>

ዕንባሽን ፈራሁት!? (በ ዲያቆን መኩሪያ ጉግሳ)

ዕንባሽን ፈራሁት ማማዬ መልሽው
በኢትዮጵያ አምላክ ባክሽ አታፍሽው
አበባዬ ስሚኝ አንዴ ልለምንሽ
ይሄን የፈላ ዕንባ ዋጥ አርጊው ስወድሽ
አምልጦ ካይኖችሽ መሬት ዱብ ካለ
ወየው ለግፈኛው ወየው ለበደለ
የአይኖችሽን ዕንባ እንጃ ውስጤ ፈራ
እሳት መስሎ ታየኝ የሰዶም ገሞራ
ገና ዳር ላይ ቆሜ ወላፈኑ ፈጀኝ
የብልጣሶር እቶን ባቢሎን መሰለኝ
ማማዬ ብሶትሽ አጥንቴን አመመኝ
ይሄን የዕንባ ጩኸት ልጄ ባክሽ ተይው
በቃ ሳታለቅሺ ዝም ብለሽ ለምኚው
እና ምን ይደረግ ከእውነት ተወለድሽ
ሀሰት ከሚጠላ ሀቀኛ ተፈጠርሽ
ለነገ ሀገርሽ ሲል እርሱም ተሰቃየ አንቺም ዋጋ ከፈልሽ …
አውቃለው አንቆሻል ማማ እረዳሻለሁ
ልብሽ መሰበሯን ልክ ነው አምናለሁ
ቢሆንም ቢሆንም ባክሽ አታልቅሺ ዕንባሽን ፈራለሁ
እናንት የቀን ጀግኖች በቅን ፍረዱልኝ
ይሄን ያልወደቀ ዕንባ መልሱልኝ
የእናንተን እንቡጦች ልደት ስታከብሩ
በደስታ ሲዘሉ ሻማ ስታበሩ
ደሞ እንዳይጠርጋቸው የዕንባ ክምሩ
ለራሳችሁ ነገ ዛሬ ማማን ማሩ
አይደለም አንድ ኬክ አስር ኬክ ቁረሱ
በውስኪ ተራጩ በጮማ ደግሱ
ግን ልማጸናችሁ የዚችንም ጨቅላ ዕንባዋን መልሱ …
በዕንባ ቀለብ ሀገር የማያለቅስ የለም
ኢትዮጵያ ምድር ላይ ይሄ ብርቅ አይደለም
ባለፉት ዓመታት ስንት ስቃይ ቆጥረናል
እናት ደም ስታለቅስ የዐይን ምስክር ነን አብረን አንብተናል
ብቻ ግን እኔንጃ ያንቺን ዕንባ ሳየው ከሁሉም ያስፈራል
ግን ኮ’ ማማዬ አባትሽ ጨካኝ ነው
ካንቺ በላይ ሀገር እንዴት ነው እሚወደው?
ሲያከር ነው እንጂ …
ስልጣን ተገን አርጎ ሀገር ቢበዘብዝ ጥፋቱ ምንድን ነው?
ይሄ ርካሽ ጥበብ ለአንድዬ ላባትሽ እንዴት ተሰወረው?
ጓደኞቹ ዛሬ ዶላር ላይ ተኝተው ብውስኪ ሲዋኙ
ስልጣኑን ወርውሮ ለሀገሩ ክብር ጨከነ መናኙ
ማንንም ላይሰማ ለእውነት ባዘነ
ከሀገር በላይ ላያይ አይኖቹን ከደነ …
ግን ምን ዋጋ አለው …. 
ያንቺ አይን ደሞ በዕንባ ተገለጠ
እንኳን አባትሽን እኛን በጠበጠ …
ልማጸንሽ ማማ እንባሽን መልሽው
በኢትዮጵያ አምላክ ባክሽ አታፍሽው
የአይኖችሽን እንባ እንጃ ውስጤ ፈራ
 እሳት መስሎ ታየኝ የሰዶም ገሞራ …
               በቃ ማማዬ … !!
Filed in: Amharic