>

አቶ አንዳርጋቸው ወንጀሉ "ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ዴሞክራሲ ይገባቸዋል!" ማለቱ ነው እባክዎን ይፍቱልን!?! (አበበ ቶላ)

”…ዘመኑ የእርቅ እና የይቅርታ ነው…” ሲሉ ጮክ ብለው የተናገሩት ንግግር ከበርካታ ኢትዮጵያውያን አዕምሮ ውስጥ ታትሞ እያንዳንዷን ቀን በተስፋ እና በጉጉት እየጠበቅን ነው… ተስፋ እና ጉጉቱ ለኛ ለግላችን አይደለም። እኛ በደህናው ግዜ ያመለጥን ብልጣ ብልጦች ነን!!! ነገር ግን እርስዎን ወደ ስልጣን ያመጣዎት የህዝብ ምሬት አሟሯቸው ”ኢትዮጵያውያን፤ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ እና ነጻነት ይገባቸዋል!” ብለው የተሻለ ስርዓት ለመመስረት የአቅማቸውን ሲሞክሩ በመንግስትዎ ቁጥጥር ስር የዋሉ የነጻነት ናፋቂዎች ነጻ የሚወጡበትን ቀን በጉጉት እና በተስፋ እየጠበቅን ነው።
ወደዚህ ስልጣን ከመጡ ጀምሮ እንዳላረፉ እና ባልተለመደ መልኩ ታች ድረስ እየወረዱ የህዝቡን ብሶት በማዳመጥ እና ምላሽ በመስጠት እንዲሁም ከእስካሁኑ ኢህአዴግ አይተን የማናውቀው የአገር አንድነት ግንባታ ላይ መስጭ ሃሳቦችን በማንሳት አደጋ ላይ ያለነውን ሰዎች እንደ አገር እንድንቀጥል በመምከር እና በመማጸን ቀላል ግምት የማይሰጠው ስራ እየሰሩ እንደሆነ የምንገነዘብ ብዙ ነን!
ነገር ግን መነሻዎ ላይ እንዳሉን ”ዘመኑ የ እርቅ እና የይቅርታ” መሆኑን ለማስመስከር የሚረዱ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያድርጉ አልተመለከትንም። ዛሬም በርካታ ነጻነት እና ፍትህ ናፋቂዎች በመንግስትዎ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ነው።
ባለፈው የዋልድባ መነኮሳትን መፈታት አስመልክቶ ለባህርዳር ህዝብ ሲገልጹ ‘መነኮሳቱን መፍታት ቀላል ስራ እንዳልሆነ’ በነገሩን ወቅት ያለብዎን ጫና ተረድተናል። ቢሆንም ግን እባክዎን ይሄንን ጉዳይ እንደ ጉዳይዎ ይዘው ከዳር ያድርሱልን!
አቶ አንዳርጋቸው ወንጀሉ ነጻነትን መፈለጉ ነው! አቶ አንዳርጋቸው  ወንጀሉ ለአገር አንድነት ሲል ቤተሰቡን ለእግዜር አደራ ብሎ በረሃ መውረዱ ነው! አቶ አንዳርጋቸው ወንጀሉ ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ዴሞክራሲ ይገባቸዋል ማለቱ ነው!
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን እንደምንም ብለው በምፍታት እና በማስፈታት እውነትም ‘መጪው ግዜ የእርቅ እና የይቅርታ ነው’ ያስብሉን!

እባክዎን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

Filed in: Amharic