>

የግፍ ብዛት  የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ እንዲታገል አደረገው፤ ...አመረርን!!! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

ዛሬ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 እሁድ ነው። ነገ ሚያዝያ 30 ነው።
ሚያዝያ 30 ቀን 1997 እሁድ ነበር፤ እናም ታላቁን ሰልፍ ከዛሬ ጀምሮ ብናስበው አይከፋም።
ሚያዝያ 30 ቀን 1997 አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የወጡት እነማን ነበሩ?
1.   መንግሥትን በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ካርድ የመለወጥ ተስፋ !!!
2.   ለውጥን በደስታ የመቀበል ድፍረት !!
3.   የነፃነት ስሜት !!!
4.   የሀገራዊ አንድነት ስሜት !!!
ከሚያዝያ 30 በፊት በነበሩት ጊዜዓት እነዚህ ድንቅ ስሜቶች በትላልቅና ትናንሽ ከተሞች እና በገጠርመንደሮች ታይተው ነበር። ሚያዝያ 30 ቀን 1997 ተጠቃለው አገራዊ ሆነው በመምጣት አዲስ አበባን አጥለቀለቋት !!!
ግንቦት 8 ቀን 1997 መለስ ዜናዊ በእነዚህ ስሜቶች ላይ ጥላቻ፤ ግድያ፣ ውሸት፣ እስራት፣ ስደት፣ ድብደባ፣ ዘረፋ አዘመተባቸው ።  የግፍ ብዛት  የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ እንዲታገል አደረገው፤ ….    አመረርን !!!
ከሚያዝያ 30 እና ተከትለውት ከመጡ ኩነቶች የምንማራቸው ቁም ነገሮች ምንድናቸው?
1.   የግፍ ብዛት ምሬት እንደሚፈጥር፣ እና
2.   በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የሚደረጉ ትግሎች ተቀናጅተው አገራዊ ቅርጽ ይዘው መምጣት እንዳለባቸው።

ለኔ ኢሕአዴግ የወደቀው የዛን ዕለት ነው!

ፍቃዱ ዘ ሀይሉ
ልክ የዛሬ 11 ዓመት፣ እሁድ ቀን፣ ይሄኔ አዲስ አበባ በሽርጉድ ተንጣለች። ከሰፈሬ ልጆች አንዱ በጠዋት መጥቶ “እንሂድ” አለኝ። “ለ7:00 ሰዐቱ አሁን?” አልኩት። ጥሎኝ ሄደ። አንዲት ጓደኛዬ ያገባችው እንደትላንት ነው። (ቅዳሜ‘ለት) የሠርጉን የኪራይ ዕቃ ስንመልስ የሙሽሪት ወንድሟ “በእናትህ በፍቄ ነገ አትሂድ” አለኝ። “ለምን?” አልኩት። ለኔ አስቦ ነበር። ረብሻ ይነሳል ብሎ ፈርቶ። “ከተነሳ ረብሻው ይብላኝ” ብዬ ሄድኩ። ሰዉ ሰልፍ የወጣም አይመስል። ንግሥ እንጂ! የሠላማዊነት መጨረሻ የዛን ዕለት ታየ! ‘ደግሞ ይታይ ይሆን?’ እላለሁ።
የሚያዝያ 30/1997ቱን ሰልፍ አይተው ያስመለሳቸው፣ ራሳቸውን የሳቱ ባለሥልጣናት እንዳሉ ሰምቻለሁ። የዛን ቀን እኔ አምስት ሰዐት ነው ከሰፈሬ የወጣሁት። ሰልፉ ሰፈሬ መጥቶ ነው የተቀላቀለኝ። ሰልፉ የተጠራው መስቀል አደባባይ ቢሆንም ሰልፈኞች ግን መንገዱን ሁሉ ግድቡ እንደሞላበት ጎርፍ አጥለቅልቀውት ስለነበር፥ ሰዎች ሰልፉን የሚቀላቀሉት (ወይም ሰልፉ የሚቀላቀላቸው) እዚያው ሰፈራቸው ነበር።
ለኔ ኢሕአዴግ የወደቀው የዛን ዕለት ነው!
ኢሕአዴግ ከዚያ በኋላ ሕዝቡን ጠላ። ተቃዋሚውም ሕዝቡን ከዳው። ኢትዮጵያም የዛሬዋን ሆነች።
ተስፋ!
ቁጭት!
Filed in: Amharic