>

“ኦሮማራ” በቡልቻ ደመቅሳ አንደበት!

(ሸገር ታይምስ)

ሰሞኑን ሸገር ታይምስ ከኦቦ ቡልቻ ደመቅሳ ጋር ቃለመጠይቅ አካሂደው ነበር፡፡ በቃለመጠይቁ ወቅት ስለኦሮሞና አማራ የእርስበርስ ግንኙነት ተጠይቀው የነበረ ሲሆን ሀሳባቸውን እንዲህ ሲሉ አካፍለዋል፡፡

ሸገር ታይምስ፡– ኦሮሞና አማራ አንድ ነን፣ ማንም አይለየንም የሚሉ መድረኮች ሲዘጋጁ አስተውለናል። በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ደግሞ ሁለቱ ህዝብ እንዳይጠናከርና ወዳጅ እንዳይሆን የማይፈልጉም አሉ ይባላል። እርስዎ ስለሁለቱ ህዝብ ምን ይላሉ?

አቶ ቡልቻ፡- አጼ ምኒልክና ራስ ጎበና አብረው ነው ያደጉት። አብረው ነበሩ፣ ይነጋገሩ ነበር አሁን እኔና አንተ እንደምንነጋገረው። አጼ ምኒልክ ራስ ጎበናን “ማንም የለም ከጎኔ መጥተህ እርዳኝ” ባሏቸው ግዜ “እኔ ኦሮሞ ነኝ ካንተ ጋር መስራት አልችልም” ብለዋል ራስ ጎበና? አላሉም፡፡ ራስ ጎበና ጋር ጉግስ ይጫወቱ ነበር፣ የአጼ ምኒልክን ችግር አዩ፣ ገባቸው። እሽ እከተልሃለሁ አሏቸው። ምን ስራ ትሰጠኛለህ አላሉም፣ “እሽ እከተልሃለሁ ነው” ያሉት፡፡ እሳቸው እንግዲህ አጼ ምኒልክ ሸዋን ይዘዋል፣ ወለጋ፣ ሃረር ከእርሳቸው ኮማንድ ውጭ ነው።

ኦሮሞ ግን እንደተበታተነ በየአገሩ ቀረ፣ ይህንን ለማሰባሰብ አጼ ምኒልክ ጎበናን መረጡ። ተስማሙ አብረው መጡ፣ ወደ አዲስ አበባ፡፡ አሁን ከምንነጋገርበት አንጻር አንዴት እንዳልተፈራሩ አልገባኝም። እኔ ኦሮሞ ነኝ እርሱ አማራ ነው ብለው እንዴት አልተፈራሩም? ‘ይገለኛል፣ ይጠላኛል’ ለምን አልተባባሉም። እንደዛሬው ልዩነት አለን ብለው አላሰቡም፡፡ “አንድ አገር ነን” ብለው ነው ያሰቡት፡፡ ልዩ ልዩ አገርም አለን ብለው አላሰቡም። ጎበናም ምንም ሳይጠይቁ ከእርሳቸው ጋር ገቡ አብረው በሉ ጠጡ ተጋቡ፡፡ ይህንን ነው የማውቀው። ሁለቱም አይፈራሩም አብረው ነው ለዘመናት የኖሩት ተጋብተው ተዋልደዋል።
ሸገር ታይምስ፡- አጼ ምኒልክን ለኦሮሞ የተለየ ጥላቻ አንዳላቸው አድርገው የሚያነሱ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ ነገር እንዴት ያዩታል?

አቶ ቡልቻ፡- በፍጹም ጥላቻ የላቸውም። ‘አሮሞ የሚባል ስም አልወድም እገላቸዋለሁ፣ ወላይታን አልወድም እፈጃቸዋለሁ፣ አደሬን አልወድም’ ብለው አንድን ህዝብ መርጠው ጠላቴ ነው ብለው አያውቁም፡፡ አስበውም አያውቁም። አገር እንዲሰለጥን ነው፣ ህዝብ ሁሉ እንዲሰለጥን ነው የተቻላቸውን ሁሉ ያደረጉት። ለአንድ ህዝብ የተለየ ጥላቻ ኖሯቸው ይህንን ህዝብ እንውጋው ብለው ይነጋገራሉ ብዬ መገመት እንኳን አልችልም፡፡ እሳቸው ለአገራቸው ስልጣኔ ነው የለፉት ማንንም አይጠሉም ነበር። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ሌሎች ናቸው፡፡

ሸገር ታይምስ፡- ታዲያ ሁለቱ ህዝብ እንዳይግባቡ አደረገ የሚሉት ማንን ማነው?

አቶ ቡልቻ፡– እነሱ ናቸው ቅድም የነገርኩህ፣ አለቃ ለመሆን ሁሉም ሰው እንዲቀበላቸው አማራና ኦሮሞ አብረው በልተው እና ተጋብተው ነው የኖሩት ስለዚህ ይጣላሉ ብዬ አልገምትም። ኦሮሞና አማራ ቢጠላሉ ኖሮ ለምን ይጋቡ ነበር? ለምን አማራ ለኦሮሞ ልጁን ይድራል፣ አማራስ ለምን ለኦሮሞ ልጁን ይድራል?

ስዩም ተሾመ

 


  • ምንጭ፦ ከሸገር ታይምስ ቃለመጠይቅ ላይ ተቀንጭቦ የተወሰደ
  • ምስጋና፦ ይህን ቃለ-ምልልስ ቀንጭቦ በፌስቡክ ገፁ ያጋራንን Ermias Tokumaን እናመሰግናለን፡፡
Filed in: Amharic