>

"ከገዱ አንዳርጋቸው ጋር ግንኙነት አላችሁ" የህወሀት አዲሱ ፍረጃ?!? (የዋልድባ አባቶች)

ከግዮን መጽሄት ጋር ቆይታ ያደረጉ የዋልድባ አባቶች

 በቅርቡ ከወህኒ የተለቀቁት የዋልድባ መነኮሳት በሕወሃትና በመነኮሳቱ መካከል ያለው ውዝግብ 40 አመታትን ያስቆጠረ መሆኑን ይፋ አደረጉ። ሕወሃት ጫካ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ በገዳሙ ሰላዮቹን ማሰማራቱን ይናገራሉ። መነኮሳቱ አባ ገብረኢየሱስና አባ ገብረስላሴ በገዳሙ መጸለይ ወንጀል ሆኖ በመከላከያ ሰራዊቱ መደብደባቸውን ተናግረዋል። ከታሰርን በኋላም ራሳችንን እስክንስት ተደብድበናል ያሉት የዋልድባ መነኮሳት በድብደባው ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት አላችሁ ተብለናል ብለዋል። በቅርቡ ከወህኒ የወጡት ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት ሀገር ቤት ከሚታተመው ጊዮን መጽሔት ጋር ባደረጉት በዚህ ቃለ ምልልስ በገዳሙ ውስጥ የሕወሃት ሰላዮች በመነኮሳቱ ስም እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል። የዋልድባን ገዳምን ለማረስ በ2004 እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት መነኮሳቱ ይህንን መቃወማቸውን አስታውሰዋል። ይህንን ተቃውሞ ያስተባብራሉ የተባሉ መነኮሳትን በመጠቆም የሚያሳስሩትና የሚያሳድዱት አባ ገብረሕይወት መስፍንና አባ ሰላማ የተባሉ የሕወሃት ሰላዮች ነበሩ ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። እነዚህ ግለሰቦች ሌላው ቀርቶ መነኮሳቱ ተሰባስበው ጸሎት ሲያደርጉ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት መልዕክት እየላኩ  እንዳንጸልይ ያስደበድቡን ነበር ሲሉ ተናግረዋል። ሁለቱ የዋልድባ መነኮሳት  ሕወሃት ወደ ዋልድባ ገዳም ለመጀመሪያ ጊዜ ብቅ ያለው በ1972 እንደነበር ያስታወሳሉ። በወቅቱ የገዳሙን ከፊል ቦታ ለእርሻ አትክልት እንፈልገዋለን እያሉ አባቶችን እያስጨነቁ ባሉበት ሰአት በድንገተኛ የደርግ መንግስት ጥቃት የህወሃት ታጣቂዎች  ከአካባቢው ለመሸሽ መገደዳቸውንም የቀደሙ አባቶችን በመጥቀስ አስታውሰዋል። እንደገና ከ8 አመት በኋላ በ1980 ሲመለሱም ብዙዎቹ ታጋዮች በዘንዶና በነጭ እባብ በመጠቃታቸውና በከፊልም በማለቃቸው የእርሻ መሳሪያቸውን ጥለው እንደሸሹ ገልጸዋል። በሌላም አጋጣሚ በከፍተኛ የጎርፍ አደጋ መጠቃታቸውንም መነኮሳቱ አስታውሰዋል። ሕወሃት በዚህ ሁሉ በመነኮሳቱ ላይ ሲያቄም መቆየቱን ነው የተናገሩት። ገዳሙ ለሃገር የሚጸለይበት ኢትዮጵያዊነት የሚሰበክበት በመሆኑም በሕወሃት እንዳልተወደደ ገልጸዋል። በዚህ መልክ የቀጠለው አለመግባባት የዋልድባ ገዳም አካባቢን ለስኳር ፋብሪካ ግንባታ ማዋል በሚል የተጀመረው ፕሮጀክት ይበልጥ እንዳባባሰው መነኮሳቱ ገልጸዋል። በወቅቱ የመነኮሳቱ ተወካይ የሆኑት አባ ገብረኢየሱስ መንግስት ከሚፈልገው በተቃራኒ የመነኮሳቱን ፍላጎት ይዘው ጠንክረው በመቆማቸው ማሳደድ እንደተጀመረባቸው ገልጸዋል። ታህሳስ 28/2009 በ40 ያህል መሳሪያ በታጠቁ ወታደሮች ተከበው መያዛቸውን ገልጸዋል። ርህራሄ በጎደለው ሁኔታም ደበደቡን ሲሉ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል። የዋልድባ ገዳም አይነካ በማለታችን በግንቦት 7 አባልነት ተጠርጥራችኋል በሚል አሰሩን ሲሉም ገልጸዋል። ያለማቋረጥ የደበደቡን የሕወሃት ወታደሮች ናቸው።ደህንነቶች ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ታርጋ በለጠፈ መኪና ውስጥ ነበሩ። ከነሱም ውስጥ አንዱ ደህንነት ደብድቦኛል ሲሉ አባ ገብረኢየሱስ ገልጸዋል። ሁለቱም መነኮሳት በዚህ ሁኔታ ታስረው ከአመት በላይ በወህኒ ቆይተዋል። በድብደባ ብዛት ገላዬ በወቅቱ  ሸቷል፣ምልክቱ ዛሬም በገላዬ ላይ ቀርቷል ያሉት አባ ገብረኢየሱስ ከአማራ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  እና ከግንቦት 7 ጋር  ግንኙነት አላችሁ  እያሉ ያለማቋረጥ ደብድበውናል ብለዋል። እየዘለፉ፣ርቃናችንን ሀፍረተ ስጋችን እየታየም ተደብድበናል ብለዋል መነኮሳቱ። ድብደባው  ከእኛም ባሻገር እስር ቤት ውስጥ ባሉ የኦሮሞና የአማራ ልጆች ላይ ሲፈጸምም አይተናል ብለዋል። በመጨረሻም ሕወሃት አሰረን እግዚአብሔርና የኢትዮጵያ ሕዝብ አስፈታን ሲሉ ለግዮን መጽሄት ገልጸዋል።

Filed in: Amharic