>

ኤፈርት ቢወረስ ባይወረስ የትግራይ ህዝብ አይሞቀው አይበርደው! (ናትናዔል አስመላሽ)

ኢፈርት የትግራይ ህዝብ አይደለም! ሆኖም አያቅም! ህወሓት የሚባል የማፍያ የገዳዮች ስርአት እስካለ ድረስ ኢፈርት ለወደፊቱም የትግራይ ህዝብ አይሆንም! ስለዚህ ኢፈርት ቢወረስ ባይወረስ ለትግራይ ህዝብ የሚጨምርለትም የሚቀንስለትም ሳንቲም የለም። ኢፈርት ቢወረስ ፋብሪካው ተነቅሎ አዲስ አበባ ወይንም ሌላ ቦታ ይሄዳል ማለትም አይደልም፣ ኢፈርት መውረስ ማለት በኢፈርት ስም የሚነገድበት የትግራይ ህዝብ የትርፉ ተካፋይ እና ባለቤት ማድረግ ማለት ነው!!! በሌሎች ክልልሎች የሚገኙ የኢፈርት ድርጅቶችም ቢወረሱ ህዝቡን የትርፉ ተካፋይ ማድረግ ማለት ነው፣ ጥረት እና ድንሾ መውሰድ ይቻላል። በመጀመርያ ደረጃ የኢፈርት መቋቋም ትርጉሙ ምንድነው? ኢፈርት የተቋቋመበት ዋና አላማ.
.
1. ለትግራይ ህዝብ ስራ በመፍጠር እድሜ ልኩ የህውሓት ተገዢ ማድረግ እና ጸረ ህወሓት እንዳይነሳ ማድረግ ነው። በኢፈርት ድርጅቶች የተቀጠሩ ሰራተኞች ህወሓትን መቃወም አይችሉም፣ ከተቃወሙ ከስራ ይባረራሉ፣ ከስራ ከተባረሩ ገቢ አልባ ይሆናሉ፣ ገቢ አልባ ከሆኑ ቤተሰብ የማስተዳደር አቅም አይኖራቸውም፣ ባጭሩ ሂወታቸው አደጋ ላይ ነው፣ ሂወታቸው አደጋ ላይ ላለማውደቅ ህወሓትን ከመቃወም ይልቅ ዝምታን ይመርጣሉ። የኢፈርት በትግራይ መገንባት ዋናው አላማ ይህ ነው። ጸረ ህወሓት ተቃውሞን ማፈን፣ ይህ ደግሞ ላለፉት ሃያ አመታት በተግባር ታይተዋል።
2. ህወሓት የተባለ የቤተሰብ ስብስብ በኢኮኖሚ ማደለብ እና የቤተሰብ ስብስብ የሆነውን ህወሓት እድሜ ልኩ ስልጣን ላይ እንዲኖር ወይንም ገዢ ሆኖ እንዲቀጥል ማድረግ ነው። የህውሓት ባለስልጣናትን የአገር ሃብት እንዲዘርፉ መንገድ መክፈት እና ልጆቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን በኢፈርት ገንዘብ በውጭ አገር እንዲማሩ፣ እንዲታከሙ፣ ቤት እንዲገዙ፣ እንዲኖሮ እና የውጭ የባንክ ሂሳብ ከፍተው የመንግስት ለውጥ ሲመጣ አገር ጥለው መኖር እንዲችሉ ማድረግ ነው።
3. በትግራይ ተወዳዳሪ የሆነ ኢንቨስተር እንዳይገባ ማድረግ፣ ነጋዴዎች ተወዳድረው ትልቅም ትንሽም ፋብሪካ እንዳይሰሩ ማድረግ፣ ባጭሩ የኢፈርት አላማ ትግራይ በመኖፖል መግዛት፣ ትንሹን ነጋዴ ወይንም ሃብታም በትልቁ ኢፈርት በተባለ ድርጅት ተወዳዳሪ እንዳይሆን ማድረግ ኢፈርት አላማው ይህ ነው። ኢፈርት አላማው በሌሎች ኢንቨስተሮች ትግራይ ውስጥ ስራ እንዳይፈጠር ማድረግ እና ነጻነት ያለው ዜጋ እንዳይፈጠር ማድረግ ነው።
ታድያ የኢፈርት ድርጅቶች ግብ ይህ ከሆነ፣ ኢፈርት ቢወረስ ባይወረስ ለትግራይ ህዝብ ምኑ ነው? ከኢፈርት ድርጅቶች የተጠቀመ የትግራይ ህዝብ ነው የሚል የትግራይ ተወላጅ ካለ ኢፈርት ካለው ትርፍ ምን ያክል እንደተከፈለው ይንገረን? በኢፈርት ድርጅቶች እንደ ዜጋ፣ እንደ ዜጋ ስል እንደ ትግራዋይ በችሎታው እና በትምህርት ደረጃው ከኢፈርት እና የህወሓት ባለስልጣናት ዘመድ አዝማድ ጋር ተወዳድሮ የተቀጠረ ትግራዋይ ማን ነው?
ህወሓት ኢፈርት የትግራይ ህዝብ ነው ስትል፣ ኢፈርት የትግራይ ህዝብ አይደለም ብሎ ሲከራከር የነበረ አሁን የኢፈርትን መወረስ የሚያስቆጣው ከሆነ እሱ ራሱ ኢፈርት ነው፣ ኢፈርት ማለት ደግሞ ህወሓት ማለት ነው፣ ስለዚህ የኢፈርት መወርስን የሚያስቆጣው ትግራዋይ ካለ እሱ ራሱ ህወሓት ነው። በኢፈርት ድርጅቶች የተመረቱ ምርቶች ትግራይ ውስጥ በእጥፍ እየተሸጡ አዲስ አበባ እና አዋሳ በርካሽ እየተሸጡ ኢፈርት አይወረስም የሚል ትግራዋይ ካለ እሱ ራሱ ኢፈርት መሆን አለበት። የህውሓት ባለስልጣናት እድሜ ለማራዘም ብለህ ኢፈርት አይወረስም ብለህ መከራከር ያስተዛዝባል፣ ሰከን ረጋ በል፣ ኢፈርት የትግራይ ህዝብ አይደለም ሆኖም አያቅም፣ ኢፈርት የስብሓት ነጋ እና ቤተሰቦቹ ነው!!!
Filed in: Amharic