>
5:13 am - Thursday March 30, 2023

"ይህ ሰው ገና ያልገለጽናቸው እልፍ ገጾች ያሉት ግዙፍ መጽሀፍ ነው" (ኢትዮ አይስ ፔጅ)

ተዋወቁት  ይህ ሰው ብዙ ያልተፈተሹ ታሪኮች እና ያልተነገሩ እውነቶች ያሉት አንድ ግን ደግሞ ብዙም ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ታሪከ ሲመረመር ከበሻሻ እስከ አጋሮ- ከአጋሮ እስከ ጂማ- ከጂማ እስከ አዲስ አበባ- ከሀገሪቱ እልፍ ጥጎች እስከ ጦር አውድማ እልፍ ወጎች- ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ- ከደቡብ አፍሪካ እስከ አሜሪካ/ አውሮፓ እና እስከ መላው አለም የሚዘረጋ የትጋት፣ የቅንነት፣ የሀገር ፍቅር፣ የወገን ተቆርቋሪነት፣ የአይበገሬነት፣ የአሸናፊነት፣ የአዎንታ ሀይል ባለቤትነት፣ የውብ አመለካከት ነቅእነት…. ወዘተ ታሪክ ያለውና ገና ያልገለጽናቸውው እልፍ ገጾች ያደመቁት ግዙፍ መጽሀፍ ነው፡፡ ይህ ሰው ኢንሳን ጸንሶ የወለደና በሁለት እግሩም እንዲቆም ያደረገ፤ በኋላም በባለጊዜዎች ተገፍቶ ገለል የተደረገ ባለ ብዙ ራእይ ሰው ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በዶክተሩ ምናብ የተሳለውና- የደከመለትም ኢንሳ ይሄ አይደለም፤ ከዚህ የሚርቅ ቁመና ያለውና የሀገር መከታ የሚሆን ኢንሳን ነበር ዶከተሩ የነደፈው፡፡) ይህ ሰው የሳይንሰ እና መረጃ ማእከልን ያቋቋመና ከፌዴራል ተቋማት ውስጥ በሁሉም መመዘኛዎች ግንባር ቀደም ተቋም እንዲሆን ያስቻለ አይደክሜ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያቤትን ለአንድ አመት ብቻ መርቶ በግማሽ ምእተ አመት እውን ሊያደርጉት የሚከብድን ስኬት ማስመዝገብ የቻለ አጃኢበኛ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ ተጠሪ ተቋማት፣ ለኦሮሚያ ክልል አመራሮች እና ባለሙያዎች… ወዘተ በራሱ መልካም ግንኙነት እና ዲፕሎማስያዊ መንገድ የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ የትምህርት እድል በማመቻቸት ስራዎች ድርቀት ሳይሆን በእውቀት እንዲመሩ ያደረገ ድንቅ ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ኢትዮጵያችን ከበለጸጉት ሀገራት ተርታ የምትሰለፈውና እነርሱ ወደ ተሻገሩበት ከፍታ መሻገር የምትችለው ትምህርታችን፣ ጤናችን፣ ኢንደስትሪያችን፣ የትራንስፖርት ስርአታችን፣ ግብርናችን ……. ወዘተ በሳይንስ እና ቴከኖሎጂ ሲደገፍ ብቻ ነው በሚል ስልጡን እሳቤ አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረገ ያውን በትረ ሙሴ ፕሮጄክት የጸነሰ፣ ያበሰለ እና ወደ ትግበራ ያሸጋገረ ሩቅ አሳቢ ሰው ነው፡፡ ( በነገራችን ላይ በትረ ሙሴ የተሰኘው ፕሮጄክት እጅግ ግዙፍ እና ሊባልለት የሚገባውን ያህልም ያልተባለለት አቢይ ፕሮጄክት ነው፡፡ ሌላ ጊዜ ስለ በትረ ሙሴ የሆነ ነገር ለማለት ሞክራለው፡፡) ይህ ሰው በኦሮሚያ ከተማ እና ቤቶች ልማት ቢሮ ውስጥ በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የቢሮው ሀላፊ በነበረበት ጊዜ የመስሪያ ቤቱን ሁለንተናዊ ገጽታ የቀየረ እና የሰራተኞችን የስራ ተነሳስኦት አስደናቂ በሆነ መልኩ የጨመረ ግሩም መሪ ነው፡፡ ይህ ሰው በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ሆኖ በሚሰራበት በአሁኑ ጊዜም የድርጅቱን የ አስር አመት ስትራቴጂክ እቅድ ያሰናዳ፣ ኦህዴድ ትላንቱን ዘክሮ- ዛሬውን መርምሮ እና ነገውንም ተንብዮ እንዴት/ ወዴት መሄድ እናዳለበት ፈሩን የተለመና የማይደፈሩ ውሳኔዎችን በልበ ሙሉነት የወሰነ ልባም የለውጥ ፊታውራሪ ነው፡፡ ይህ ሰው (በተጓዳኝ ያሉት ዲግሪዎች እንዳሉ ሆነው) ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ (Phd) ድረስ በዘለቀው የአካዳሚኩ አለም ጉዞው ሁሉንም የትምህርት- የጥናት እና የምርምር እርከኖች በእጅግ በጣም ከፍተኛ ማእረግ የተሻገረ ጂኒየስ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ይህ ሰው ከደጋግ ጀግኖቹ የኦሮሞ ምድር ባፈራው ኢትዮጵያዊነቱ ፍጹም የማይደራደር፤ ሀገሩን እና ወገኑን በፍጹም ፍቅር የሚወድ የኦሮሞ እና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው፡፡ ይህ ሰው ☞ ኢትዮጵያዊ ☞ ኦሮሞ ☞ የኦህዴድ ማእከላዊ ጽህፈት ቤት ሀላፊ በመጨረሻም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነው ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር….. ዶክተር አቢይ አህመድ☞

Filed in: Amharic