>
5:18 pm - Sunday June 14, 5840

ሞትን የማይፈሩ - ሠላምን የማይደፍሩ - የአንድ እናት ሕዝቦች - የሠላምን ፋና - ለዓለም አበሠሩ . !! (አሰፋ ሀይሉ)

— ግን እኛስ ? ? ?   
ይህን የሰሜንና ደቡብ ኮርያ ድንበር ማቋረጥ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ይህ አስፈሪ የፀጥታ ቀጣና — ላለፉት 65 ዓመታት  — በወዲህ እና በወዲያ በኩል ሆነው  — በኒውክሊየር የጦር መሣሪያ ጭምር እየተረጫጩ  — ሁለቱ አንድ የነበሩ ሕዝቦች  — ታይቶ በማይታወቅ ፍጥጫ እና ሥጋት — የሰቆቃ ዓመቶቻቸውን ያስተናገዱበት  — የሰቆቃወ ኤርምያስ ሥፍራ ነው፡፡ አሁን ግን ይህን የዓለማችንን እጅግ አስፈሪ የፀጥታ ቀጣና  — ሁለት ለሠላም ቆርጠን ተነስተናል ያሉ  —  ሁለት ከአንድ የዘር ግንድ አብራክ የወጡ  — የሁለት ዓለም  — የሁለት ኮርያ — የሰሜንና የደቡብ ባላንጣ መሪዎች  — ኪም ጆንግ ኡን እና ሙን ጃኤ-ኢን  — የፍጥጫ ድንበሩን  — ለሠላምታ በተዘረጉ እጆቻቸው  — ሰብረውታል!!
ጦርነትና የጦርነት ሥጋት አስከፊ ጥላውን በጋረደበት በዚህ የኮርያኖች የፀጥታ መስመር  — ሠላም እጅጉን አስፈሪ ነገር ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ድንበሩን አቋርጦ መጨባበጥም የማይታለም ነበር፡፡ ይህ እንኳን ሰው  — በራሪ ወፍ እንኳ — ከአንዱ ድንበር ወደሌላው የማይበርበር  — አሰቃቂ የፍጥጫ ድንበር  — በትናንትናው ዕለት  — ትልቁን የኮርያውያን ጀግኖች ሕዝቦች የሠላም ተስፋ ለዓለም ያስተላለፈ ክስተትን አስተናገደ፡፡ ኡን እና ሙን  —  በዚህ የማይታሰብ ሥፍራ — ለሠላም  —  እና ስለ ሠላም  — እጅ ለእጅ ተጨባበጡ፡፡ ተቃቀፉ፡፡ ትናንት የሚሊዮን ኮርያውያን ህይወት በተቀጠፈባት በዚህች ሥፍራ — የትናንቱን የልዩነት ተጋድሎ ፍቀው  — የወደፊቱን የሠላም ፋና ለመለኮስ ጉዞ የጀመሩ — የሁለት ጀግኖች ሕዝቦች ጀግና መሪዎች  — የማይደፈረውን ሠላምን ደፈሩ!!
ኮርያዎች ይህን የሠላም ታሪክ ለዓለም አበሠሩ፡፡ እኛስ???? እኛስ??? — እኛና ወንድሞቻችን ኤርትራውያንስ — እንዲሁ ከድንበር ወዲህና ወዲያ ማዶ  — በስናይፐሮቻችን እየተያየን — እንደተፋጠጥን — ሠላም እንደራቀን — በሥጋትና በፍራት ታጥረን — ወደፊታችንን በዚሁ ዓይነት እንገፋው ይሆን?? ዛሬ የአንድ እናት ልጆች የሆኑት ጠንካሮቹ የኮርያ ሕዝቦች — በኛ ይብቃ፣ ትውልድ ይዳን ብለው — የሠላምን ፋና ለዓለም አብስረዋል፡፡
እኛስ ለመሆኑ — የአንድ እናት — የአንድ ማህፀን — የአንድ ጀግና ኩሩ የሃበሻ ልጆች — እኛ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማች፣ እህትማማች፣ ባለጋራ ታሪክ፣ ባለጋራ እሴት፣ ባለጋራ ባህል፣ ባለጋራ ጀግንነት ሕዝቦች — አስፈሪ የሆነብንን ሠላም — እጅ ለእጅ ተጨባብጠን — በፍቅር — ስለፍቅር — ለትውልድ — ለወደፊት አብሮነታችን — ለጋራ ብልጽግናችን — መቼ ይሆን — እንዲህ ጦርነትና ሞትን የማይፈሩት ሕዝቦቻችን — መቼ ይሆን — እንደሠማይ የራቀብንን — አስፈሪ የሆነብንን — ተናፋቂውን ሠላም — በመካከላችን እንዲወርድ — ታላቁን የሠላም፣ የእርቅ፣ የአብሮነትና የወዳጅነት ሠላምታ — ታላቁን የወዳጅነት እጅ — ታላቁን የሠላም እርምጃ — ታላቁን የሠላም ፊሽካ — ለኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ሠላምን ፈላጊ ወንድማማች ሕዝቦች — የምናበስራቸው???
መቼ ይሆን ለመሆኑ የእኛስ መሪዎች — እንደ ኮርያዎቹ ታሪክ ሠሪ መሪዎች — ከተከዜ ድንበር አልፈው — ከዛላምበሣ ድንበር አልፈው— ከኢሮብ ድንበር አልፈው— ከሰንዓፌ ድንበር አልፈው — ከመረብ ድንበር አልፈው — ከማናቸውም ሠው ሠራሽ ድንበር አልፈው — በምድራውያንም — በሠማያውያንም ፊት እጅጉን የተወደደችውን ሠላምን  — ሠላም! ሠላም! ሠላም! ሠላም! ሠላም ለኩሉ!!!  — የሚልተስፋ — ለሕዝባቸው የሚያበስሩት? — መቼ ይሆን ያ ሠላም ሲበሠር በእውን የምናይበት ያ ቀን??? ናፈቀኝ፡፡ ተመኘሁ፡፡ ተመኘን፡፡ መልካሙን ሁሉ ተመኘን፡፡
አምላክ ልቦናችንን በመልካምነት መዓዛ ያውደው፡፡ አምላክ የሃበሻ ሕዝቦችን ልቦና ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ አምላክ ኢትዮጵያን እና የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን ሃገር ኤርትራን እና ሕዝቦቻቸውን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ሠላም ለዓለም ሁሉ ይሁን፡፡
አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic