>

እመዋና እማሙ - የሁሉት ብሄር ሰዎች  (ፋሲል የኔአለም)

የእኛ ቤት በእነ እመዋና እማሙ ቤቶች መካከል ይገኛል። እመዋ የአክሱም ሰው ናት። እመዋ የምንላት እንደ እናት ስለምናያት ነው እንጅ እውነተኛ ስሟ ሌላ ነው፤ ከእመዋ ቤት የገባ ሁሉ እንደ ልቡ በልቶና ጠጥቶ ይወጣል፤ የእመዋ ጠላ ይባላል። ወጧም ግሩም ነው። በቀኝ በኩል ደግሞ  እማሙና ባለቤታቸው ይኖራሉ። እማሙ የሆድሮጉድሩ ሰው ናቸው።  እማሙ አንድ የጎጃም ሰው አግብተው አዲስ አበባ ሲኖሩ ቆይተው  በሸምግልና ጊዜያቸው  ከባላቸው ጋር ወደ ጎጃም መጡ ። የታመመ ሰው ሲጠይቁ መቼም ወደር የላቸውም።
ነፍሱን ይማርና የእመዋ ባል፣ አያ ተሻለም፣ የአክሱም ሰው ነበር።  አልፎ አልፎ  ከአባቴ ጋር በድንበር  ቢጨቃጨቁም ፍቅራቸው እስከ  ሞት  ዘልቋል። በጣም የሚገርመው፣ ጠዋት ላይ በድንበር “ሊጋደሉ ነው” የተባሉ  ሰዎች፣  ከሰዓት በሁዋላ ቡና አፍልተው አብረው መጠጣታቸው ነው። እናቴ ቡና ታፈላና “ ሂድና እመዋን ጥራት” ብላ ልጅ ትልካለች። እመዋም ቡናዋን ጠጥታ  ትመለሳለች።  አባቴም ቢሆን ከአያ ተሼ ጋር አረቂውን እየተጎነጨ ሲጫወት ያመሻል። አይ የጎጃም አረቂ፣ ሁሉም ቀረ። ከእነ እማሙም ጋር እንዲሁ የድንበር ውዝግብ ነበረን።የእማሙ ባል አዲስ አበባ የኖሩ በመሆናቸው በአገሬው አጠራር ስልጡን ናቸው።   ሰዎችን አይቀርቡም። አብዛኛውን ጊዜ ሬዲዮ በማዳመጥ የጡረታ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ። ከአባቴ ጋር ከተጣሉ በሁዋላ ቂማቸውን ቶሎ መርሳት ስለሚቸግራቸው ኩሪፊያቸው ይረዝማል። ሚሽታቸው እማሙ ግን ቂም የሚባል ነገር አይዙም፤ ኦሮሞ ቂም አይዝም እንዴ?  በጠዋት መጥተው “እንደምን አደራችሁ” ለማለት የሚቀድማቸው ሰው አልነበረም። ይህ ሁሉ የሆነው በደርግ ዘመን ነው።
እመዋና እማሙ በዛሬው ትውልድ ቋንቋ መጤዎች ናቸው።   በአማራ ምድር የሚኖር ትግሬና ኦሮሞ ከአገሬው ሰው ጋር በድንበር እስከመጨቃጨቅ  የሚደርስ መብት ነበረው ብዬ ብናገር ምናልባትም ለዘመኑ ወጣት እንቆቅልሽ ሊሆንበት ይችላል።። ትግሬዋ እመዋና  ኦሮሞዋ እማሙ መጤነት ተሰመቷቸው አያውቅም። አባቴም እነሱን “ መጤዎች” ብሎ ተናግሯቸው አያውቅም። ለእነ እመዋም ሆነ ለአባቴ መሬት የአንድ ብሄር ብቻ ንብረት ሳይሆን የኢትዮጵያ ነው።  የሶስቱ ሰዎች ጸብ  የድንበር እንጅ ከመጤነት ጋር የተያያዘ አልነበረም ። በዚያን ጊዜ “በአማራ መሬት ትግሬና ኦሮሞ ምን አገባው? ወይ አንገታቸውን ደፍተው በሰላም ይኑሩ ካልሆነም ክልሉን ለቀው ይውጡ ብሎ ” ብሎ የሚያስብ ሰው ከነበረ፣ ያ ሰው ከማርስ የመጣ መሆን አለበት።  ዛሬስ ?
ዛሬ ወላጆቼና አያ ተሼም በህይወት የሉም። እመዋ በህይወት ብትኖርም እንደ ድሮው ኢትዮጵያዊነት ተሰምቷት ስለመኖሯ አላውቅም፤ ግን  አይመስለኝም።
ከእነ እማሙ ጋር የነበረው የድንበር ውዝግብ ሁዋላ ላይ መልኩን ቀየረ። አዲስ ተሹሞ የመጣው የወረዳ አስተዳደሪ የእነ እማሙን አንድ ክፍል ቤት  ወርሶ መኖሪያ አደረገው።  ባለስልጣኑም ብዙ ሳይቆይ ደርግ ወደቀና ቤቱን ለቆ ወደ ሌላ አካባቢ ሄደ። ቀጥሎም አንድ የአገው ምድር ሰው የሆነ  የኢህአዴግ ባለስልጣን ገብቶ ተቀመጠ። የድንበር ውዝግቡ በእኛና በኢህአዴጉ ባለስልጣን መካከል ቀጠለ።
እንዲህ አይነቱ ገጠመኝ በተለያዩ አካባቢዎችም ይኖራሉ። በደርግ ዘመን በነበረው የአስተዳደር ስርዓት፣ ህዝቡ  ባይተዋርነት ሳይሰማው  በፈለገው ቦታ ላይ በነጻነት ይኖራል። ህወሃት/ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ግን ነገሮች ተቀያየሩ። “ የእኔ ክልል ” የሚል ነገር መጣና የተለዬ ብሄር ተወላጅ  በአንድ ክልል በነጻነት መኖር  የማይችልበት ደረጃ ተደረሰ። የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል፣ ደቡብ፣ ኦሮምያ ወዘተ “ክልላችሁ አይደሉም” እየተባሉ ተባረሩ።  በአማራ ክልል ያለው ሁኔታ እንደሌለች ክልሎች ባይከፋም፣ መጠቃት የወለደው ስሜት ህዝቡን መራር እያደረገው መምጣቱን መካድ አይቻልም ።  በአጠቃላይ ሲታይ ግን አገሪቱን ያቆማት ማህበራዊ ገመድ እያረጀና እየተበጠሰ በመሄድ ላይ ነው። ክልላዊነቱ በዚህ ከቀጠለ፣  ገመዱ ተበጣጥሶ ፍች የምንፈጽመበት ጊዜ እሩቅ ላይሆን ይችላል። የፍችን ጉዳት ደግሞ የተፋታችሁ ታውቁታላችሁ።
ስለ ጎረቤቶቻችን ተናግሬ ስለ ወላጆቼ ባልናገር ጽሁፌን ጎደሎ ያደርገዋል።
አባቴ የጎንደር  ሰው ነው ። ወገራ። አጎቱ ወደ ጎጃም ተሰዶ ሲኖር በንግድ ስራ የናጠጠ ሃብታምም ሆነ ፤ አባቴም የአጎቱን እግር ተከትሎ ወደ ጎጃም መጣና እሱም ነጋዴ ሆነ። እናቴ  ደግሞ የጎጃም ሰው ናት።  ከልጅነቷ ጀምሮ ያደገችው ከሴት አያቷ ጋር ነው። የሴት አያቷ፣ ባል አስር አለቃ አያሌው ጎበና ቆፍጣና ወታደር ነበሩ፤ የራያ አካባቢ ሰው ናቸው ይባላል። እናቴን አሳደጓት እንጅ አይወልዷትም፤ የእናቴ የስጋ አባት የጎጃም አርሶአደር ናቸው። አስር አለቃ ለወታደራዊ ግዳጅ ከአገር አገር ሲዞሩ እናቴም አብራ ዞራለች፡፡ ከቦረናዎችና ሶማሊዎች ጋር አብራ የልጅነት ጊዜዋን አሳልፋለች።  አፋሮችንም ታውቃቸዋለች።  አስር አለቃ ክቡር ዘበኛ ሆነው  ሲመደቡ ወደ አዲስ አበባ ተዛወረች ፤ ፊደልም ቆጥረች ። በልጅነቴ ስለ ቦረና ወተት፣  ስለ ግመል፣ ስለ አፋር፣ ስለ ልዕልት ተናኘ፣ ስለ ልዕልት ጸሃይ፣ ስለ ክቡር ዘበኛ ወዘተ  ያወኩት ከእናቴ ነው። ስለልጅነት ህይወት አውርታ አትጠግብም፤ በተለይ ስለ ቦረና። በመጨረሻ አስር አለቃ  ወደ ጎጃም ሲዛወሩ እናቴም ጎጃም መኖር ጀመረች። የመማር እድሏም አከተመ።
እናቴ  የ12 ወይም የ13 ዓመት ልጅ እያለች አንድ ኤርትራዊ አስተማሪ ለጋብቻ  ቤተሰቦቿን ጠየቀ። በወጉ ሳይጋቡ መምህሩ ሻዕቢያን ወይም ኢህአፓን ሊቀላቀል ነው አሉ ( አላውቅም) ወደ ኤርትራ ሄደ ። አባቴ ወደዳትና በ16 ዓመቷ አገባት።  አባቴ መደበኛ ትምህርት ሳይማር ማንበብ፣ መጻፍና አራቱን የሂሳብ መደቦች ጠንቅቆ ያውቃል።  የሂሳብ ችሎታው እኔን ብቻ ሳይሆን ብዙዎችን እንዳስደመመ ነበር።  አባቴ እናቴን በሂሳብ ሲበልጣት፣ እሷ ደግሞ እሱን በንባብ፣ በጽሁፍና በመጽሃፍ ቅዱስ እውቀት ( ግብረገብ ስለተማረች) ታስከነዳዋለች። በሁለቱ መካከል የነበረው “እኔ እበልጥ” ፉክክር ለእኛ  የደስታ ምንጫችን ነበር። አባቴና እናቴ የንባብ ፉክክር የሚያደርጉ ከሆነ፣ አባቴ በመወዳደሪያነት የሚመርጠው መጽሃፍ  የክርስቶስ ሰምራን ገድል  ነው። ክርስቶስ ሰምራን በጣም ይወዳታል፤  ገድሏንም በቃሉ ሸምድዶታል። እናቴ ደግሞ በ”ክርስቶስ ሰምራ” መወዳደር አትፈልግም። “ሌላ መጽሃፍ ይምጣ” ትላለች። እሱ “መጽሃፍ መጽሃፍ ነው”  ብሎ እምቢ ይላል። እንደምንም እሽ ካለ ግን በንባብ ይረታል። አባቴ  ሲሸነፍ በጣም ስለሚናደድ እንግሊዝኛ አወዳድሩን ይላል። ታዲያ እንግሊዝኛውን የሚጠይቀው ራሱ ነው።  “ ኮፐርስቲያ፣ ኮፕራክቶ”  ምን ማለት ነው? ይላታል።  እናቴ “አይ ያንተ እንግሊዝኛ ከኮፐረስቲያ አያልፍ ” ብላ ታጣጥለዋለች።  ሳቅ!
ይቅርታ በትዝታ ነጎድኩ። ወደ ተነሳሁበት ሃሳብ ልመለስ። እናቴ በኮረዳ እድሜዋ ቦረና ብትቆይ ኖሮ ምናልባትም የቦረና ሰው ልታገባ ትችል  ነበር። እኔም ግማሽ ኦሮሞ ልሆን እችል ነበር።  ኤርትራዊውን  መምህር ብታገባ ኖሮ ደግሞ ግማሽ ኤርትራዊ ልሆን እችል ነበር። አዲስ አበባ ብትቆይ ኖሮ ደግሞ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም። እናቴን ከአዲስ አበባ አባቴን ደግሞ ከጎንደር አምጥቶ  እኔ አማራ ሆኜ እንድወለድ እቅድ ያወጣው ማን ነው?  እሱ ብቻ አይደለም አወላለዴም እኮ የሚገርም ነው።  እናቴ እኔን አርግዛ ውሻ ነከሳት፤ ጎንደር ከተማ ውስጥ የውሻ መድሃኒት አዋቂ ስለነበሩ አባቴ ከጎጃም ወደ ጎንደር ይዟት ሄደ። መንገድ ላይ ምጥ ተያዘች። “መኪና ውስጥ ሊወለድ ነው” ስባል እንደምንም ጎንደር ደረሰችና  ቡልኮ የሚባል ሰፈር በአጎቴ ቤት ውስጥ ተወለድኩ። አባቴ እንደ አጼ ፋሲል እንድሆን በመመኘት መሰለኝ ፋሲል አለኝ። እኔ ጎንደር ከተማ ውስጥ ከአማራ ወላጆች እንድወለድ በስውር ያቀደው ማንነው? ነው ወይስ በዘፈቀደ ነው የተወለድኩት? ያቀደው አካል ለምን ከሌላ ብሄር ሰው እንድወለድ አልፈለገም? ለምን ጎንደር? ለምን አሜሪካ ወይም ደቡብ አፍሪካ እንድወለድ አልተደለደልኩም? ለምን የእኔ እጣ ፋንታ ጎንደር ተወልዶ ፣ ጎጃም  አድጎ፣  ሆላንድ መኖር ሆነ? ነገስ የት ነው እምኖረው?
የብሄር ፖለቲከኛ በሆነ አጋጣሚ ወይም እኛ በማናውቀው ስውር እቅድ አንድ ቦታ የተወለድክ መሆኑን  ይረሳና፣ ልክ አንተ ፈልገህ እዛ ቦታ ላይ እንደተወለድክ አድርጎ ያስባል። ስትወለድ የብሄርህ ታርጋ  ተለጥፎብህ የተወለድክ አስመስሎ  ያቀርበዋል። ስትሞትም አብሮ የሚከተልህ አስመስሎ ይሰብክሃል። እዚህ ላይ፣ ገና ሞቼ ስላላየሁት የብሄር ታርጋ ሰማይ ቤት ያገልግል አያገልግል አላውቅም። እውነቱን እዛ ስሄድ እጽፍላችሁዋለሁ። ለአሁኑ ግን ብሄር የአዕምሮ የፈጠራ ውጤት (construct) መሆኑን እንቀበል ። የአዕምሮ የፈጠራ ውጤት ደግሞ ሊፈርስ ይችላል (Anything constructed can be deconstructed)::  ብሄርተኝነትም እንዲሁ።
በብሄር ፖለቲካ ስትነደፍ … ( ይቀጥላል)
Filed in: Amharic