>

"መናናቅ አያዋጣም፤ ልክ እንደ በቆሎው ምሳሌ!" (ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ) 

መናናቅ መጠላላት ትክክል የማይሆነው ፤የሚናቅ ሰው የሚናቅ ማህበረሰብ ስለሌለም ጭምር ነው፡፡ አሶሳ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ድንበር ጠብቋል፡፡ ድንበሩ ክፍት ከሆነ ወለጋ የለም ማለት ነው፡፡ሸዋ የለም ማለት ነው፡፡ መናቅ አይቻልም፡፡
ኦሮምያ ተማምኖ የሚተኛው ወንድሞቼ ቤኒሻንጉል ህዝቦች ድንበር ይጠብቃሉ ብሎ ነው፡፡ቤኒሻንጉልም ወደመሃል ሃገር ሲያስብ ወንድሞቼ አሉ ብሎ ማሰብ አለበት፡፡
በቆሎ በመጠንዋ  ከጤፍ ከፍ ትላለች፡፡ከፍ ስለምትል ጤፍን ትንቅና አሁን ሰው በከንቱ ይለፋል እንጂ ጤፍ ምን ዱቄት ከማህፀኑ ይወጣል ተብሎ ነው ወፍጮ ቤት የሚላከው ትላለች፡፡ በቆሎ መጠንዋ ተለቅ ተለቅ ስለሚል እስዋ ስትፈጭ ዱቄት ስለሚገኝ ጤፍ ሲፈጭ ዱቄት የማይገኝ ነው የሚመስላት ግን አንድ ኩንታል በቆሎና አንድ ኩንታል ጤፍ ወፍጮ ቤት ከሄዱም በኋላ የተሸለ ዱቄት የሚገኘው ከጤፍ ነው፡፡
መናናቅ አያዋጣም በሆነ በሆነ ነገር ማለት ነው፡፡ በከለር በሃይማኖት በሳይዝ አንዱ አንዱን ቢንቅ ኪሳራ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደመር እያልን ያለነው፡፡ስንደመር እንጠነክራለን፤ ስንደመር እንበዛለን ፤ስንደመር ሃይል ይኖረናል፡፡
ለህብረብሄራዊነት ቅድሚያ መስጠት ከእውነተኛ የአገር ፍቅር ይቀዳል፤ህልውና ሁሌም ከማንነት ይልቃል ህልዉና ከሌለ ማንነት የለም።የብሄር ልዩነትችን በህብረ ቀለማዊነት የሚያስውበን እንጂ የሚያራርቀን ጥቁር መስመር አይደለም። በተናጠል ብንጓዝ የትም አንደርስም፤ 85 ብሄርች አንድ ላይ ስናጨበጭብ ይበልጥ እንደመጣለን፤ በኢትዮጵያዊነት ተሳስረንና በልዩነታችን ተቻችለን በጋራ በልማት ጅረት እንፍሰስ። መተኪያ የሌላት አገራችንን በ100 ሚሊዬን የማይበጠስ ጠንካራ ሰንሰለት አጥረን ከጥፋት እንጠብቃት ።አዋጩ ይህ ብቻ ነው ቁርሾና ቂም መዘከሩ ለዛሬ ማንነት ያለው ቫልዩ ዜሮ ነው። አዋጭው እና ሩቅ መንገድ የሚያስኬደን መደመሩ አንድ መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በዛሬው እለት በአሶሳ ከህብረተሰቡ ጋር በተወያዪበት ወቅት የመደመርን አስፈላጊነት የገለፁበት ምሳሌ፡፡
Filed in: Amharic