>

ሃቁ ሲገለጥ!!! (አርአያ ተስፋ ማርያም)

አቶ አለማየሁ ዘመድኩን ከፍተኛ የህግ ባለሙያ ሲሆኑ በፍትህ ሚ/ር የፍትሐብሔር መምሪያ ሃላፊ ሆነው አገልግለዋል። ለእውነት በመቆም የተግባር ሰው መሆናቸውን አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር መስክረውላቸዋል። “የቅንጅት አመራሮች ንብረታቸው እንዲወረስ ክስ እንዲመሰረት አድርግ” ተብለው በበረከት ስሞኦን ሲታዘዙ ‘አሻፈረኝ’ በማለት የተቃወሙና ትእዛዝ ባለመፈፀማቸው እስር የተደገሰላቸው ናቸው። ..አቶ ታምራት ላይኔ ከቀናት በፊት ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ላይ “አለጥፋቴ ነው 12 አመት የታሰርኩት” ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁት አቶ አለማየሁ  ሃቁን አጋልጠዋል።
አቶ ታምራት በቃለምልልሱ ጣልቃ ያነሱት ሌላ ጉዳይ ነበር። አቶ መለስ ቢሮ ዘንድ ሄደው ይቅርታ እንዳደረጉለት፣ ቂም እንዳልያዙ..መናገራቸውን ገልፀዋል። መረጃው በዚህ ግድግዳ ነው የሰፈረው። በተዘዋዋሪ መልስ መስጠታቸው ይመስላል። ታምራት ከመለስ ጋር መገናኘታቸውን ማመናቸው ጥሩ ቢሆንም ነገር ግን የተነጋገሩትንና ከነስፍራው ሸምጥጠዋል። ከእስር እንዲፈቱ ባደረጓቸው በረከትና አዲሱ ለገሰ በኩል መለስን ማግኘት እንደሚፈልጉ ገለፁ። ቅድሜ ምሽት አዜብ መስፍን እራት አዘጋጅተው ቤተ መንግስት ግብዣ ተጠሩ። ታምራት ሲናገሩም “መለስ ቂም የለኝም! ከአገር እሄዳለሁ። ስለፓርቲው ምንም አልናገርም። በማንኛውም ፖለቲካ ውስጥ አልገባም። አንድ ነገር ብቻ እለምንሃለሁ..አላሙዲ ቂመኛ ነው። ተከታትሎ እንዳይበቀለኝ ብቻ አድርግልኝ” ሲሉ ነበር የተማፀኑት። ሃቁ ይህ ነው! ..

* አቶ ታምራት ላይኔ “.. አስራ ሁለት አመት ካለጥፋቴ ታስሬ” ማለቱ ውሀ የማይቋጥር ሀሳብ ነው!!

አለማየሁ ዘመድኩን
 
ሰሞኑን አቶ ታምራት ላይኔ በVoice of America የአማርኛው አገልግሎት ቀርበው ስለጠቅላይ ሚንስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ኢህአድግ ቃለ መጠይቅ ሲሰጡ እኔ ካለጥፋቴ አስራ ሁለት አመት ያሰሩኝን የኢህአድግ ባለስልጣናት ቂም አልይዝባቸውም ሲሉ አዳመጥኩ ። እርግጥ ነው ኢህአድግ ባለስልጣናቱ የህዝብ ሀብት ዘረፉ ብሎ ለማሰር እና ለመቅጣት ፍቃደኝነቱ ፣ ተነሳሽነቱ እና ከሁሉም በላይ የሞራል ብቃቱ ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን አቶ ታምራት ላይኔ ስልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ በእርግጥ የሀገር ሀብት አልዘረፉም ነበር ወይ ?
ከአስራ አምስት አመት በፊት የፍትህ ሚኒስቴር የፍትህብሄር መምሪያ ሀላፊ ሆኜ ስመደብ በፊት የመምሪያው ሀላፊዎች ከነበሩ ሰዎች የተረከብኩት ፋይል አንዱ አቶ ታምራት ላይኔ ኢትዮጵያ ቡና ገበያ ኮርፖሬሽን ከሚባል የመንግስት የልማት ድርጅት “የኢትዮጵያን እዳ ለመክፈል ” በሚል 5.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቡና በወቅቱ ጠቅላይ ሚንስቴር በነበሩት አቶ ታምራት ለይኔ ትእዛዝ ጅቡቲ “ሪድ ሲ”Red Sea ለተባለ ካምፓኒ ተሽጦ ገንዘቡ ለመንግስት ካዝና ገቢ ሳይሆን ይቀራል ። በሆላም በተደረገ ማጣራት Switzerland አገር በሚገኝ አንድ ባንክ ውስጥ 9.9 ሚሊዩን ዶላር ገንዘብ(ይህ ገንዘብ ቁጥሩ ከፍ የለው አቶ ታምራት ላይኔ ለኢትዮጵያ እዳ መክፈያ በሚል ከሼክ መሀመድ አላሙዲን 16 ሚሊዩን ዶላር ወስደው ስለነበር ነው ) በአቶ ታምራት ላይኔ ልጅ (ብሌን ጌታቸው ) ስም ተቀምጦ ይገኛል ።እኛም Duglas Hurung የተባለ ጠበቃ ቀጥረን እንከራከር ነበር ።እኔም ጠበቃውን ጄኔቭ ሄጄ አግኝቼዋለሁ።ለክርክሩ ድጋፍ የሚሆን ሰነድም ለጠበቃው እንልክለት የነበረው ከእዛው ከኢትዪፕያ ነበር ።ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ እኔ አገር ለቅቄ ውጣሁ ።
አቶ ታምራት ላይኔ ይህን ያህል ብር በልጃቸው ስም በውጭ አገር ባንክ አስቀምጠው አስራ ሁልት አመት ካለጥፋቴ ታስሬ ማለት ውሀ የሚቓጥር ሀሳብ ነው ወይ?
Filed in: Amharic