>

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእስር ማዘዣ ተቆርጦብኝ ነበር አሉ

ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ከመመረጣቸው አምስት ቀን ቀደም ብሎ የእስር ማዘዣ ተቆርጦባቸው እንደነበር ገለጹ።

ዶክተር አብይ አህመድ ይህንን የገለጹት ለሃይማኖት አባቶች፣ለአባገዳዎች፣ለሀገር ሽማግሌዎች፣ለሃይማኖት አባቶች፣ለኪነጥበብ ባለሙያዎችና ለአትሌቶች በተዘጋጀ መድረክ ላይ መሆኑም ተመልክቷል።

ትላንት ምሽት በብሔራዊ ቤተመንግስት በተካሄደው ስነ ስርአት ላይ እሳቸውንና አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ በአምስት የኦሕዴድ ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ ተቆርጦ ነበር ማለታቸውን በስብሰባው ላይ የታደሙ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ከሀገር ውጪ በመሆናቸው በስብሰባው ላይ አልተገኙም።

ሚያዚያ 22/2010 በኢዮቤልዩ ቤተመንግስት በተካሄደው መድረክ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና አትሌቶች ጭምር መታደማቸው ታውቋል።

በዚህ መድረክ ላይ ለተገኙት የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የሃገር ሽማግሌዎች ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ንግግር ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የነበሩበትን አስቸጋሪ ሁኔታ ለተሰብሳቢው ገልጸዋል።

“ዛሬ እዚህ ከፊታችሁ እንድቆም ቄሮዎች ትልቅ ዋጋ ከፍለዋል”በማለት በኦሮምኛ የጀመሩትን ንግግር የቀጠሉት ዶክተር አብይ አህመድ “በትግሉ ውስጥ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆኑ አማሮች፣ደቡቦችና ሌሎችም ብሔሮች የማይናቅ ሚና ተጫውተዋል”ማለታቸውን በስብሰባው የታደሙ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ንግግራቸውን በመቀጠልም”የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ሊካሄድ 5 ቀናት ሲቀሩት እኛን ለማሸማቀቅ የማሰሪያ ትዕዛዝ አወጡብን”በማለት ተናግረዋል።

ትዕዛዙ የወጣው ማለትም እንዲታሰሩ የተወሰነባቸው እሳቸው፣የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና በሌሎች ሶስት የኦሕዴድ አባላት ላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

ሕዝቡ ከእኛ ጋር በመሆኑ የሚያስፈራን ነገርም አልነበረም ሲሉ ገልጸዋል።

ያንን ሁሉ አልፈን ግን ዛሬ ለዚህ በቅተናል ያሉት ዶክተር አብይ አሕመድ ለዚህ ነጻነት የተዋደቁ ቄሮዎችና ሌሎች ይህንን ነጻነት ቢያዩ ምን ነበር ሲሉ መቆጨታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።

ስለብሔራችን ከምንጨነቅ ለአንዲት ኢትዮጵያ ብናስብ ይሻላል በማለትም መልዕክታቸውን ባስተላልፉበት በዚህ መድረክ አቶ ለማ መገርሳ ትልቅ መስዋዕትነት መክፈላቸውን መስክረዋል።

ሆኖም አቶ ለማ መገርሳ ከሀገር ውጭ በመሆናቸው በዝግጅቱ ላይ እንዳልነበሩም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

ለኦሮምኛ ተናጋሪዎች በተዘጋጀውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በኦሮምኛ መልዕክት ባስተላለፉበት በዚህ መድረክ ዝነኛው የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ አሊ ቢራ፣ቀመር የሱፍ፣ታደለ ገመቹና ደመረ ለገሰን ጨምሮ ሌሎች ድምጻውያንም ተሳትፈዋል።

የሙዚቃ ስራዎቻቸውንም አቅርበዋል።

ከአትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ፣ስለሺ ስህን፣ጥሩነሽ ዲባባ፣ገዛሕኝ አበራና ሌሎችም መገኘታቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በክልሎች የሚያደርጉትን ጉብኝት በመቀጠል ዛሬ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ገብተዋል።

ሁለተኛውን የውጭ ጉዟቸውን ነገ በሱዳን ካርቱም እንደሚያደርጉም ታውቋል።

Filed in: Amharic