>
5:16 pm - Monday May 24, 8573

የመለስ ዘረኛ ትርክትና የበረከት ነጭ ውሸት!?! (ሳምሶን ሚካኤል)

የዛሬን አያድርገውና እውቁ የህወሃት ፕሮፓጋንዲስት ተስፋዬ ገ/አብ አንድ አስደንጋጭ እውነት ነግሮን ነበር። እንደ ተስፋዬ ትረካ የህወሃት አንድ ክፍለጦር ሰሜን ሸዋ እንደደረሰ አልዋጋም ይላል። የህወሃት ሰራዊት ለአመታት ‘የሸዋ ገዢ መደብ’ እየተባለ የጥላቻ በፕሮፓጋንዳ ሲጋት ኖሯል። ለህወሃቱ የገበሬ ጦር ቀንድና ጭራ በአዕምሮው ያበቀለላቸው አማሮች የሰሜን ሸዋን አካባቢዎች ሲቆጣጠር ካገኛቸው ኑሮን ለማሸነፍ ከሚባትሉት ምስኪኖች ጋር አልሄድ ይሉታል ። እናም የታሉ ‘ጨቋኞቹ የሸዋ አማሮች?’ ማሰኘቱ አልቀረም። በነገራችን ላይ ይህንን የዕብለት ፕሮፓጋንዳ እስካሁኗ ደቂቃ የሚያስተጋቡ ፣ አንኮበር ወይም ደብረ ብርሃን በወርቅ የተለበጡ ከተሞች የሚመስሏቸው የዴንቨር ተጋዳላዮች አሉ። Aiga Forum እና Tigrai Online   የሚከታተል እንዲህ አይነቱን የክፋት ትርክት ማስተዋሉ አይቀርም።
የህወሃትን የካድሬ ት/ቤት ይመራ የነበረው መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ ይህንን ዘረኛ ትርክት ተጠቅመው የገበሬ ጦራቸውን በቁጣና ተበደልኩ ባይነት ስሜት እያጋሙ አራት ኪሎ ለመግባት ተጠቅመውበታል።  ከዚያ በኋላ የሆነው የአደባባይ ምስጢር ነው። በስመ አማራ ሺዎች ከስራቸውና ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ ተፈናቅለዋል። ኑሯቸውን በእስርና አፈና እሽክርክሪት የፈጁትን ሲከፋም የደረሱበት የማይታወቁትን ግፉአንን ታሪክ ወደፊት ስንሰማ ጆሮአችንን ይዘን መጮሃችን አይቀርም። ያለፉት 27 አመታት ዘረኝነት የወለዳቸው ብዙ አስቀያሚ ግፎች የተፈጸሙባቸው ናቸውና።
እነመለስ ዜናዊ አማራውንና የተቀረውን ኢትዮጵያዊ በበቀል ጅራፍ ሲገርፉ እነበረከት ስምዖን ደግሞ አለም አቀፉ ማህበረሰብ (ኢትዮጵያዊያንም ጭምር) ጉዳቸውን እንዳያይ እጅግ የተጠና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ያካሂዱ ነበር። የሰሞኑን አሳፋሪ እውነት ሳንሰማ ለእረፍት ሀገር ቤት ደርሰው በመጡ ቁጥር ‘ኢትዮጵያ  በፎቅ ልትሰምጥ ነው’ የሚሉን ጀዝባ ላሜቦራዎች በሽ ነበሩ።  በየዕለቱ የምንሰማው በ11% አደግን ዜና የዚህ ውጤት ነው። በዚህ ሰሞን የምናያቸው ጣሪያ አልባ ት/ቤቶች ፣ ባለአንድ ክር  ድልድዮችና የአስከሬን ማንሻ ወሳንሳዎች ለፈረንጆቹ በቺቺኒያና ሀያ ሁለት አፍዝ አደንግዝ የኢኮኖሚ እመርታ ተደርገው ተወሽክተዋል። እንደነዘመዴነህ ንጋቱ አይነት የእኛው ጉዶች በኢኮኖሚስትነት ስም የህዝባችንን መከራ ሸቅጠውበታል።
ዛሬ ‘በአርባ ሰባት መርፌ …’ ሸገርን የተቆጣጠሩት ተጋዳላዮች ባለመዋኛ ገንዳ ቪላዎችና የዱባይ ባንኮች የሚስጥር ደንበኞች ሆነዋል። በመንግስት ወጪ የተገዙ ዘመናዊ መኪኖች ከሽንኩርት ግዢ አንስቶ ቅምጦቻቸውን ወደ እረፍት ቦታዎች ማሽከርከሪያ ይውላሉ። የክፋታቸው ብዛት በጠመንጃቸው ብርታት ለእነሱ ሲያካፋ ለሌላው ከሚከፍለው ግብር እንኳ ተጠቃሚ እንዳይሆን መበቀላቸው ነው። በአፍላ እድሜያቸው የተጋቱትን የዘር ፓለቲካ ‘አብዮታዊ ዲሞክራሲ’ የሚል ጥብቆ አልብሰው ህዝብ ያስለቅሱበታል።
ለማጠቃለል እስከዘመን ፍጻሜ የሚኖር ኢፍትሀዊ ስርዐት እንደሌለ ለገዢዎቻችን ልናስታውሳቸው እንወዳለን። ህጻናት ልጆች ንጹህ ውሀ በማያገኙባት ሀገር ፣ ጣሪያና ግድግዳ የሌላቸው ዳሶች ት/ቤት ተብለው በሚቀለድባት ኢትዮጵያ ሳሞራ የኑስና ጌታቸው ረዳ በጠርሙስ ከመቶ እስከ መቶ ሃምሳ ሺ ብር የሚያወጣ Louis XIII ኮኛክ እየጠጡ የሚኖሩበት ዘመን ሊያበቃ ግድ ይላል።
Filed in: Amharic