>
5:28 pm - Sunday October 9, 1003

የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት ብአዴን በአማራ ላይ ያደረሰው ግፍ፣ በደልና መከራ!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ቅኝ ገዢው ፋሽስት ጥሊያን ከኤርትራውያን መካከል የተማረ ሰው እንዳይኖር ተግባራዊ ያደረገውን የትምህርት ፖሊሲ ፋሽስት ወያኔ እንደወረደ በመኮረጅ ከአማራው መካከል የተማረ ሰው እንዳይኖር በባሰ ሁኔታ እየተገበረው ይገኛል። ፋሽስት ጥሊያን የኤርትራ ልጆች ከአራተኛ ክፍል በላይ እንዳይማሩ ያደረገው በእግድ ባወጣው የትምህርት ፖሊሲው ሲሆን ፋሽስት ወያኔ ግን የአማራን ልጆች እንዳይማሩ እያደረገ ያለው በረቀቀና ስልታዊ በሆነ መልኩ ነው።
«አማራ ክልል» የሚባለው የትምህርት ቢሮ አስጠናሁት ባለው ጥናት መሰረት አማራ ክልል በሚባለው ክልል ውስጥ 9310 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶ አሉ። ከነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 8794ቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ የተቀሩት 516ቱ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ናቸው። ከነዚህ ትምህርት ቤቶት መካከል 17 ነጥብ 95 በመቶ የአንደኛ ደረጃና 20 ነጥብ ስድስት በመቶ የሁለት ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች እንደሆኑ የአማራ ክልል ተብዮው ትምህርት ቢሮ በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት ነግሮናል።
ይህ ማለት አማራ ክልል በሚባለው ክልል ውስጥ ካሉት 8794 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 7300 ያህሉ የትምህርት ቤትነት ደረጃን የማያሟሉ ሲሆኑ በክልሉ ካሉት 516 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ደግሞ 413 የሚሆኑት የትምህርት ቤትነት ደረጃን አያሟሉም ማለት ነው።
ልብ በሉ! ይህ ማስረጃ በአማራ ክልል ተብዮው ትምህርት ቢሮ በመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. ከተጠና ጥናት የተገኘ ኦፊሴላዊ ነው። ጥናቱን ተከትሎ የአማራ ጋዜጠኞች ቡድን ወደ ተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተዘዋውሮ የጥናቱን እውነትነት በመስክ ምልከታ ለማረጋገጥ ሞክሮ ነበር።
በመስክ ምልከታው ከተዳሰሱት ትምህርት ቤቶች መካለል «በምዕ/ጐጃም ዞን» ይልማና ዴንሳ ወረዳ የሚገኘው የወንጨር የመጀመሪያ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት አንዱ ነው። በዚህ ትምህርት ቤት የመምህራን ብቃት፣ የቁሳቁስ አቅርቦት በተለይ የመጽሐፍትና ተዛማች የትምህርት መሳሪያዎች እጥረቶችን ማማረር ቅንጦት ነው። የጋዜጠኞች ቡድን በምስል ጭምር እንዳረጋገጠው የዚህ ትምህርት ቤት በርካታ መማሪያ ክፍሎች ሰው ሊቀመጥባቸው የማይችሉና  ለመውደቅ ቀናትን የሚጠብቁ ናቸው። ታዲያ ይህ ክፍሎቹ የወላቀለቁና የቆሙትም ለመውደቅ የቀረው ትምህርት ቤት ተመዝኖ በአጠቃላይ 89 ከመቶ ውጤት በማምጣት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ተብሏል።
እንግዲህ! ክፍሎቹ የወላቀለቁበትና የቆሙትም ለመውደቅ የቀረው ትምህርት ቤት ተመዝኖ በአጠቃላይ 89 ከመቶ ውጤት በማምጣት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ከተባለ ሌሎች አማራ ክልል በሚባለው የወያኔ ግዛት ውስጥ አሉ ከተባሉት 9310 ትምህርት ቤቶት መካከል ደረጃቸውን የጠበቁ የተባሉት 17 ነጥብ 95 በመቶ የአንደኛ ደረጃና 20 ነጥብ ስድስት በመቶ የሁለት ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰብ አይከብድም!
ይህም በመሆኑ በወያኔዋ ኢትዮጵያ ደቡብ ወሎ ኩታበር ወረዳ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ባለፈው አመት የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተፈተኑ 316 ተፈታኞች መካከል ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፍ የተደረጉት 3 ተማሪዎች ብቻ ናቸው። በተመሳሳይ ጊዜ በምስራቅ ጎጃም አምበር ከተማ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተፈተኑ 400 ተፈታኞች መካከል ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ የተደረጉት 4 ተማሪዎች ብቻ ናቸው።
ባለፈው የትምህርት አመት ውስጥ በወያኔዋ ኢትዮጵያ የአስረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ የአማራ ልጆች መካከል ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ የተደረጉት ከ32 በመቶ በታች ናቸው። በጠቅላላ ሀገሪቱ ግን የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተፈተኑ ተማሪዎች መካከል ወደ አስራ አንደኛ ክፍል ያለፉቱ 56%ቱ የሚሆኑት ናቸው። ልብ በሉ ይህ አገራዊ አማካኝ ወደ 56% ዝቅ ያለው ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ የተደረጉት የአማራ ተማሪዎች መቶኛ ዝቅተኛ ስለሆነ አገራዊ አማካኙን ወደታች ጎትቶት ነው። በዚህ መሰረት ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ የተፈቀደላቸው የአማራ ተማሪዎች መቶኛ ሲሰላ በአገር አቀፉ ደረጃ ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ ከተደረጉት ተማሪዎች መቶኛ አኳያ በ24% ያነሰ ነው።
ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ደረጃ የ10ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል የአማራ ተማሪዎችን አሀዝ ወጥቶ የተቀሩት በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የአስረኛ ክፍል ፈተና የወሰዱትን የአገሪቱ ተማሪዎች አማካኝ ሲሰላ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል የተዛወሩት ከአማራ ውጭ ያሉ ተማሪዎች መቶኛ 71 % ነው። ይህ ማለት በአገር አቀፉ ደረጃ ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ ከተደረጉት የተቀሩት የኢትዮጵያ ተማሪዎች አኳያ ሲታይ ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ የተደረጉት የአማራ ተማሪዎች መቶኛ ስሌት በ47% ያነሰ ነው። ከዚህ አሀዝ በላይ በላይ በቀጣዩ የአማራ ትውልድ ሕልውና ላይ እየተፈጸመ ያለን academic genocide ሊያሳይ የሚያስችል ማስረጃ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።
በወያኔዋ ኢትዮጵያ አማራው ከሌላው በተለየ መልኩ ግፍና በደል ደርሶበታል፤ ለሌላው ለይስሙላም እንኳ ቢሆን የተሰጠው «መብት» ለአማራ ግን ተነፍጓል የምንለው ከመሬት ተነስተን አይደለም። ወያኔ አማራ ክልል ሲል በፈጠረውና ብአዴን በሚል በፈጠረውና ለትግራይ በሚያስቡ ወኪሎቹ በሚገዛው ክልል ባጠቃላይ ካሉት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል 83 በመቶው፤ እንዲሁም በክልሉ ካሉት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውስጥ 80 በመቶው የትምህርት ቤት ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ ዳስና ዛፍ ስር ትምህርት የሚሰጡ አእምሮ ማጫጫዎች ናቸው። ባለፈው አመት ብቻ ወደ 11ኛ ክፍል እንዲያልፉ ከተደረጉት የኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል የአማራ ተማሪዎች መቶኛ ሲሰላ ከሌሎች የኢትዮጵያ ተማሪቾ መቶኛ አኳያ በ47% እንዲያንስና ስልታዊ በሆነ መልኩ educational genocide እንዲፈጸምባቸው ተደርገዋል። ይህ ቁጥር ቀላል ነገር አይደለም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች መካከል የአማራ ተማሪዎች መቶኛ ሲሰላ ከሌሎች የኢትዮጵያ ተማሪቾ መቶኛ አኳያ በ47% እንዲያንስና ተደረገ ማለት የነገ ተስፋ የሆኑት ያማራ ልጆች በ47% ይቀንሳሉ ማለት ነው።
ይህ ማለት ነገ የአማራ ሀኪሞች፣ መሀንዲሶች፣ ሕግ አዋቂዎች፣ ወዘተ. . . ቁጥራቸው በ47% ይቀንሳል ማለት ነው። ይህም በመሆኑ የነገው የአማራ ሕይወት ከዛሬው በከፋ መጠን ለአደጋ ተጋላጭ እንዲሆን ተፈርዶበታል። ምንም የማያቁት ለጋዎቹ የአማራ ልጆች በዚህ መልኩ እጣ ፈንታቸው እንዲጨናገፍና የነገ ተስፋቸው እንዲጨልም የተደረገው ጨካኙና የሰው አውሬው ወያኔ «አማራን ከምድረ ገጽ እስክናጠፋው ድረስ መናጢ ድሀና ደንቆሮ አድርገን በምድራዊ ሲኦል እያሰቃየን እንገዛዋለን» ከሚላቸው ቤተሰቦች በመወለዳቸው ብቻ ነው።
የአማራ ተጋድሎን የሕልውና ትግል ነው የምንለው በፋሽስት ወያኔዋ ኢትዮጵያ መጪው የአማራ ትውልድ ተስፋ ስለሌለው ነው። የፋሽስት ወያኔዋ ኢትዮጵያ ለዛሬውም ሆነ ለመጪው ትውልድ የአማራው መታረጃ ቄራ ሆናለች። በትምህርቱ ዘርፍ አይናችን እያየ እየሆነ ያለው ይህ ነው። ፋሽት ወያኔ ያወጀብን educational genocide አላማ የአማራው መጻኢ እድል ችጋር፣ በሽታና ድንቁርና የተንሰራፋበት፤ ወንጀል፣ እስራት፣ ጭቆና፣ ግፍና የኑሮ ጭንቀት የህይወቱ ገጽታ የሆነበት፤ ወያኔ በፍቅርና በደስታ ምድራዊ ገነት ፈጥሮ የህይወትን ሙሉ ጣዕም እየተጎነጨ ሲኖር አማራውን ግን ከገነቱ ቀርቶ ከመካነ-ንስሐው ሳይደርስ ወያኔ ባባጀለት የቁም መቃብሩ ውስጥ ሆኖ በምድራዊ ሲኦል እያቃሰተ ፈጽሞ እንዲጠፋ ማድረግ ነው።
ወያኔ ይህን ሁሉ ግፍና ስቃይ በአማራው ላይ ሲያወርድ የከረመው በአማራው መካከል ብአዴን የሚባል ለትግራይ የሚቆረቆሩ ነውረኞች ድርጅት ጭኖ ነው።  83 በመቶ የሚሆኑ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና 80 በመቶ የሚሆኑ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከደረጃ በታች የሆኑትትን ክልል የሚገዛው ብአዴን በየአመቱ ለአማራ ከተመደበው አመታዊ በጀት መካከል በርካታ ሚሊዮኖችን ባለመጠቀም ወደ ትግራይ ክልል ፈሰስ የሚያደርግ ነውረኛ ቡድን ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የወያኔን አርባኛ ዓመት ድል ያለ የንግሥ በዓል ተከትሎ ነውረኛው ብአዴንም ሕዳር 11 ቀን የ35ተኛ ዓመት ልደቱን እያከበረ ነበር።
ብአዴን ታዲያ ልደቱን ያከበረው የአማራን ሕዝብ ከፍተኛ በጀት ለበዓሉ ማክበሪያ መድቦና ከያንዳንዱ የአማራ ገበሬና ሰራተኛ የግዴታ መዋጮ በመጣል ነበር። ምስኩኑ አማራ ገንዘብ ከማዋጣት በተጨማሪ የብአዴን የልደት በዓል እንዲያጅብም በየቀበሌውና በየመስመሪያ ቤቱ ቀጭን ትእዛዝ ደርሶት ነበር። አማራው የሀገሩንና የራሱን አራጆች ልደት እንዲያከብር፣ ድግስ እንዲያሞቅና ለዲስኩራቸው እንዲያጨበጨብ ጥብቅ ትዕዛዝ የተላለፈለት ሠራተኛው በሚያገኛት ኩርማን ደሞዙ፤ ሌላው ደግሞ ከቀበሌ በሚያገኘው ስኳር፣ ዘይትና በሌሎች መሰረታዊ አግልግሎት በኩል በሚመጣበት ማስፈራሪያ ነው።
የወያኔን አማራ የማጥፋት ፕሮግራሞች ሁሉ ሲያስፈጽም የኖረው የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት ብአዴን የቀበሮ ባህታዊ ሆኖ «አማራን እንዳያንሰራራ አድርገን አከርካሪውን ሰብረን ቀብረነዋል» ለሚለው ፋሽስት ወያኔ መሳሪያ ሆኖ ኖሮ የኖረበትን የግፍ ዘመኑን አማራውን አክብርልኝ ማለቱ በደርግ ዘመን ልጃቸው በደርግ የተገደለባቸው ቤተሰቦች የልጃቸውን አስከሬን ለመውሰድ ሲጠይቁ ልጃቸው የተገደለበትን የጥይት ዋጋ እንዲከፍሉ ይጠየቁት የነበረውን ገንዘብ ያስታውሰናል።
አማራው ሲገደል የኖረው ሳያንሰው የመከራ ዘመኑን በሀሴት ለሚያከብሩት የትግራይ ወኪሎች ገንዘብ እንዲያዋጣ መጠየቁ የቁም ሞትና የበደል በደል ነው። ብአዴኖቹ ኤርትራውያን እነ በረከት ሰምዖንና ሕላዬ ዮሴፍ የብአዴንን ልደት የሚያከብሩት የታገሉለትን የአማራን ውርደት፤ የድህነት፣ የባርነትና የሰቆቃ ሕይወት ለማየት በመታደላቸው ነው። ከዚህ ውጭ ሻዕብያና ወያኔ ብአዴንን የመሰረቱበትን ሕዳር 11ን እና ሕወሓት ተመሰረትሁበት የሚለውንና በትግራይ የሚከበረውን የካቲት 11ን ቀሪው የአማራ ትውልድ የሚያስበው፣ በሃዘን፣ በቁጭትና በንዴት ተሞልቶ ሀያ ሰባት አመታት ሙሉ በብአዴን ፊታውራሪነት ሕወሓት ሲፈጽምበት የነበረውንና እየፈጸመበት ያለውን የዘር የማጥፋት ዘመቻ፣ ገፈፋና ና የተዘረፈውን ሀብቱን በማስታወስ ነው።
ከታች የታተሙት ትምህርት ቤቶች አማራ ክልል በሚባለው ክልል ውስጥ ካሉት 8794 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ከደረጃ በታች ናቸው ከተባሉት 7300 ትምርህት ቤቶች ውስጥ ከፊሎቹንና በክልሉ ካሉት 516 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከል ደግሞ ከደረጃ በታች ናቸው ከተባሉት 413 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተወሰኑት ናቸው።
Filed in: Amharic