>

አፋን ኦሮሞ በግእዝ - ከተከበሩ አንጋፋ ኦሮሞ ጀነራሎች (ግርማ ካሳ)

ጀነራል ካሳዬ ጨመዳና ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ፣ ኢትዮጵያ የሚወዱ፣ ለኢትዮጵያ መስዋትነትን የከፈሉ፣ አሁንም በጦር ሜዳ ባይሆን ለኢትዮጵያ ብልጽግናል ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት የሚተጉ፣ ጀግና የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው።

ጀነራሎቹ በአማራ ክልል ኦሮሞኛ ትምህርት እንዲሰጥ ከጥቂት ሳምንታት በፎት ጥሪ ያቀረቡ ምሁራንና አክቲቪስቶች በመደገፍ ለአቶ ገዱ እንዳርጋቸው፣ ኦሮምኛ በአማራ ክልል በግ እዝ ፊደል እንዲጻፍ ጥሪ አቅርበዋል። ስለ ግ እዝ ሲናገሩ ፣ ጀነራሎቹ ግ እዝ የአገር ቅርስ መሆኑን ገልጸው፣ የአገር ቅርስም ተበብቂ የቆየው በቀላሉ እንዳልሆነ ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለም ያሳስባሉ።

የጀነራሎቹ ደብዳቤ እንሆ

ግልጽ ደብዳቤ
ለተከበሩ አቶ ገዱ አንዳርጋችው

ለአማራ ክልላዊ መንግስት ፕሬዘዳንት

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታችን ይድረስዎት። እርስዎና የክልል መንግስትዎ በዚህ ወሳኝና ፈታኝ ወቅት፣ የአገርንና የሕዝብን ችግር ለመፍታት እያደረጋችሁት ስላላለው ትልቅ መረባረብ ያለንን ትልቅ ምስጋና ለማቅረብ እንወዳለሁ።

በአማራ ክልል የኦሮምኛ ቋንቋ እንደ ትምህርት እንዲሰጥና፣ መጠቀሚያ ፊደሉም፣ የግእዝ ፊደል እንዲሆን የሚጠይቅ ፣ ከጥናታዊ ዝርዝር መረጃ ጋር የተጻፈ ደብዳቤ፣ ለክቡርነትዎ ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች መጻቸውን ሰማንና እኛም ለሀገር እንደሚያስብ አንድ ዜጋ ድጋፋችንን ልንሰጥ አሰብን።

ክቡር ፕሬዘዳንት ፣

ከአጼ ሃይለስላላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ አገራችንና ሕዝባችንን ባለን አቅም ለማገልገል ሞክሪናል። የአገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ደማሽንን አፍሰናል።አጥንታችንን ከስክሰናል። ከኛ በበለጠ ቁጥርቸው ቀላል የማይባሉ ወገኖቻችን የመጨረሻዉን የሕይወት መስዋትነት ከፍለዋል። የኛ የምንለው፣ ባህላችን ቋንቋችን፣ ቅርሳችን ፣ ነጻነታችን ተጠብቆ የኖረው በነጻ አይደለም። ትልቅ ዋጋ ተከፍሎበት ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ የሀገር ቅርስ የሆነው እና ሰፊው የኦሮሞ ሕዝብ የሚናገረው የኦሮሚኛ ቋንቋ በአማራ ክልል እንደ አንድ ትምህርት ቢሰጥ ሕዝብን ከሕዝብ ከከማስተሳሰሩም ባሻገር የአማራ ክልል ዜጎቻችን የኦሮሚኛ ቋንቋ ማወቃቸው በሰፊው የኦሮሚያ ክልል በቀላሉ የስራ እድል ይፈጥርላቸዋል።

ቋንቋ መግባቢያ ነው። ቋንቋ ማወቃችን ይጠቅመናል እንጅ አይጎዳንም። ቋንቋ የልዩነት ምክንያት ሊሆን አይገባም። ዜጎች አቅምና ጊዜ ከፍቀደ ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲያውቁ ማበረታት አስፈላጊ ነው። የበለጠ መቀራረብ፣የበለጠ መግባባት የሚያመጣ ነው።

ከዉጭ ወራሪዎች በደማችን አገራችን ተከላክለናል። ሆኖም ግን ልናሸንፋቸው ያልቻልናቸው ጠላቶች አሉን። የውስጥ ጠላቶች። ዘረኝነት፣ ድህነት፣ መከፋፈልና ጥላቻ። እነዚህን ጠላቶቻችን ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ …..ሳንባባል፣ እንደ ኢትዮጵያዉያን አንድ ሆነን ለማሸነፍ ተረባርበን ካልሰራን እንደ አገር የትም አንደርስም። አገር የምትገነባው በፍቅርና በአንድነት ነው። ኢትዮጵያዉያን እርስ በርስ ስንቀባበል፣ ስንከባበር፣ ስንያያዝ ነው የሚያምርበን። አዎን ኦሮምኛ የኛ ነው። አማርኛ የኛ ነው። ትግሬኛ የኛ ነው። ከኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የኛ ነው። የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው።

ዉድ የተከበሩ አቶ ገዱ

ከዳር ሆነ መተቸት ቀላል ነው። አገርን ማስተዳደር ግን ከባድ ነው። መናገር ቀላል ነው። ተግባር ግን ቀላል ነው። ማፍረስ ቀላል ነው። መገንባት ግን ቀላል ነው።፡መለያየትና መከፋፈል ቀላል ነው ።ማቀራራብና አንድ ማድረግ ከባድ ነው። መጥላት ቀላል ነው። መውደድ ግን ከባድ ነው። ያለብዎት ሃላፊነት ከባድ መሆኑን ጠንቅቀን አናውቃለን። ብርታቱን፣ ጥበቡንና ጥንካሬዉን ፈጣሪ አብዛቶ እንዲችሮት እየተመኘን ፣ ላቀረብናቸው ጥያቄዎች ትልቅ ትኩረት እንደሚሰጡት ተስፋ እያደረግን ለሚሰጡን ቀና ምላሽ ከወዲሁ ልማመሰግን እንወዳለን።

ከታላቅ አክብሮት ጋር

ብ/ጄነራል ካሳዬ ጨመዳ
ብ/ጄነራል ዋሲሁን ንጋቱ

Filed in: Amharic