በደቡብ አፍሪካ ሰባት7 ኢትዮጵያውያን ተገደሉ!
በደቡብ አፍሪካ በ48 ሰዓታት ውስጥ ሠባት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ተገደሉ!!
ይህ ነገር ተቃዋሚን የማፅዳት ዘመቻ ይሆን ?
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን
ከጆሀንስበርግ በ60 ኪሎ ሜትር በምትርቀው ፓልም ሪች ወይም ቶኮዛ በሚባል አካባቢ ከትላንት ወዲያ ጀምሮ እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ 7 ኢትዮጵያውያን የተገደሉት በተደራጁ ዘራፊዎች እና ገዳዮች በተወሰደ እርምጃ መሆኑ ታውቋል።
5ቱ የተገደሉት ትላንት ምሽት መሆኑን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ በቦታው ደርሶ ጉዳዩን እየተከታተለው መሆኑን አስታውቋል።
የሟቾቹ ኢትዮጵያውያንንም አስክሬን ወደ ሀገር ቤት ለመላክ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም ገልጿል።
በደቡብ አፍሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደዚህ ወቅት እና ጊዜ የከበደ ተደራራቢ የሞት እና የሀዘን ጊዜ የለም። ሀዘን ተደራርቦ እየመጣባቸው ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ 9 ኢትዮጵያውያን በደቡብ አፍሪካ መገደላቸው በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያንን በሀዘን አቆራምዷል።
በአክቲቪስት ገዛሀኝ ገብረመስቀል ነብሮ ግድያ ሀዘን የመታው ኢትዮጵያዊ ገዛህኝን ሸኝቶ ወደ ቤቱ ሳይገባ ሌላ ኢትዮጵያዊ ተገድሏል።
ባለፉት 48 ሰዓታት ደግሞ 7 ኢትዮጵያውያን በአንድ አካባቢ መገደላቸው ተሰማና ሀዘንኑን የከፋ አደረገው።
ለኢሳት ዜናውን ያደረሱት በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒት አባላት እንደገለጹት ትላንት እኩለ ሌሊት የተደራጁ ዘራፊዎች እና ነብሰ በላ ገዳዮች ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት መንደር ገብተው 5ቱን ገድለው ንብረታቸውን ዘርፈው ሸሽተዋል።
ከጆሀንስበርግ በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ፖልም ሪጅ ወይም ቶኮዛ በሚባለው መንደር ከትላንት በስቲያ አንድ ኢትዮጵያዊ በስለት ተወግቶ የተገደለ ሲሆን በማግስቱ ትላንት ሌሊት በዚያችው መንደር አምስት ኢትዮጵያውያን መገደላቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ አበበ ትላንት ሌሊት የአምስቱ ኢትዮጵያውያን ግድያ እንደተፈጸመ የይድረሱልን ጥሪ ተደርጎልን ወደ አካባቢው ስናመራ ዛሬ ጠዋት አንድ ሌላ ኢትዮጵያዊ መገደሉን ሠማን ሲሉ ገልጸዋል።
በድምሩ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ሠባት 7 ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ፖልም ሪጅ በተባለ መንደር መገደላቸውን ነው አቶ ታምሩ የገለጹት።
ግድያው ከዘረፋ ጋር ብቻ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደማይቻል ቢገመትም ጉዳዩ በምርመራ ላይ በመሆኑ የግድያውን ትክክለኛ ምክንያት አሁን ላይ መግለጽ እንደማይቻል አቶ ታምሩ ተናግረዋል።
የተገደሉት የሰባቱ ኢትዮጵያውያን ማንነት ስም እና የቤተሰብ አድራሻ የታወቀ በመሆኑ ለቤተሰብ የማሳወቅ ስራ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ ታምሩ ነገ የሁለቱ አስክሬን ወደ ሀገር ቤት እንደሚላክም አስታውቀዋል።
በአሁኑ ጊዜ በፖልም ሪጅም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተፈጠረው ሁኔታ ተረብሸዋል።
ያንን የማረጋጋት ስራ እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል። በየጊዜው አስክሬን መሸኘት ለእኛ ኢትዮጵያውያን አስቸጋሪ እና ከባድ ሆኖብናል ያሉት አቶ ታምሩ በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዝምታ መገረማቸውንም ገልጸዋል።
ኤምባሲው ጉዳዩን በተመለከተ እስካሁን የሰጠው አስተያየትም ሆነ ምንም አይነት መረጃ የመሰጠትም ይሁን ለዜጎቹም ፍትህ የወሰደው እርምጃም የለም።