>

በእምዬ ምኒልክ ስም እየማሉ ከጦር ግምባር የወደቁ ሁለት ጀግኖች!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

ዛሬ ሁልቆ መሳፍርት ከሌለው አኩሪ ታሪካችን አንዱ የሆነው የድል ቀን ነው።  የታሪክ ተመራማሪዎች ” ታሪክ ራሱን ይደግማል ” የሚሏት ሀይለ ቃል አለቻቸው።
ጆርጅ ኦርዌል የተባለው ታዋቂው እንግሊዛዊ ደራሲ ደሞ  <<  ያለፈውን  ታሪክ የተቆጣጠረ የአሁንን ብሎም የወደፊቱን መቆጣጠር ይችላል ።>> ይላል።
የባለፈውን ታሪክ ጀግኖች አባቶቻችን ተቆጣጥረውታል የወደፊቱን ደሞ እኛ ልጆቻቸው እንደምንቆጣጠረው  እርግጠኛ በመሆን ቀኑ ሳያልፍብኝ ይችን ልበል።
ዛሬ ይሄን የድል ቀን ምክንያት አድርጌ እልፍ አእላፍ ከሆኑ ጀግኖች አባቶቻችን ሁለቱን ብቻ በአጭሩ  ልዘክር ። “ሁለቱ በምን ተመረጡ ?” ለሚል  ጠያቂ ወደ መጨረሻ ምክንያቴን እገልፃለሁ ።
1 ~ አቢቹ 
2~ ባልቻ አባ ነፍሶ 
1 ~ አቢቹ  ከሰሜን ሸዋ ሰላሌ የዘመተች የ16 አመት ልጅ ነች  ። ( አንች ያልኳት ሁሉም የታሪክ ፀሀፍት አንች ስለሚላት ነው)  ።
አቢቹ ከጣሊያን ጋር በተደረገው ጦርነት ስሟ እንደ ሰደድ እሳት ሲሰራጭና ትግራይ አካባቢ ያሉ ባንዳዎችን እንደ መስቀል ችቦ ስታነዳቸው ከንጉሱ
” ልጁን አቁሙት ! ” የሚል ትእዛዝ ለጦሩ መሪ ተላከለት ።
አቢቹ ለዚህ ትእዛዝ የሰጠው መልስ የሚደነቅ ነበር ።
የሀበሻ ብዱ በሚል በተተረጎመው የአዶልፍ ፓርካስ መፅሀፍ ላይ ከአቢቹ ጎን በመሆን  ንግግሩን የሰማው አዶልፍ ፓርካስ የአቢቹን መልስ ቃል በቃል  እንደዚህ ብሎ ፅፎታል
<<  ደጃዝማች! ! ከአገሬ የመጣሁት የምኒልክን አገር በጠላት ስትወረር ቁጭ ብዬ አላይም በማለት በምኒልክ ስም ለእናቴ ምዬ ነው።
ለአንተ ግን አሁንም በምኒልክ ስም፣ በምኒልክ
አምላክ በድጋሚ ቃሌን እሰጣለሁ። ለአንተ እሞታለሁ። ተመለስ
ላልከው ግን፣ የት ነው የምመለሰው? ምንስ መመለሻ ቤት
አለኝና? እዚህም እዚያም እሳት እየነደደ እንዴት ቁጭ ልበል ?” በማለት ጥሎን ወደ ሚመራው  ሰራዊቱ ሄደ ይላል።
( አዶልፍ ፓርካስ የሀበሻ ጀብዱ)
2 ~ ባልቻ አባ ነፍሶ~ ባልቻ  በሁለት ጦርነቶች ተሳትፎ በጀግንነት የወደቀ የአገሬ አንፀባራቂ ጀግና ነው። በአድዋ ጦርነት መድፉንም ጣሊያንንም አገላብጦ ድል አድርጎ ከተመለሰ በኋላ ከ40 በኋላ በ 85 አመት እድሜው ጣሊያን ተመልሶ ሲመጣ  ባልቻ ምን አለ?
<< የምኒልክን አገር እኔ ባልቻ በህይወት እያለሁ ተደፍራ አልመለከትም !!” ብሎ በምኒልክ ስም እየፎከረ ጦር አውሮፕላን የታጀበ ጣሊያንን ገጥሞ ለአገሩ ወደቀ  ። ( አልቤርቶ ስባኪ Ethiopian under Mussoloni)
አይን ምስክር የነበሩት ፈረንጆቹ በስፋት እንደፃፉት  እነዚህ ሁለት ጀግኖች የወደቁት ” በእምዬ ምኒልክ ስም እየማሉ ነው።
ያውም ልብ አድርጉ ሁለቱም በእምዬ ምኒልክ ስም ለአገራቸው ሲወድቁ ምኒልክ በህይወት አልነበረም ።  ከምኒልክ ሞት በኋላ 3 ነገስታት ( ኢያሱ ፣ ዘውድቱና አፄ ሀይለስላሴ) ተቀያይረው አልፈው እያለ እነዚህ እንቁ ጀግኖች ለምኒልክ ያላቸው ፍቅር ወደር አልነበረውም።
አሁን ወደ ቁም ነገሩ ልምጣና ይሄን አጭር ፅሁፍ ልዝጋው ። እነዚህ ሁለት ጀግኖች  በተረት ተረት ለሰከሩ የኦሮሞ ብሄርተኞች ፍቱን መድሃኒቶች ናቸው ። እነዚህ ጀግኖች በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘፈን እየተዘፈነላቸው ነው። በጣም ጥሩ ነው። ነገር ግን ራሳቸው ጀግኖቹ ምስክርነታቸውን እንደሰጡት አንድያ ህይወታቸውን ለአገራቸው የሰጡት በምኒልክ እየማሉ እየተገዘቱ እንደነበር አብረው ከዘፈኑ ግጥም ጋር ቢጨምሩበት ታሪካቸው ምሉእ ይሆናል ። እነሱም በአፀደ ነፍስ እያሉ ሀሴት ያደርጉ ነበር።
በመጨረሻ በደም የቆየች አገር በተረት ተረትና በከንቱ ነገር  ከማድበስበስ ተቆጥባችሁ የአባታችሁን  አደራ ቅርጥፍ አድርጎ የበላ ዱርዬ ብሄርተኞች  አትሁኑ።
መልካም የድል በአል  !!!
Filed in: Amharic