠሉ?
ምንም ይሁን  “ወልቃይት  የትግራይ ነች” ካሉትጋር ስለተከራከሩ ለምን ይገደላሉ? ለምን ይታሰታሉ? ለምን ይደፈራሉ? ለምን መሬታቸውን ይነጠቃሉ? የሚል አጀንዳ  ስለ ሰው ልጅ ግድ ይለኛል ለሚል ሁሉ ጥያቄ መሆን አለበት። የማንነት መብት በማንሳታቸው የአካል ደህንነትና በህይወት የመኖር መብታቸው ለተገሰሰው ሰዎች ጥብቅና መቆም ሰብአዊነት እንጅ ፖለቲካ አይደለም! የወልቃይት ጥያቄን አንስተው ስለሚበደሉት መቆም ለሰብአዊነት መከራከር እንጅ ብሔርተኝነት አይደለም!
እኔም የአካል ደህንነት እና በሕይወት የመኖር መብታቸው ስለተገሰሰው ወንድምና እህቶች የአቅሜን እቆማለሁ! የቻልኩትን እጮሃለሁ! የወልቃይት ጥያቄ የሰብአዊነት ጥያቄ ነው!
የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምላሽ ባያገኝም በስፋት ይነሳበታል በተባለው የባህር ዳሩ ጉባኤ ላይ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው የተገኙት ብጹእ አቡነ አብርሀም ቤተ ክርስቲያኒቱ በስርአቱ እየደረሰባት ያለውን በደል ከብዙ በጥቂቱ አሰምተዋል።
ቆራጡ አባት ኖላዊ አቡነ አብረሐም ዛሬም ታሪክ ሰሩ!
ብፁዕ አቡነ አብርሐም ለዶ/ር አብይ አህመድ በባህር ዳር ውይይት ላይ ያቀረቡት አቤቱታ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዚህች ሀገር ባለውለታና ባለቤትም ጭምር ነች፤ በዚህ ዘመን የሃይማኖት እኩልነት እየተባለ ይህች ቤተክርስቲያን እየተጎዳች፣ ማንነቷን እያጣች ነው፡፡ ስለዚህ በእርሰዎ ዘመን የዚህች ቤተክርስቲያን ውለታ ሊታወስና በየትኛውም ቦታ ሊከበርላት ይገባል፡፡ የእኔ ስለሆነች ሳይሆን ውለታዋና ክብሯ ሊመለስላት ይገባል፡፡ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት በባለስልጣናት እየተበደለችና እየተጎዳች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሊስተካከልና ሊታይ ይገባዋል፡፡ መርጣ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ብላ በሁሉም ቦታና ጊዜ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያስተማረች ፣ ለሀገር መሰረት የጣለች ቤተክርስቲያን ነች፡፡  እናት ቤተክርስቲያን እየተጎዳች ደግሞ ሀገር መገንባት አይቻልም፡፡
ዶ/ር አቢይም አባታችን የመከሩኝን እፈፅማለሁ፤ ስለ ሀገር አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን ለማፅናትና ለመገንባት እርሰዎም በፀሎት ያግዙኝ ሲሉን ተደምጠዋል፡፡
በእውነት ለእኝህ ግሩም አባት በየጊዜው የተዋህዶ ልጆች እንድንነቃቃና አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ለሚያደርጉ ከኔ እድሜ ላይ ቀንሶ ይስጣቸው!
Filed in: Amharic