>

ለአንዳርጋቸው ፅጌ ከታገሉት መካከል ቀዳሚው! (ጌታቸው ሽፈራው)

አሸናፊ አካሉ ይባላል። በእነ ዘመነ ካሴ ክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ ነበር። በዚህ ክስ ስምንት አምት ከአምስት ወርም ተፈርዶበታል።
አሸናፊ አካሉ “ከአንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል” ተብለው ከተከሰሱት ወጣቶች መካከል ነው። ወቅቱ አንዳርጋቸው ታፍኖ ድምፁ የጠፋበት ወቅት ነበር።
እነ አሸናፊ አካሉ አንዳርጋቸውን ምስክር ጠርተው፣ ለሰብአዊ መብቱ ለመታገል ጥረዋል!
እነ አሸናፊ የመንግስት ጠበቃ ነበራቸው። በመሰረቱ ጠበቃ ነበር የመከላከያ ምስክር ዝርዝር ማቅረብ የነበረበት። እነ አሸናፊ 1ኛ ቁጥር ላይ አንዳርጋቸወረ ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት አስቀምጠው ሲመለከት ጠበቃው ደነገጠ። መንግስት የሌላ ሀገር ደህንነትን በሚሊዮን ዶላር ገዝቶ ያመጣውን አንዳርጋቸው ፅጌ የሚባል ሰው መከላከያ መቁጠር ለጠበቃው ቢያስፈራ አይገርምም።  ጠበቃው ደንግጦ አልቀረም። “ይቅርባችሁ!” ብሎ ቢመክራቸው! አላመኑለትም። እነ አሸናፊ አንዳርጋቸውን በመከላከያ ምስክርነት የጠሩት በእሱ ምስክርነት ፍርድ ቤቱ ነፃ ይለቀናል ብለው አይደለም።  እንዲያውም እንደሚብስባቸው አይጠፋቸውም!
ሕጉ በሚለው መሰረት ማንም ሰው በምስክርነት ከተቆጠረ ቀርቦ መመስከር አለበት። በታዕምር ይህ ህግ ከሰራ ደግሞ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት መቅረብ ይችላል። ሰው ያየዋል። እሱም ምስክርነቱን ሳይሆን ፍርድ ቤቱን ተጋፍቶ የደረሰበትን ሊናገር ይችላል በሚል ነው። በመሆኑም ጠበቃቸው “ይቅርባችሁ፣ ማንን እየጠራችሁ እንደሆነ አውቃችሁታል? አብዳችኋል……” ስላላቸው አልተውትም።  ጠበቃው ምክሩን አልሰሙት ሲሉ የወሰደው አማራጭ “እኔ ከደሙ ነፃ ነኝ” ማለትን ነው። አይፈረድበትም! ” የምስክሩን ዝርዝር ራሳችሁ አቅርቡ” አላቸው።
በመሆኑም እነ አሸናፊ በፍትህ ስርዓቱ ባያምኑበትም አንዳርጋቸው ለሕዝብ እንዲታይ፣ ምን አልባትም ፍርድ ቤት ቀርቦ የደረሰበትን በደል እንዲናገር ጥረት አደረጉ። “ከአንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገናኝታችኋል ብላችሁ ክስ መስርታችሁብናል፣ ስለሆነም ለቀረበብን ክስ መከላከያ ምስክር ሊሆነን የሚችለው አቶ አንዳርጋቸው ነው። አቶ አንዳርጋቸው ቀርቦ ስለመገናኘት አለመገናኘታችን ይመስክር” ብለው መከላከያ ምስክር ጠሩት።
መከላከያ አስመዝግቡ ሲባሉ “1ኛ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ!” አሉ እነ አሸናፊ
መሃል ዳኛው ጀሮውን ያመነ አይመስልም። የቱ አንዳርጋቸው ስለመሆኑ ጠየቀ።
አሸናፊም ” የግንቦት 7 ዋና ፀሀፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር ተገንኘታችኋል ተብለን ነው የተከሰስነው፣ አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ መንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛል ተብሎ በመንግስት ቴሌቪዥን ተነግሯል። እሱን መከላከያ ምስክር አድርገመዋል”
መሃል ዳኛው ታረቀኝ “መከላከያ  የሚሆን ሰው አጥታችሁ ነው?”
(እነ)አሸናፊ አካሉ:_ “ከእሱ ጋር ተገናኝታችኋል ስለተባልን  ሊከላከልልን የሚችለው ብቸኛው ሰው እሱ ነው።”
ዳኞቹ ተወያይተው እንዲያስመዘግቡ ተፈቀደ!
በመጀመርያው የምስክርነት ቀን አልቀረበም። ፖሊስ መንግስት ዶክመንተሪ የሰራበትን አንዳርጋቸው ፅጌን “የት እንዳለ አላውቅም” አለ።  ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው  የሞትና የእድሜ ፍርደኛ ስለሆኑ ቃሊቲ ሊታሰር ስለሚችል ለቃሊቲ ትዕዛዝ አስፃፈ። በቀጣዩ ቀጠሮ ቃሊቲ ማዘዧ አልተፃፈልኝም ብሎ ቀጠሮ አራዘመባቸው። ደግመው ማዘዣ ላኩ።  ቃሊቲም ቀጥሎ “እኔ ጋር የለም” አለ።
 ይህ ሁሉ እነ አሸናፊ  ተሰላችተው የአንዳርጋቸውን ምስክርነት እንዲተውት ነው። እንደማይተውት ሲታወቅ ዐቃቤ ሕግ ፍርድቤቱ አቶ አንዳርጋቸው ምስክር ሆኖ እንዳይቀርብ ይታገድልኝ አለ። ታገደለት። እነ አሸናፊ  አካሉ ይግባኝ ጠየቁ።  አቶ አንዳርጋቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ  ይመስክር ተባለ። ቃሊቲ እንዲያቀርበው ትዕዛዝ ተፃፈ። ቃሊቲ እስር ቤት ተከታታይ ቀጠሮዎችን የማይረባ ምክንያት አቅርቦ አንዳርጋቸው ሳይቀርብ ቀረ።
እነ አሸናፊ ሲሰለቻቸው ይተውታል በሚል ነበር። እነ አሸናፊ አልሰለቹም። ዐቃቤ ሕግ ግን ይግባኝ “ቀርቦ ይመስክር” ባለበት ሌላ እግድ ጠየቀ። ምስክርነቱ ታገደ። እነ አሸናፊ ደግመው ይግባኝ አሉ። ተፈቀደላቸው። ቃሊቲ አላቀርብም አለ።………ከዛም ብዙ ሂደቶች ነበር። እነ አሸናፊ አንዳርጋቸው በሕዝብ እንዲታይ ያላደረጉት ጥረት አልነበረም። ድርጅቶች ከታገሉለት ባልተናነሰ እስረኞቹ  ስለ አንዳርጋቸው ሰብአዊ መብት ታግለዋል። አልቀረበም እንጅ! ሕግ ባለመከበሩ!
አሸናፊ አካሉ  የተሰማውን በግልፅ የሚናገር ሰው ነው። ስለ እሱ፣ ስለሌሎችና ስለ ሀገሩ በመናገሩ በእስር ቤቱ አስተዳደሮች ተጠመደ።  የቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ ተገኘለት። ሸዋሮቢት ተወስዶ ተሰቃየ።  በቂሊንጦ ቃጠሎ ክስ ተመሰረተበት። “በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች ፍትህ አይገኝም” የሚለው አሸናፊ አካሉ በአሁኑ ክስ “ጠበቃ አያስፈልገኝም” ብሎ በግሉ ይሟገታል!
አሸናፊ ይህ ሁሉ በደል ደርሶበት አሁንም ብርታቱ የሚገርም ነው!
Filed in: Amharic