>
5:13 pm - Monday April 19, 5052

የተፈፀመው "መንግስታዊ" በቀል ነው (ጌታቸው ሽፈራው)

  ቤንሻንጉል ክልል ከማሽ ዞን  ድንጋሮ ወረዳ  በለው ደዲሳ ቀበሌ  ጥቅምት 16/2010 ዓም ከምሽቱ 3 ሰዓት አካባቢ 2 ወጣቶች በግል ጉዳይ ይጣላሉ። አንድ የቤንሻንጉል ተወላጅ መመታቱ ተሰምቷል።  ሆስፒታል ያደረው  ይህ ወጣት ጠዋት ይሞታል።
  ይህን ልጅ ገድሏል የተባለው ጥላየ አንዷለም የተባለ ወጣት ነፍሱን እስኪስት ተደብድቦ ታስሯል። ሆኖም በዚህ አላበቃም። የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አስከሬኑን ከሆስፒታል ሲመለስ ሕዝብን መቀስቀስ እንደጀመረች ተፈናቃዮቹ ይናገራሉ።
በተመሳሳይ የወረዳው  ሚሊሻ ፅ/ቤት ኃላፊም ከታጠቀ ጦር በተጨማሪ ህዝብን በመቀስቀስ በአማራ ተወላጆች ላይ በርካታ ግፍ እንዲፈፀም አድርጓል። ጥቅምት 17/2010 ዓም 13 ሰው ተገድሏል። 49 ሰው ቆስሏል። 527 አባውራ ተፈናቅሏል።  ለሶስት ቀን ያህል ወደ ኦሮሚያ ክልል ሸሽተው ጥበቃ ባይደረግላቸው ከዚህ የባሰ በደል ይደርስባቸው እንደነበር ገልፀዋል። በዚህ ወቅት የፌደራልም ሆነ የአማራ ክልል መንግስት ያደረገላቸው እገዛ አልነበረም።
ከተባረሩት መካከል አብዛኛዎቹ ብዙ ቤተሰብ ያላቸው ናቸው።በአሁኑ ወቅት ባህርዳር የሚገኙት 160 ያህል ተፈናቃዮች ናቸው። ቀሪዎቹ ተበትነዋል። በቅርቡ ከባህርዳር ተጭነው ወዳልታወቀ ቦታ የተወሰዱም ይገኙበታል ተብሏል።
የቤንሻንጉል መንግስት ተፈናቃዮች ህገ ወጥ እንደሆኑ ገልፆአል። ይሁንና የተገደሉት፣ የቆሰሉት፣ ንብረታቸው የወደመው፣ የተፈናቀሉት ሁለት ግለሰቦች መካከል በነበር ፀብ ነው። የቤንሻንጉል መንግስት የወረዳ አመራሮች ሕዝብን በማነሳሳት ጭምር ነው ያፈናቀሏቸው።
 ቤታቸው ተቃጥሏል። የ13 ሰው ህይወት አልፏል። 49 ሰው ቆስሏል። ይህ የሆነው የቤንሻንጉሉን ወጣት የገደለው ጥላየ አንዱዓለም የሚባል የአማራ ተወላጅ ነው በሚል ነው።  በግል ጉዳይ በተጣሉ ግለሰቦች ምክንያት አንድ ሰው ስለሞተ  በሕዝብ ላይ የተፈፀመው በቀል ነው። በቀሉን የፈፀሙት ዜጎች አይደሉም። ይህን በቀል የፈፀሙት ደግሞ የመንግስት አመራሮች ናቸው። ተፈናቃዮቹን ሕገ ወጥ እያለ የሚወቅሰው የቤንሻንጉም መንግስት 30 ያህል የቤንሻንጉል ተወላጆችን ለተፈፀመው ተጠያቂ አድርጎ አስሮ ነበር። ከታሰሩት መካከል ግን አንድም የወረዳ ወይንም የቀበሌ አመራር የለም ተብሏል። ለይስሙላህ የታሰሩት ወጣቶችም እንደተፈቱ እየተገለፀ ነው።
Filed in: Amharic