እነዚህን ማን ከሰው ይቆጥራል? እንደ አይጥ በመርዝ መፍጀት ነው እንጅ!”
የጣሊያን ንጉስ ኢማኑየል እና ቤንቶ ሞሶሎኒ

ጣሊያናዊያን በአባቶቻችን የተዋረደውን ክብራቸውን ሊያስመልሱ ኢትዮጵያዊያንም የአባቶቻቸውን ክብር ለማስጠበቅ ውጊያው የማይቀር ሆነ። የሞሶሎኒን ታንኮች በባዶ እግራቸው የሚሄዱ ነፍጠኞች ተጋፈጧቸው። አጤ ኃይለስላሴ “ድንበሬ በሰላቶ እንዳይሸራረፍ እንግሊዝ የተቻላትን ታድርግ” ሲሉ መወትወታቸውን አላቆሙም። ንጉሱ ጣሊያን በኢትዮጵያዊያን ላይ ቦምብ ለማውረድ የሚረዷትን የጦር አውሮፕላኖች ማጓጓዟን እንዲያስቆሙላቸው የዓለምን ሃያላን ተማጸኑ። ይህን ካላደረጋችሁ ታሪክ ይፈርዳል አሉ። እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እና አውሮፕላኖች የታጠቀው የፋሽስት ጦር አሮጌ መውዜር እና ምንሽር፣ጎራዴ፣ ጋሻ እና ጦር በያዙ ኢትዮጵያዊያን አሳሩን ያይ ገባ። ጣሊያን መግቢያ ቀዳደው፣መውጫ ማምለጫው ጠፋበት። ሲጨንቀው ጊዜ በኢትዮጵያዊያን ላይ የመርዝ ጋዝ አዘነበባቸው። የተከዜ ወንዝ ቀይ እስኪሆን ድረስ ኢትዮጵያዊያን ደማቸው ፈሰሰ። የባዲራችን ቀይ ቀለም ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ነጻነት ሲፈስ የኖረውን፣የፈሰሰውን እና የሚፈሰውን የኢትዮጵያዊያን ደም እና መስዋዕትነት እንደሚወክል ስንቶቻችሁ ታውቆ ይሆን? የጣሊያን ንጉስ ኢማኑየል እና ሞሶሎኒ ውስኪ እየተራጩ በኢትዮጵያዊያን ላይ ተሳለቁ። “እነዚህን ማን ከሰው ይቆጥራል? እንደ አይጥ በመርዝ መፍጀት ነው እንጅ!” እያሉ አላገጡ። ኢትዮጵያዊያን በዚህ መንገድ እየራባቸው፣እየጠማቸው ሲዋጉ በአንጻሩ ሌሎች ጥቂቶች ሆዳቸውን እየሞሉ ለሞሶሎኒ ምስል እየሰገዱ በአርበኞች እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ግራ የተጋባውን ጣሊያን መንገድ ይመሩ ነበር። እንዲህ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ባንዳ በመባል ይታወቃሉ።
“ባንዳና አህያ ሁለቱ አንድ ናቸው
ጋማና ጅራት ነው የሚለያያቸው” የተባለውም ስለዚህ ነው።
የሆነ ሆኖ የአጤ ኃይለስላሴ ንግግር እውነት ነበር። ታሪክ በቁማቸው ፍርዱን አሳያቸው። አውሮፓዊያኑ ላይ የአዶልፍ ሂትለር እሳት እዚህ ቀረ ከማይባል ግፍ ጋር ይዘንብባቸው ያዘ። ናዚ ጀርመን ከእንግሊዝ በስተቀር ድፍን አውሮፓን በምርኮ ያዘ። ያልወረራቸው ጥቂት ሃገራት አንድም በግዛታቸው ውስጥ ናዚ መተላለፊያ መንገድ እንዲያገኝ ፈቅደዋል አሊያም ለሚያደርገው ጦርነት ድጋፋቸውን ችረዋል ወይም ደግሞ “ጥይት አታዝንብብን እንጅ የፈለከውን አድርግ” ብለውት ንቆ የተዋቸው ናቸው። ናዚ ፈረንሳይን እንደ ቡሄ ቤት አፈራረሳት። ኢትዮጵያዊያን ያለማንም እገዛ በዱር በገደል እየወደቁ ፋሽስትን ማርበድበድ ቀጥለዋል። ናዚ ጀርመንም አውሮፓዊያንን ሲኦል ምን ሊመስል እንደሚችል በምድር ላይ ያሳያቸው ይዟል። በአውሮፓ የሂትለር እሳት ተባብሶ በተቀጣጠለበት ወቅት የኢትዮጵያ አርበኞች እጅግ መራራ የሕይወት ዋጋ ከፍለው ኢትዮጵያችንን ከፋሽስት መንጋጋ ነጻ አወጧት። ጣሊያን በኢትዮጵያ ምድር በድጋሚ ተሸነፈች። ኢትዮጵያን በአፍሪካ ለማንም ወራሪ ያልገበረች ብቸኛ ሃገር አደረጓት። ጣሊያን እና ጣሊያናዊያንም ሽንፈታቸውን ሊቀበሉ ግድ ሆነ። ከኢትዮጵያ በተባረረች ማግስት ከሂትለር ጋር ያበረችውን ጣሊያን ለመቅጣት የአሜሪካ ጦር የጣሊያንን ድንበር ጥሶ በቀናት ውስጥ ሮምን ተቆጣጠረ። ጣሊያን በሃገሯም ላይ ዳግም መራራ ሽንፈት ልትጎነጭ ግድ ሆነባት። ቤኔቶ ሞሶሎኒ እምጥ ይግባ ስምጥ ደብዛው ጠፋ። በመጨረሻም ተደብቆ ከኖረበት ጉድጓድ ወጥቶ በጀርመን ደህንነቶች ከለላ ሊያመልጥ ሲል በአሜሪካ ወታደሮች ድንበር ላይ ተይዞ ለጣሊያናዊያን ተላልፎ ተሰጠ። ጣሊያናዊያን ውርደት ያተረፈላቸውን ቤኔቶ ሞሶሎኒን ዘቅዝቀው ሰቀሉት። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊያን ያለማንም እገዛ የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ህልም ሲያጨነግፉ በጀርመን ፍዳቸውን ከሚያዩት አውሮፓዊያን አንዳቸውም እንኳ ያለ አሜሪካ የገንዘብ፣የስንቅ፣የሎጅስቲክ እና ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ ራሳቸውን ነጻ ማውጣት አልቻሉም ነበር። ታዲያ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የውርደት ማቅ እንዳንለብስ ላደረጉት ነፍጠኞቹ ኢትዮጵያዊያን ታላቅነት ደጋግሜ ብጽፍ ምን ይገደኛል? ማንስ ተው ይለኛል? እዚያው ጣሊያን ሃገር ሮም ውስጥ የሃገሬን ባንዲራ በኩራት እንዳነሳ እና ቀና ብየ እንድሄድ ላደረጉኝ ነፍጠኛ አያቶቼ ዘላላማዊ ክብር ይሁን እላለሁ።በቃላት ከዚህ በላይ መግለጽ ብችል ምንኛ ደስ ባለኝ ነበር። አዎ! ለጀግናዎቹ አርበኞቻችን ዘላለማዊ ክብር ይሁን!!!!!!!