አማራው “ክልሉ” በሚባለው አካባቢ አኗኗሩ ያሳቅቃል። ተዝቆ የማያልቅ የገፀ-ምድርና የከርሰ-ምድር ሀብት እያለው በአስከፊ ድህነት ይማቅቃል። ከክልሉ ውጭ ሄዶ ሠርቶ ያገኘውን ሀብትና ንብረት ተነጥቆ ይፈናቀላል። ባልኖረበትና ባልተጠቀመበት “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ” ይባላል።
አማራው እንዴት የቀድሞ ሥርዓትን ይናፍቃል? ካለፉት ሥርዓቶች የተረፈው ቢኖር ድህነት ብቻ ነው። እነ አፄ ምኒልክ ግዛት ከማስፋፋት በመለስ የተወለዱበትን ሰሜን ሸዋ አካባቢን እንኳ ዘወር ብለው አላዩትም። ባለፉት ሥርዓቶች “ተፈፀሙ” በሚባሉት በደሎች ሳቢያ “አይጥ በበላ ዳዋው ተመታ” እንዲሉ; ለአማራው የተረፈው ነገር ስዴት; እስራት; ግርፋት; እንግልትና ሞት ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሥርዓቱ የፀጥታ ኃይሎች እየታፈኑ “ማዕከላዊ” በሚባለው የማሰቃያ ቦታ የቆዩ የአማራ ተወላጆች የደረሱባቸውን ስቃዮችና አካላዊ ጉዳቶች በግልፅ ችሎት ለተሰዬሙ ዳኞች/ለፍ/ቤቶች እያመለከቱ ነው። በወንዶች ብልት ላይ ውሀ የተሞላ ላስቲክ በማንጠልጠል እንዲሮጡ መደረጉ ተሰምቷል። በዚህም ሳቢያ ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ዘርን የመተካት ፀጋ ተነጥቀዋል። ሴቶችን ልብሶቻቸውን አውልቀው ከወንዶች ፊት እርቃናቸውን እንዲቆሙ በማድረግ እንደተሳለቁባቸው ሀቁ እየመረረን ሰምተናል። በአደባባይ አይገለፁ እንጅ ሊያስቧቸው እንኳን የሚዘገንኑ ፆታዊ ጥቃቶች ተፈፅመውባቸዋል። ንፁሃን ዜጎችን እጅና እግራቸው የፊጥኝ በማሰር; ቄራ ውስጥ እርድ እንደሚፈፀምባቸው እንስሳት ጣሪያ ላይ በማንጠልጠል ሰው ሆኖ መፈጠርን የሚያስጠላ ግርፋትና ስቃይ; ጥፍር በጉጠት መንቀልን ጨምሮ ሌሎችም ዘግናኝ የጭካኔ ድርጊቶች ተፈፅመውባቸዋል።
በአማራው ላይ የተፈፀሙት ፈርጀ-ብዙ ግፍና በደሎች ሰብኣዊነትን የሚፈታተኑ ናቸው። በአማራው ላይ ስለወረደው መከራና ስቃይ መስማት ብቻ አጥንት ድረስ ዘልቆ ይሰማል። የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት በአማራው ህልውና ላይ የሰነዘረው ጥቃት; የፈጠረው ቁስልና ህመሙ ውስጣችንን ዘልቆ እንዲሰማን የግድ አማራ መሆን አያስፈልግም። በአማራው ላይ የተፈፀመውን ፈርጀ-ብዙ ግፍና በደል ለማውገዝ ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው። ይህን ሁሉ ግፍና በደል እያዬና እየሰማ ስለአማራው የማይጮህ ወገን ስለፍትህ ለመናገር አፍና የሞራል ብቃት አይኖረውም።
በተለይ ደግሞ እኛ ኢትዮጵያውያን በዘመናት ሂደት በተፈጠሩ ፈርጀ-ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች እርስ በርስ ተሳስረናል። ያለምንም ገደብ ተጋብተንና ተዋልደን በደም ተዋህደናል። ስለሆነም በአማራው ላይ የደረሰው መከራ; ስቃይና ሁለንተናዊ ችግር የሁላችንም ስቃይና ህመም መሆን አለበት። ችግሮቹን አማራው ብቻውን ሊሸከማቸውና ሊፈታቸው አይችልም; አይገባምም። ግፍና በደሎቹን ለማውገዝም ሆነ የጋራ ችግሮቻችን ለመፍታት ሁላችንም በአንድነት መቆምና በጋራ መታገል አለብን።
ዛሬ በአንዱ ብሔር/ማህበረሰብ አባላት ላይ ማንነትን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ፈርጀ-ብዙ ግፍና በደሎች ሁላችንንም ሊሰሙን; ሊያሙንና ልናወግዛቸው ይገባል። እርግጥ ነው; በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ ግፎችን በደሎች መፈፀማቸውም አይዘነጋም። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል በኦሮሞ ልጆች ላይ የተፈፀሙ ግፍና በደሎች “ኦሮሞ ሆኖ መፈጠር ወንጀል ነውን?” የሚያሰኝ ጥያቄ የሚያጭሩ ነበሩ።
በሌሎችም ላይ ብዙ ያልተነገሩ ፖለቲካዊ; ኢኮኖሚያዊ; ማህበራዊና አስተዳደራዊ በደሎች እንደተፈፀሙ/እንደሚኖሩ ይገመታል። ስለሆነም ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍትሕ; ለዜግነት እኩልነትና ነፃነት; ለፍትሐዊ የልማት ስርጭትና ተመጣጣኝ ዕድገት; በህዝብ ይሁንታና ፈቃድ ላይ ለተመሠረተ ዴሞክራሲያዊና ተጠያቂነት ላለበት አስተዳደራዊ ሥርዓት መስፈን በአንድነት ካልቆምንና በጋራ ካልታገልን ዕጣ ፈንታችን በተናጠልና በየተራ መታፈን; መታሰር; መገረፍ/መሰቃዬት; መሞት; መፈናቀልና መሰደድ; ብሮም አገር አልባ መሆን ይሆናል። አገር አለን ብንል እንኳን የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት በሆነ ብሔራዊ ቀውስ በምትታመስ አገር ልንኮራ አንችልም።
ተበታትነንና በተናጠል መቆም ራሳችንን ለአገዛዝ ሥርዓትና በየተራ ለሚፈፀሙ ፈርጀ-ብዙ ጥቃቶችና በደሎች ከማጋለጥ/ከማመቻቼት ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው የእስካሁኑ ተሞክሯችን በቂ ማረጋገጫ ነው። በዚህ አካሄዳችን ከቀጠልን ወደከፋ የእርስ በርስ ግጭት; ማባሪያ ወደሌለው ጦርነትና ብሔራዊ ቀውስ ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው። ስለሆነም ተበታትነን በተናጠል መጮህና እርስ በርስ መካሰስ ገዥዎቻችን በቀደዱልን ቦይ ወደ ጥፋት አዘቅት ከመፍሰስና የመከራ ጊዜያችንን ከማራዘም ውጭ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም። በአንድነት እንቁም???
“አንድነት ኃይል ነው”