>
5:13 pm - Monday April 19, 4573

አንዳርጋቸዉ ጽጌና ታምራት ላይኔ! (ስንት አየሁ በአይኔ)

ሰሞኑን ስለ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ በፌስቡክ መንደር ብዙ እየተባለ ነዉ፡፡ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን በአካልም ሆነ በሌላ መንገድ አላዉቃቸዉም፡፡ የደረሰባቸዉ ሁኔታ ግን እጅግ ያሳዝነኛል፡፡ ምስላቸዉ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ ምንትያ ልጆቹን ስመለከት በእዉነት የሚሰማኝን የሃዘን ስሜት በቃላት መግለጽ አልችልም፡፡ አቶ አንዳርጋቸዉ መያዛቸዉን ስሰማ ግንቦት ሰባት አለቀለት ነበር ያልኩት፡፡ ይለቅለት አይለቅለት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸዉ የሚያዉቁት፡፡
ለማንኛዉም አቶ አንዳርጋቸዉን አንድ ጊዜ ብቻ የያኔዉ ኢህዴን የዛሬዉ ብአዴን በጠራዉ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ እግር ጥሎኝ በርቀት የማየት ዕድል  ገጥሞኝ ነበር፡፡ ወሩ የካቲት ይሁን መጋቢት ቢምታታብኝም ዘመኑ ግን 1985 ዓ/ም ነበር፡፡ እና ስለ አንዳርጋቸዉ የሆነ ነገር በተባለ ቁጥር ትዝ የሚለኝ  በዚያ ኮንፈረንስ በአቶ ታምራት ላይኔና በእሳቸዉ መካከል ተፈጥሮ የነበረዉ ዱላ ቀረሽ  የሃሳብ ጦርነት ነዉ፡፡
ነገሩ የሆነዉ እንዲህ ነበር፡፡ የያኔዉ ኢህዴን ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የጠራዉ ጦሳ ስር በከተመችዉ ደሴ፣ ሆጤን ተንተርሶ በተገነባዉ ወሎ የባህል አምባ አዳራሽ ዉስጥ ነበር፡፡ የስብሰባ አደራሹ ከህዝብ ስራና ከኢህዴን ሰራዊት በመጡ ተሳታፊዎች ጢም ብሏል፡፡ ሁሌም ከመድረክ የማይጠፉት “ጓዶቻችንና እንዳያልፉት የለም” የሚሉት የኢህዴን መዝሙሮች ሲዘመሩ ወቅቱ በታጋይነትና በመንግስትነት መካከል የመዋለል (አዲስ ጥገኛ ገዥ መደብ በመሆንና ባለመሆን መካከል) ሁኔታ ስለነበር ለፍትህና ለእኩልነት ቅርብ የሆነዉ ታጋይ በተደበላለቀ ስሜት ዉስጥ ሆኖ ነበር የተከታተለዉ፡፡ ነገሮች በፍጥነት እየተበላሹ ስለነበር ለዚህ ለዚህስ ደርግ ባልወደቀ ይሻል ነበር በሚል ስሜት ተዉጠዉ የሚያነቡም ነበሩ፡፡
የመክፈቻዉ ዝግጅት ማታ ተጠናቆ በሚቀጥለዉ ቀን መደበኛዉ ኮንፈረንሰ ተጀመረ፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ቁመናና መልክ አንጻር እያነጻጸርን ታጥቦ ሊጠጣ የሚችል ፣ ሲናገር የሚደመጥ፣ አይኑን  ሲያርገበግብ የሚያስገርም እያልን እናሞካሻቸዉ የነበሩት የወቅቱ የኢህዴን ሊቀመንበር  አቶ ታምራት ላይ የመክፈቻ ንግግር አደረጉ፡፡ ከመክፈቻ ንግግራቸዉ ቀጥሎ ከፊት ለፊታችን በሚገኘዉ ደረጃ ወጥተዉ እሳቸዉ መሃል፣ አቶ በረከት ስምዖን በቀኝ፣ አቶ ሃይሌ ጥላሁን በግራ ተሰየሙ፡፡
ለዉይይት የተዘጋጀ ጽሁፍ የነበረ ቢሆንም የተሳታፊዉ ፍላጎት ግን ከጽሁፉ ጋር የሚሄድ አልነበረም፡፡ የፈለገ ይሁን ተብሎ ጽሁፍ በምዕራፍ በምዕራፍ እየተከፈለ በንባብ እየቀረበ የሰራዊቱን ሁኔታ በሚመለከት አቶ ሃይሌ፣ የህዝብና የአስተዳደር ስራዉን አቶ በረከት፣ በጎደለዉ አቶ አዲሱ (በተለይም የአማራዉን ክልል በተመለከተ)፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ የአዲስ አበባዉን ሁኔታ መሰረት እያደረጉ ማብራሪያ መሰጠቱን ቀጠሉ፡፡ አቶ ታምራት ላይኔ ደግሞ በንባብ የቀረበዉን መሰረት በማድረግ የየዘርፉ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ያቀረቡትን ማብራሪያ  በማካተት አጠቃላይ ድርጅቱ ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሳየት በሚያስችል መንገድ ጨምቀዉ በማቅረብ ኮንፈረንሰኛዉ ሙሉ ስእል እንዲይዝ ማድረጉን ቀጠሉ፡፡
የኮንፈረንሰኛዉ ጉጉት ጽሁፉ ላይ ያለዉ ሳይሆን በመሬት ላይ በሚታየዉ እዉነት መነጋገር ስለነበር  ግድቡን ጥሶ እንደሚፈስ ጎርፍ አይነት ሆኖ መድረኩን ይቀዉጠዉ ጀመር፡፡ አሁን ላይ እንዲህ ተባለ፡፡ እንዲያም ተነገረ፡፡ ይህም ጥያቄ ተነሳ ከማለት ህወሃት ላይ አሁን የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ተነስተዉ ዉይይት ሳይሆን ጦርነት ተካሄደ ብየ ብዘጋዉ ይቀላል፡፡
ትንሽ ጥቀስ ከታብልኩ ግን ወልቃይት፣ ራያ፣ ከኤርትራ በተባረሩ ወገኖች ላይ የተወሰዱ ግፈኛ እርምጃዎች፣ ከአማራ ክልል ዉጭ  በሚኖረዉ አማራ ላይ ይሆን የነበረዉ፣ የህወሀት ሁሉንም ነገር የመጠቅለል አባዜ፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ጠቃሚ ነገሮች እየተጫኑ ወደ ሰሜን  የሚሻገሩበት ሁኔታ፣ ጢጣ የነበሩ የኢህዴን የጦር ጉዳተኞች የሚያስታወሳቸዉ ጠፍቶ ለልመና የተዳረጉበት ሁኔታ፣ የኢህዴን  ሰራዊት በሽፍታ ምንጠራ ስም እንዳይማር በየገጠሩ የሚንከራተትበት ሁኔታ ወዘተ ወዘተ እየተነሳ ብዙ የሃሳብ ጦርነት ተካሄደ፡፡
ስብሰባዉ እንዲህ ተጋግሎ እየቀጠለ እያለ ነበር ከዚያ  በፊት የማናዉቃቸዉ ሰዉ እጃቸዉን አዉጥተዉ መናገር የጀመሩት፡፡ እኝህ ሰዉ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌ ናቸዉ፡፡ ንግግራቸዉ እጅግ የሚጥም ነበርና አፋችን ከፍተን  ሰማናቸዉ፡፡ ልጅነትና መሃይምነት ገድቦች በቅጡ ሳልረዳቸዉ ቀርቼ ካልሆነ በስተቀር የንግግራቸዉ ማዕከል የኢህዴን ከፍተኛ አመራር ማሳየት የጀመራቸዉ ከህዝብ የመራቅ ዝንባሌና ምቾት ፈላጊነት ለወለዳቸዉ ችግሮች እጅ የመስጠት ምልከቶችን መሰረት ያደረገ ነበር፡፡
የሰጡት አስተያየት አንድ ከፍተኛ አመራር የብዙሃኑን አስተያየት ደግፎ ሲናገር የመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር ቤቱ ግልብጥ ብሎ ነበር የደገፋቸዉ፡፡ ንግግራቸዉ ሃይለኛና በቀላሉ ሊታጠፍ የማይችል፣ ትኩረታቸዉም ከፍተኛዉ አመራር ላይ ያደረገ፣ አሁን በመታየት ላይ ያሉት ችግሮች በእንጭጩ ካልተቀጩ በሂደት መዘዛቸዉ ከባድ እንደሚሆን የሚያመላከት፣ ይህን የሚናገሩት እሳቸዉ የጎደለባቸዉ ነገር ስላለ እንዳልሆነ፣ በዚህ ፍጥነት ታጋዩን በዚህ ደረጃ ቅሬታ ዉስጥ የሚከት  ችግር መፈጠሩ አደገኛ መሆኑን የሚጠቁም፣ ሌላዉ ቢቀር በጦርነት አካላቸዉን አጥተዉ ሰርተዉ መብላት የማይችሉ ታጋዮች በዚህ ደረጃ ኑሯቸዉ እንዲቃወስ ተደርጎ በመታገላቸዉ መኩራት ሲገባቸዉ ጸጸት እንዲያድርባቸዉ ማድረግ እንደማይገባ የሚጠቁም፣ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች የሚያመለክቱት የአመራር ችግር መኖሩን እንደሆነ በማስመር በቤቱ ለተራመደዉ አቋም ያላቸዉን ደጋፍ ከገለጹ በሗላ ወደ አራሳቸዉ ትዝብት ተሸጋገሩ፡፡
የአባላትን ንግግር ደግፎ እንዲህ አይነት ሙህራዊ ንግግር የሚያደርግ ሰዉ ያየነዉ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለነበር የአዳራሹ ጸጥታ ፍጹም ነበር፡፡ ደሴ ሲፈጥራት ቀዝቃሳ ብትሆንም ሁሉም ሳሉን አፍኖ ይዞ ስለነበር የሚስል አልነበረም፡፡ ኮሽታ የሚባል የለም፡፡ ምን አልፋችሁ ከወዲያኛዉ ጫፍ ብረቷ መርፌ አይደለችም ከመርፌ ያነሰች ስንጥር ብትወድቅ አንኳ መስማት በሚያስችል ደረጃ ሁሉ ነገር ጸጥ ረጭ ብሎ ንግግራቸዉን ቀጥለዋል፡፡
“በከፍተኛ የድርጅቱ አመራር አካባቢ የምቾት ፈላጊነት አመለካከትና ተግባር ጎልቶ ይታያል፡፡ ህዝቡንና ታጋዩን የመራቅ ዝንባሌዎች አሉ፡፡ ዉሎአችንና ግንኙነታችን ከቱጃሮች ወደ መሆን እየሄደ ነዉ፡፡ በዚህ ፍጥነት መኪናና ቤት እያማረጡ መቀያየር የመልካም ስነ ምግባር ምልክት አይደለም፡፡ ይህን ሁሉ የምናገረዉ እኔ በግል የጎደለብኝ ጥቅም ስላለ አይደለም፡፡ ሁሉንም አይነት ጥቅማጥቅ ከፍተኛዉ አመራር በሚያገኘዉ ደረጃ ነዉ የማገኘዉ፡፡  እንዲህ የሚያናግረኝ የህዝብ ጉዳይ እንጅ የግል ጉዳይ አይደለም፡፡  በኮንፈረንሰኛዉ የቀረበዉን አስተያየት ከራሴ ትዝብት ጋር ደምሬ ስመለከት አደጋዉ ቀላል ሆኖ አይሰማኝም” ወዘተ ብለዉ ሃሳባቸዉን አጠቃለሉ፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር የአቶ ታምራት የቀይ ዳማ ፊት በበርበሬ ድልህ የታሸ መስሎ ፍም የመሰለዉ፡፡ አይናቸዉም ደም መስሎ በፍጥነት ይርገበገብ ጀመረ፡፡ አቶ ታምራት ከአቶ አንዳርጋቸዉ ጸጌ ንግግር ሃረጎችን በመምዘዝ ንግግራቸዉ ቀጠሉ፡፡ ”አንዳርጋቸዉ አንደተናገረዉ እኔ ታምራት ላይኔ ለህዝብ ያለኝን ወገንተኝነት የማሳየዉ ቡትቶ የለበሰ ህዝብ ጋር በመዋል አይደለም፡፡ በየስርቻዉ በመዞር በደሳሳ ጎጆ የሚኖሩ የኔ ቢጤዎችን በመጎብኘት ሊሆን አይችልም፡፡ በርበሬ ተራ ወርጄ ከእነሱ ጋር ጊዜየን በማሳለፍ  ለህዝብ መቆሜን ማሳየት አልችልም፡፡ ከተራዉ ዜጋ ጋር ቡና በመጠጣት ህዝበኝነትን አትርፍ ይሆናል እንጅ ህዝብን መጥቅም አልችልም፡፡ የሚበላዉና የሚለብሰዉ ያጣን ህዝብ አይቼ ከንፈሬን በመምጠጥ የህዝብ ወገንተኝነት አይገለጽም ፡፡ ህዝባዊነትና ለህዝብ ያለ ተቆርቋሪነት ከዚህ አይነት ተራ ህዝበኛ ግንኙነት ርቆ የሄደ ነዉ፡፡ እኔ ታምራት ለህዝብ መቆሜን የማረጋግጠዉ ለህዝብ የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን፣ ህጎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ነዉ፡፡ ተግባራዊ እንዲሆኑም ቀጣይ የሆነ አመራር በመስጠት ብቻ ነዉ” ብለዉ ብዙ ተናገሩ፡፡
ንግግራቸዉ በሙሉ በሃይለኛ ስሜት የተሞላ መሆኑ ከንግግራቸው ፍጥነት፣ ከድምጻቸዉ ሞገድ፣ ከፊታቸዉ ቅላት፣ ከአይናቸዉ በፍጥነት መርገብገብ፣ ከሰዉነታቸዉ ያልተለመደ ንቅናቄ ለተሰበሳቢዉ በቀላሉ የሚገባ ነበር፡፡ በቃ ከአቶ አንዳርጋቸዉም ሆነ ከጠቅላላ ተስብሳቢዉ የቀረበዉን ቅሬታ መሰረት የሌለዉ ለመቶ አመት በዘለቀዉ የአማራዉ ገዥ መደብ ትምክህተኛ አመለካከት የተለወሰ መርዝ ነዉ በሚል እንዳለ ዉድቅ አደረጉት፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር በሁለቱም መካከል ስሜተኝነት ገንፍሎ ግጭት የሚመስል ነገር የተፈጠረዉ፡፡ አቶ አንዳርጋቸዉ በስሜት ዉስጥ ሆነዉ አሁንም ንግግራቸዉን ቀጠሉ፡፡ “እኔ የግለሰብን ስም በመጥቀስ አልተናገርኩም፡፡ የግለሰብን ሰም መጥቀስም አስፈላጊ አይደለም፡፡ የምናገረዉ ከችግራችን መዉጣት እንድንችል እንጅ በግል የጎደለብኝ ነገር ስላለ አይደለም፡፡ አሁን ካለኝ የመንግስት ስልጣን በላይም አልፈልግም፡፡ ነገሮችን የማይበት መንገድ ግን ለግሌ ባላቸዉ ፋይዳ አይደለም፡፡ በስሜት ተነድቸ የተናገርኩት አንድም ነገር የለም፡፡ ሌላዉ ይቀርና እዚህ ጢጣ ያሉ የኢህዴን የጦር ጉዳተኞች ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ ቀያሪ ልብስ የሚያቀርብላቸዉ፣ ቀለብ የሚሰፍርላቸዉ ጠፍቶ ደርግ በወደቀ ማግስት ለልመና መዳረጋቸዉን በአካል ሄዶ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የመንግስት ባለስልጣን ተልእኮ ምን እንደሆነ ያን ያህል የተራራቀ ግንዛቤ በመካከላችን የለም፡፡” ወዘተ በሚል ተናገሩ፡፡
#ልብ በሉልኝ የሁለቱም ንግግር ቃል በቃል የተወሰደ ሳይሆን ከ5ኛ ክፍል ባልዘለለ አንደበቴ የቋጠርኩት የንግግራቸዉ ይዘት ነዉ፡፡
ለማንኛዉም አሁንም አቶ ታምራት የመልስ መልስ ለመስጠት ጉሮሮአቸዉን ሲጠጠራርጉ አቶ በረክት ስምኦን በመሃል ገብተዉ በሁለቱ የተፈጠረዉን የዉጥረት ስሜት የሚያረግብ ምክር አዘል ንግግር አደረጉ፡፡ የአቶ በረከት ንግግር “አንተም ተዉ አንተም ተዉ” አይነት ቢሆንም ትንሽ ግን ወደ አንዳርጋቸዉ ያደላ ሆኖ ተሰምቶኝ ነበር፡፡ በዕረፍት ስዓትም አቶ በረከትና አቶ አንዳርጋቸዉ አይለያዩም ነበር፡፡ ያም አለ ይህ አቶ በረከት በሰጡት አስተያየት ሁኔታዎች ተረጋግተዉ ስብሰባዉ ቀጠለ፡፡ አቶ አንዳርጋቸዉ ከዚህ በሗላ ስለመናገራቸዉ ትዝ አይለኝም፡፡
እንግዲህ አቶ አዳርጋቸዉን በአካል ሳይሆን በአሻጋሪ ያየሁበት አጋጣሚ ይህን ይመስላል፡፡ በእዉነት በታጋዩ ልብ ወዲያዉ ነበር ሰርገዉ የገቡት፡፡  ምን ዋጋ አለዉ ኮንፈረንሱ ተጠናቆ ብዙ ሳይቆር “ያ ሃይለኛ ሙህር አመለጠን” ሲባል ሰማን፡፡
የደሴዉ ኮንፈረንስ በከንረንሰኛዉ ፍላጎት ሳይሆን በማዕካዊ ኮሚቴዉ ፍላጎት መሰረት ቢጠናቀቅም አቶ ታምራት 1989 ዓ/ም በስነ ምግባር ችግር ምክንያት መሆኑ ተጠቅሶ ለእስር ሲዳረጉ (በምክር ቤት ያመኑ መስለዉ ቆይተዉ ምክንያቱ ሌላ ነዉ  ቢሉም ራሳቸዉ) “ምነዉ ያኔ የአቶ አንዳርጋቸዉን ምክረ ሃሳብ ተቀብለዉ ቢሆኑ ኖሮ” ብለን የተቆጨንበት አይረሳኝም፡፡
Filed in: Amharic