>

ፍቱት ያንን ጀግና! (ፋሲል የኔዓለም)

 የአንዳርጋቸው ጽጌ ( አንዲ) የፖለቲካ እምነት እና የኑሮው ሁኔታ ተቀራኒ መሆኑ ሁሌም ይገርመኛል። ሲበዛ ነጻ ሰው ነው፤ ሲበዛ ለሰው ልጅ ነጻነትና ለማህበራዊ ፍትህ ሲጨነቅ የሚውል ሰው ነው።  የመሰለውን በድፍረትና በግልጽ የሚናገር፣  ተንኮል የሚባል ነገር ባጠገቡ ያላለፈበት እጅግ ሲበዛ የዋህ ( ደግ) የሆነ ሰው ነው። ጥሩ ፖለቲከኛ ቢሆንም ፖለቲካን ፖለቲካ ከሚያሰኙት ነገሮች አንዱ የሆነው “ተንኮል” የሚባለው ቅመም የሚጎድለው ሰው ነው። ተንኮል አልባ ፖለቲከኛ ልንለው እንችላለን። ስለግለሰቦች መብትና ነጻነት ያለውን ተቆርቋሪነት ስታይ የጥሩ ሊበራል ምሳሌ አድርገህ ልትወስደው ትችላለህ። አኗኗሩን ስታይ  ደግሞ “ ይህስ ኮሚኒስት እንጅ ሊበራል አይደለም” እንድትለው ያደርግሃል። ስለ ግለሰቦች ህይወት ሲጨነቅ፣ እራሱ ግለሰብ መሆኑን ዘንግቶ ነው። ለግል ህይወቱ    የማይጨነቅ፣ ምን እበላለሁ ምን እጠጣለሁ፣ ምን እለብሳለሁ የማያስጨንቀው ጥሩ ኮሚኒስት ወይም ጥሩ የገዳም መነኩሴ የአኗኗር ዘይቤ የሚከተል ፣ በእምነት ሊበራል በአኗኗር ህይወት ኮሚኒስት የሆነ ሰው ነው።
በ1997 ዓም ወላጆቹ የሰጡትን ቤት አይቼው ነበር። አንድ ክፍል ቤት ነው። ቤቱ ውስጥ  አንድ የሸራ አልጋና የተወሰኑ መጽሃፎች ነበሩ። እዚህ ነው የምታድረው አልኩት? “አዎ” አለኝ።
አንዲ ወደ አውሮፓ ሲመጣ ሆቴል እንዲያዝለት የሚፈለግ ሰው አይደለም። የሆነ ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር፣ የጓደኞቹ ቤት እያለ አንዲን ሆቴል ውስጥ አታገኘውም። አልጋ ባይኖርህ ፍራሽ አንጥፈህለት ብታስተኛው ደስ ብሎት ያድራል። የሚያስደስተው ቤተሰባዊ የሆነ ጨዋታ ነው።
አንድ ጊዜ ለስብሰባ ሲሄድ“ ሰውዬ ኮት ልበስ እንጅ?” አልነው፣ “ ባክህ ተው አንተ ደግሞ” ብሎ አንድ ኮት ፈልገን በግድ አስለብሰን ወደ ስብሰባ ልከነዋል።
አንዲ ቀንና ሌሊት ሲሰራ ቢውል የማይደክመው ሰው ነው። ችግሩ ሁሉም ሰው እንደሱ እንዲሰራ ይጠብቃል፤ ስራውን ካልሰራህ ፊት ለፊት አልሰራህም ብሎ ይነግርሃል።
 አንዲ ስራውን የሚሰራው ወንድሙ በሰጠው አንድ አነስተኛ ክፍል ውስጥ ሆኖ ነው። ሰዎችን እንዳይረብሽ ሌሊቱን ቁጭ ብሎ ሲሰራ ያድራል።
አንዲ የፈለገውን ቢናገርህ ቂም አትያዝበት፣ የፈለከውን ብትናገረውም ቂም አይዝብህም። በጀርባ አያማህም፤ ሊያርቅህ እንጅ ሊጎዳህ አያስብም።
አንዲ ሁሌም በብድር እድሜ እንደሚኖር ይናገራል። የሆነ ነገር ስትለው “ጓደኞቼ ሁሉ  አልቀዋል፤ እኔ የብድር ህይወት ነው የምኖረው” ይልሃል። በጨዋታው ማሃል  ሁሉ የ60ዎቹን የትግል ጓዶቹን ታሪክ ማንሳት ያስደስተዋል።
አንዲ በእሱ ዘመን ስለነበሩት ወጣቶች ጽናትና ፍላጎት ቢናገር አይደክመውም። ይህን የቄሮ፣ የፋኖ፣ የዛሬማ… ትውልድ ስራ ቢሰማ ምን ያክል ሊደሰት እንደሚችል ሳስብ መግለጽ ይከብደኛል።
አንዲ ወያኔን በእጅጉ ይንቃል። ተቀናቃኝን መናቅ ተገቢ ነው አይደለም ሊያከራክር ይችላል፤ እሱን ግን “ወያኔን መናቅህ ትክክል አይደለም” ብላችሁ  ልታሳምኑት አትችሉም። በፍጹም።
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር አንዲን በመፍታት ለለውጥ መዘጋጀቱን በተግባር ማሳየት አለበት። አንዲ የለውጥ ሃዋርያ እንጅ አሸባሪ አይደለም። ፍቱት!
Filed in: Amharic