>

የወልቃይት ጉዳይ በህገ-መንግስቱ የማይፈታበት ምክንያት (የዋግነሽ አድማሱ)

1. የህወሃት ማኒፌስቶ ስለማይፈቅድ:- በህወሃት ማኒፌስቶ የትግራይ መሬት ማለት በደቡብ አለውና፣ በሰሜን መረብ ወንዝ ሲያካልሉት በምእራብ በኩል ደግሞ ወልቃይትንን እና ጠለምትን ያጠቃልላል ብሎ በግልፅ አስቀምጦታል። በዚህ አገባብ ህወሀት ስትመሰረት ይዛው የተነሳችለትን አላማ በቁሟ ትቀይራለች ብሎ ማመን ዛሬም የህወሃትን ባህሪ በአግባቡ ካለማወቅ የመጣ የመረዳት ዳተኝነት ነው ብየ አስባለሁ።

2. ሌላው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 48 ስለ ክልሎች ወሰን እንዲህ ሲል በግልፅ ያስቀምጠዋል። “የክልሎችን ወሰን በሚመለከት ጥያቄ የተነሳ እንደሆነ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈጸማል። የሚመለከታቸው ክልሎች መስማማት ካልቻሉ የፌደረሽን ም/ቤት የህዝብን አሰፋፈር እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል” ይላል። በዚሁ አንቀፅ ንኡስ አንቀጽ ሁለት ላይ ደግሞ “ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ አንድ መሰረት የቀረበ ጉዳይ ከሁለት አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በፌደረሽኑ ም/ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል።

እንግዲህ ይሄን የሚለው ህገመንግስቱ ነው። የፌደረሽን ምክር ቤት በሁለት አመት ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ የወልቃይት ጉዳይ ስንት አመት ሁነው? የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴወችስ የፌደረሽን ም/ቤት ቢሮ ማንኳኳት ከጀመሩ ስንት ዘመናትን አስቆጠሩ። አብዛኛዎቹ ኮሚቴወቹ እኮ ጥያቄያቸው ሳይመለስ እያረጁ በወጣት ተተክተዋል።

ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንኳን ለዚህ ጥያቄ መልስ ሊሰጥ የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች እወክላለሁ የሚል ተቋም ኮሚቴወቹ አናግረውት ግቢውን ሳይለቁ ለደህንነት ደውሎ ያሳፈናቸው ማን ሆነና። ኮሚቴወቹ ከጎንደር ደውለው ቀጠሮ አሲዘው ነገ እመጣለን ብለው ለፌደረሽን ምክር ቤት ሲናገሩ እየመጡላችሁ ነው ብሎ ለደህንነት የሚደውል እና እንጦጦ ላይ ኮሚቴወቹ እንዲታፈኑ ያስደረገ መስሪያቤት እንዴት በህገመንግስቱ አግባብ የወልቃይትን ጉዳይ ይፈታል ብለን እናስብ?

3. ሌላው ብአዴን የወልቃይትን ጉዳይ አጀንዳየ ብሎ አለመያዙ ነው። የብአዴን ባለስልጣናት በወልቃይት ጉዳይ ሲጠየቁ ከሚሰጧቸው መልሶች ጥቂቶቹ፤ ወልቃይት ትግራይም ሆነ አማራም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ አልወጣም፣ የወልቃይት ጥያቄ የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ ሳይሆን ጎንደር የሚኖሩ ወልቃይቴወች እና ዲያስፖራው የሚያራግቡት ጥያቄ ነው እና ወልቃይት የትግራይ ነው የሚሉት ናቸው።

ይህ የሚያሳየው ብአዴን የወልቃይትን ጉዳይ አጀንዳ ማድረግ አለመፈለጉን ነው። ብአዴን ይሄን የሚያደርገው የችግሩን ጥልቀት እና አሳሳቢነት ሳይረዳ ቀርቶ አይመስለኝም ይልቅ ህወሃትን አስደስታለሁ ብሎ ኮሚቴወችን እስከማፈን ድረስ ዘልቆ ሄዷል። ዛሬም ድረስ ብአዴን የወልቃይት ጉዳይ እንዲነሳበት አለመፈለጉን የሚያሳዩ ሁኔታወች መጥቀስ ይቻላል።

በቅርቡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ጎንደር በተገኙበት ወቅት ወልቃይትን የሚመለከት የተጻፈበት ባነር እንዳይገባ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረጋቸው፣ በስብሰባ ላይም ስለወልቃይት ጉዳይ ሊናገሩ ይችላሉ የተባሉትን ሰወች ጥሪ ሳያደርጉ መቅረታቸው ቢታወቅም በእነ አታላይ ዛፌ እና ሌሎች የወልቃይት እና የጎንደር አማራወች ትጋት ጥያቄው አጥጋቢ ሊባል በሚችል መልኩ ተደራሽ ሁኗል።

ጠ/ሚኒስትሩም እነዚህ ትንታግ አማራወች ወጥረው ስለያዟቸው ይመስለኛል ግማሽ
መንገድ መጥተው የወልቃይት ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ነው ያሉት እንጅ ብአዴን አጀንዳውን አቅርቦላቸው እንዳልሆነ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ይህ የሚያሳየው የወልቃይት ጉዳይ በራሱ በአማራው ትግል ጫንቃ ላይ መውደቁን ነው።

4. ሌላኛው አማራጭ ህዝበ ውሳኔ ነው። ብአዴንም ጫና በዝቶበት፣ ጠ/ሚንስትሩም እንዳሉት ትኩረት ሰጥተውት ጉዳዩ እልባት እንስጠው ቢባል ሊሆን የሚችለው ህዝበ ውሳኔ ነው።

ህዝበ ውሳኔ ማለት ምርጫ ነው። ህወሃት ከ1972 ዓ.ም አካባቢውን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሰፈራን ፕሮግራም እንደ ስትራቴጅ ይዞ ሲሰራበት ቆይቷል። ስልጣን ከያዘም በኋላ ከኢትዮጵያ ውጭ የነበሩ ስደተኞችን (ለምሳሌ ከሱዳን እስከ አስር ሺ ስደተኛ ትግሬወችን አስፍሯል ) እና በአገር ቤት በትግራይ ክልል እና በሌሎች የሃገሪቷ ክልሎች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችን በስፋት እንዳሰፈረ የወልቃይት የአማራ ማንነት ኮሚቴወች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጉዳይ ነው።

ህወሃት የራሱን ሰወች ማስፈር ብቻ ሳይሆን አማራወቹ ላይ በሚያደርሰው ተፅእኖ አማራወቹ ለስደት፣ ለሞት እና ለእስር ተዳርገዋል። በዚህ 27 አመት ውስጥ አማራወቹን የማፍለስ ስራ ሲሰራ ትግሬወቹን የማስፈር ስራ ተሰርቷል።

በሌላ አነጋገር አማራወቹን የመቀነስ ስራ ሲሰራ የትግሬወቹን ቁጥር የመጨመር ስራ በተጠና መንገድ ተሰርቷል ማለት ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ የህወሃት የምርጫ ማጭበርበር እና የኮረጆ ግልበጣ ኤክስፔሪያንስ ተጨምሮበት የምርጫ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ መገመት ስለሚቻል አሁንም ህዝበ ውሳኔ የሚባለው ጭምብል አማራው በወልቃይት ላይ የሚያነሳውን ጥያቄ ይፈታዋል የሚል እምነት የለኝም።

Filed in: Amharic