>

ፓርላማው እና የአዲስ አበባው ቢሯችን (ደረጄ ደስታ)

አሁን ሰው ፓርላማን እሚያክል ነገር ይረሳል?

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ብዙ ጊዜ “ጥያቄው በሕገመንግሥቱ መሠረት ምላሽ ያገኛል ” – እሚሏት ነገር አለቻቸው። ምነው አሁንስ ይሄን ሕገመንግሥት የት አግኝቼው በጠየቅኩት ማለት አይቀርም። ሕገመንግስቱስ ይገኛል ጥያቄ አመላለሱ ነው የተሰወረው። ሰዋሪዎቹ እንደሚሉት “አንድ ነገር መደበቅ ከፈለግክ ፊት ለፊት አስቀምጠው” እየሆነ ነው እንጂ ነገሩስ ፊት ለፊት ተቀምጧል። የት ነው የተቀመጠው? ፓርላማ ላይ ነዋ! የትኛው ፓርላማ ይሄ እምናውቀው እነ አባዱላ…?
አይደለም አይደለም… አይ የኛ ነገር ! እንደው እንደ ኢትዮጵያኮ የታደለች ሀብታም አገር የለም። ፓርላማን እሚያክል ነገር ትረሳለች። ኢትዮጵያ እኮ ሁለት ፓርላማ ነው ያላት። ልክ እንደ ሴኔት እና ሐውስ ባይሆንም  (እሱን ያጠቃቀሰ) የህዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እሚባሉ ሁለት የተለያዩ ፓርላማዎች አሉ። እና ያ እንደ ሴነት የቃጣው ሁለተኛው ፓርላማ የፌደሬሽን ምክር ቤት ይባላል። በፌደራሉ መንግሥት አባል ክልሎች የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች (ወክሏቸዋል የተባሉ) አባላት የሚወከሉበት ምክር ቤት ነው። እያንዳንዱ ብሔር፣ብሔረሰብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል። አንድ ሚሊዮን ተጨማሪ ሕዝብ ያለው አንድ ወኪል እየተጨመረለት ይሄዳል። እና ይህ ምክር ቤት ሕገ መግንስቱን የመተርጎም ሥልጣን ይኖረዋል። የመንገጠል ጥያቄዎችን የክልልና የማንነት ውዝግቦችንም ሆነ ሌሎች ተመሳሳይ ሕገመንገስታዊ ጉዳዮችን አጣርቶ የመዳኘት ሥልጣን አለው። በዓመት ሁለቴ እየተሰበሰበ “ህገመንግስታዊ” የተባሉ ጉዳዮችን ቆላልፎና ጠላልፎ ይሄዳል። ከዚያ በኋላ “በሕገ መንግሥስቱ መሠረት” ሲባል ይኖራል። እንዲህ እንደዋዛ በጓሮ በር ገብቶ እሚወጣ ተቋም መሆን አልነበረበትም። ከደጅ ያለን ጋዜጠኞች የአዲስ አበባ ቢሯችን ቶሎ ቢከፈትልን እኮ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥተን እንከታተለው ነበር።
ለማንኛውም ፓርላማው አሁን ስብሰባ እየተቀመጠ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አምስተኛ የፓርላማ ዘመን ሶስተኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባውን ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል። ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት ጉባኤው ከሚነገጋገርባቸው እሚከተሉት ይገኙበታል። ( እንግዲህ ልብ ያለው ያስተውል)
አዲስ በተዘጋጀ የመንግስታት ግንኙነት የፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ ተወያይቶ ፀድቃል…ፖሊሲው የፌደራል መንግስት ከክልሎች እንዲሁም ክልሎች ከክልሎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበት የሚዘረዝር መሆኑን ተገልጿል። (ምንድነው እሱ ? ምኑ ነው ምን መሆን ያለበት?)
የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ የህገ መንግስት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ያላቸውን ዘጠኝ የውሳኔ ሀሳቦችንም ተወያይቶ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።( እነዚህ 9 ነገሮች ምንድናቸው? ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለሰሞኑ አንዳንድ ጥያቄዎች ህገመንግሥቱ መልስ ይሰጣል ካሏቸው ነገሮች ውስጥ እዚህ ውስጥ እሚካተቱ ነገሮች ይኖሩ ይሆን?)
ምክር ቤቱ የህገመንግስት ትርጉምና የማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፣ የዲሞክራሲያዊ አንድነትና የህገ መንግስት አስተምህሮ፣ የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የበጀት ድጎማና የጋራ ገቢዎች ድልድል ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ላይ ይወያያል ብለዋል። (ሲወያዩብንም ሆነ ሲወያዩልን እኛም በህዝብነት ጉዳዩን አውቀን አብረናቸው ብንወያይ ደግ ነበር። በተለይ ይሄ የማንነት ጉዳይ እሚባል ነገር የዋዛ አይደለም። ሄዶ ሄዶ መድረሻው አይታወቅም።)
(የማንነት ውሳኔውን ተከትሎም) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፊታችን ሰኞ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር 4ኛው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ የሚካሄድበትን ቀን አስመልክቶ ይወያያሉ ተብሏል። ስለዚህ አወዛጋቢ አካባቢዎች ወዴት እንደሚቆጠሩ ወይም እንደሚደመሩ ይለይ ይሆናል። ምክንያቱም 4ኛው የህዝብና ቤት ቆጠራ ባለፈው የካቲት ወር ይካሄዳል ቢባልም በተለያዩ ምክንያቶች ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ ይታወሳል። አሁን አገሪቱ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሬን በረጋግጄ እከፍታለሁ ልትል መቻሏን ስንገምት የህዝብ ቆጠራው ውጤት እዚያ ላይ ሊጫወት እሚችለውን ድርሻ ሳንዘነጋ ነው። መቸም አሜሪካኖቹ ፖለቲከኞች እሚወዛገቡበትን “ጀሪ ማንደሪንግ” እና “ሪዲስትሪክቲንግ” (Gerrymandering and Redistricting) እሚሏትን፣ ለምርጫ ሲሉ ህዝብና ቀበሌን እንደ ካርታ እየበወዙ እሚያጠጋጓትን እያስታወሰን ነው። ሁለት ፓርላማ ከተኮረጀ ተንኮሉስ ምን ይላል? ከሰዎቹ አቅም በላይ ትልቅ ሥልጣን የተሰጠውን ይህን ምክር ቤት ችላ ማለት አገሪቱን እያመሱ ያሉትን ጉዳዮች ችላ እንደማለትም ሊሆን ይችላል። አብይን መደገፍም ሆነ መቃወም ተቋም ይዘው እንጂ ስተው እየሆነ መሆኑም ደግ አይደለም።
(ወደፊት በአዲስ አበባ ከሚከፈተው የዘኢትዮጵያ ጋዜጣ ቢሮ ለተጠናከረው ዘገባ….)
Filed in: Amharic