>

የህወሓት ዕቅድ፥ የእስር ማዘዣው እና የብአዴን ጆከር! [ስዩም ተሾመ]

በእርግጥ ፖለቲካ ማለት ልክ “Bicycle” ነው፡፡ ሁልግዜም በማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል መሽከርከር አለበት፡፡ ለውጥና መሻሻል ከቆመ ልክ እንደ “Bicycle” ፖለቲካዊ ስርዓቱም ተንጋሎ ይወድቃል፡፡ ህወሓት የማይለወጥ የፖለቲካ ቡድን ከመሆኑም በላይ ሌሎች እንዳይለወጡ የሚያደርግ ፀረ-ለውጥ ቡድን ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ቆሞ-ቀር ቡድን የሌሎችን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ያለመታከት ጥረት ያደርጋል፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ጠፍቶ መንግስታዊ ስርዓቱ ለመውደቅ እየተንገዳገደ ባለበት ወቅት እንኳን ህወሓት በኦህዴድ መሪነት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማስተጏጏል ላይ-ታች ሲል ነበር፡፡

አዲሱ የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን እንደመጣ የወሰደው የለውጥ እርምጃ ፀረ-ለውጥ አቋም ከሚያራምደው የህወሓት ቡድን ራሱን ማላቀቅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የክልሉ ፕረዜዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ የወሰዱት እርምጃ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ  ይችላል፡፡ ቅርበት ካላቸው ሰዎች በተደጋጋሚ ጠይቄ እንደተረዳሁት፣ የአቦ ለማ የስልክ ግንኙት ሲያደርግ የነበረው በቀጥታ ከቀድሞ ጠ/ሚኒስተር ሃይለማሪያም ደሳለኝ እና በጎንዮሽ  (horizontally) ደግሞ ከቀድሞ የትግራይ ክልል ፕረዜዳንት ኣይተ አባይ ወልዱ ጋር ብቻ ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ እንደ አባይ ፀሐዬ፣ ጌታቸው አሰፋና ሳሞራ ዬኑስ የመሳሰሉ የህወሓት ፈላጭ-ቆራጭ አመራሮችን ስልክ አያነሳም፡፡ በአካል ወደ ለማ ቢሮ ሲሄዱም እንደ ማንኛውም ሰው ተፈትሸውና ትጥቃቸውን ፈትተው ነው፡፡ በአጠቃላይ ከኦቦ ለማ ጋር የሚነጋገሩት በድርጅቱ ኢህአዴግ ወይም በጠ/ሚኒስትሩ አማካኝነት በተጠራ ስብሰባ ላይ ብቻ ነው፡፡

የፈለጉትን ሰው በፈለጉት ቦታና ግዜ ጠርተው ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት የሚታወቁት የህወሓት መሪዎች እንደ ለማ መገርሳ ያለ ትንታግን  በይፋዊ ስብሰባ ላይ ማሳመን ሆነ ማስፈራራት አይችሉም፡፡ የለማ ቡድን (TeamLemma) በሚል ከድርጅቱ ኦህዴድና ከኦሮሞ ልሂቃን ለለውጡ አስፈላጊው ብቃትና ቁርጠኝነት ያላቸውን ሰዎች መርጦ በዙሪያው አሰባሰበ፡፡ በዚህ መልኩ አዲሱ የኦህዴድ አመራር ከህወሓቶች ቁጥጥርና ጫና ራሱን ነፃ በማውጣት የለውጡን ንቅናቄ በራሱ መንገድ መምራት ጀመረ፡፡ በጥቅሉ የለማ ቡድን ልክ ቄሮዎች፣ መሪው ኦቦ ለማ መገርሳ ደግሞ ልክ እንደ የቄሮዎቹ መሪ አቦ ጀዋር መሃመድከህወሓቶች ክትትልና ቁጥጥር ውጪ ሆነው እንደነበር  መገንዘብ ይቻላል፡፡
የለማ ቡድን ወደ 20ሺህ የሚጠጉ እስረኞችን በምህረት መልቀቁ ይታወሳል፡፡ በመቀጠል የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊስ ሙሉ በሙሉ ከክልሉ ህዝብ ጎን እንዲቆም አደረገ፡፡ በዚህ መልኩ የክልሉ አመራርና የፀጥታ መዋቅር እንደ ቀድሞ የህወሓት መገልገያ መሆኑ አበቃ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኦቦ ለማ ወደ ባህር ዳር በመሄድ ከአማራ ክልል እና ህዝብ ጋር ያለውን አንድነትና ትብብር ለማጠናከር መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡በብአዴንና እህደዴ የተጀመረው ትብብር ወደ ምሁራንና የህዝብ-ለህዝብ ትብብር እያደገ መጣ፡፡ በዚህ ምክንያት በፍርሃትና በመለያየት ላይ የተመሠረተው የህወሓት የበላይነት ተፍረከረከ፡፡ የህወሃት አመራሮችና ልሂቃን “መርህ አልባ ጉድኝት” በማለት ያጣጣሉት ትብብር የህወሓትን የበላይነት ለመገርደስ የሚያስችል ጥርስ አወጣ፡፡

ህወሓቶች የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን እንደ ቀድሞ መለያየትና ማስፈራራት ሲሳናቸው ያላቸውን የመጨረሻ አማራጭ ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅድ አወጡ፡፡ ቅርበት ካላቸው የኢህአዴግ ባለስልጣናት ባገኘሁት መረጃ መሠረት የዕቅዱ ዋና አዘጋጅ አስር (10) ሺህ ዶላር አበል  ተከፍሎት ከአሜሪካን ሀገር የመጣ ነባር የህወሓት አባል ነው፡፡ ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም “አይጋፎረም” በተሰኘው ድረገፅ ላይ “የኢህአዴግ የመፍረስ አደጋና የኢትዮጲያ ቀጣይ እጣ ፋንታ” በሚል ርዕስ ባወጡት ፅሁፍ የህወሓት/ኢህአዴግን ዕቅድ እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

 “… ኢህአዴግ ለህዝቡና ለዓላማው የሚቆረቆር ከሆነ ለግለ-ሰዎች ዝና መበገር የለበትም። ህዝበኞች እንደሆነ የአንድ ሳምንት አጀንዳ ከመሆን አያልፉም፡፡ ስለሆነም በተጨባጭ መረጃ የተገኘባቸው በቀጥታ ወደ ቃሊቲ እንዲወርዱ ማድረግ የተለያየ የፖለቲካ ሴራ የፈፀሙ ግን ደግሞ ተጨባጭ መረጃ ከሌለ መረጃ እስከሚመጣ መጠበቅ ሳይሆን ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድ፡፡ … ይሄ ተጠናክሮ በሚሄድበት ይህን ስርዓት ማስቀጠል የሚፈልግ ህዝብና አገር ወዳድ በርካታ ስለሆነ ከነዚህ ሆዳሞችና ከሃዲዎች በኋላ የሚፈጠር ስጋት አይኖርም።”

ከላይ በተገለፀው መሠረት “በኢህአዴግ” ስም የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል ያለው ብቸኛ አማራጭ በድርጅቱ ውስጥ የለውጥ ንቅናቄ የጀመሩትን የእህዴድና ብአዴን አመራሮች በማሰር ወደ ቃሊቲ መላክ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ህወሓቶች አንድ ቅድመ-ሁኔታ አስቀምጠዋል፡፡ ይኸውም የተነሳውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በድጋሜ ማወጅና ሀገሪቱን በወታደራዊ ሃይሉ ቁጥጥር ስር ማዋል ነው፡፡
በዚህ መሠረት በመጀመሪያ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ ብቻ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ግዜ አዋደጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ አልተሳካም! ቀጠሉና “ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት” በማለት በእጅ አዙር የአስቸኳይ ግዜ አዋደጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ እሱም ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ ስልታዊ ማፈግፈግ አደረጉና 17 ቀናት የፈጀውን የኢህአዴግ ስብሰባ አደረጉ፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይ የህወሓቶች ዓላማ አንድና አንድ ብቻ ነበር፡፡ እሱም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅና “ህዝበኞች” ያሏቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ለቃቅሞ ማሰር ነው፡፡

በተጠቀሰው ስብሰባ ላይ በኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ከተነሱት ጥያቄዎች ውስጥ “የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ” የሚለው ይገኝበታል፡፡ በወቅቱ ኦቦ ለማ  መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድን በጉያቸው አቅፈው ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ኦቦ በቀለ ገረባን ማሰር ለህወሓቶች ፋይዳ የለውም፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ከጎናቸው አስቀምጠው እስክንድር ነጋ እና አንዷለም አራጌን ማሠር ለእነሱ ፋይዳ-ቢስ ነው፡፡ በአንፃሩ እነዚህን የፖለቲካ እስረኞች መፍታት በሀገር  ውስጥ ሆነ በውጪ በሚገኘው ማህብረሰብ ዘንድ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ህወሓት ግን ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን የሚፈታው  “ህዝበኞች፥ Populist” ያላቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ለማሰር ነው፡፡ በዚህ መሠረት ህወሓቶች ” እሺ… የፖለቲካ እስረኞች ይፈታሉ፡፡ ነገር ግን፣ አመፅና ሁከት ከተነሳ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ይታወጃል” የሚል የድርድር ሃሳብ አቀረቡ፡፡ እስረኞችን በማስፈታት የህዝቡን ጥያቄ የመለሱ የመሰላቸው የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች በሃሳቡ ተስማምተው ስብሰባው ተጠናቀቀ፡፡

በዚህ ስምምነት ተቀናቃኞቹ ህወሓትና ኦህዴድ ሁለቱም የተሳሳተ እሳቤ ነበራቸው፡፡ ኦህዴዶች “ምንም አይነት አመፅና ሁከት በሌለበት ህወሓቶች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አያውጁም” የሚል የተሳሳተ እሳቤ ነበራቸው፡፡ ህወሓቶች ደግሞ “ዋና መጠቀሚያቸው የሆኑት ጠ/ሚኒስትር ያለ እነሱ ፍቃድ ከስልጣን አይወርዱም” የሚል እሳቤ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን፣ ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ከህወሓቶች የሚደርስባቸውን ዛቻና ማስፈራራት ተቋቁመው መልቀቂያ አስገቡ፡፡ ህወሓቶች “እንገድልሃለን” ብለው  እስከማስፈራራት ደርሰው የነበረ ሲሆን ጠ/ሚኒስትሩ ደግሞ ለሁለት ቀናት ያህል ፀሎት እንዲደረግላቸው እስከመጠየቅ ደርሰዋል፡፡

የጠ/ሚ ሃይለማሪያም መውረድ ህወሓቶችን በፍርሃትና ጭንቀት ያራዳቸው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛ፦ ሃይለማሪያም ሲወርድ ህወሓቶች መተኪያ የሌለውን መጠቀሚያቸውን ያጣሉ፣ ሁለተኛ፦ ኦህዴዶች በጥብቅ የሚሹት ቦታ ለውድድር ክፍት ይሆናል፡፡ በመሆኑም በሁለቱም መልኩ ሚዛኑ ወደ ኦህዴድ ያዘነብላል፡፡ ስለዚህ ህወሓቶች ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በ17ቱ ቀን ስብሰባ ያገኟትን ካርድ በመምዘዝ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ ነው፡፡ እንደሚታወሰው ምንም አይነት አመፅና ሁከት በሌለበት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አወጁ፡፡ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ ቢደረግም አይናቸውን በጨው አጥበው ሀገሪቱን በወታደራዊ ዕዝ ለመምራት መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡

የአዋጁ ዓላማ፤ አንድ ቱቦ የሚያገለግላቸውን አዲስ ጠ/ሚኒስትር መምረጥ እና ‘”ህዝበኞች’ ያሏቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች ወደ “ቃሊቲ” መላክ ነው፡፡ ለዚህም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከመመረጡ ቀደም ብለው ዋና ዋና ላሏቸው የኦህዴድ አመራሮች የእስር ማዘዣ ቆርጠው ይጠባበቁ ጀመር፡፡ ምን ያደርጋል ታዲያ! ብአዴን ጆከሩን ለኦህዴድ አሳልፎ በመስጠት ህወሓትን ጨው አደረገው፡፡  እንሆ አብይም ጠ/ሚኒስተር  ሆኖ ተመረጠ፡፡ ህወሓቶች ለእነ አብይ ያወጡት የእስር ማዘዣ በብአዴን የጆከር ጨዋታ ከንቱ ሆኖ ቀረ፡፡

 Seyoum Teshome | May 2, 2018 at 7:28 pm
Filed in: Amharic