>

አይ እነ ነውር ጌጡ!?! (ደረጄ ሀብተወልድ)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አሶሳ ሄደው ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሲናገሩ፣ በርካታ የአማራ ተወላጆች ከቤንሻንጉል እንዲፈናቀሉ ተደረገ።
*ስለ አንድነት በሚነገርበት ቀን  በተግባር ግን “ይህ የእናንተ ክልል ስላልሆነ ውጡ”ተባሉ።
-በኬንያ ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን በሚፈቱበት ሁኔታ ከኡሁሩ ኬንያታ መንግስት ጋር ስምምነት እንደደረሱ በተነገረበት በዛሬው ዕለት  ደግሞ በሞያሌ በርካቶች መገደላቸው እየተነገረ ነው።
*በውጭ ሀገር የታሰሩ ኢትዮጵያውያንን ሲያስፈቱ፣በእርሳቸው ሀገርና አካባቢ ሰው ይጨፈጨፋል።
ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የዛሬውን የሞያሌ ገዳዮች አውግዘዋል።ማውገዝ ብቻ ግን በቂ አይደለም። በማውገዝ  ብቻ የቆመ ግድያ የለምና።
በእርግጥ ይህን የሚያደርገው ማነው?
ህወኃቶች- አብይን አቅመ ቢስ እንደሆነ በማሳዬት ከደጋፊዎቹ ለማቆራረጥ የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች ሰውዬውን ይበልጥ በማግዘፍ ሴራቸውን ባዶ ሳያደርግባቸው የሚቀር አይመስለኝም።
ዶክተር አብይን “አንዳርጋቸውን ፍቱ” ብለን አጥብቀን ስንጠይቃቸውና በዚህም ጉዳይ ስንነቅፋቸው፣ አንዲ ታስሮ የቆዬው በእርሳቸው ውሳኔ ነው ከሚል ሳይሆን፣ ” እንደ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በማያዙበት ሥልጣን  ላይ ተቀምጠው” የወንጀለኞች ሽፋን እንዳይሆኑ ለማስጠንቀቅ እና  ደፋር ውሳኔ እንዲያሳልፉ ለመግፋት ነው።
እንጂማ  ራሳቸው ዶክተር አብይ፦
“የዋልድባ መነኮሳት የተፈቱት በእልህ አስጨራሽ የውስጥ ትግል ነው” ብለው ሲነግሩን በዚያች ሀገር የፖለቲካ እስረኞች እንዳይፈቱ እንቅፋት የሆነው ማን እንደሆነ በደንብ ገብቶናል።
ኢትዮጵያ ለዜጎቿ መታጎሪያ መሆኗ ለገዥዎቹ አላሳፍራቸው ማለቱ አልበቃ ብሏቸው በጎረቤት አገሮች እስር ቤት ተውሰው ሲያጉሩን መኖራቸውን በተዘዋዋሪ እየነገሩን መሆናቸውን የገባቸው አልመሰለኝም!
ጭራሽ አድሱ ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ሊያፍርበት የሚገባውን ጉዳይ እንደ ትልቅ ስኬት በአደባባይ የፕሮፖጋንዳ መስሪያ አድርገውት ቁጭ አሉ!
አይ እነ ነውር ጌጡ!
አሁንም እንላለን፦ በዜጎች ላይ የሚፈጸመውን ፡ግድያ በማስቆም፣ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታቱ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደፋርና ፈጣን ውሳኔ ሊያሳልፉ ይገባል!!!
Filed in: Amharic