>

የአፄ ቴዎድሮስ  ለመቶ ሀምሳ አመታት ነዶ ያልጠፋ ወኔ!!! (ፍቅር ያሸንፋል)

የአፄ ቴዎድሮስን ከውልደት እስከ ዕለተ ሞታቸው ያለውን ሂደት እንደሚከተለው ለማብራራት ወደድኩኝ።
በቅድሚያ ግን ይሄን ከብዙ ፅሁፎች የተመሳከረ ሀሳብ ሳቀርብ የቴዎድሮስ አብዝቶ ደግነት እና በፍፁም ስስት እማያውቅ ንጉስ መሆኑን የመሰከሩ ሚሲዮናውያን እንደነበሩ እየገለጥኩ ቴዎድሮስ በበረኃ በነበረ ጊዜ ህዝቡ ተርቦ ነበር። ይሄኔ ግን በዙፋን ያሉት ምንም ሳያደርጉ ቢቀሩም መይሳው ያከማቸውን እህል ለተራበው በመስጠት መሬትን ለእርሻ እንዲውል ዛፍ ሲመነጥር ቆይቷል። ይሄ በልባቹ ይቆይ..! እነሆ የካሳን ህይወት በስሱ ቃኙልኝ..?
የአጤ ቴዎድሮስ አባት ልጅ ኃይሉ የቋራ ገዢ ሲሆኑ እናታቸው ወይዘሮ አትጠገብ ደግሞ ከአጤ ፋሲል የልጅ ልጅ የሚወለዱ የተከበሩ ሰዎች ናቸው። አጤ ቴዎድሮስ የተወለዱት እንደሚባለው ቋራ ሳይሆን ደንቢያ ውስጥ ፈንጃ በምትባል ስፍራ ነበር። ይቺን ከተማ የቆረቆሯት የዘመኑ መስፍን የነበሩት ደጃች ማሩ ናቸው። የዘመኑ መስፍን ደጃች ማሩ ከቋራ እስከ ጎንደር ከዛም እስከ ደብረታቦር ዘልቆም ግማሽ ጎጃምን ያስተዳድሩ ነበር። በዚህ ስልጣናቸው በቋራ ላይ በገዢነት የሾሙት ልጅ ኃይሉን ነበር። ደጃች ማሩ ግን ቋረኞችን ይጠራጠሩ ስለነበር በወዳጆቻቸው ምክር ልጅ ኃይሉን አስጠርተው የታላቅ እህታቸውን እጅግ ውብ የሆነችውን ልጅ ይድሩላቸዋል። ልጅ ኃይሉም በቋራ ከባለቤታቸው ክንፉ የተባለ ወንድ ልጅን ይወልዳሉ። በዚህም ሂደት ውስጥ ደጃች ማሩ ልጅ ኃይሉን ለማመን ስለቸገራቸው ልጅ ኃይሉን ከባለቤታቸው ነጥለው። ለደብረታቦሩ ገዢ ከነ ልጇ የልጅ ኃይሉን ምሽት ለዛ ገዢ ዳሯት። ልጅ ኃይሉን ደግሞ ፈንጃ ላይ ግዞተኛ አርገው አቆዩዋቸው።
የደጃች ማሩ አማካሪዎች አንድ ቀን ወደ ደጃች ቀርበው ለልጅ ኃይሉ ኮሶ እንኳን የምታጠጣው አንዲት ሴት እንዳርለት ሲሉ ይማፀኗቸዋል። ደጃቹም ከትንሽ ልመና በኋላ የይሁንታ ቃላቸውን ይሰጣሉ። ይሄኔ ነው የካሳ ወላጅ እናት ከጎንደር ወደ ልጅ ኃይሉ የመጡት። በዘመኑ የገዢው ጠንቋዮች አተረጓጎም /አሟርት/ ስልጣንህን የሚነጥቅህ እና የሚገልህ ካሳ የተባለ ሰው ነው ተብሎ ለደጃች ማሩ ቀድሞ ተትንብዮለት ነበር። ይሄ በእንዲህ እንዳለ ልጅ ኃይሉ ከአጤ ፋሲል ዘር ከሚወለዱት ከወይዘሮ አትጠገብ ሌላ ወንድ ልጅን ወለዱ ልጁንም ማን እንበለው ብለው ሲመክሩ አባት እኔ ካሳ ብዬዋለሁ አሉ። /ካሳ የማለታቸው ምክኒያት የቀድሞ ወንድ ልጃቸው ከነባለቤታቸው ለደብረ ታቦሩ ገዢ ስለተሰጠባቸው እንደሆነ ልብ ሊሉት ይገባል።/ …በሟርተኞች አፍ ካሳ በተባለ ሰው እንደሚጠፉ የተነገራቸው ደጃች ማሩ ይሄን ሲሰሙ ተሸበሩ ልጁንም ለማጥፋት አንድ አሽከራቸውን ላኩት። ያ አሽከራቸው ግን ያን ለማድረግ አልደፈረም እና ወደ ልጅ ኃይሉ በመሄድ ሁሉን አጫውቶ ከዛ ስፍራ አስመለጣቸው።
ልጅ ኃይሉ ባለቤታቸውን ከጎንደር አድርሰው እሳቸውም ከቋራ ከተቱ። የልጅ ኃይሉ ባለቤት በለሊት ቤተክርስትያን ደውል በማስደወል ህዝቡ እንዲሰበሰብ አድርገው ሁሉን ታሪክ አጫወቱ። ደጃች ማሩ በታቦት የሚያምኑ ስለነበሩ የካህናቱን ልመና ተቀብለው እንደ ፈርኦን ወንድ ልጅን ማስገደላቸውን ተዉት! እንደ ሙሴ በጨቅላነቱ ከሞት የዳነውም ካሳ በጎንደር ከእናቱ ዘንድ አድገ። እድሜው 5 ዓመት ሲሞላው የነአጤ ፋሲል ዘር ሳይማር መቅረት የለበትም ተብሎ ልጅ ካሳ ጎርጎራ አከባቢ በሚገኝ ገዳም የቅስና ትምህርቱን እንዲማር ተደረገ። ከዛም ልጅ ኃይሉ ልጃቸውን ወደርሳቸው ወስደው ለማሳደግ ከወይዘሮ አትጠገብ ቢጠይቁ እናት በፍፁም ከልጄ አልለይም በማለታቸው ለቋራ ቅርብ ነው ወደተባለ ገዳም ተቀይረው መማር ጀመሩ። ታዲያ ካሳ ይሄኔ ነው የአውሮፓውያንን ስልጣኔ እና አረብኛ ቋንቋን የለመደው። ይሄም የሆነው መሲኃ የተባሉ መነኩሴ በአሌክስ አንድሪያ ግብጥ የተምረው፣በኢየሩሳሌም ብዙ አመት የኖሩ፣ የኢሮፓን ስልጣኔ የሚያውቁ፣ ኢብራይስጥ፣አረብኛ፣ፈረንሳይኛ ወዘተ ቋንቋዎችን መናገር የሚችሉ የሀበሻ ሰው በዚያ ገዳም ነበሩ።
ታዲያ እኛ አባት ካሳን ሲያዩት ትምህርት የሚቀበል አዕምሮው ብሩህ የሆነ ሰው በመሆኑ አጅግ አብዝተው ወደዱት! ወደራሳቸውም አቅርበው የአውሮፓን ስልጣኔ ነገሩት አረብኛ ቋንቋንም በልጅነቱ አስተማሩት። ካሳ ከእርሳቸው በቆየበት ዘመን ታላቅነትን አብዝቶ ተማረ! ኋላ የቀረች ኢትዮጵያም በለጋ እድሜው ኃሳብ ሆነችበት…
ዘመን ጉዞውን ቀጥሎ ደጃች ማሩ በኢስላሙ በራስ አሊ ተደምስሶ ስለጠፋ የልጅ ኃይሉ ታላቅ ልጅ የሆነው ክንፉ የአባቱን ኃገር ለማስተዳደር ይመጣል። ወጣቱ ካሳም ከወንድሙ ዘንድ መኖር ይጀምራል! በዘመኑ ትልቅ ጦርነት ነበር ያም ጦርነት ግብፆች እየመጡ ኢትዮጵያን ይወሩ ነበር ቱርኮችም በሱዳን እየገቡ ኢትዮጵያን ይወሩ የነበረበት ጊዜ ነው። ካሳና ክንፉ አብረው በመቀናጀት ኃይለኛ ተዋጊ ሆኑ። የመጣባቸውንም ጠላት ድባቅ እየመቱ መልሰዋል። አንድ ቀን ቁጭ ብለው የጦር ጥቃት ንድፍ በሚነድፉበት ጊዜ ካሳ አንድ ስልት ያመጣል እሱም ከነሱ ሰው ሳይጎዳ እነዛኛውቹ በተኙበት ሌሊት ሄዶ የማውደም ኃሳብ ነበር። ይሄም ኃሳብ በተግባር ላይ ሲውል የተሳካ ዘመቻ አስገኝቶላቸዋል። ከድሉ መልስ ፈንጫ ላይ ደግሰው ካሳ እየተዘዋወረ ህዝቡን እና ወታደሩን ብላ ጠጣ ሲል ቆይቶ ታላቅ ወንድሙ ክፉ ጥርጣሬ አድሮበት ኑሮ ካሳን ጠላው። ነገ ይገለብጠኛል የሚል ስጋት ያደረበት ገዢ ደጃች ክንፉ ካሳን አንተ ወዲያ በል ብለው ካራ ይወረውሩበታል ካሳም እጅግ ደንግጦ ወደ ስደት ተነሱ። በስደታቸውም ጎጃም ደርሰው ለደጃች ጎሹ አሽከርነት ይቀጠራሉ። ደጃች ጎሹም በሟርተኞች አፍ ካሳ በተባለ ሰው እንዲጠፉ ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም ካሳን አይተውት ግን ሊሰዱት አልወደዱም። እንደውም ከልጄ አለይህም ብለው ሟርቱን ትተው ካሳን በቤታቸው አኖሩት።
ካሳ በመስፍኑ ደጃች ጎሹ ቤት ሳሉ የወንድማቸውን መሞት ሰምተው እጅግ ያዝናሉ በዚህም የወንድሜን ቀብር ልሂድ ብለው ተነሱ።  ደጃች ጎሹም ከሄደ አይመጣም ብለው ሰጉ ካሳ ግን እመጣለሁ ከዛ ምን አለኝ ሲሉ መለሱ። ከዛም ደጃች ጎሹ የራስ አሊ ወታደሮች እንዳይዘርፉት በማለት ከወታደሮች ጋ ሰደዱት። ከወታደሮቹ መኃል አንዱ ግን የካሳን የጨቅላነት ዘመን ያስቀጠለ ነበር እና ካሳን ጠጋ ብሎ ቢጠይቀው የልጅ ኃይሉ ልጅ መሆኑን ተረድቶ ሁሉን አጫወተው ተቃቅፈውም ተላቀሱ። ካሳም ያን ሰው በል ና እናቴን ታገኛተለህ ብሎ ከጎንደር ወደ እናቱ ወሰደው። በዛም አብረው ሰነባበቱ በጊዜው ጎንደርን የራስ አሊ እናት እቴጌ መነን ትገዛ ነበር። ካሳም በዛ መቆየት ስላልወደዱ ወደ ቋራ ዘለቁ። ቋራ በደረሱ ጊዜ የቋራ ህዝብ በደስታ የጌታችን ልጅ መጣ ሲሉ ተቀበሉት። ካሳንም ግዛን ንገስብን ሲሉም ተማፀኑት። ይሄን የሰሙ የእቴጌ መነን ጭፍሮች ካሳን ለመያዝ ሲመጡ ካሳ ወደ በረሃ ሸሽተው ይገባሉ። በዛም ጉምዞችን እና ሌላውን አግባብተው መዋጋት ይጀምራሉ። ይሄኔ እነ ራስ ዓሊ ጭንቀት ጀመራቸው። ከዛም በሽማግሌ አስጠርተው ሹመት እንስጥህ ብለው አስጠሩት። ልጃቸውንም እንዲያገባ አደረጉት። የራስ አሊ ልጅ ውብ ስለሆነች ብዙ መኮንኖች ይመኟት የነበረች ናት። የሚመኟትም መኮንኖች ሁሉ በካሳ ላይ ጠላት ሆኑበት። ይሄን ያስተዋለች የካሳ ሚስት ተዋበች /እቴጌ/ እንዴት ስትል ብስጭት ትላለች። በእቴጌ መነንም የሚደርስበት ንቀት እና ስድብ ያበግናት ስለነበር ካሳን እንዲሸፍት ትገፋፋው ጀመር። ከዛም በለሊት ጠፍተው ሚሽታቸው ከሟች ወንድማቸው ሰራዊት ዘንድ በጭልጋ አቆይተው እሳቸውም ቋራ ሄደው ሰራዊት ይሰበስባሉ። ከዛም ሚስታቸውን ወደ ቋራ በሰራዊት ያስመጣሉ። የካሳን መምጣት የሰማ የቋራ ሹም ሸሽቶ ይሄዳል… የነ ራር አሊ መኮንን የሆነ ወንድ ይራድ የተባለ ሰው ተዋበችን ይመኝ ስለነበር የሸሸውን ሹም አንተ ሽንታም ይሄን የኮሶ ሻጭ ልጅ ፈርተ ትሸሻለህ ሲል ካሳን ሊወጋ ተነሳ።  በእውነቱ የካሳ እናት ኮሶ ሻጭ ሆና ሳይሆን እነ ራስ አሊ ጉልበቱን ለመቀነስ እና ካሳን ለማጥላላት የተጠቀሙት የስም ማጥፉያ እንጂ በእናቱም በአባቱም የተትረፈረፈ ንብረት የነበረው ነው። ከነሱም በላይ ዙፋን የሚገባው ከአጤ ፋሲል ዘር የሚወለደው ሳሳ መሆኑን አሳምረው ያውቃሉ።
ታዲያ ያ ወንድ ይራድ የተባለ መኮንን ካሳን አንጠልጥዬ አመጣለሁ ብሎ ተነሳ። ከሳም ሊወረው የመጣወን ጦር እንዳልነበር አድርጎ ካወደመው ኋላ ወንድ ይራድን ከነ ነፍሱ አስማርኮ አስመጣው። እናቴ በየት ኮሶ ስትሸጥ አይተኃታል በማለት ተቆጥቶት ቀድሞ ሚስቱ እንድታዘጋጅ ያዘዛትን ኮሶ በተፈጥሮው ኮሶ ለማይወደው ለወንድይራድ አስጋተው። ከዛም የፊጥኝ አስረው ጣሉት ይሄንን የሰማች እቴጌ መነን እራሴ እዋጋለሁ ብላ ተነሳች እሷንም ማርኮ ከነ ባሏ በድንኳን አኖራት። እቴጌ መነንም በብስጭት እየተሳደበች ተዋበችን አንቺ ነሽ ይሄን ሽፍታ ልብ እንዲያወጣ ያደረግሽ በማለት መራገሟን ጀመረች። ይሄኔ ወሎና ጎጃም ላይ የዘመተው ራስ አሊ የእናቱን መታሰር ሲሰማ ወደ ኋላ ይመለሳል ከመኳንንቱም ጋር መክሮ እዳንገለው አንችለውምና በህርቅ እንሂድበት ይላሉ። ካሳም ወታደሮቻቸውን አስቀርቶ እነሱን ይሰዳቸዋል።
ራስ አሊ የወገራን መስፍን፣ ደጃች ውቤን፣የጎጃሙን ሁሉ ሰብክ በአንድ አመሳጥሮ ክርስትናን የማይወደ አረመኔ ተነስቷል እና እንውጋው ሲል ጠየቃቸው። ደጃች ውቤ ወታደር እልክልኃለው እኔ ግን በምፅዋ ጠላት ስላስቸገረኝ አልመጣም ይሉታል። የሰበሰቡትን ሰብስበው ካሳን ቢገጥሙት አሁንም ድል በካሳ እጅ ሆነች። ራስ አሊም ሸሽቶ አመለጠ። ካሳም የጎንደርን ዙሪያ መሳፍንት ጠርጎ ጨረሰ። ይሄኔ ደጃች ጎሹ በካሳ ላይ ዘመቱበት። ካሳ ግን ወንድሙ በተነሳበት ጊዜ ከሳቸው ሸሽቶ እንደ ልጃቸው አኑረውታል እና ሊገጥማቸው አልፈቀደም ነበር። አብዝቶ ቢማፀናቸውም ሊሰሙት አልፈቀዱም እና ተዋግተው ተሸነፉ። ካሳ ግን ለወታደሩ ሁሉ እንዳይገሏቸው  አስቀድሞ የነገሩ ቢሆንም ወታደሩ ገሏቸው ኖሮ ካሳ አምርረው አልቅሰው ቀበሯቸው። ጎጃምና ጎንደርም በካሳ እጅ ነፃ ወጣ። ቀጣይ የሆነው ደጃች ውቤ ነበር እና ያን ባለ ብዙ ወታደር ደምስሰው ወሎን አስገብረው ሸዋ ቢዘልቁ የሸዋው ንጉስ በህመም ቀድሞ ስለሞተ ካሳ ልጅ ምኒልክን ለግዞት ወሰዱት ልጅ ምኒልክም በካሳ ቤት እንደ ንጉስ ልጅ ሆኖ አደገ።
ከዚ በኋላ ቴዎድሮስ ንጉሰነገስት ሆኑ። ታዲያ በዚህ ጉዞው ካሳ ዙፋን አይገባውም ሲሉ ያሙታል ካሳም እጅግ ተበሳጭቶ የኔ የዘር ሐረግ ከዳዊት እስከ ሰለሞን ከሰለሞን እስከ ፋሲል ከዛም እስከኔ ሊቆጠር ይችላል ብሎ ተናገር። እንዲሁ አንድ ቀን ሊቃናት ተሰብስበው ከዳዊት አንስተው የዘር ሀረግ ሲቆጥሩ ከአንድ ቦታ ላይ ማለፍ ሲያቅታቸው ካሳ በቁጣ እኔ አስተምራችኋለው ብሎ ተናግሯቸዋል።
በዘመኑ የገቡት ሚስዮናውያን ካሳን መስድብ እና ማማት ይጀምራሉ ከተሳዳቢዎቹም ውስጥ የግብፁ አቡነ ሰላማ አንዱ ነው። አፄ ቴዎድሮስ ግብፆችን እንደማይወዷቸው የሚያውቀው አቡነ ሰላማ ቴዎድሮስ ሽፍቶችን ሲቀጣ እና የተነሱበትን ጠላቶቹን ሲያወድም የተበሳጩት አቡነ ሰላም አንተ ክርስቲያን አይደለህም ሲሉ ይሰድቡታል ካሳም አንተ ነህ ክርስቲያን ያልሆንከው ብዙ፡ቁባቶች እንዳሉህ አውቃለሁኝ በማለት ይቆጣቸዋል። ከተሳዳቢዎቹ ሚሲዮናውያን ጋ አብሮ በመሆን ግዞት የወረደው አቡነሰላማ ቤተክርስቲያን በካሳ ላይ እንድታምፅ ያሴር ነበር። ይሄውም ተሳክቶለታል። አፄ ቴዎድሮስ ወደ ንግስት ቪክቶሪያ የሰደደው መሳሪያ የሚሰራ ሰው ላኩልኝ የሚለው ጥያቄ በመልዕክተኛው ችላ ባይነት እና በሀገሪቱ ወኪል ችላ ባይነት በመዘግይቱ ሚሲዮናውያኑ ለብዙ እንግልት ተዳርገዋል። በመጨረሻም የቴዎድሮስ ደብዳቤ ከአመታቶች በኋላ ታይቶ ለመድፍ መስሪያ የሚሆኑ ቁሶችን ለመግዛት እና ባለሙያውችን መድበው ወደ አቢሲኒያ ለመላክ ከወሰኑ በኋላ ከሽንፈት ቆጥረውት አፄ ቴዎድሮስ ላይ በህንድ የሰፈሩ የእንግሊዝ ወታደሮች ዘመቱ። ካሳ በወቅቱ ወታደሮቹ እየከዱት የነበረ ሲሆን ቀድሞውንም በስርዓት ለመመራት አይፈልጉም ስለነበር ከ150ሺ የሚበልጥ ወታደር የነበረው ካሳ እንግሊዝን ሲዋጋ 50ሺ የሚሆን ወታደር እንኳን በቅጡ አልተሰለፈለትም ነበር።
እንግሊዞች ወትሮውንም የጦሩ መዳከሙን ባያውቁ እና ባይሰሙ ኖሮ ካሳን ለመውጋት አይደፍሩም ነበር። የሆነው ሁሉ ሆኖ ከእስረኞቹም መካከል የአፄ ቴዎድሮስን ጀግንነት እና ታላቅነት እንዲሁም ራዕዩን የማያከብሩለት ጥቂቶች ናቸው። አፄ ቴዎድሮስ በጊዜው ኃያል የተባለውን እንግሊዝን ጦር ከመግጠም ይለቅ አለመሸሻቸው ለእንግሊዞች ቢደንቃቸውም ንጉሱን ግን በሰላም እጅ እንዲሰጡ ቢጠይቋቸውም እምቢታቸው እና በጀግንነት እስከ መጨረሻው መታገላቸው አስደንቋቸዋል። አፄው በመቅደላ ሲወድቁ ጫማም በእግራቸው አልነበረም የለበሱትም ልብስ ከተራው የገበሬ ልብስ የማይሻል ነበረ።
ምቾትን ንቀው ውድ ነፍሳቸውን የገበሩልን ውድ የሀገራችን ነገስታቶች ስማቸው ከመቃብር በላይ ከፍ ብሎ ለዘለዓለም ይጠራል።
እንግሊዞች አጉል ጀብዱዋቸውን ለወር ያክል ሲዘክሩ ይቆያሉ እኛ ግን በኃገራችን አበሻን አላስንቅም ወንዶችን ሁሉ የገደልኩ እኔ በሴቶች ልሞት አይገባኝም ሲል እራሱን የሰዋውን ታላቅ ንጉስ ለመዘከር ያቺን፡ቀን ብቻ እንጠብቃለን! ቴዎድሮስ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እራሱን ማጥፋቱ የእንግሊዝን የዘመቻ ጉዞ ትርጉም አልባ ከማድረጉም በላይ ኪሳራቸውን አብዝቶታል።
“ገደልን እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለም በእጃቸው
ምናሉ እንግሊዞች ሲገቡ ከኃገራቸው
መቼም ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው”
የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትላንቷ አቢሲኒያ በካሳ ደም እና ላብ የዘመናዊ ስልጣኔ መሰረቷን ስለገነባች መቼም አትወድቅም። ኢትዮጵያ እራሷን በራሷ እንደ ካሳ ካላጠፋች ሌላ ባዕድ እንደማያጠፋት ጣሊያኖች ብቁ እማኞች ናቸው። ፈጣሪ የካን ነፍስ በገነተ ያኖርልን ዘንድ እየተመኘሁ በጀግናው ሞት ትፎክሩበት እና ትኮሩበት ዘንድ እኔ ወዳጃቹ እመክራለሁ።
✎✍በታሪኩ_ሐብታሙ®/ታታ/✔ ክርስቶስ በተወለደ በ2010 ዓመተ ምህረት ሚያዝያ በባተ በ5ኛው ቀን ሸዋ አዲስ አበባ ላይ ተጣፈ።
ምንጭች ☞ የኢትዮጵያ የ፭ሺ ዘመን ታሪክ…
              ☞ አፄ ቴዎድሮስ ጫማ አልባው ንጉስ
              ☞ የኢትዮጵያ ታሪክ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ
             ☞ አንድ ለናቱ እና
             ☞ የተለያዩ ሚዲያዎች ናቸው።
Filed in: Amharic