>

"ኢትዮጵያ እኮ "አብደላ ጊዮርጊስ" የሚባል ቤተ-ክርስቲያን ያለባት አገር ናት።" (ፕ/ር መድሃኔ ታደሰ)

* ችግር የሚሆነው የብሄር ጥያቄን መነሻ አድርጎ ኢትዮጵያን ለመመንዘር ሲሞከር ነው። ኢትዮጵያን መነሻ አድርጎ የብሄር ጥያቄን መመለስ ግን ትክክለኛው መስመር ነው።
“”””””””
* ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጭቆና የመንደርተኛ የብሔር ሊሂቃን ሕዝባቸው ላይ የሚያደርጉት ጭቆና እንጂ፣ አንዱ ብሔር ሌላኛውን ብሄር የጨቆነበት ሁኔታ አልነበረም።
“”””””””
* ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ የሃሳብ አመለካከት አንድነት የወለደው መሪ ሳይሆን ይልቅስ የተቃርኖው ውጤት ነው።
“”””””””
* ከዛሬ አስራ ምናምን ዓመት በፊት “ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን እያዳከመ፣ ራሱንም ከውስጥ እያዳከመ በስተመጨረሻ ኢትዮጵያን የሚያረጋጋ ኃይል ሊያሳጣት ይችላል” የሚል ነገር ተናግሬ ነበር። ይሄ ሃሳቤ አሁንም እንዳለ ነው።
“”””””””””
* ኢህአዴግ ውስጥ ቅቡልነት ያላቸው ኃይሎች እየተፈጠሩ ነው።
“”””””
* ነፃ የመንግስት ተቋማትን ለመፍጠር ገዥው ፓርቲ ቁርጠኛ ካልሆነ የፖለቲካም ሆነ የዲሞክራሲ ሽግግር ማድረግ አይቻልም።
“”””””
* የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት የመፍረስ አደጋ የሚያጋጥመው –
1) ኢህአዴግ የሀገሪቱን የዲሞክራሲ ሽግግር ካዘገየ፣
2) ፅንፈኛ ብሄርተኞች “የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት እንደገና ፈርሶ መሰራት አለበት” የሚል አመለካከት መያዛቸው፣
“”””””””
* ፓርቲና ሀገር መለያየት አለበት። የኢህአዴግ ቀውስ የሀገር ቀውስ መሆን የለበትም።
“”””””””
* ፌዴራሊዝም ያለ ዲሞክራሲ የማይታሰብ ነው። ፌዴራሊዝምን ያለ ዲሞክራሲ ለመተግበር መሞከር ሀገረ መንግስቱን እንደማፍረስ ይቆጠራል።
“”””””””
* “የኦህዴድ ወደ ስልጣን መምጣት ለኢህአዴግ ተደማሪ አቅም ነው” የሚለውን አስተሳሰብ በተወሰነ ደረጃ እቀበለዋለሁ።
“””””””
* የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውስንነት አለበት፤ የኢትዮጵያ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ብቻ አይደለም። ወደ ታሪካችን ስንሄድ አንድነትም  ትስስር ነበር። ኢትዮጵያ እኮ “አብደላ ጊዮርጊስ” የሚባል ቤተ-ክርስቲያን ያለባት አገር ናት።
“”””””””
* ኢትዮጵያን በተመለከተ የተለያዩ ትረካዎች ቢኖሩም፣ ኢሕአዴግ ግን “የብሔር ጭቆና አለ” የሚለውን አንድ ትረካ ብቻ ይዞ ነው የተነሳው።  ስለዚህም የመንግስት ግንባታውን በዚህ የአንድ ወገን ትረካ ላይ ብቻ አረገው።


አዲሱ ክስተት ኢህአዴግን 

የድርጅት ማንነት ቀውስ ውስጥ ሊከተው ይችላል

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ

 

ፕሮፌሰር መድሃኔ ታደሰ በኪንግስ ኮሌጅ ሎንዶን ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ በምስራቅ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ጥልቅና ሰፊ ትንተናዎች በመስጠት የሚታወቁ የሠላምና ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው።

በገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ውስጥ በተከሰተው አዲስ የኃይል ዝምድና፣ የኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ከመንግስት ግንባታ አንፃር የነበረው ዳራና ደረጃ፣ ለዘብተኛ ፖለቲካ፣ እና በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሕዝብ እየቀረቡ ባሉ አዲስ ፖለቲካዊ ትርክቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕይታ እንዲያካፍሉን አነጋግረናቸዋል።

በተጨማሪም ኦህዴድ በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የኦሮሞ ፖለቲካዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት የጀመረውን አዲስ አቅጣጫ ያለውን እድል አካፍለውናል። የቀድሞው የድርጅቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሰነዶች አዲሱ የለውጥ ኃይል ይዟቸው ይቀጥላል ወይንስ አዲስ የፖሊስና የስትራቴጂ ሰነዶች ይቀርፃል የሚለውም ተዳሷል። እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ፍላጎት በአዲሱ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለውን ሥፍራ ተመልክተውታል።

መልካም ንባብ።

ሰንደቅ፡- የኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ከመንግስት ግንባታ አንፃር አሁን የደረሰበትን ደረጃን እንዴት ይመለከቱታል? የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያደረጉት ንግግር ከብሔር ፖለቲካ እድገት ጋር እንዴት የሚታይ ነው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡-ከሀገር ግንባታ አንፃር ከተመለከትነው የብሔር ወይም የመደብ ጭቆናንን ለመተንተን ስትነሳ ጨቋኞቹ ያደረጉትን ብቻ መነሻ አድርገህ መውሰድ ሳይሆን፤ “የጨቋኞቹ” ልጆች የሚባሉት የብሔር የመደብ ጭቆናን ሽረውታል። መፃኤ ዕድላችንን በሚያስማማ መልኩ ነው ታሪክ መተንተን ያለበት። ይህም ሲባል ጭቆናም ከነበረ፣ የብሔር ጨቋኞች ናቸው ከሚባሉት ቤተሰብ የወጡ ልጆች ሕይወታቸውን የሰውለት በእነሱ ደምና ሕይወት ጭቆናው መሰረዙን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ጠቃሚ ነው። ለዚህ ነው ወደፊት ተመልካች ትረካ የሚያስፈልገን። ስለዚህ በቤተሰቦቹ የብሔር ጭቆና አስተሳሰቦች ላይ ወደኋላ ተመልሰህ ልጆቹን ወደጎን አድርገህ፣ አሁንም የምታገለው የብሔር ጭቆና አለ የሚል ብጣሽ የፖለቲካ መንጠላጠያ ይዘህ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። የብሔር ፖለቲከኞች ችግር በብሔር ብርድልብስ ብቻ ተሸፍነው ስለሚንቀሳቀሱ አካባቢያቸውና አገሪቱን በቅጡ አይገነዘቡም።

ወደታሪክ ውስጥ ከዘለቅንም የጨቋኞች ልጆች የሻሩትን ታሪክ ከግምት አለማስገባት ብቻ ሳይሆን፤ በሐይማኖት በብሔርም በባሕልም የተወሳሰበ የመንግስት ግንባታ ነው፣ ኢትዮጵያ የነበራት። የብሔር ወይም የሃይማኖት ስብጥርና ትስስር ወይም ቁርኝትን ወደ ጐን መተው አትችልም። ሶዶ፣ ሐረር፣ ሰላሌ ወይም ወሎን ማየት ይበቃል። ስለዚህ ልዩነቱን ብቻ ነጥለህ ማጮህ ሙሉ ሥዕል አይሰጥህም፤ የተሳሳተ ግንዛቤ ውስጥ ትወድቃለህ። በብሔር ጥያቄ ብቻ ተንጠልጥለህ የምትፈታው የብሔረሰብ ጥያቄ በኢትዮጵያ ውስጥ የለም። ብሔርን ማንጠልጠያ ብቻ አድርጎ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት መንቀሳቀስ የሰነፎች ምርጫ ይመስለኛል። ይህም ሲባል፣ ብዙ ላለማሰብ፣ ላለመጣር፣ ላለማንበብ፣ ላለመመራመር፣ ጠልቆ ላለመረዳት ከመፈለግ የመነጨ አድርጌ ነው የምወስደው።

ሌላው የኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስትና የሀገር ግንባታ የተጠናቀቀው፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ አንድ ሰፊ ሕዝብ ነው። ከዚህ አንፃር የመንግስት ግንባታ ሒደቱ የብሔሮችን ጥያቄ በማጉላት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ሆኖም የብሔር ፖለቲካው ከመንግስት ግንባታ አንፃር ያለው ችግር ከጊዜ ጋር እየተሻሻለ እየተዛመደ ያደገ ከኢትዮጵያዊነት ጋር፣ ከመንግስት ጋር፣ ከሕዝብ ጋር፣ ከታሪክ ጋር ያለውን ትስስር በሚያጎላ መልኩ አልተሰራበትም። ለዚህ ምክንያቱ የብሔር ፖለቲከኞች በድሮ ዓለም የመኖር አዝማሚያ ነው።

እንደውም አብዛኞቹ የብሔር ፖለቲከኞች ቆሞ ቀር ናቸው ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ ማሕበራዊ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ጋር አብረው እየተለወጡ፣ ደረጃ በደረጃ ለውጦቹን እየገመገሙ እያዩ አይደለም የሚገኙት። ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ማሕበራዊ በተለይ የብሔር ቅራኔውን በተመለከተ ብዙ ለውጦች አሉ። ይህንን የለውጥ ሒደት ከግምት ውስጥ ያላስገባ አንድ የብሔር ጥብቆ ብቻ በመያዝ ሌሎቹን ለውጦች ያላማከለ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። የብሔር ጥያቅን ከመመለስ አንፃር የመሬት ላራሹ አዋጅ ከየትኛው ሕገ-መንግስታዊ መግለጫ በላይ ነው። ጨቋኞች ተብለው የሚወነጀሉ ብሔሮች ልጆች ለዚህ ትግል ምን አበረከቱ? ቢባል ግልጽ ነው። ይሄን ግምት ውስጥ ያስገባ ትረካና የፖለቲካ አቋም ነው የሚታየው። ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ናት ተብሎ በተማሪዎች እንቅስቃሴ ተጀመረ፣ ሙሉ ትርጉም የሚሰጥ አባባል አልነበረም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የሁሉም የአርሶ አደሩ የደሃው እና የሌሎችም እስር ቤት ስለነበረች። ቀጥሎ መሬት ላራሹ መጣ፣ ደርግም በቋንቋና በተለያዩ ምክንያት ለብሔረሰቦች ጉዳይ ትኩረት መስጠት ጀመረ፣ ጥናትም አስጀመረ። ይሄ ሁሉ የፖለቲካ ሂደት ነው። በኋላም ኢሕአዴግ መጣ፣ ከእነዚህ ሂደቶች ጋር አብሮ ያደገ የፖለቲካ አቋም፤ የብሔር ፖለቲከኞች ማራመድ አልቻሉም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ፣ በተለይ አክራሪ የብሔር ፖለቲከኞች ሁሌ ብርድ ልብስ ለብሰው ስለሚንቀሳቀሱ የብሔር ብርድ ልብስ ሲሸፍናቸው ራሳቸውን መግለጥናና ማየት አለመቻላቸው ነው። አብደላ ጊዮርጊስ የሚባል ቤተ-ክርስቲያን ያለባት አገር እኮ ናት፤ ኢትዮጵያ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለፓርላማ ያቀረቡት ንግግሮችና የተወሰኑ ቃላቶችና አቋሞች ከላይ የሰፈሩትን ነጥቦች ግምት ውስጥ ያስገባ በሚመስል መልኩ ለዘብ ያለ ወደመሐል የመጡ ናቸው። ምክንያቱም የብሔር ፖለቲካ በኢትዮጵያ ውሱን ነው፤ የኢትዮጵያ ጥያቄ የብሔር ጥያቄ ብቻ አይደለም። ወደ ታሪካችን ስንሄድ አንድነትም ነበር፣ ትስስር ነበር፤ አንዱ ይገፋል አንዱ ይመጣል፤ አንዱ ይወራል አንዱ ያስገብራል፣ ሌላውም በተራው እንደዚሁ። እነዚህን ያላየ የብሔር ፖለቲካ ብቻ ነው የሚያቀነቅነው። ሁለተኛ የብሔር ፖለቲካ ከመንግስትነት ጋር፣ ከሕዝብ ጋር፣ ከባሕልና ከታሪክ ጋር፣ ከዜግነት ጋር፣ ከወደፊት ሀገር ምስረታ ጋር በተቆራኘ መልኩ በአጠቃላይ ተፈትሾ አይደለም የተያዘው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርም ስናዳምጠው፣ የብሔር ፖለቲካን ወደዋነኛ ጠርዙ እንዲመጣ የሚረዳ የተወሰነ እንቅስቃሴ የሚታይበት ሁኔታ ነው የሚሰተዋለው።

ሰንደቅ፡- ዶ/ር አብይ የመጨረሻውን የሥርዓተ-መንግስቱን ስልጣን መያዛቸው፣ ከኦሮሞ ፖለቲካ ጋር እንዴት የሚተነተን ነው? በኢሕአዴግ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ የሚታይ ነው? ወይንስ ከአጠቃላይ የኦሮሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ጋር ተጋሪ ሒደት ነው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ኢሕአዴግ አንድ ትረካ ይዞ ነው የተነሳው። ይኸውም፣ የብሔር ጭቆና አለ፤ ስለዚህም የመንግስት ግንባታው በእሱ ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት የሚል ትረካ ነው የያዘው። ይህ ትረካ አንዱ ሲሆን ሌሎች ትረካዎችም አሉ። ሌሎች ታሪኮችን አያካትትም። የሌሎች ስሜቶችን አያካትትም። የአብዛኞቹ ብሔር ብሔረሰቦች ከመንግስት ጋር ያላቸው ዝምድና ነው፣ ብሔርተኝነት የሚያስብለው። ከሀገርና ከመንግስትነት ጋር ያላቸው ዝምድና የተለያያ በመሆኑ ሁሉንም የሚያካትት ትረካ አይደለም። ይህም ሆኖ ግን፣ በተለይ ለተለጠጠው የኦሮሞ ብሔርተኝነት እድል የሰጠ ትረካ ነው። እንደዛም ሆኖ፤ ኢሕአዴግ የብሔሮችን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ አልመለሰም፤ ሙሉ ለሙሉም ገላጭ በሆነ መልኩ ትረካውን አላስቀመጠም። በሁለቱም ነው ጉድለቱ የሚታየው። የኦሮሞ ፖለቲካም በዚሁ መሐል ነበር የሚዋዥቀው።

አጠቃላይ የኦሮሞ ፖለቲካን ስትመለከት የተለያዩ የኃይልና የአስተሳሰብ ማዕከሎች አሉ። አንዱ በኢሕአዴግ ውስጥ ባለው ማዕቀፍ በተለይ ድርጅቱ ባስቀመጠው የፖለቲካ አቅጣጫ የኦሮሞ ጥያቄ ሊመለስ ይችላል ብሎ ሲንቀሳቀስ የነበረው፤ ኦሕዴድ ነው። ሁለተኛው፣ ትክክለኛ ፌደራሊዝም በቋንቋም፣ በሐብት ክፍፍልም፣ በዴሞክራሲም ሙሉ ለሙሉ የማስተዳደር መብት ይገባናል የሚሉ በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው። ሶስተኛው፣ የአባገዳው ማዕከል ነው። ይህ በአብዛኛው የኦሮሞ ኃይሎችና አስተሳሰቦች የሚያሳትፍ የቅቡልነት ሠርተፊኬት ተቋም ነው። አራተኛው፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ነው። ይኸውም፣ እስከመገንጠል ድረስ የፖለቲካ ጥያቄ የሚያቀነቅን ነው። አምስተኛው፣ ዲያስፖራው የኦሮሞ ኮሚኒቲ ማዕከላት ያሉበት ሲሆን ግማሹ ከአካባቢው አሰላለፍ ጋር በመቀናጀት በኢትዮጵያ ውስጥ የመንግስት ነጠቃን እንደ አማራጭ የማይቃወም ነው። ሌላው፣ የኢትዮጵያ አገራዊ መንግስት ሥርዓት በአበሾች የተገነባ በመሆኑ፣ ይህንን አፍርሶ ከመስራት ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለው የሚያምኑ ናቸው።

ከላይ የሰፈሩት ስድስት የተለያዩ ማዕከላትና አስተሳሰቦች ብዙ ጫፍ ላይ ነው የሚረግጡት። ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ አብዛኛዎቹ በሰለጠነ ፖለቲካ አገር ውስጥ በቀላሉ ሊፈቱ ይችላሉ። ከዚህ አንፃር፣ ከታሪክ አንፃር፣ ከዝምድና አንፃር፣ ከመንግስትነት ከሀገር አንፃር፣ ከኦሮሞ ሕዝብና ሌሎች ከኦሮሞ ብሔር ጋር ካላቸው ግንኙነቶች አንፃር፣ ለዘብ ያለውና ወደ ትክክለኛው መስመር እየመጣ ያለው አሁን በዶክተር አብይ የሚቀነቀነው ነው።

ሰንደቅ፡- የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫው ለኦሮሞ ሕዝብ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው። ይኸውም፣ “የመደብ ጭቆና ምን ያህል አስከፊ እንደሆና አዎንታዊ ለውጥን እንደሚገታ ባለፈው ታሪክህ ካንተ በላይ የሚገነዘብ የለም። በአሁኑም ሰዓት ተመሳሳይ መደባዊ ጭቆና ዳግም በሀገራችን እንዳያቆጠቁጥ ትግልህን አጠንክረህ መቀጠል ይገባሃል።” የሚል ነው። ኢሕአዴግ በ”ብሔር ጭቆና” ላይ የተመሰረትኩ ፓርቲ ነኝ እያለ፤ ኦሕዴድ “የመደብ ጭቆና” ትረካ ማንጸባረቁን እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያንን አንድ ሊያደርግ የሚችል የመደብ ጥያቄን ሲገፋበት አልታየም። የብሔሩን እያጦዘ የመደቡን እያቀዘቀዘ ነው የተጓዘው። ከፖለቲካ ኢኮኖሚው አንፃር ግን የመደብ ጉዳይ አስተሳሳሪ ኃይል ነው። ቀደም ብዬ ካስቀመጥኩት ነጥብ ጋር የሚያያዝ ነው የሚመስለኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ ከብዙ ነገሮች ጋር ተያይዞ ነው የሚታይ እንጂ በራሱ ብቻ ወሳኝ ጥያቄ ተደርጎ የሚወሰድ አይዳለም። ከታሪካችን አንፃር ብዙ ትስስሮች መስተጋብሮች አሉ። አብሮ የመኖር ጉዳይ አለ። አሁን በአብዛኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሬቶች ወይም ክልሎች አሁን ላይ ያሉ ብሔሮች፣ ራሳቸውን በሚገልጽበት መልኩ የተፈጠሩባቸውም አይደሉም። የመፍለስ፣ የመጓዝ፣ የመምጣት፣ የመሄድ፣ የመፈናቀል የታሪካችን አንድ ሂደት ነው። ስለዚህ ታሪካችን የፈተሸ በትክክለኛው ቦታውን ያስቀመጠ የብሔር ፖለቲካ ሲራመድ አልነበረም፤ በተለይ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ።

ሁለተኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጭቆና በመንደርተኛ የብሔር ሊሂቃን ሕዝባቸው ላይ የሚያደርጉት ጭቆናም በአጎራባች ሊሂቃንም ጭምር ነው። የጨቋኞች የዕርስ በርስ ውድድር ነው የነበረው። ስለዚህ አንዱ ብሔር አንዱን የጨቆነበት ሁኔታ የለም። የሊሂቃን ጭቆና ነው የነበረው። የብሔር ሊሂቃን በመንደራቸውም ጨቋኞች ነበሩ፣ የአጎራባች ሊሂቃንም ሲስፋፉ የያዙትን ቦታ ከያዙ በኋላ ዴሞክራሲያዊ ፍትሃዊ ሥርዓት አልመሰረቱም። በዚህ መልኩ ነው መተንተን ያለበት።

ሶስተኛ፣ የመደብ ጥያቄው ኢትዮጵያ ውስጥ ተረሳ። እንደአንድ ሀገር እንደአንድ ሕዝብ አንድነታችንን በተለይ የብሔር ፖለቲካውን መገዳደር ይችል የነበረው የመደብ ጉዳይ ነው። አብዛኛው ድሃ፣ ፍትህ የሌለበት፣ ደሃ አርሶ አደር በመሆኑ ነበር። የኢትዮጵያ ታሪክ እንደውም የመንግስት ስልጣን በሕዝብ ላይ በኃይል መጫኑ ነው የሚገልጸው። እውነተኛ የታሪክ ሚዛኑን አልያዘም ማለት ነው። ኦሕዴድና አቶ ለማ ወደመሐል የመምጣት አዝማሚያ ምን አልባት ይህ ሁኔታ አጠቃላይ ዕይታ ተደርጎበት መሻሻልና የብሔር ፖለቲካን የምናይበት መነጽር የማስተካከል ሂደት ተደርጎ ሊታይ የሚቻል ከሆነ እሰየው ነው። እዚህ ላይ ነው ኢሕአዴግ ውስጥ ያለውን የኃይል ሚዛን እና የአመለካከት መጣረስ በግልፅ የሚወጣው።

ሰንደቅ፡- የእርስዎን ትንታኔ በመዋስ፣ በኢሕአዴግ ድርጅቶች መካከል አሁን ላይ ያለውን የኃይል ዝምድና (power relation) እንዴት ነው የሚረዱት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ኢሕአዴግ ውስጥ ካለው የኃይል ዝምድና ከታሪክ አንፃር ሕወሓት ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበር የነበረው። ቀድሞ ትግል የጀመረ፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙን የቀመረ፣ ሌሎችንም ረድቶ ደርግን በማሸነፉ ስልጣን የያዘ ኃይል ስለነበረ ነው። ይህ ሁኔታ በሂደት እየተቀየረ ነው የመጣው። የመንግስት ስልጣን ውስጥ ሲመጣ የነበረው አብዛኛው ካድሬና ታጋይ በተለያየ መልኩ ስሜቱ ስለተጎዳ ድርጅቱ ውስጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ብሶቶች እየጨመሩ የመጣበት ሁኔታ ነበር።

በኢሕአዴግ ዋናው የኃይል ዝምድና የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሲታይ ሕወሓት ከመንግስት ስልጣን ከተያዘ ከሶስት አመት በኋላ ከአባላቶቹ መካከል በነበረው መቃቃር ጉልበቱና ግለቱ እየዛለ መጣ። ከዛም የኤርትራ ጦርነት መምጣቱን ተከትሎ ሕወሓት ለሁለት ተሰነጠቀ። ይህ ክስተት ድርጅቱን በጣም ያዳከመ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የብአዴን እርዳታ በመጠየቅ ሕወሓት ላይ የበላይነት በሚጎናጸፉበት ሁኔታ፣ የህወሓት የውስጥ አንድነት፣ ጠንካራነት፣ የአይበገሬነት ምስልም አብሮ በሌሎች የኢሕአዴግ ድርጅቶች ዘንድ ተሸረሸረ።

ይህ በሆነበት ሁኔታ ሕወሓት በአንድ ሰው አመራር እጅ በመውደቁ አብዮታዊነቱ፣ የውስጥ አንድነቱ፣ ስሜቱ፣ የትግል ወኔው፣ የድርጅት ፍቅሩ በተወሰነ ደረጃ እየተዳከመ መጥቶ ምርጫ 97 ደረሰ። ምርጫ 97 ሲመጣ ደግሞ በነበረው የተቃውሞ ማዕበል የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ኦሕዴድን አስጠርተው ኢሕአዴግ በአባላት እንዲጥለቀለቅ አደረጉት። እነዚህ ሁሉ ተዳምረው፣ የሕወሓትን ተፅዕኖ ፈጣሪነትና የመሪነት ሚና የሃሳብ አፍላቂነት የጠንካራ ድርጅት ተምሳሌትነት ሚናንን እየሸረሸሩት መጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሲያርፉ በድርጅቱ ውስጥ የኃይል ሚዛኑ መገዳደሩም እየጨመረ መጣ።

ከምርጫ 97 በኋላ ኢሕአዴግ በሚሊዮኖች ያጥለቀለው አባል፣ ከመጀመሪያ የኢሕአዴግ መርሆዎች ጋር ብዙም የማይተዋወቅ ኃይል ነው። እንደውም የሌሎች የኦሮሞ የኃይል ማዕከላት አስተዋፅዖ ተጨምሮበት ኦሕዴድን በኢሕአዴግ ውስጥ የኃይል ማዕከልና ተፅዕኖ ፈጣሪ ደረጃ አድርሰውታል። የፖለቲካ ምህዳሩ የኋልዮሽ ሲጓዝ፣ ከወጣቱ እንቅስቃሴና ከሕዝቡ ብሶት ጋር ተዳምሮ፣ አጠቃላይ አሳታፊ እና የሃሳብ ብዝሃነት ምህዳሩ እየጠበበ ሲመጣ ሕዝቡ የራሱን ስሜቶች በደሎች ችግሮች የሚገልፅበት መንገድ እየተዘጋ ሲመጣ፣ ዋናዎቹ የህዝቡን ስሜት በደል የሚያንጸባርቁ ኃይሎች በይፋ ኢትዮጵያ ውስጥ በማይንቀሳቀሱበት ሁኔታ፣ የኢሕአዴግ ኃይሎችና አባል ድርጅቶች የእነዚህን ሕዝቦች ስሜትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ወኪሎች ሆነው የመጡት። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ቀውስ ተፈጠረ፤ የለውጥ ስሜት ተቀሰቀሰ። ይህንን የለውጥ እንቅስቃሴ ማን ይምራው በሚል መተጋገል ውስጥ በመገባቱ ኦሕዴድ ከለውጥ ፈላጊው ኃይል ጋር በመተሻሸት የለውጡን ጥያቄ በመጨበጥ፣ ኢሕአዴግ ውስጥ ኃይሉን አፈርጥሞ መገዳደር ጀመረ።

በነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ ነው፣ የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት መታየት ያለበት። ምክንያቱም እንደከዚህ ቀደሙ በተባበረ ድምፅ፣ በውስጥ ድርጅታዊ ቀመር ወይም በስምምነት ወይም በሹመት ሁሉም ድርጅቶች ያመጡት አመራር አይደለም። በውስጥ ትግል የመጡ አመራር ናቸው። በውስጥ ፍልሚያ ላይ የውጭ ተጽዕኖ ተጨምሮበት ነው። ይህም ሲባል፣ ኦሕዴድ የእራሱን የኃይል ማዕከልና መሰረት ተጠቅሞ፣ የሕዝቡን ብሶት ተጠቅሞ፣ ግጭቶቹን ተጠቅሞ፣ በድርጅቱ ውስጥ በፖለቲካና በግምገማ የበላይነት ሳይቀዳጅ እንደውም እያቀረቀረ ቆይቶ፤ በምርጫ አሸንፎ ለስልጣን የበቃ ኃይል ነው። ለዚህም ነው በተለየ መንገድ የተገኘ ስልጣን የሚሆነው። የተለያዩ ታክቲኮች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ተጠቅመው ያገኙት ሥልጣን ነው።

ሰንደቅ፡- በትግል የተገኘ ውጤት መሆኑን ካስቀመጡ፤ በቀጣይ በድርጅቱ ላይ ሊኖረው የሚችለው ተፅዕኖ ምን ይመስላል? ድርጅቱ የቀረፃቸው የፖሊሲ የስትራቴጂ የማስፈጸሚያ መመሪያዎች በአብዛኛው የአቶ መለስ የአስተሳሰብ ተፅዕኖዎች ያረፈባቸው ከመሆኑ አንፃር፣ የለውጥ ኃይሉ ሚና በሰነዶቹ ላይ ምን ሊሆን ይችላል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የድሮዎቹ አቶ መለስ የነደፏቸው የኢሕአዴግ ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎች አቋሞች በርግጠኝነት እንደነበሩት ይቀጥላሉ ብሎ ለመናገር አይቻልም። ምክንያቱም በመለስ ውርስና በኢሕአዴግ የሃሳብ አንድነት ላይ ልዩነቶች አሉ። ከላይ እንዳስቀመጥነው፣ ከብሔር ጥያቄ ይነሳል፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ይመጣል፣ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ሊመጣ ነው፣ ምን ዓይነት ሥርዓተ መንግስት ሊመጣ ነው፣ ምን ዓይነት የውጭ ዝምድና ሊመጣ ነው፣ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊመጣ ነው የሚሉትን ስንመለከታቸው፤ አንድ አይነት የሃሳብ አንድነትና ስምምነት እንደድሮ ይቀጥላል ማለት አይቻልም። የዶ/ር አብይ ተስፈንጥሮ መውጣት ኢህአዴግን ለድርጅት ማንነት ቀውስ ዳርጐታል። የግድ ማንነቱን ማስተካከል ሊኖርበት ነው።

ሁለተኛው፣ ኢሕአዴግ በራሱ የአስተሳሰብ ሥርዓት መታወክ ያጋጠመው ነው የሚመስለኝ። መፍትሄውም አንድ ሰው ወደ ስልጣን ማምጣት አይደለም። አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚለው ፍልስፍና ያሸጋግራል የሚባለው፣ ከካፒታሊዝም ወደ ሶሻሊዝም ነው? ከሶሻሊዝም ወደ ኮሚኒዝም ነው ያለነው? በየትኛው ምዕራፍ ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት ነው ሊተገበር የሚችለው? አሁን ካለው የዓለምና የአገሪቱ ሁኔታ ጋር እንዴት ይታያል? የሚለው በፓርቲው ውስጥ ግልፅ አልነበረም። የፓርቲ የበላይነትና የልማታዊ መንግስት የአውራ ፓርቲ አስተሳሰብ ስለሚያጠናክር ብቻ እንደርዕዮተ ዓለም ማዕከላዊ ነጥብ ሆኖ እስካሁን ቆይቷል። ይህንን እንኳን በዶክተር አብይ የሚመራው አዲሱ ኃይል ቀርቶ የቀድሞ የኢሕአዴግ መሪዎች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚገልጹት አይደለም።

ስለዚህ ለዘብተኛ በተወሰነ ደረጃ ሊብራል የህዝቡን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንፃር፣ የሕግ የበላይነትና ፍትህን ከማስፈን አንፃር፣ ኢሕአዴግ የደከመላቸው ብዙ ያልተሳኩለት ነገሮች ላይ ሲታይ ለውጦች መጠበቅ ይቻላል። ስለዚህ የቀድሞዎቹ የኢሕአዴግ የንድፈ ሃሳብ መዛግብት እስካሁንም ውጤታቸው እምብዛም ነው። በተለይ ከፖለቲካ ሽግግር አንፃር ከአሁን በኋላም ቀጣይነታቸው አስተማማኝ አይደለም። አንደኛ የሃሳብ አንድነትና ጥራት በኢሕአዴግ ውስጥ አልተከሰተም። እንደዛማ ቢሆን ዶ/ር አብይ አህመድ ሊቀመንበር ሆኖ አይመረጥም ነበር። ምክንያቱም ኢሕአዴግ ውስጥ በነበረው በአብዮታዊነት፣ በወገንተኝነት፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት፣ ሕዝበኛ ተብሎ በመወቀስ፣ በአብዛኛው ባለፈው ጊዜ ኢሕአዴግ በነበረው ስብሰባ አሸናፊ ያልነበረ በዚህ ደረጃ ብዙ የተወቀሰ ኃይል ነው፤ በፖለቲካ ጥሎ ማለፍ ምርጫ አሸንፎ የወጣው። ይህ ማለት የኢሕአዴግ የሃሳብ አመለካከትና አንድነት የወለደው መሪ አይደለም። በድርጅቱ ውስጥ ያለውን ተቃርኖ የሚያሳይ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ስለዚህም በአጠቃላይ ሲታይ አዲስ ያልረጋ ጅማሮ ነው የሚመስለኝ። አሁንም የሃሳብ አንድነት፣ የድጋፍ አንድነት ስለሌለ ሁሉም ነገር በቀላሉ ይራመዳል ማለት አይደለም። የተለያዩ የኃይልና የአስተሳሰብ ማዕከላት መኖራቸው አይቀርም። የኃይል ማዕከላት ብዝሃነት እየተፈጠረ ነው። በመንግስት ስልጣን ውስጥም የአመለካከትና የኃይል አሰላለፉ ማዕከሎች መኖራቸው አይቀርም። አሁን ያለው ሽግግር ጅማሮ ነው እንጂ በደንብ ድጋፍ ያገኘ መሰረቱ የጠነከረ ለውጥ ነውም ማለት አይቻልም። በመገዳደር የመጣ የለውጥ ጅማሮ ነው ካልን፣ ለውጡ ሊዘልቅ የሚችለው በትግል (Political Contestation) ነው ማለት ነው። ለውጡን ተከትሎ ያለው የኃይል ዝምድና የተለያዩ የኃይል ማዕከላት እርስ በእርሳቸው የሚገዳደሩበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። እንደቀድሞ ከላይ እስከታች በቁጥጥር ስርዓትና አመለካከት ጥራት፣ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት፣ ድርጅቱን ቀጥ አድርገህ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እያየህ የሚጓዙበት ሁኔታ ከአሁን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ አይኖርም።

ሰንደቅ፡- የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊና አንድ የሕወሓት ሥራአስፈፃሚ አባል ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት፣ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ሙሉ ድጋፍ ከፓርቲው እንዳልተደረገላቸው በአደባባይ ተናዘዋል። እርስዎ በሰጡት ትንታኔ ደግሞ ዶክተር አብይ በፖለቲካ ትግል እንጂ በሃሳብ የበላይነት በተባበረ ድምጽ አልተመረጡም ካሉ፤ ገዢው ፓርቲ እንደፓርቲ እና እንደመንግስት ተረጋግቶ የመቀጠሉን ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የአቶ ኃ/ማሪያም ችግር የነበረው የገቡበት ቤት፣ በውርስ የገቡበት አዳራሽ የተከፋፈለ ቤት ሆኖ መገኘቱ ነው። አሁንም ቢሆን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ወደ ተለያየ ሩጫ ውስጥ መግባታቸው አይቀርም። ይህ ምን ማለት ነው፣ የዶክተር አብይ ወደ ስልጣን መምጣት በተለምዶ እንደሚደረገው ኢሕአዴግ ውስጥ አስቀድሞ በማዕከል የተወሰነ ውሳኔ አይደለም። በስምምነት በተባበረ ድምጽ ድሮ በዝግ ስብሰባ ብቻ እንደሚደረገው በኢሕአዴግ የፖለቲካ መስፈርት ማለት ከድርጅቱ ፍላጎት ቁመና አንፃር ነበር ሊቀመንበር የሚመረጠው። አሁን በተቃራኒው ነው የሆነው። የግራ ዘመምና ኮሚኒስታዊ አመዳደብ ዓይነት አይደለም። አሁን ኢሕአዴግ ውስጥ የሃሳብ አንድነት በሌለበት ሁኔታ፣ አንድ የጠራ የሃሳብ የበላይነት የያዘ አመለካከት በሌለበት ሁኔታ ኢትዮጵያን የማረጋጋት ሁኔታ የሚቻል አይደለም። ድሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከአንድ ፓርቲ በላይ መሆኑ ግልፅ ስለሆነ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ መድረክ መክፈትና ማጠናከር ነው ወሳኙ። ወደ ኖርማል ፖለቲካ ሂደት ውስጥ መግባት አለብን። በሌሎች አገሮች በተለመደው የፖለቲካ ውድድር።

ኢትዮጵያን ኢሕአዴግ ብቻውን ማረጋጋት እንደማይችል ግልፅ ሆኗል። ኢሕአዴግ እንኳን ኢትዮጵያን እራሱን ማረጋጋት በማይችልበት ደረጃ ውስጥ ደርሷል። ከአስራ ምናምን አመታት በፊት እንዳልኩት ኢሕአዴግ ሌሎቹን እያዳከመ፣ እራሱንም ከውስጡ እየተዳከመ ኢትዮጵያ የሚያረጋጋ ኃይል ሊያሳጣት ይችላል የሚለውን አመለካከት ይዤው የቆየሁት ነው። ውስጡን ማረጋጋት እየከበደው የመጣ ኃይል ሌሎቹን ሊያረጋጋ አይችልም። ማድረግ የሚችለው የፖለቲካ መድረኩን ከፍቶ ሁሉም ይመለከተኛል የሚሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ ሒደት ነው ማስጀመር ያለበት። ይህ እንግዲህ ትልቁ የዶክተር አብይ ሥራ ነው የሚሆነው። በሌላ መልኩ ግንዛቤ መውሰድ ያለበት ኢህአዴግ ውስጥ ቁቡልነት ያላቸው ኃይሎችም እየተፈጠሩ ነው። ስለዚህ ሂደቱ ሁለት መልክ ይዟል።

ከዚህ አንፃር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ያልተለመደ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ አለ። ይኸውም፣ አንደኛ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ሽግግርን ማኔጅ የማድረግ ልምምድ የለንም፤ የፖለቲካ ሽግግር (Political Transition) አድርገን ስለማናውቅ። ሁለተኛ፣ የዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሂደት በቅጡ አናውቀውም። ልምድም ያስፈልገናል። መነጋገርም ያስፈልገናል። መመካከርም ያስፈልገናል። ከዚህ አንፃር ቅድሚያ መሰጠት ያለበት የመንግስት ተቋማት ከፓርቲ ነፃ ሆነው እንዲጠናከሩ መፍቀድ ነው። ኢሕአዴግ ማድረግ የሚችለው የፖለቲካ ምህዳሩን ለመክፈት ነፃ የመንግስት ተቋማት እንዲጠናከሩ ማስቻል ነው። ነፃ የመንግስት ተቋማት ለመፍጠር የገዢው ፓርቲ፣ የሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች የዜጎች ጥረት ታክሎበት ካልተሳካ በስተቀር የፖለቲካም የዴሞክራሲ ሽግግር የማይታሰብ ነው።

ተሽቀዳድሞ ወደ ምርጫ መሄድ በራሱ አደጋ ነው። እነዚህን ተቋማት እንደገና ማዋቀር አለብን፣ ጠንካራና ገለልተኛ ተቋማትን። የኢትዮጵያ የመንግስትነት ቀውስ የሚጀምረው የህግ የበላይነት ባለመኖሩ ነው። ይህንን ችግር ለመፍታት የግድ የፖለቲካ ሒደቱ መፍታታት አለበት። መድረኩ ክፍት መሆን አለበት። መድረኩ ክፍት ሲሆን ግን በተጓዳኝ የመንግስት ተቋማት እንዲጠናከሩ ማድረግ ይገባል። የመንግስት ተቋማትን መወንጀል፣ ማሸማቀቅና ማዋረድ፣ ቅቡልነታቸውን ማሳጣት አደገኛ ነገር ነው። ምክንያቱም የመንግስት መፍረስ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ትላልቆቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች የሚያደርጉ ኃይሎች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ለውጥ ሽግግር ለማድረግ እያመቻቹ አይደለም፣ ከኢሕአዴግ ጀምሮ። ይህ የሚያስከትለው የሥርዓት መፍረስ ብቻ ሳይሆን የሥርዓተ-መንግስቱ መፍረስን ያስከትላል።

ምክንያቱም ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ አንድን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር በሚያላትሙ መስመሮች ላይ የሚዋዥቁ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ። ይሄ ትክክል አይደለም። ሁለተኛ፣ የመንግስት ተቋማትን ከአንድ ሕዝብ ጋር ወይም ወገን ጋር በማገናኘት ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነታቸው እንዲጠፋ የሚያደርጉ የፖለቲካ ኃይሎችም አሉ። ለምሳሌ ለተቋማቱ አሰራር ተጠያቂው ኢሕአዴግ ሊሆን ይችላል። መከላከያውን ለሀገር ውስጥ ጉዳይ የሚጠቀምበት ከሆነ፣ መጠየቅ ያለበት ኢሕአዴግ እንጂ የመከላከያ ተቋም አይደለም። የምትወነጅለውን ቅቡልነቱን የምትነሳውን ተቋም መለየት አለብህ። አደጋው ሁሉም የማይቀበለው ተቋም አድርገህ ስታበቃ፣ እንደሀገር መቀጠል ከባድ ሊሆን ይችላል። መጠየቅ ያለበትን ለመጠየቅ የፖለቲካ አቅጣጫ ማበጀት ይመረጣል።

ሌላው፣ የመንግስት መፍረስ አደጋ የሚያጋጥመው ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲያዊ ሽግግርን ሒደት ባዘገየ ቁጥር ነው። ሌላው፣ የተወሰኑ ብሔርተኞች የኢትዮጵያን መንግስት ሥርዓት እንደገና አፍርሶ መገንባት ነው የሚያዋጣን የሚለው ሲሆን፣ ምንም ያልተጠናበት ከእውቀት የራቀ ከታሪክም ያፈነገጠ አመለካከት መያዛቸው ነው። የፖለቲካ ቁምጥና፣ ሊባል የሚችል። ለምሳሌ በሶማሊያ፣ በየመን እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ አንድ ጊዜ የመንግስት ሥርዓት ከፈረሰ በኋላ ዳግም ወደነበረበት ለመመለስ አልተቻለም። ማስተዋል ይጠይቃል። የኢትዮጵያን ሥርዓተ-መንግስት ዴሞክራሲያዊ አድርጐ ማሻገር አንድ ነገር ነው፣ የማፍረስ አዝማሚያው ግን የጤና አይደለም። የተዳበሉ የሚመስሉትን መለየት ያስፈልጋል።

እኔ እንደሚመስለኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ የዴሞክራሲ ሽግግር፣ የሥርዓት ለውጥ በሰላማዊ ሲቪል በሆኑ እንቅስቃሴ ከአመጽ በራቀ ሁኔታ ማካሄድ የግድ ይላል። የኢትዮጵያ የመንግስት ሥርዓትን ሊያፈርሱ የሚችሉ ትረካዎች ውስጥ መዳከር ግን አደገኛ ነው። ሁለቱን ለያይተን ማየት አለብን። በተያያዘ፣ የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ ችግሮችን ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ለመፍታት መሞከር በተለይ አሁን ካለው የብሔር ፖለቲካ አንፃር አደገኛ ነው። ስለዚህ የሀገር ውስጥ የህዝብ ጥያቄዎችና የፖለቲካ ኃይሎችን የውጭ የፖለቲካ ትስስሮች እንዴት አድርገን ነው መለየት ያለብን የሚለውን ለዶክተር አብይ ወይም ለኢሕአዴግ ብቻ የሚተው ሳይሆን ለአብዛኛው ሕዝብም፣ ተቃዋሚ ኃይሎችም ትልቁ ጥያቄ ይመስለኛል። በተለይ አሁን ከደረስንበት አንፃር ካየነው።

ለምሳሌ ኦሕዴድ የተነሳው የሕዝቡን ጥያቄዎች ሌላ አጀንዳ ካላቸው ፖለቲከኞች ነጥቆ የራሱ አጀንዳ አድርጎ ነው። ይህ ማለት ፖለቲካውን አለዝቦ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን አብዛኛዎቹ ጥያቄዎች መመለስ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድነት ይጠቅማል። ለፖለቲካ ሽግግር ለዴሞክራሲያዊ ለውጥም ሊጠቅም ይችላል። የሕዝብ ችግሮችን ይዘን፣ ጥያቄዎቹን የራሳችን በማድረግ የህዝብ ወኪሎች መሆን ያለብን እኛ ነን የሚል ፉክክር ውስጥ ነው የተገባው። በጣም ጤነኛ ፉክክር ተደርጎ ሊወሰድም ይችላል። ምክንያቱም የህዝብ ጥያቄን ይዞ ዳር የሚያደርሰው ማን ነው የሚለውን ለመመለስ ሕዝብ ምርምር ውስጥ እንዲገባ ስለሚጋብዝ ነው። ስለዚህ ባለፉት ሶስት ወራት ትልቅ ለውጥ የታየበት ነው። የሕዝብ ብሶትና የአካባቢው እጆች፤ የሕዝብ ብሶትና ሀገረ-መንግስቱን የመዳጥ የፖለቲካ ጫፎች ጋር መዳበል ነበር አደጋ የነበረው።

ይህንን ለይቶ በማውጣት ኦሕዴድ በትልቁ ሊሰራ የሚችል ይመስለኛል። ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ በወሳኝ መልኩ በሌሎች ጫፍ በረገጡ ቡድኖች ተቀንቅኖ ከቀጠለ አደጋው የከፋ ነው የሚሆነው። የሕዝቡን ጥያቄ ወደ እራሳችን አምጥተን፣ የሕዝቡን ትክክለኛ ፍትሃዊ ጥያቄ የለውጥ መሪዎች እኛነን። ማለት ተገቢ ነው። ስለዚህ ማነው የለውጡ መሪ ብለው በለውጡ አቅጣጫ ፉክክር ካደረጉ ለሀገሪቷም ጥሩ ነው የሚሆነው። የለውጥ ትረካውን መቆጣጠርና የለውጥ ፈረሱን ማስጫን ወሳኝ የፖለቲካ ትግል አቅጣጫ ሆኗል።

ሰንደቅ፡- በኢሕአዴግ ውስጥ የሃሳብ አንድነት እንደሌለ አስቀምጠዋል። ከዚህ አንፃር በፌደራል መንግስት እና በክልሎች መካከል ሊኖር የሚችለው የኃይል ዝምድና እንዴት ይታያል? የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ከክልሎች ተቆርሶ የተሰጠ መሆኑ እየታወቀ፣ ፓርቲዎቹ ቦታውን ለመያዝ ከፍተኛ መተጋገል ውስጥ ለምን ገቡ? ከዚህ የፖለቲካ ቀውስ ውስጥስ የሚገኙ እድሎች ይኖሩ ይሆን?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- እድሎች አይጠፉም። የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ዋና ችግሩ የነበረው በአንድ ፓርቲ ጡንቻ ውስጥ መውደቁ ነው። ስለዚህም ትክክለኛ ፌደራሊዝም ሊሆን አይችልም። ያ ፓርቲ ማዕከል ላይ ሲዳከም፣ ፌደራሊዝሙ አደጋ ውስጥ ይገባል። ያ ፓርቲ የሃሳብ አንድነትና ጥንካሬ በሚያጣበት ሰዓት የፖለቲካ አለመረጋጋት ያመጣል። ሲጀመር የኢህአዴግ ቀውስ የአገር ቀውስ መሆን የለበትም። አንድ ፓርቲ በተተራመሰ ቁጥር አገር በመላ የሚተራመስ ከሆነ ቅስም ሰባሪ ነው።

አንደኛ፣ ፌደራሊዝም ያለዲሞክራሲ የማይታሰብ ነው። ፌደራሊዝምን አለዲሞክራሲ ለመተግበር መሞከር፣ ፌደራሊዝሙን እና አገረ-መንግስቱን ከማፍረስ አይተናነስም፤ የነበረውም ችግር ይኸው ነው። ሁለተኛው፣ የኢሕአዴግ የበላይነት በክልሎች የኃይል ዝምድና ላይ የራሱን ተፅዕኖ አሳርፏል። ያ ማለት ምንድን ነው? የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ሁለት አቅጣጫ ያለው ፌዴራሊዝም ነው። በአንድ በኩል ያልተማከለ አስተዳደር ወደታች ይዘረጋል፤ የፓርቲ ስልጣን ከላይ ይጭናል። በፓርቲው ነው እንጂ፣ በክልሎችና በማዕከላዊ መንግስት ጋር የኃይል ዝምድና ግንኙነት ላይ የተመሰረተ አይደለም። ይህንን መቀየር አለብን፤ የተሳሳተ ነው። ምክንያቱም ያ ፓርቲ ጠንካራ ሲሆን ትክክለኛ ፌደራሊዝም አይሆንም። የፓርቲ ማዕከላዊነት ስላለ። ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ኢህአዴግ ይሁን ሌላ ፌደራልና ክልል መንግስታት የራሳቸው ዝምድናና መስተጋብር ሊኖራቸው ይገባል። በሕግ የተደነገገ የራሳቸው ግንኙነት መኖር አለበት።

ክልሎች ማዕከል ላይ ተፅዕኖ አልነበራቸውም። ማዕከሉ ላይ ተፅዕኖ አልነበራቸውም። ምክንያቱም ፓርቲው ሁሉንም ነገር ጨምድዶ ስለያዘ ነው። ለፌደራሊዝም አደጋ ነው። ስለሆነም በማዕከልና በክልሎች መካከል ያለው ግንኙነት በሕግ እንጂ በፓርቲ መመራት የለበትም። በአንድ ፓርቲ ካድሬዎች አይደለም ፌደራሊዝም ጸንቶ የሚቆየው። ፓርቲው በመዳከሙ የማዕከል ሆነ የክልል ቀውሶች እያጋጠሙ ነው የሚገኘው። መሆን አልነበረበትም፣ የመንግስት ተቋማት ከፓርቲ ነፃ መሆን ነበረባቸው። የፌደራልና የክልል ማዕከሎች ከፓርቲ ነፃ መሆን ነበረባቸው፤ አሁን በገዢው ፓርቲ ቀውስ የተነሳ የተለየ ነገር እየመጣ ያለ ተሞክሮ ነው፣ እንማርበታለን። ክልሎች እየጠነከሩ ናቸው። ማዕከል ላይ ጣቶቻቸውን መቀሰር ጀምረዋል። ተፅዕኖ ማሳደር እየቻሉ ነው።

እንደአሁኑ በአመጽና እና በለውጥ በወጣቱ ኃይል ባይሆን ይመረጥ ነበር። በሕገመንግስቱ በሥርዓትና በሂደት ቢሆን ኖሮ ይመረጥ ነበር። በውይይትና ሕገመንግስቱን ከመተግበር አንፃር ብንተገብረው ብንማርበት ይሻል ነበር፤ ኢሕአዴግ ግን ይህንን አልፈቀደም። ኢሕአዴግ በተዳከመበት ሁኔታ ውስጥ ክልሎች ተሰሚነታቸውን እና ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል። መቀጠልም አለበት። ሒደቱም ወደ ትክክለኛ ፌደራሊዝም እያደረሰን ይመስለኛል። ጠቅላይነትም፣ አግላይነትም የማይታይበት ፌደራሊዝም ሊሆን ይችላል። አቅጣጫ ተቀምጦለት መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው።

ሰንደቅ፡- የኦሕዴድ የፖለቲካው ፍሬ ህዋስ (Nucleus)፣ በአንድ በኩል የኢሕአዴግ የፖለቲካ እድገት ተደማሪ ማሳያ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ። በሌላ በኩል በኢሕአዴግ ውስጥ እየወጣ ያለ አዲስ ተገዳዳሪ ኃይል ነው የሚሉ አሉ። እነዚህ ክርክሮች ለእርስዎ ምን ትርጉም አላቸው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- ለኢሕአዴግ ተደማሪ አቅም ነው የሚለውን በተወሰነ ደረጃ እቀበለዋለሁ። እንደውም ድንገተኛ ባልታሰበ መልኩ የኢሕአዴግ ፖለቲካና ተቀባይነት በአንድ ደረጃ ከፍ እንዳደረገው ነው የምቆጥረው። ለምንድን ነው? ኦሕዴድ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ቢሆንም ከፖለቲካ ታማኝነት ከፓርቲ ጥቅም ከፓርቲው ፖሊሲዎች ቀኖና ውጪ፣ የሕዝቡን ጥያቄ እንጨምርበት የሚል ዓላማ ያነገበ እንቅስቃሴ ነው ያደረገው። በግርድፍ ሲታይ የህዝቡን ጥያቄ ተቀበለን ለለውጥ እንጠቀምበት የሚል አቅጣጫ ነው፣ ኦሕዴድ የጠየቀው። ይህ የኦሕዴድ ጥያቄ፣ የኢሕአዴግና የኢትዮጵያ ፖለቲካን ወደ አንድ ደረጃ ሊያሸጋግረው የሚችልበት እድል በጣም ሰፊ ነው። ይሄ ክስተት ለህወሓትም ጥሩ ነው። ዞሮ ዞሮ ነገሮች ይቀየራሉ፣ የፖለቲካ እድገትና ሂደት ነው። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ እንደ አዲስ ለመገምገምም ያስችላል።

የሁለተኛው መከራከሪያ ነጥብ፣ ኦሕዴድ እንደአዲስ ተፃራሪ ኃይል ነው የሚባለው ትንተና ተቀባይነቱ ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱም ኦሕዴድ ከኢሕአዴግ ወጥቶ የሕዝቡን ጥያቄ ተገን አድርጎ ስልጣን ላይ ቢወጣ ነጠቃ ነው (state capture)፣ ፀረ-ኢሕአዴግ ነው ማለት ይቻላል። በኢሕአዴግ አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ፣ የሕዝብን ጥያቄ እንደተሸከመ ፈረስ ተንቀሳቅሶ ወደ ተፅዕኖ ፈጣሪነት መምጣቱ፣ ለፓርቲው ኢሕአዴግ ለመሰረተው ሕወሓትም ጥሩ ነው፣ የሚመስለኝ። በበጎ ቢታይና ቢወሰድ ሁሉም አትራፊ የሚሆኑበት ፖለቲካ ለማራመድ ያስችላቸዋል። በተለይ ህወሓት ሙሉ ለሙሉ እንዲለወጥና አዲሱ ምዕራፍ ሌላ አዲስ አመራር እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ አዲስ የትግል ስልት እንዲፈትሽ ሊረዳው ይችላል።

ሌላው፣ የኦሮሞን ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ከማለዘብ አንፃር ወሳኝ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኦሮሞ ፖለቲካ በሁለት የጠርዝ ፅንፍ ውስጥ የሚገኝ ነው። ከዚህ አንፃር ኦሮሞነትን በኢትዮጵያዊነት መነፅር አይቶ ለመፍታት የተመረጠው መንገድ ትክክለኛ ስትራቴጂ አድርጌ ነው የምወስደው። ችግር የሚሆነው፣ የብሔር ጥያቄን መነሻ አድርጎ ኢትዮጵያንን ለመመንዘር ሲሞከር ነው። ኢትዮጵያን መነሻ አድርጎ የብሔር ጥያቄዎችን መመለስ ግን ትክክለኛው መስመር ነው።

ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ሥርዓትም፣ ከፌደራሊዝምም፣ ከብሔር ጥያቄም፣ ከዴሞክራሲ ለውጥም፣ ከኢሕአዴግ የወደፊት አቅጣጫም አንፃር፤ ኢትዮጵያን መነሻ አድርጎ ምላሽ ለመስጠት የመጣው የለውጥ ሒደት በበጎ ተወሰዶ፣ እንደእድል ቢታይ ተመራጭ ነው የሚሆነው።

ሰንደቅ፡- በኦሮሞን ፖለቲካ ውስጥ በመገንጠልና በማጆሪቲ ዲክታተርሺፕ መካከል የሚዋልሉ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ኦሕዴድ ኢትዮጵያን መነሻ በማድረግ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያደርገው የለውጥ ሒደት ላይ ሊኖራቸው የሚችለው ሚና ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የመጣውን እድል በትክክል ከተጠቀምንበት የሁሉም አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ኦሕዴድ የኦሮሞ ፖለቲካን ወደመሐል ለማምጣት የሚያደርገው እንቅስቃሴ የኦሮሞን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካንም ከጠርዝ አስተሳሰብ የመታደግ እድሉ ሰፊ ነው። ይህም ሲባል፣ ከውጭ ኃይሎችም፣ አፍርሰን እንደገና እንሰራለን ባዮችን አለሳልሶ በሰከነ መንገድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ ጤናማ መድረክ የሚገባበትን መደላድልን ጭምር ነው የሚያመጣው። ይህ ሲሆን፣ ፅንፈኝነት፣ ጠላትነት፣ ፀረ-ኢትዮጵያዊነትም ይከስማል። በሕግ የሚመራ፣ የተለመደ፣ እና ዓለም ዓቀፍ አሰራር ወደሚከተል ፖለቲካ ሲገባ የኦሮሞ ፖለቲካ የጠርዝ ጫፎቹ እየዶመደሙ፣ መሐሉ እየደነደነ ጠንካራ እየሆነ ይሄዳል። ውጤቱም፣ ኢትዮጵያዊነትን ያጠናክራል፤ ሰላም ያመጣል፤ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ያዳክማል። ስለዚህም እድሉን በትክክል ከተጠቀምን የምናገኘው ጥቅም ዘርፈ ብዙ ነው።

ሁሉም እንደሚያውቀው የምስራቅ አፍሪካ የደህንነት ቲየሪ (mutual destabilization) እርስ በእርስ መተራመስ ሲሆን፤ ከዚህ አንፃርም ስንመለከተው የኦሮሞ ፖለቲካ ወደመሐል መምጣቱ እርስ በእርስ የመተራመስና የመተነኳኮስ ሁኔታዎችን የማዳከም አቅሙም ከፍተኛ ነው። ከኢትዮጵያና ከአካባቢው የፀጥታ ስስ ብልቶች አንፃር ለውጥ ሊያመጣ የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ነው።

 

ሰንደቅ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር በሰላም ለመወያያት ጥሪ አቅርበዋል። በኤርትራ በኩል የተሰጠው ምላሽ፣ ቅድመ ሁኔታን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ይኸውም ባድመን መጀመሪያ አስረክቡን የሚል ነው። ይህን ጉዳይ እንዴት አዩት?

ፕሮፌሰር መድሃኔ፡- የኤርትራ መንግስት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጎ ምላሽ ያውም በፍጥነት ይሰጣል ብዬም አልገመትኩም። ምክንያቱም፣ የኤርትራ መንግስት የፖለቲካ ካርዶችን ከማቃጠል አንፃር፣ የዶ/ር አብይ መመረጥ ሥጋት ነው። ከላይ ካሰፈርኩት የኦሮሞ የኃይሎችና የኃይል ማዕከላት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ አንዱ ክፋይ ለምሳሌ የአስመራው ኦነግ ነው። ዶ/ሩ የኦሮሞን ፖለቲካ ጥያቄን ወደመሐል በማምጣት በሰለጠነ መልኩ ያውም በኢትዮጵያዊነት መነሻ ለመፍታት ሒደት ላይ ከመሆናቸው አንፃር ከዚህም በላይ በኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ላይ ተደራጅተው ወደ ስልጣን የመጣ ኃይልና ግለሰብ በመሆናቸው፤ በትንሹም ከተሳካላቸው የኤርትራ መንግስት የኦነግን ካርድ በተደራጀው ኃይልና በእሳቸው ላይ ለመጫወት ያለው እድል በጣም ጠባብ ነው የሚሆነው። የኤርትራ መንግስት ለጣልቃ ገብነት የሚሆኑ አስቻይ ሁኔታዎች በሌሉበት ሁኔታ የሰላም ድርድሩን አይደለም፣ የዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆንን በቀናነት ይቀበለዋል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።

ሁለተኛው፣ ከኤርትራ ጋር በመንግስት ደረጃ እርቅ ለማድረግ የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ ከአካባቢው ሀገሮች ፖለቲካ ኢኮኖሚ ጋር መመቻቸት አለበት። ይህ ምን ማለት ነው? የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተመሰረተው አካባቢውን በማነቃነቅ በሚገኝ የተለየ የኢኮኖሚ ጥቅም ላይ ያተኮረ ነው። በኢኮኖሚ ትብብር፣ በንግድ፣ በሽርክና እና በፀጥታ ትብብር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አይደለም።

የኤርትራ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የመነሻ ፅንሰ ሃሳቡ፣ ትልልቆች ውስጣቸው የተከፋፈሉ ሀገሮች የሰፈሩበት፣ ብዙ ሕዝብና ቅራኔ ያላቸው፣ ብዙ የኢኮኖሚ ዕምቅ አቅም ያለበት አካባቢ ውስጥ ያሉ ሀገራት የማድረግ አቅም እየመከነ በሄደ ቁጥር፤ በእነዚህ ሀገሮች ውስጥ የመበጥበጥና የመፍረስ አደጋዎች እየጨመረ ስለሚሄድ፤ በቁጥጥር መዳፍ ውስጥ (Tightly controlled) የምትመራ ትንሽ አገር ትጠቀማለች ይላል። የኤርትራ ብሔራዊ የኢኮኖሚና የፀጥታ ጥቅም ከሀገሮቹ ትርምስ ከሚገኘው የኢኮኖሚ ጥቅም እና የፖለቲካና የፀጥታ የበላይነት የተመሰረተ፣ የተለየ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ትንታኔ ነው የሚከተሉት። ስለዚህም ባሕሪውና አረዳዱ ሙሉ ለሙሉ መቀየር አለበት።

ወደሕዝብ ለሕ

Filed in: Amharic