>

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን ዲሞክራሲም፣የሕውሃት-ኢሃድግ ጉዳይ አይደለም

  • ዶ/ር አቢይ አህመድ እባክዎት ማስመሰሉን አቁመው በዕውነተኛው ሥልጣንዎ ተጠቅመው፤ምን መቅደም እንደአለበት ደግመው ይመረምሩታል?
  • ቢያውቁም ባያውቁም ነፃነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ ነው፤
  • የመንግሥት(ሕውሃት-ኢሃድግ)ጉዳይ አይድለም።

     አብይ ኢትዮጵያዊ

በምርጫዎ ውጤት ማግስት ለትውውቅ ተብሎ ከቤተ-መንግሥት እንደገቡ፣ተጣድፈውም ይሁን አጣድፈዎት፤ከግቢው ወጡ እና በአራቱም ማዕዘናት ጉዞዎትን ፈፀሙ።እርስዎ ወዲህ ወዲያ ሲሉ እነዚያ በሕዝብ አመፅ ተወግረው ሊዋረዱና በአደባባይ ሊለቀሙ የነበሩት አዛውንቶች የዘመኑ ዘረኞችና ዘራፊ ባለሥልጣናት እንደ አይጥ ውር-ሽር-ጉድ ሲሉ ከተሌቪዥን ላይ ተመለከትን፤ በትዕግስት ”ለኢትዮጵያ ሲባል”ብለንም፣አይጧን አሳለፍናት።ለእርስዎ ሲባል አምጠን ችለን ትከሻችን ግን ሸክሙን አልቻለውም፤በሚሊዮን ስንሰማ ከረምንና ዘረፋው ቢሊዮን አለፈ፣ዓይን አውጥቶ።ምኑ እና ስንቱ ተነግሮ ያልቃል?ዛሬም አይበቃም?

     የሚዘነጋው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመሪዎችና ከባለሥልጣናት የበለጠ ምንም አለው፤ይህን ያልተገነዘቡ ግን ዜጋው ከባዕዳን የበለጠ ምንም የለውምና ሕዝቡን እንደፈለግነው እናደርገዋለን ብለው በጊዜ እና በሕግ ጥላ ሥር ተሸሽገው የፈለጉትን ርምጃ ይወስዳሉ።

    እናም አሁንም ቢሆን፣ሕዝብ ይገደላል፤ይታሰራል፤ይሰደዳል፤ይታፈናል፤ቢያንስ ባለዎት የጠቅላይ ሚኒስቴር አስቸኳይ አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ተጠቅመው ማቆም ሲችሉ አላየሁም አልሰማሁም ሊሉን ከሆነ፣ይቀጥሉበት።እንኳንስ እርስዎ ይቅሩና የመንግሥት ጋዜጠኞችም እንደ ዱሮው አፍ አውጥተው ባይዋሹም መነገር ስሌለበት፣”እርስዎ ስለሚታጠቁት ቀበቶ፣””በየመስኩ ስለተሰማሩት ከብቶች የቀለም ዓይነት፣”ባጠቃላይ ምንም በሰው ልጅ የመኖር እና ያለመኖር ፋይዳ የሌላቸውን ዜናዎች በማቅረብ ላይ ተጠምደዋል።እንዳይገርምዎት ከሚገደሉትና ከሚፈናቀሉት በላይ ግምት እየሰጡ የሚነግሩን፣ወደትግሬ ክልል ስንት ቢሊዮን ብር ለ እንትን እንደተፈቀደና ከብርሃን ፍጥነት ቶሎ ቶሎ ገንዘብ ሲታደላቸው፣ስንሰማ፣እርስዎስ ከየት እንደመጡ እንድንመረምር እንደገና ያስገድዱናል።

     እንደሚያውቁት “ማዘናጋት”በፖለቲካ ጭዋታ ውስጥ ነብስ ያስከፍላል፤ለዚህም ነው በትውውቅ ሰበብ በመዘናጋት በእነእንትና ወጥመድ እርስዎ የሕዝብ ነብስ የሚገብሩት።ዕውነት ይሁንብዎና ከነፃነት በፊት መምጣት ያለበት ነገር አለ ብለው ያምናሉና ነው? ?ብርቱ ጉዳይ አለብኝ ብለው ፣የሕዝብን አደራ ለሞጭላፊ አሳልፈው የሰጡት?እኛ ግን ንደታሰርን፣እየተገደልን፣እየተፈናቀልን ሳለ ነው ትተውን ሲከፋም ወደጅቡቲ የሄዱት? ?ብዙ አስተያት ልሰጥዎ ባይገባኝም፤ውጤቱን ግን ለማሳሰብ ወደድኩ። ከኋላዎት ያለውን ሰበብ እና ምክንያት በእርግጠኝነት እኔ ለማወቅ አለመቻሌ፣አሊያም እርስዎ ራስዎ ለመንገር የሚችሉበት ጠንካራ ሁኔታ ላይ አይደሉም ብዬ ተጠራጠርኩ።ይሁን እንጂ ማንም ለሁለት ጌቶች ሊገዛ ስለማይገባውና የእርስዎ”ምርጫም ” ኢሕአድግ”-ሕውሃት፣ብቻ እንደሆነ አረጋግጠው ልናልና፤አሁን በጥንቃቄ ሕዝብ ጉዳዩን መርምሮ ለመተግበር የእኛው ውሳኔ ሆኗል፦በቀላል አቀራረብ በምሳሌ ሳስቀምጠው።

      በገዳይ እጅ የተያዘ ሰው በሩቁ ለሚያየው አዳኙ:-በገዳዩ እጅ ላይ እንደወደቀ በሩቁ ሆኖ የያዘው ሰው ገዳዩ እንደሆነና እሱም ሳያውቅ፣ሊገድለኝ ነው ብሎ አደጋ ላይ መሆኑን ለማሳወቅ እና ዕርዳታ ለማግኘት፣ገዳዩ ሳያውቅ ለሚረዳው ሰው እንዴት ማሳወቅ ይኖርበታል?.?.?ምክንያቱም ገዳዩም ሊገድለው እንደያዘው እንዳይታወቅበት ልክ ጓደኛው እንደሆነ አስመስሎ ይስቃልና ነው።ይህ ነው ዶክተር አብይ ላይ እየሆነ ያለው፤ቁምነገሩ ፈልጎ ነው ወይስ አይደለም??? ለማለት ዕውነተኛ ሁኔታውን አናውቅም።የፈለግነውን ያህል ብንተነትነውም ዕውነተኛውን ሁኔታ አውቃለሁ የሚል ካለ ውሽታም ብቻ ነው።ሁላችንም በፍፁም አናውቅም፤በመሠረቱ ሠይጣን ዓለምን የሚገዛበት አንደኛው ዓላማ ውሸትን እንደ ዕውነት ማስመሰሉ ነው፤ለውሸቱ መኖሪያ ደግሞ፤ዋና መሳሪያው “ማስመሰል”ብቻ ነው።

     በዘመናችንም በሩቅም ሆነ በቅርብ የምናያቸው ሠይጣናዊ ተግባሮች፣ወንጀሎች፣ቤተ-ሠይጣኖች፣ ቡድኖች፣ድርጅቶች በግልፅ የሚያደርጉት ይህን”ማስመሰልን” ነው።የሰይጣንን ክፉ ተግባራት ሁሉ ከመሠረታቸው ብናይ በ”ማስመሰል”ላይ የተፈጸሙና የሠይጣን ተግባሮች ናቸው፤እሱንም የሚያመልኩ ሁሉ የወንጀሎቻቸው ምንጭ “ማስመሰል” መሆኑን በግልጽ ልንገነዘብ እንችላለን።እናም” እሳቸውን፣ ዶ/ር አቢይ አህመድን”በዕምነታቸው ሰበብ ጉድፍ ፈላልገው ሊያጥላሏቸው የፈለጉት፣አንዱን ሆነው አላገኟቸውም።አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴርን “እስላም” ሲሏቸው፣ክርስቲያን ይሆናሉ፤ወያኔ ሲሏቸው የሕዝብ ሆነው ብቅ ይላሉ፤አሊያም እኛ ነን ያሳደግነው ለሚሉት ትግሬዎቹ ሳይሆኑ የእናታቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን አረጋገጡና ኢትዮጵያዊነታቸውን በአደባባይ በቃላት አረጋገጡ።ሥያሜ ነውና ወላጅ አባት ግን መስማማታቸውን በአደባባይ የተገለጠ ነገር አላየንም አልሰማንም።የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋዛ አይደለምና ማንነትህን እንዴት ታረጋግጥልናለህ ብሎት አፋጠጣቸው፤ በማንነቱ የሚተማመን ገፍቶ እስኪመጣ ይጠብቃል እንጂ በመሰለኝ አይነሳምና ብዙም አልተወራም።የሕውሃት መንግሥት አፈቀላጤ ሲባሉ የሕዝብ ብሶትን በየዓይነቱ ይደረድራሉ፤ አማራም ናቸው ያሉትም ሆነ የእኛ ኦሮሞ ናቸው ብለው የተኩራሩትም ቢሆኑ በዚህ በኩል ሲያዩዋቸው ሌላውን ይሆኑባቸዋል፤የፈረንጁን አሃዝ ስድስት እና ዘጠኝ ቁጥር ሆነው ልብ ይሏል፣እንደየቦታው በምክንያት ማንነታቸውን ይቀያይራሉ።

   አጥብቆ ጠያቂ የናቱን ሞት ይረዳልና፦ከታሪክ መዝገብ የተማሩት ኢትዮጵያውያን፣ ለማን ነው? ብለን በተግባር አይተን ልናረጋግጥ የሚያስችል በቂ ግዜ የለንምና “ሕዝባዊ መንግሥት አሁኑኑ ይቋቋም”ይላሉ።እኩሌታዎቹ ደግሞ፣ቃሉን ሰጥቶናል ፍላጎቱን አሳይቷል ዳሩግን”እሳቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጅ እንዳይሆኑና ሕዝብ በተሳሳተ መንገድ እንዲጠላቸው የሚያደርጉት ፀረ-ኢትዮጵያ የሆኑ የባንዳ የልጅ ልጆች ከበስተጀርባው ስለአሉ ነው፤”ልጆቹ እና ሚስቱን በአጥፍቶ ጠፊነት መያዣ እንዳደረጉበትስ ማን ሰው ጠርጥሮለታል?”ብለው በጥያቄ ከመወጠር ችላ አላሉም።እናም ኢትዮጵያውያን ብለዋልና፣”ከጎናቸው ሆነን ልንረዳቸው ይገባል፤”የሚሉ እንያቸውን ደግፈውታል።

      የእኔ አስተያየት ደግሞ ስለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴራችን አመጣጥ፣አካሄድ እና አቅጣጫ የሚገቡ መሠረታዊ የታሪክ ሐቆች አሉና በጥንቃቄ ገና አልተገነዘብንም ስለዚህም አሁን ልንወስን አይገባም ባይ ነኝ፤ዳሩ ግን በዚህ የለውጥ ማዕበል “ሕዝብ የሱናሚ ጎርፍ ሆኖ ከሚጠራርግህ ፤እንደ +ድንጋይ ክምር ቢናድብህ ይሻላል ይላሉ።የ”የኮንሶ ሕዝብ፦ምክንያታቸውን ሲሰጡ፦”የድንጋይ ክምር ቢናድብህ ሕዝብ ተባብሮ ያነሳልህል፦ሕዝብ ቢናድብህ ግን ማንስ ያነሳልሃል ብለው በጥያቄ ይመልሱልናልና። ታዲያስ የሕዝብ አገልጋይ ወይስ የመንግሥት ባለሥልጣን ሆኖ መቅረት፤ከሁለት አንዱን መምረጥ ግዴታ ነው።ምክንያቱም “ሐቀኛነቱን ተገንዝቦ ሰዉ በሕሊናው ቅዱስ እና ቅን ተግባሮችን ብቻ መርጦ እንዲመገብ ይረዳዋል።ቅንነትና ቅዱስ ተግባሮች የሕዝብ ፍላጎት ሲሆኑ ምንጊዜም የነዚህ ባሕርያት ያላቸው ሰዎች የሕዝብ ድጋፍ እና ጥበቃ አይለያቸውም፤ብሕሊና የማይገዙ ይጠፋሉ።

     ስለዚህም ሕሊናዬ ሚዛን ላይ ነገሮችን ወይም ተግባሮችን የሚያስቀምጠው ከሁለቱ የዳኝነት ልዩነት አንጻር ነው፤(ርኩስ ወይም ቅዱስ)እና አሊያም ከሁለት ነባራዊ ዓለሞች(ሥጋዊናመንፈሳዊ) ተፈጥሮዎች የሚመነጩ መሆናቸውን በማገናዘብ ነው።ከዚሁ ጋር ትንንቁ እና ትግሉ ምን ዓይነት እንደሆነ፣እንዴት መቋቋም እንደሚገባን፣ በምን አይነት ሕግ፣ደንብና ፖሊሲ መሆን እንደሚገባው ለመግለፅ አይደለም።አቶ አቢይ፣አብይ እና ዐቢይ የሥም ትርጉም ቢኖራቸውም ይህ ጠቅላይ ሚኒስቴር እና ዶክተር፣ “አብይ”(አብዮት ይጠብቃቸዋል)እንጂ “ዓቢይ” አቢይም(በፊደላት ሕግ)አሊያም ዐቢይም(የመንግሥት እንጅ የሕዝብ ባለመሆናቸው)ይመስላሉ እንጂ ዐቢይ አይደሉም፤ወደፊት ሲነቁ ሊሆኑ ይችላሉ።አሁን በቅድሚያ ከእርሳቸው የሚጠበቀው ቃላቸውን ማሰሪያ እነዚህን መፈፀም ነው፤እነዚህ የሕዝቡ የነጻነት ዋስትናዎች ናቸው፦ይህ የትግል ግፊት የመጣው በአሜሪካ የተወሰነው የወያኔዎች ንብረት መወረስ አዋጅ አር ኤች ፻፳፰ በማለፉና ዋናው ማስፈፀሚያው ለውሳኔ ከቀረበ ወያኔዎች ለሃያ ሰባት ዓመታት የዘረፉት ንብረትም ሆነ፣ልጆቻቸውን የሌላ ዜጋ ያደረጉ በመሆኑ፣ቀጣዩ አዋጅ አር ኤች ፻፷፰ እንዳይፀድቅ ይሄው ሁሉን ለኢትዮጵያውያን አስረክበናል ለማለት ነው።ዶክተር አቢይ አህመድ እንዲመረጥ እና ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዲለቅ ያደረጉትም አሜሪካኖች መሆናችው፣እንዲሁም ዶክተሩንም ከጎንህ እንቆማለን ያሉትም ጉጅሌዎች ፈቅደው አይደለም።በአሁኗ ሰዓትም ቤተመንግሥት ውስጥ ተንኮል እየሸረቡ እንደሆኑ እናውቃለን። አሁን በቅድሚያ ከእርሳቸው የሚጠበቀው ቃላቸውን ማሰሪያ እነዚህን መፈፀም ነው፤እነዚህ የሕዝቡ የነጻነት ዋስትናዎች ናቸው፦

፩ኛ/ በ”ነፃነት” ምክንያት የፖለቲካ እስረኞችን አሁን በሙሉ መፍታት
፪ኛ/አስቸኳይ አዋጁን ማንሳት
፫ኛ/ከሕገ-መንግስቱን ፀረ-ዲሞክራሲ የሆኑት በአስቸኳይ አዋጅ እንዲሰረዝ ማድረግ
፬ኛ/የዕርቅ እና የሰላም ጉባዔ በአስቸኳይ አዋጅ እንዲደረግ ቅድመ ሁኔታዎችን አሁን ማመቻቸት።
፭ኛ/የሽግግር መንግሥት ለሕዝባዊ መንግሥት እንዲያዘጋጅ ሁኔታዎችን አሁን ማመቻቸት ናቸው።

“ካልተሳፈሩበት “ቀድሞ”ተሽቀዳድሞ፤

ጊዜ ታክሲ አይደለም፣አይጠብቅም ቆሞ።” እነልዑለ-ሥላሴ ቴማሞ ከአስፋወሰን ኮምፕሪሄንዝቭ ፪ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፩፱፻፷፬ ዓመተ ምህረት።ለዚሁም ምኞታቸው ቸሩ አምላካችን እግዚአብሔር ለውዲቷ አገራችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ብሎ ሁላችንንም ይርዳን፤የሰው ሥጋ የለበሱ ርኩሶች አጠገባችን እንዳሉ ልንዘነጋ ሳይገባን፤ይልቅስ በመጠጋገን የሚሆን አይደለም።”ነፃነት”ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴራችን የኢትዮጵያ ሕዝብ የመጀመሪያው አጀንዳችን ነው ፤አወቁም አላወቁም፤ዲሞክራሲም፣የሕውሃት-ኢሃድግ ጉዳይ አይድለም።

አፋችን ደርሶ ብናቆየውም፤አክታን ብንደብቀውም።
በውርደት እያየነውም፤ጉጅሌን በፍፁም አናድነውም።
አክታም ቢሆን ይሄው ነው፣ወደ ውስጥ እንኳ ብንምገውም፤
ሆዳችን ቢሸነፍ ለተፈጥሮ: -ከሕሊና ግን አናድነውም።

ጸሃፊውን ለማግኘት:- Abiy Ethiopiawe abiyethiopiawe@gmail.com

Filed in: Amharic