>

<< አብይ አህመድን አትናቁት ፣ እንደ አይጥ ተሹለክልኮ ገብቶ እንደ አንበሳ መናከሱ አይቀርም ።>>  (ቬሮኒካ መላኩ)

የፕሮፓጋንዳ ሀያልነት በአለም ላይ የታወቀ ነው።   የሰው ልጅ አንጎል በፕሮፓጋንዳ ለመነሁለል የተመቻቸ ነው።አዶልፍ ሂትለር << አለም በፕሮፓጋንዳ የምትነዳና ልቧን   እስከ ጥግ ድረስ  የምትከፍት ሴት ነች> > ብሏል   🙂  እዚች ላይ እኔ በዚህ አባባል  ሪዘርቬሽን እንዳለኝ ይታወቅልኝ ። 🙂
የምንኖርባትን ፕላኔታችንን  በፅሁፍ ስራው ለሁለት ገምሶ  ለግማሽ ክፍለ ዘመን ሲያቆራቁሳት የነበረው የአለማችን ባለ ብሩህ አእምሮ ባለቤት  ካርል ማርክስም ስለፕሮፓጋንዳ ተፅእኖ ፈጣሪነት በቲዮሪም በተግባርም በቤተሰብ ህይወቱ  ሞክሮ አሳይቶ አልፏል።
ካርል ማርክስ ከመካከለኛ ገቢ ካላቸው ቡርዣ ቤተሰብ ቢወለድም እሱ ግን እልም ያለ ጠብሻም ነበር።
ራሱንና ቤተሰቡን እንኳን ለማስተዳደር  ገቢ ስላልነበረው ከጓደኛው ከኤንግልስ “ኮይን”  እየፈለጠ ነበር ዳቦ የሚያበላቸው ።
እንደውም “ፈለጣን ” በአለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመረው ካርል ማርክስ ሳይሆን አይቀርም። 🙂
 ታዲያ ማርክስ ቀኑን ሙሉ ሁልቆ መሳፍርት የሌለው ወረቀት ከምሮ ሲቸከችክ ውሎ ማታ ቤቱ ሲገባ ልጆቹን ምንም የሚያበላቸው ዳቦ ስላልነበረ ፕሮፓጋንዳ አብልቶ ያስተኛቸዋል።
ማርክስ በኪሱ ዳቦ ይዞ ቤት  ባይገባም ልጆቹን  ደስ ብሏቸው እንድተኙ ለማድረግ 10 ደቂቃ አይፈጅበትም ነበር ።
ማርክስ የልጆቹን  ፀጉር እያሻሸ ለ 10 ደቂቃ አስማተኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ አዘል ተረቱን ሲለቅባቸው አኒስቴዥያ እንደወጉት ሰው ልጆቹ በደስታ  እንቅልፍ ይዟቸው ጭልጥ ይላል።
አቢይ አህመድ የፕሮፓጋንዳን ሀያልነት በደንብ የተረዳ  እጅግ ብልህ መሪ ነው። ህዝቡን በተስፋ ብቻ እያስፈነጠዘው ነው። ነገር ግን አቢይ የወሬ ሰው ብቻ እንዳይመስላችሁ ።ቀስ እያለ ለስለስ ብሎ እያሳሳቀ የሚወስድ ወራጅ ውሃ ነው።  ኢህአድግ የምትባለውን ድርጅት ቀስ በቀስ ሰርስሮ ገብቶ በቁጥጥሩ ውስጥ አስገብቶ አላማውን የሚያሳካ መሪ ነው። አብይ በምንም ተአምር ለአሻንጉሊትነት የሚመች መሪ አይደለም። ሰውየው እጅግ በጣም አምቢሽየስ ነው።
ስለ አብይ አህመድ እኔ የሚሰማኝ ከ 80 አመታት በፊት ባልቻ አባ ነፍሶ ስለተፈሪ መኮንን(አፄ ሀይለስላሴ)   የተናገሩት አይነት ስሜት ነው።
<< ተፈሪን  አትናቋት ! ተፈሪ እንደ አይጥ ተሹለክሉኮ ገብቶ ሲናከስ ግን እንደ አንበሳ ነው። >>
እኔም የአድዋውን እና የማይጨውን ጀግና  ባልቻን አመስግኜ << አብይ አህመድን አትናቁት ፣ እንደ አይጥ ተሹለክልኮ ገብቶ እንደ አንበሳ መናከሱ አይቀርም ።>>  እላለሁኝ
Filed in: Amharic