>

ከመነኮሳቱ ጋር ይፈታል ተብሎ የነበረው ተከሳሽ አሁንም በእስር ላይ ነው (ጌታቸው ሽፈራው)

“ፍርድ ቤት ፈትቶኛል፣ እኔን ያሰረኝ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው!” 
በእነ ተሸጋር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ 2ኛ ተከሳሽ ነጋ ዘላለም መንግስቴ
ነጋ ዘላለም መንግስቴ ይባላል። የፌደራል ፖሊስ አባል ነበር። የተቋሙ አሰራር ስላልተመቸው ከ5 አመት በፊት በፈቃዱ ከስራው ለቅቋል። ነጋ ቤተሰብ አስተዳዳሪና  የአንዲት ልጅ አባት ነው።
ነጋ በ2008 ዓም በተቀሰቀሰው የአማራ ሕዝብ ተቃውሞ ሰበብ ታስረው ከተሰቃዩት መካከል ነው። ማዕከላዊ ለአራት ወር ያህል ቆይቷል። የትህነግ ታጋዮች በማንንነቱ ምክንያት ብዙ ስቃይ እንደፈፀሙበት ይናገራል።  ኮማንደር ተክላይ ሳይቀር ሕዝብን በጅምላ እየሰደበ እንደመረመረው አጫውቶኛል። ነጋ ምርመራ ጨርሶ ከጨለማ ቤት ከወጣ በኋላም እንደገና ወደ ጨለኛ ቤት መልሰውት ተሰቃይቷል።
በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ ከ35 ሰዎች ጋር ተከሶ የነበረው ነጋ  32ቱ ክሳቸው ተነስቶ ሲለቀቁ ከሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት ጋር በእስር ላይ ቆይቷል። መነኮሳቱ ሲፈቱም  ይፈታል ተብሎ የነበረው ነጋ አልተፈታም።
በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ ከተከሰሱት መካከል ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች “ፍርድ ቤቱን ደፍራችኋል” ተብለው 6 ወር ፍርድ ተላልፎባቸው ነበር።  አራቱ ክሳቸውም ተነስቶ፣ ፍርዱም “በይቅርታ” ተብሎ ተፈትተዋል። ነጋ ግን አልተፈታም። በእነ ተሻገር ወ/ሚካኤል ክስ መዝገብ ከተከሰሱት በተጨማሪ በእነ ጉርሜሳ አያኖ ክስ መዝገብ “ፍርድ ቤት ደፍራችኋል” በሚል ሁለት ጊዜ የተፈረደባቸው አራቱ የኦፌኮ አመራሮችም ክሳቸው ሲነሳ መፈታታቸው ይታወሳል።
ነጋ ዘላለም “ፍርድ ቤት ደፍሯል” በሚል በተቀጣበት በእስር ቤት እንዲቆይ ከተደረገ እንኳ በአመክሮ ሚያዝያ 11/2010 ዓም መፈታት ነበረበት። ነገር ግን ነጋ አሁንም አልተፈታም!
ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት በተፈቱበት ወቅት ለነጋም መፍቻ ተፅፎ እንደነበር ታውቋል። የነጋ ቤተሰቦች ከአማራ ክልል ድረስ መጥተው ጉዳዩን ለማስጨረስ ለሳምንት ያህል ተከላትመዋል። ቂሊንጦ እስር ቤት ከመነኮሳቱ ጋር የተፃፈለትን መፍቻ እንዳሳያቸው ለማወቅ ተችሏል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ሄደውም  ያገኙት መረጃ የሚያሳየው ተመሳሳይ ነበር። ሆኖም የቃሊቲ እስር ቤት ነጋን አልፈታውም።
“እኔን ያሰረኝ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ነው፣ ፍርደረ ቤት ፈትቶኛል። የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች ለምን እንዳሰሩኝ ለመጠየቅ ብጥርም ሊያናግሩኝ ፈቃደኛ አይደሉም……ክሱ ተነስቷል፣ ፍርዱን በአመክሮ ጨርሻለሁ……ለምን እስካሁን እንዳሰሩኝ እኔም ግራ ገብቶኛል” ሲል አጫውቶኛል። ነጋ ዘላለም ቃሊቲ ዞን 3 በእስር ላይ ይገኛል።
Filed in: Amharic