>

"....መለስን ፎቶ ካላነሱ እዚህ ምን ሊሰሩ መጡ!?” (በያሬድ ይልማ)

ይሄን ፎቶ ዛሬ ሳየው በቅርብ ከሶስት እንግሊዛዊያን ቱሪስቶች ጋር ሆኜ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያንን ለማስጎብኘት ሄጄ በነበረበት ወቅት የሆነውን የሚገርም ትዝብት አስታወሰኝ፡፡
በቱሪዝም ሞያ ላይ አንደመስራታችን፣ በአዲስ አበባ ጉብኝት ወቅት እንግዶችን ወደ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ይዘን ከምንሄድባቸው ምክንያቶች በጥቂቱ፣-
 የቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አንፃር መንበረ ፀባኦት በመሆኑ ለኢትዮጵያ ክርስትና ወሳኝ የቤተክርስቲያ ታሪክ ማሳያ ስለሆነ፣
 በጃንሆይ ትእዛዝ እንደመሰራቱ የካቴድራሉ አርክቴክቸራል አሰራሩ ልዩ ስለሆነ፣
 ልክ ባታ ማርያም፣ እንጦጦ ኪዳነምህረት እና አራዳ ጊዮርጊስ ቤተስኪያን ላፍሪካና ጥቁር ህeህብ ብርሃን ፈንጣቂው እምዬ ምኒሊክ ጋር ጠለቅ ያለ ግላዊም አገራዊም ግንኙነት እንዳላቸው ሁሉ ፤ ይህ የቅድስት ስላሴ ቤተስኪያን ለግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለስላሴ፣ በህይወት ሳሉ ቅዳሴ ታድመው አምላካቸውን ያመልኩበት የነበረ፣ ቤተስኪያኑ ከተጀመረበት ኋላም እስከተጠናቀቀበት እሳቸው የመሩት የግንባታው ታሪክ፣ ከዚያም የአርበኞችን ተጋድሎ
 ከሁሉ በላይ ምእራባዊያንን የሰው ልጅ ካምላክ ሃሳብ የተነሳ አንድ ናቸው እንጂ በቆዳ በዘራቸው አይለያዩ ያሉበት የሊግ ኦፍ ኔሽን ንግግራቸው እስከ (ጣሊያን) ዳግም ወረራ ድል ማግስት ድረስ ያሉ አንኳር ዝክሮች፣ ቀዳማዊ ሃይለስላሴን ማእከል ያደረጉ ስእላዊ መረጃዎች በግደግዳዎቹ ያተካተቱ ስለሆነ፣
 አስገራሚው የቀዳማዊ ሃይለስላሴና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን ከድፍን ግራናይት የተሰራ የአፅማቸው ማረፊያ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ ስላለ፣
 በተለይ ደግሞ ቅድስት ስላሴ በውስጠኛው የመስኮቱ ክፍል እጅግ ልዩ በሆነው የመስታወት ላይ ጥበባዊ አሳሳል (የስቴይንድ ግላስ ) ዘይቤ ፣ እንደ ኦርቶዶክስ እምነት መንበረ ፀባኦትነቷ ፣ የሰውን ዘር አመጣጥ ካዳም ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግስተ ሳባ እስከ ትስአቱ ቅዱሳን፣ እንዲሁም የክርስቶስ ወንጌል ከውልደቱ እስከ እርገቱ ፣ በዚሁ ማራኪ የመስታወት ላይ (የስቴይንድ ግላስ) ዘይቤ ቤተስኪያኑ ላይ ተስሎ ስለሚገኝ፣
 የታላቁ ኢትዮጵያዊ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌ ድንቅ የስላሶች ምሰላ ስራ በውስጡ የያዘ ስለሆነ፣
 እንዲሁም ከተለያዩ የግድግዳ ላይ ቅርፃቅርፆች እስከ ታዋቂ እና ታላላቅ ኢትጵያዊያን አርበኞችና የሃገር ባለውለታዎች የክብር ማረፊያ ስለሆነ ነው ለእንግዶች የጉብኝት አካል አድርገን ልናስጎበኝ ቱሪስት ይዘን ስላሴ ቤተክርስቲያን የምንሄደው፡፡
ታዲያ በቅርብ ጊዜ ይዤያቸው የሄድኳቸው እንግዶች ጎብኚ ቢሆኑም ባጋጣሚ ለአፍሪካ ፖለቲካ ቅርብ ስለነበሩ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ለትግራይ ህዝብ ነፃነት ብለው ስለገቡበት የትግል ጅማሬያቸው፣ ኋላም ስላደረጓቸው የተለያዩ የሃገር ውስጥ ፖለቲካዊ እርምጃዎች ባጠቃላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በሚያስገርም ጥልቀት የሚረዱ፣ አቶ መለስ በአንድ የዩናይትድ ኪንግደም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያቀረቡትን ተቀባይነት ያላገኘ፣ “ከአብታዊ ዲሞክራሲ” ጋር የተያያዘ ፅሁፍ ይዘት እና ትንተና ሳይቀር የሚያውቁ ስለነበር፣ ሟቹን መለስን እንኳን አድንቀው ሃያአራት ሰአት የሚጠበቀውን መቃብሩን ፎቶ ሊያነሱት ይቅርና፣ መሳሪያ በያዙ ወታደሮች መጠበቁን ሲያዩም ፈገግ ብለው ነበር፡፡
በመቃብሩ በኩል ስናልፍ ታዲያ፣ የቤተክርስቲያን ጉብኘታችንን አገባድደን እየወጣን ስለነበር፣ ቀስ እያልን ሁለት ወታደሮች የሚጠብቁትን የመለስን መቃብር፣ እንዲሁም መለስ በህይወት እያሉ ፣ የእንግሊዛዊውን ፖለቲከኛ የዊሊያም ሄግን መፅሐፍ እንደያዙ የሚታየውን ፎቶ ገርመም አድርገው ሲያልፉ፣ ከጠባቂ ወታደሮቹ አንዱ መሳሪያውን እንደያዘ የማስፈራራትም ጭምር በሚመስል አኳኋን ድምፁን ቆፈጠን አድርጎ፣ “ስማ ፈረንጆቹን ፎቶ አንሱ በላቸው!” አለኝ፣ “አይ ማንሳት ስላልፈለጉ ነው ወዳጄ!” ብዬ ስመልስለት ተናዶ “ መለስን ፎቶ ካላነሱ ታዲያ እዚ ምን ሊሰሩ መጡ፣ ይዘህ ውጣ ከዚህ!” ብሎ ተቆጣኝ! ያው ባጠመንጃ አይደል እሺ ብዬ እየወጣሁ፤
“እንደው እኛ እራሳችን እንኳን እዚህ ነዋሪዎቹ ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ እያለ የዚህን ሟች ሬሳ ለምን ይሆን የሚጠብቁት” ብለን እንደምንገረም እነኚህ ወታደሮች ሊገምቱ ይቅርና፣ ጭራሽ ፈረንጅም ሳይቀር እንደነሱ ስለመለስ አስቦ ስላሴ የሚመጣ ይመስላቸዋል ብዬ እየተገረምኩ፣ በትንሹም ቢሆን የኔን ስሜት በሚጋሩኝ ነቃ ያሉ እንግሊዛዊ እንግዶች ዘና እየተሰኘሁ ከቅዱስ ስላሶች ቤት ፣ የመለስን መቃብር ለጠባቂዎቹ ትቼ ወጣሁ! ይኸው ዛሬ ይቺ ፎቶ፣ ትዝ አስባለችኝ፡፡ አይ! “መለስን ፎቶ ካላነሱ ታዲያ እዚ ምን ሊሰሩ መጡ!”
Filed in: Amharic