>

"ህዝብ ዋጋ የከፈለበትን ትግል የብቻዬ አታድርጉት አይገባኝም" - ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ

 አለማየሁ ማህተመ ወርቅ
“ሕዝቡ እስከሞት ድረስ ዋጋ የከፈለበትን እና እየከፈለበት ያለውን ትግል እኛ ይችን ትንሽ መስዋእትነት ከፈልን ብለን መውሰድ የለብንም፤ ድሉ የሁላችንም ነው!!
ይህንን የምለው ለትህትና አይደለም እውነት ስለሆነ ነው..”
ይህንን ያለው እጅግ ጠንካራ እና አስደናቂ ስብእናን የተላበሰው ጋዜጠኛ እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ነው።
በአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት (አምነስቲ ኢንተርናሽናል) ጋባዥነት ወደ ኬንያዋ ርእሰ መዲና ናይሮቢ የመጣው እስክንድር ነጋ   ከአቀባበሉ ጀምሮ በቆይታው እጅግ ደስ መሰኘቱን ገልጿል።
በስደት የሚገኙ ጋዜጠኞች እንዲሁም በሀገር ውስጥ በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ከአመራር አንስቶ በተለያየ እርከን በንቃት ይሳተፉና ይታገሉ የነበሩ ዛሬ ግን በአስከፊውና ፋሽስታዊው ስርአት ተገፍተው ለስደት የተዳረጉ  ወጣቶች ለእስክንድ ያሳዩት አክብሮትን እና ፍቅርን የተሞላ አቀባበል እጅግ ልቡን እንደንካውና ፈጽሞ ያልጠበቀው መሆኑን ነው የተናገረው።
የእስክንድርን የእንኳን ደህና መጣህ የክብር አቀባበል እንዲሁም አለም አቀፍ የፕሬስ ቀንን በማስመልከት ናይሮቢ በሚገኝው “ስማርት ቪው” ሆቴል የሻማ ማብራት ስነስርአት የተካሄደ ሲሆን እስክንድር ያደረገውን አጠር ያለ ንግግር የጀመረው ስለ ፍትህ እና ዴሞክራሲ ሲባል በአገር ቤት መተኪያ የሌላትን ክቡር ህይወታቸውን ላጡ፣ የአካል መጉደል ለደረሰባቸው፣ በእስር ላሉ፣ በስደት ለሚንከራተቱ በአሰቃቂው የስደት አለም ኬንያ ናይሮቢ ላይ ህይወታቸውን ላጡ ጋዜጠኛ ሚልዮን ሹርቤ እና ለጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ የህሊና ጸሎት በማስደረግ ነበር።
“….ዛሬ የህዝባችን የዴሞክራሲ ጥማት እና ፍላጎት የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷል ይሄ ደግሞ ስርአቱ ህዝቡ ላይ ያደረሰው አሰቃቂ ግፍ እና ጫና ውጤት ነው ይህ ጫና መታመቅን ይመጣል የታመቀ ነገር ደግሞ መፈንዳቱ አይቀርም፤የእነርሱ ጫና እና አፈና በበረታ ቁጥር ህዝቡም በዚህ ስርአት ላይ ጥገናዊ ሳይሆን ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ካልቻልን የዴሞክራሲ የፍትህ እና የአንድነት ጥያቄያችን ምላሽ አያገኝም ብሎ ስላመነ እስካሁንም ዋጋ ሲከፍል ኖሯል ከዚህም የበለጠ ዋጋ ከፍሎ በመረጠው መንግስት መተዳደር እና የዴሞክራሲ ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ የህይወት ጭምር ዋጋ ከፍሎ ከእስር ካስወጣኝ ህዝብ ጎን እንደምቆም ቃል እገባለሁ… ድል ለዴሞክራሲ.”
እስኬ ይህን ብሎን ሻማችንን ለኩሰን የፍቅር የአንድነት ራት ተገባብዘን ለቀጣይ የትግል ህይወቱ መልካሙን ሁሉ ተመኝተን በድል ተመለስልን ብለን ጀግናችንን ሸኝተነዋል።
የግርጌ ማስታወሻ – ለዚህ ዝግጅት ማማር ጊዜያቸውን ገንዘባቸውን ሰውተው አስቸጋሪ ውጥ ውረድን ያደረጉት ጋዜጠኛ ኤልያስ ጉዲሳን እና ጋዜጠኛ መልካም ሰላም ሞላን እንዲሁም ሌሎችን ከልብ እናመሰግናለን ይሄን ፍቅር አንድነታችንን እግዚአብሔር ይባርክ።
Filed in: Amharic