>
5:13 pm - Wednesday April 19, 1730

  የበረሃው ዲፕሎማት (መሳይ መኮንን)

ስለአንዳርጋቸው ጽጌ መጻፍ ከባድ ነው። ስብዕናውን፡ የተጓዘባቸውን የህይወት መስመሮች፡ ከልጅነት እስከዕውቀት የወጣባቸውንና የወረደባቸውን ዳገትና ቁልቁለት በብዕር ቀለም ወረቀት ላይ ለመግለጽ ቃላት አቅም ያላቸው አይመስለኝም። እሱ ልዩ ሰው ነው። አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ የአንዳርጋቸውን የተለየ ስብዕና ለመግለጽ የተጠቀመው ሀረግ ምናልባት የቀረበ መግለጫ ሊሆን ይችላል- ”አንዳርጋቸው- የኢትዮጵያ ልዩ አፈር”
በአካል አንድ ጊዜ ነው የተገናኘነው። በመንፈስ ግን ሁሌም አብሮኝ የሚኖር ነው። ዛሬ ከጨለማው እስር ቤት ውስጥ ቢሆንም ውስጣችን የተከለው የትግልና የጽናት መንፈስ ከልባችን ጓዳ ሁሌም እንዲኖር አድርጎታል። ለእኔ አንዳርጋቸው አንድ ሰው ብቻ አይደለም። እሱ ብዙ ነው።  የትግል አጋር፡ አስተማሪ፡ መሪ፡ ሞዴል፡ የሙያ አማካሪ፡ ጸሀፊ፡ ገጣሚ፡ ዲፕሎማት… ዝርዝሩ ይቀጥላል።
ላንቺ ነው ሀገሬ የተሰኘው ዜማ መቼም ስለሀገር ፍቅር የሚንቦገቦግ ኢትዮጵያዊ ከልቡ እያነባ የሚያዜመው ነው። ይህን ዜማ ግጥሙን የጻፈው አንዳርጋቸው መሆኑን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? አንዳርጋቸው የደራሲነት ደም አለው። ለመጽሀፍ ያልበቁ ብዙ ጽሁፎች እንዳሉት አውቃለሁ። ቁጭ ካለ ይጽፋል። በረሃ ውስጥ አረፍም፡ ጋደምም ካለ ይሞነጫጭራል። ላንቺ ነው ኢትዮጵያ ‘’ብሄራዊ መዝሙር’’ የመሆን አቅም ካላቸው ግጥሞች ተረታ የምመድበው ነው። ትልቅ ስራ ነው። ጥልቅ የሀገር ፍቅር የተገለጸበት ነው። አንዳርጋቸው ስለእናት ሀገሩ እስከጥግ ያለውን ፍቅርና መንሰፍሰፍ ያሳየበት ግጥም ነው- ላንቺ ነው ኢትዮጵያ።
ስለአንዳርጋቸው ብዙ ማለት ይቻላል። ብዙም ተብሏል። ለሶስት ቀናት ለሚካሄደው የአንዳርጋቸው ይፈታ ዘመቻ የሚሆን አንድ ነገር ልጽፍ ተነሳሁ። ሰለምኑ ልጻፍ? ስለእሱ ምን የተለየ ነገር እኔ ዘንድ አለ? አንድ ቀን በተገናኘንበት አጋጣሚ ያለኝን ልጻፍ ይሆን? እሱም ቢሆን ለሌላው ከሆነው፡ የተለየ አይደለም። ነገር ግን ከተሰለፍኩበት ሙያ አንጻር ያካፈለኝ ምክሩ ነውና ልግለጸው። ለመጨረሻ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ የመጣ ጊዜ ነው። በአካል ሳገኘውም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው። የመጨረሻ እንዳልሆነ ደግሞ እርግጠኛ ነኝ። ሲናገር መቼም እንደጥዑም ዜማ ከጆሮ የሚንቆረቆር፡ አንደበቱ የሚጥም፡ ትህትናው የሚማርክ ሰው ነው። የሀሳቡ ጥልቀት፡ ያስደምማል። ከሚናገረው መሬት ጠብ የሚል ነገር የሚወጣው አይደለም። ልብ ሰርስሮ፡ አእምሮን በርብሮ ከህሊና ጓዳ የማይፋቅ ትልቅ መልዕክት ትቶ የሚያልፍ ነገር ነው ከአፉ የሚወጣው። ሲናገር ውሎ ቢያድር የማይሰለች ተአምረኛ ሰው ነው አንዳርጋቸው።
እናም እንዲህ አለኝ ‘’የእናንተ ሃላፊነት ትልቅ ነው። ሙያውን ለነጻነት መሳሪያ አድርጋችሁታል። ግን አደራ። መሬት ላይ ያለው ትግልና ፕሮፖጋንዳው እንዳይቀዳደሙ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለባችሁ። ትግሉ ከኋላ ቀርቶ ፕሮፖጋንዳው ከቀደመ አደጋው ከባድ ነው። እኛንም ልታግዙን የምትችሉት በህዝቡ ዘንድ ታማኝነታችሁን በሚገባ መሰረት ካሲያዛችሁ ነው። ፕሮፖጋንዳው ከቀደመ መታመን ይርቃችኋል። ያን ጊዜ ትግሉም ይጎዳል።’’ ይህ የአንዳርጋቸው ምክር ነው። ከጆሮዬ ላይ ድምጽ አሁን ድረስ ያቃጭላል። በሀገር ፍቅር ስሜት፡ በወኔ፡ በነጻነት ጥማት የተሰለፍንበትን ሙያ እንዳከብረው፡ እንድጠብቀው ከልቤ ያስቀመጠው ድንቅ አባባል ነው።
የሙያ አማካሪ ያልኩትም ያለምክንያት አይደለም። የሙያው ምሶሶ የሆነውን የመታመን ዋጋ የሚያውቅና የሚያከብር የምር እውነተኛ ሰው ሆኖ ያገኘሁበት ምክር ነው። በተለምዶ የምናውቀው ፖለቲከኛ ሆኖ አላገኘሁትም። ፖለቲካ ቁማር ነው፡ አስቀያሚ ጨዋታ ነው፡ ማይክ ከያዘ ውሸት ተናግሮ ስልጣን ለመያዝ የሚፍጨረጨር ነው። ይህ አንዳርጋቸው ጋር አይሰራም። ፖለቲካ እሱ ዘንድ ቁማር አይደለም። ጨዋታም አይደለም። ለአንዳርጋቸው ፖለቲካ እውነት ነው። ለህዝብ ነጻነት የሚገለገልበት መሳሪያ።
ስለ አንዳርጋቸው ያልተጻፈ የለም። እሱን በግል ከሚያውቁት አንስቶ በታላቅነቱ የተዛመዱት በሚሊየን የሚቆጠሩ የመንፈስ ልጆቹ  ስለእሱ ተናግረው አይጨርሱም። ይሀው አነገሱት። ታላቅነቱን መሰከሩ። ለጠላትም ለወዳጅም የአንዳርጋቸው ማንነት ከአጽናፍ እስከአጽናፍ ይታወቅ ዘንድ የመንፈስ ልጆቹ እንቅልፍ አጥተው እያደሩ ነው። ከዚህ በላይ ታላቅነት ከወዴት ይኖር ይሆን?
ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ወዳነሳሳኝ ጉዳይ ላምራ። የበረሃው ዲፕሎማት። 
ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ኤርትራ አቅንቼ ነበር። እውነት ለመናገር ወደ ኤርትራ እንድሄድ በግሌ ውሳኔ ላይ የደረስኩት በአንዳርጋቸው ምክንያት ነው። ከእሱ መታፈን ወዲህ ውስጤ የተፈጠረው እልህና ቁጭት በቃላት የሚገለጽ አይደለም። በአረመኔዎች እጅ ላይ ከወደቀበት ጊዜ አንስቶ ሁል ጊዜ ራሴን እጠይቃለሁ። ‘’አንዳርጋቸው ከእኛ የተለየ ለኢትዮጵያ ምኗ ስለሆነ ነው ይህን ሁሉ ዋጋ የሚከፍለው?’’ በእሱ ጫማ መግባት የሚቻል አይደለም። የእሱን ያህል ጥንካሬ መላበስ ከእንደገና መፈጠር የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። ሰው እንዴት ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለሀገሩ እንዲህ መከራውን ይበላል? ከትላንት እስከ ዛሬ ፡ ከኢህአፓ ዘመን እስከአሁን፡ እድሜውን በሙሉ ስለራሱ ሳይሆን ስለእኛ የኖረ ሰው እንዴት በእነዚህ የትውልድ ኩሶች ስቃይና መከራ ይፈጸምበታል? ለእኔ ከቁጭትም በላይ ውስጤን የሚንጠኝ ጉዳይ ነበር። በየትኛውም መለኪያ ከእግሩ በታች በሆኑ ሰዎች እጅ ላይ መውደቁ ያንገበግባል። ከአጥንት ድረስ በሚዘልቅ የቁጭት ስሜት ያማል።
እናም ቢያንስ የሄደበትን ያህል ርቀት መሄድ ባልችልም የተኛበትን አፈር ለማየት ውሳኔ ላይ ደርሼ ነው ወደ ኤርትራ ያቀናሁት። ኤርትራ የአቶ አንዳርጋቸው ሁለተኛ ቤቱ ናት። ከአስመራ አውሮፕላን ማረፊያ አንስቶ በመንገድ ላይ ስንጓዝ መንገድ ላይ የማየው ሁሉ የእሱ ዱካ የረገጠው እየመሰለኝ በስስት ነው እራመድ የነበረው። ስለእሱ የተለየ መሆን ከማውቀው በላይ የማላውቀው ብዙ ነገር እንዳለ የተረዳሁበት ቆይታ ነው- የኤርትራው። የሚያድርበትን፡ የሚለብሰውን፡ የሚጫማውን፡ የሚበላውን የሚጠጣውን ሁሉን አየሁት። ተአምር ነው። እነዚያ የትውልድ ጥቀርሻዎች ሀገሪቱን በአጥንቷ እስክትቀር ይግጧታል፡ አንዳርጋቸው ስለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሲል ስጋውን በሚበላ ትግል ውስጥ ለመግባት ይወስናል። የሁለት ዓለም ሰዎች። ሁለቱም የኢትዮጵያ ልጆች። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር።
አንዳርጋቸው የተለየ መሆኑ ኤርትራውያንም በሚገባ ይምሰክሩለታል። አንድ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ የሚሰራ ሰው ያጫወተኝን ብቻ ላካፍላችሁ። በኤርትራ በርካታ የኢትዮጵያ የነጻነት ድርጅቶች አሉ። በብሄር ከተደራጁት አንስቶ ከ10 በላይ ነጻ አውጪዎች ኤርትራ መሽገዋል። እናም የጋራ ስብሰባ ሲኖራቸው መሪዎቻቸው ከበረሃ መጥተው አስመራ ይገናኛሉ። ታዲያ ሁሉም የድርጅት መሪዎች የሚንቀሳቀሱበት መኪና አላቸው። ሹፌር አላቸው። ስብሰባ ሲመጡ በሹፌራቸው ታጀበው ነው። አንዳርጋቸው ግን አንዲት ሳይክል አለችው። ከአስመራ መኖሪያ ቦታው የስብሰባ አዳራሽ ሲመጣ በዚያች ሳይክል የአስመራን ዳገትና ቁልቁለት ወጥቶና ወርዶ ነው። በላብ ተነክሮ እያለከለከ ከስብሰባው እንደሚገባ ነው ኤርትራዊው ያጫወተኝ። ሳይክሏን አይቻታለሁ። ከሚያድርበት ክፍል ተንጠልጥላ ባየኋት ጊዜ አይኖቼ እምባ አረገዙ። የእግሩን አሻራ ከሳይክሉ መርገጫ ላይ ያየሁት መሰለኝ።
ወደ በረሃ አመራን። ከአስመራ ተነስቶ በስተደቡብ ከረን፡ ሰነዓፌን አልፎ ከታጋዮቹ መንደር እስኪደረስ ያለው በረሃ አይጣል ነው። ጸሀይ ያለ የሌለ ጉልበቷን የጨረሰችበት ቦታ ይመስላል። ፊት ያከስላል። የተረገመ ምድር፡ እግዜር ሲፈጥረው በኩርኩም የደቆሰው አከባቢ ነው። ሰው እንዴት በዚህ በረሃ አይደለም ለመኖር ሊያልፍበት ይመጣል? አይ አንዳርጋቸው?! ያንተ ነገር በምን ቃል ተነግሮ ይበቃ ይሆን? ወደ አንዳርጋቸው መኖሪያ አመራን። ስድስት ልጆችን ይዞ ትግሉን ወደጀመረበት ጭው ያለ በረሀ። የማየው ሁሉ የአንዳርጋቸው እጅ የነካው እየመሰለኝ እሳሳለሁ። ቀና ስል ከሰማይ ላይ የአንዳርጋቸው ምስል የማይ እየመሰለኝ ድንግጥ እላለሁ። ከርቀት ጉብ ያለ ነገር ላይ ተቀምጦ የማየውም ይመስለኛል። የአንዳርጋቸው ልጆች ስለአዳርጋቸው እየዘመሩ ተቀበሉን። የማየው ነገር የበረሀውን ጉዳት አስረሳኝ። የአንዳርጋቸው ልጆች ቲሸርቱን አድርገው በፍጹም የጽናት ስሜት ሳገኛቸው ሰውዬው ይበልጥ ገዘፈብኝ። እንዴት ያለ ድንቅ ሰው ነው ባካችሁ?!
በረሃው ስለአንዳርጋቸው ድካም ይመሰክራል። ጥሻው የአንዳርጋቸውን ጽናት ይናገራል። ያቺን የሚተኛባትን ሰሌን አየኋት። ጠረኑ እንዳለ ነው። የጀግና ጠረን። ልብ ያሸፍታል። የመጀመሪያ የቆረቆራትን የትግል ሰፈር በሚገባ ጎበኘኋት። አፈር ቁጥቋጦው ድንጋይ ጠጠሩ ስለአንዳርጋቸው የሚነግሩኝ እየመሰለኝ አዳምጣቸኋለሁ። ምሽት ላይ ፍየል ታርዶ ክሽን ያለ ጥብስ ተመገብን። የአንዳርጋቸው ልጆች የሰሩት ጥብስ ጣት ያስቆረጥማል። ሙያም ያስተማረን እሱ ነው። ሰው እንዳይመስልህ? እንደኛው አፈር ላይ ተንከባሎ፡ እንደኛው ሰርቶ ለፍቶ የሚኖር ሰው ነው። እንጨት ፈልጦ እሳት አንድዶ፡ ሽሮ ሰርቶ የሚያበላን፡በረሃውን ያስረሳን፡ በእውቀት ያነጸን፡ በጽናት ያቆመን፡ ታላቅ አባታችን መሪያችን ነው። የአንዳርጋቸው ልጆች ስለአንዳርጋቸው ሲናገሩ አመሹ። ልብ ይነካል። ከአእምሮዬ በላይ ሆነብኝ። እሱ ፊት መቆም ከባድ ነው። እሱ በእርግጥም ትልቅ ነው። ልዩ ነው።
ከሰማሁት አንዱን ላካፍላችሁ። አንዳርጋቸው የበረሀው ዲፕሎማት ነው። በኤርትራ በረሃ የመሸጉ የኢትዮጵያ የተለያዩ የነጻነት ቡድኖች የጎሪጥ የሚተያዩ፡ በአንድነት ለመስራት ዳገት የሆነባቸው፡ በየአጥራቸው ውስጥ ሆነው የብቻ ትግል ላይ የተጠመዱ፡ ነበሩ። የአንዳርጋቸው ኤርትራ መግባት ይህን ታሪክ እንደቀየረው ይነገራል። አንዳርጋቸው ከሁሉም ይግባባል። ከሁሉም ጋር ይሰራል። የተጣላን ያስታርቃል። የነጻነት ድርጅቶቹን ለማቀራረብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል። አንዳርጋቸው የስፖርት ውድድሮች በነጻነት ቡድኖቹ መሃል ያደርጋል። በእግር ኳስ፡ በእጅ ኳስና በሌሎች ስፖርታዊ ውድድሮች የእርስ በእርስ ጤናማ ግንኙነት እንዲኖር አድርጓል። በርቀት የሚተያዩ ቡድኖች በአንዳርጋቸው ተቀራርበዋል። የተኳረፉ ታርቀዋል።
አንዳጋቸው በአፋር ነጻ አውጪ መንደር ስሙ ትልቅ ነው። በደሚት ሰፈር የሄደ ሰው ስለአንዳርጋቸው መልካም ሰምቶ ይመልሳል። ከጋምቤላ፡ ቤንሻንጉሉ፡ ከሁሉም ዘንድ አንዳርጋቸው አንድ ነው። አስታራቂ፡ ዲፕሎማት። ድግሳቸው ላይ የክብር እንግዳ ነው። ወታደራዊ ምርቃት ሲኖር በክብር ተጥርቶ ሽልማት የሚሰጠው አንዳርጋቸው ነው። እንደመሪ በሁሉም ቦታ ስሙ ትልቅ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር የነበሩት ብ/ጄነራል ከማል ገልቹ አንድ ምሽት አስመራ ቢራ እየጠጣን ስለአንዳርጋቸው በነገሩኝ ልሰናበታችሁ።
‘’እዚህ ያሉት ሃይሎች አንድም ቀን ቁጭ ብለው አውርተው አያውቁም። እኔ እዚህ ከመጣሁ ስምንት ዓመት ሆነኝ። ለምሳሌ ከአርበኞች ግንባር መሪው ከቶ መዓዛው ጌጡ ጋር ተገናኝተን አናውቅም። ለዚህ ሁሉ ዓመታት እነሱም በዚያ እኛም በዚህ እንራመዳለን እንጂ ለሰላምታ እንኳን የሚበቃ ግንኙነት አልፈጠርንም። አንዳርጋቸው ከመጣ በኋላ ግን ከሰላምታ ባሻገር ስለጋራ ትግል ማውራት ጀመርን። አንዳርጋቸው አገናኝ ድልድይ ነበር። የእሱ በወያኔ እጅ መውደቅ የተፈጠረውን መልካም ግንኙነት እንዳያጠፋው እሰጋለሁ።’’
ይህ በኤርትራ የሁሉም መሪዎች ቃል ነው። አንዳርጋቸው የበረሃው ዲፕሎማት ነው። አንተ ሰው ድንቅ ነህ። ታላቅም ነህ። ከብረቱ ፍርግርግ ውስጥ ሆነህም ጠላትን የምታርበደብድ ጀግና ነህ። እዚያው አትቀርም። የለፋህላት፡ የገረጣህላት፡ የተንከራተትክላት ሀገርህ ላይ በነጻነት እንደምናይህ ተስፋ አለኝ።
Filed in: Amharic