>
5:21 pm - Saturday July 20, 9907

የመድረኳ ልእልት እቴጌ አለም ጸሀይ ወዳጆ!!! (አለባቸው ደሳለኝ አበሻ - ለንደን)

ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ተውኔት ደራሲ፣ ገጣሚ፣ መሪና የጥበብ ሥራ ተቆርቋሪ

በዛሬው ዝግጅቴ በቲያትር ትወናዋ የተመልካችን ቀልብ ያስደመመች በኢትዮጵያ የቲያትር ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ያላት :: በሴት ተዋናይ ዘርፍ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ስለደረሰችው የንጋት ጀንበር ፣ በአፃፃፍ ክህሎቷ ጥልቀትና ምጥቀት በነፃነት ሐሳቧን የገለፀች :: የእድሜዎቿን እኩሌታ የተለያዩ ቲያትሮችን በመጫዎት በመድረክ ላይ ተወርዋሪ ኮኮብ ሆና በትወና ያሳለፈች :: በዚህም ብቃቷ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣች :: የሀገራችን ታዋቂ ደራሲያኖች ያቀረቧቸውን ድርሰቶች የያዙትን ጠንካራ ባህሪያት ሐሳብ የመፍቻ ቁልፍ ሆና ከነ ውበታቸው ከነለዛቸው በአላት የትወና ብቃት የተጫወተች ፣ ያዘጋጀች ::
በሞያ አጋርቿና በአድናቂዎቿ ” የመድረኳ ልዕልት ” እቴጌ የሚለውን የክብር ስም የተሸለመች ::በርካታ ግጥሞችን በመፃህፍ በካሴት በሬድዮ ያቀረበች ስለመድረኳ” እቴጌ” ተዋናይ ፣ አዘጋጅ ደራሲ የአለም ፀሐይ ወዳጆን የህይወት ጉዞ አጫውታችሁ አለሁ ::
ፊታውራሪ ሀብተ ጉዎርጊስ ት/ ቤት ገና የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሁና የኪነጥበብ የሞያ እሳት በውስጧ ተቀጣጥሎ በተዛዎረችበት መዳህኒ አለም ት/ቤት ጌዜ ሳታባክን የትምህርት ቤቱ የቲያትር አዳራሽ ተቆጣጠረችው :: የ12 ኛ ክፍል  ትምህርቷን እንዳጠናቀቀች በብሄራዊ ቲያትር ቤት የሚሰጠውን የሁለት ዓመት የትወና ኮርስ ካጠናቀቀች በዃላ ያለምንም ተፎካካሪ አገሯን ለቃ እስከወጣችበት ግዜ ድረስ በኢትዮጵያ ቲያትትር ታሪክ ውስጥ የተለየ  ቦታ የነበራት የመድረክ ንግስት ነበረች:: በወቅቱ የነበሩ አድናቂዎቿ እንደነገረኝ ከሆነ ” አለም ፅሐይ ወዳጆ የምትደነቀው በትወና ስራዋ ብቻ ሳይሆን  የሚፍለቀለቀው የተፈጥሮ ውበቷ ጋር ተደምሮ በሰው ላይ  የሚጭረው የስሜት አድናቆት እንዲህ ነው ብሎ መግለፅ ያስቸግር ነበር ይላሉ  ::  ትኩር ብለህ አይተህ አይንህን ማዘዝ ያቅተሀል :: ውበቷ የፈነዱ ደማቅና ደስ የሚሉ አበባዎችን የምታይ ነው እሚመስልህ ::በዚህ ላይ ሁልግዜ ፍፁም እርጋታ የሚታይባት እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለፅ የማይቻል ግርማ ሞገስ የተላበሰች :: መድረክ ላይ ስትተውን ደግሞ እንደ እንዝርት ስትሽከረከረር  ተመልካቹ አብሯት የሚተውን ይመስል ነበር :: እኔ በእድሜዬ ያዬሁት ለድምፃዊ ሲጨበጨብ እንጅ ለተዋና ሰው ከተቀመጠበት ተነስቷ ሲያጨበጭብ ገጥሞኝ አላውቅም ያሉኝ የአክባሪ ወዳጄ ሐሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ ታሪክ ፅሀፊም በአንድ ወቅት በሐገር ፍቅር ቲያትር ቤት የቪነሱ ነጋዴ ስትጫዎት ከመጠን በላይ በመደነቅ ቆመው ካጨበጨቡት ውስጥ አንዱ ነኝ ::
አለም ፀሐይ እራሷ እንደምትለው እራስህን ብቁ አርገህ የተሰጠህን ባህሪ ለመተወን የምትችለው መልካም ጤንነት ካለህ ብቻ ነው:: ምክኒያቱን ስታብራራው በጣም ትንሽ መስሎ የሚታየን ውስጣዊ ስሜታችን ጥልቅና የሰፋ ክልል በመሆኑ ተግባርህንና ስሜትህን ይቆጣጠራል :: ይህ አዕምሯዊና መንፈሳዊ አላማ የአስተሳሰብ ስርአት እንዳለው ሁሉ የትወና አጨዋወት ቴክኒክ የመጨረሻ ችሎታህ ጋር የምትወክለው ባህሪ መመጣጠኑን ማረጋገጥ ስትችል ነው ብቃትህ የሚለካው  ትላለች :: እንደኔ አስተያየት ከሆነ
ለአለም ፀሐይ. ወዳጆ ለትወና ብቃት ተመልካቹ የተለየ ቦታ የሰጣት እራሷን ሰብሰብ አድርጋ ስለሞያዋ ስለዝንባሌ አዕምሮዋን በማሳደግ የሞያን ብቃት ” ድል” እንዴት አድርጎ መለማመድ እንደሚቻል ቀንድማ የተገነዘበች በመሆኗ ፣ ሁሉንም የሐገሯን ሕዝብ ታሪክ ጠንቅቃ በማወቋ ፣ አንዱ ምክኒያት ይመስለኛል ::
በሌ በኩል የማህበራዊ ተቆርቋሪነትን ኃላፊነት መቀበል መቻሏ በራስ ክብር በራስ መተማመን እንደዋና መታወቂያዋ አድርጋ በመውሰዷ ::
ነው ::
ምናልባት በአንዳንድ ሰዎች ግንዛቤ  ከውስጤ ፈንቅሎ  የሚወጣውን እውነተኞ ስሜቴን በመግለፄ ከሚገባት በላይ ያደነኳት ሊመስል ይችላል  ::
ማድነቅ የሚባለው አባባል ቃል በቃል ሲተረጎም የአንድ ነገር ዋጋ ወይንም ክብር ማወቅ ማለት ነው ::
እንደ አለም ፀሐይ ወዳጆን የመሳሰሉትን ሰዎች ደግሞ ከህይወት የሚፈልጉትን ሁሉ የሚጋኙ ስለሆነ በሁሉም ቦታ ማለትም በስራ በቤት ፣ በመንገዳቸውና ፣ ከህብረተሰቡ ጋር አንድ ላይ ተሰባስበው ሰንደቅ መስለው  ይታያሉ  ::  እንደዚህ የመሰሉ ቁርጠኛ ሰዎች ደግሞ ራሳቸውን ወገናቸውን የሚጠቅሙ ስራዎች ለመስራት የሚያሳዬት ቁርጠኝነት መገመት አስቸጋሪ አይሆንም
ደራሲ ክፍሌ አቦቼር አለም ፀሀይ ወዳጆን እንዲህ ይገልፃታል ::
   “ዓለም ፀሐይን ለመግለጽ ከምትጽፈው ወይም ከምትናገረው በላይ ትርቅብሃለች ::
  እኔና ዓለም እንደ አለቃ ኪዳነ ወልድ የ”አብዮት” አተረጏጎም በ”ድሃ-ረብሻ” ውስጥ ሳይሆን :ለመልካም ህይወት ምኞትና  ጉጉት በተደረገው የህዝብ ዓመጽ ማዕበል መባቻ ላይ ነው የተገናኘነው ::
   ፍፃሜው ባያምርም ከጅምሩም ሆነ እስከ ዕድለ ቢሱ መቋጫ ድረስ የወገንን ህልም (የእኛም ተካቶ) ለማሳካት እንደ ዜግነት በጋራ እንደየ ግል ተሰጧችን የየግል ጥረታችንን የ”እኛ” ባልናት የዕትብት አፈራችን መስክ ላይ ቆመን የልቦናችንን ሃሣብ : ዕምነትና እውነት ለወገናችን አጋርተናል ::
     ዓለም ከእዚህ የዘመን ዘበዝ የተመዘዘች : በዚህ የዕሳት ወላፈን የተፈተገች : ነጥራና ተፈልቅቃ የወጣች የኪነ-ጥበብ “ፈርጥ” ነች ::
     እሷ በፈለገቺው ብቻ ሳይሆን : አንተ በፈለከው ቦታ ብታኖራት : ከተመኘኸው ወይም ከጠበከው በላይ ሁና የምትገኝ ብርቱና ብቁ የኪነ-ጥበብ ሰው ነች ::
    ደራሲ ናት :: የሰላና የተባ ብዕር አላት :: ጽሑፎቿ ከጥልቅ ሃሣብ ክምችታቸው ባሻገር : በ”ወዛ-ወግ”
የታጨቁ ናቸው :: ትጽፋለች : ታዘጋጃለች :ትተውናለች :: በጥቅሉ በኪነ-ጥበብ ዙርያ “ሁሉን-ነች” ከማለት ይልቅ ራሷ “ጥበብ ነች” ቢባል ይመጣጠናሉ ::
    ጥቂት ሰዎች ለተለየ ጥቂት ነገር ይወለዳሉ :: ዓለም ከእነዚህ አንዷ ነች :: “መሆን አለብኝ” ብላ ካሰበቺው በላይ “ሁኚ” ተብላ የተወለደች ነች ::
   ጥረቷና ለሙያው ያላት ፍቅር ደግሞ የተለየ ቦታ ላይ ያስቀምጣታል :: ለዚህም ነው በዕለት ሳይሆን በሰዓት ተለክቶ የተሰጠ የስደት ህይወት ኑሮ ሳይበግራት ባዕዱን ሀገር በ”ሀገራዊ ጥበብ ቃና” የረታቺው !!
የመድረኳ ልዕልት እቴጌ ስለተሰኜችው አንጋፋ ተዋናይ ስለ አለም ፀሐይ ወዳጆ የህይወት ጉዞ
ተዋናይ፣ አዘጋጅ፣ ተውኔት ደራሲ፣ ገጣሚ፣ መሪና የጥበብ ሥራ ተቆርቋሪ
ብትወና የጥበብ ሙያ የሰለጠነች፣ ገና ከመመሪቋ በፊት ጀምሮ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትርን ያገለገለች፣ ከተመረቀችም በኋላ ዋናዎቹን ሚና የተጫዎች ።  በባህል ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የጥበብ ባላሙያዎች ምክር ቤት መሪ ተዋናይ ተብላ ተሰይማ የበረች ናት ::
ዓለምጸሐይ ወዳጆ የሙያ ሥልጠና በጀርመን፣ በሶብየት ሕብረት፣ በቡልጋሪያ፣ በችኮስሎቫኪያና እንዲሁም በሌሎች አገሮች ቀስማለች።
ዓለም የአንጋፋ መሪ ተዋናይነትን ስፍራ በዕውቁ ብሔራዊ ቲያትር ቤት ሙሉውን የወጣትነት እድሜዋ ገብራበታለች ። ታላላቅ በተባሉ ቲያትር ቤት  ውስጥ በተሠሩ ድራማዎች በሙሉ በመሪ ተዋናይነት ተጫውታለች።  ጥቂት በማይባሉ ሌሎች ቲያትር ቤቶች ውስጥ እየተጋበዘች በትርፍ ሰዓቷ ሠርታለች። ዛሬም ድረስ ለመቁጠር እንኳን አዳጋች የሚሆን ብዙ የዘፈን ግጥሞችን በመጻፍ ለዕውቅ ኢትዮጵያውያን  ዘፋኞች  አበርክታለች።  ዓለምጸሐይ ወዳጆ፣ በተጫወተችባቸው ገጸባሕሪያት ሁሉ፣ በሚያሰነደቅ ጥበብ በመጫውት ተግባሯ ትታወቃለች። ከብሔራዊ ትረካ ተውኔቶች ባሻገር፣ በክላሲካል ድራማዎች  ፣ ፖርሽያን በመተግበር ብየቤኑስ ነጋዴ፣ የኦፊሊያን ገጸባህርይ በመተግበር በሐምሌት፣ ጁሊየትን በመተግበር በሮሚዮና በጁሊይት፣ ስትጫወት ገጸባህሪዎቹን ሙሉ በሙሉ በግሩም ሁኔታ  እንደተካነችው :  ይነገርላታል።
ዓለምጸሐይ ወዳጆ፣ በቆዩትና በአዲሶቹም አርቲስቶች፣ እንደዕንቁ የምትታይ ናት ::   ያበረከተቻቸው ሥራዎቿ  ሁሉ እንደታሪክ ቅርስ የሚታዩና በወመዘክርም እንደ የአገር ንዋይ ተመዝግቦ ሊቀመጥላት የሚገባት ናት ::   የአርቲስቷ ሥራዎች በሠፊዊ የሚወሱላትና ልብን የሚነኩ፣ ሕዝባዊ ለውጦችን የሚያንጸባርቁ፣ ባህላዊና ዘመናዊ የሆኑ ሥራዎችን በማበርከት፣ ሁላችንንም ሰሜቱ የሚነኩ ዓለማቀፋዊ ሆኔታዎችን በማንጸባረቅ ያሳዩ ናቸው። ዐለም : የሚቆረቁራትን አርዕስቶች እያነሳች፣ ከኢትዮጵያ ባህልና ለማድ እያነጻጸረች አቅርብልናለች። በአማርኛ ቋንቋ፤ የግጥሞቿ ጣዕም፣ ብቋንቋው ለተካኑ አርኪና ሴሜትን የሚነኩ የሚያስደስቱ ታላላቅ ስራዎችን ሰርታለች ።  በግል ሰብዕናዋ ደግሞ የተለየ የሚያደርጋት ልዬ ተስጥኦ አላት ::
አለም ፀሐይ የራሷ የሆነ የህይወት መመሪ ያላት ተዋናይ ነች ::እራስን በትክክል ለማወቅ የቆዳ የቀለም የትውልድ የዘርና የሐይማኖት ልዬነቶችን አታበረታታም::  ማንም ሰው በተፈጥሮው እኩል ነው የሚል ግልፅ የሆነ የህይወት አቋም አላት :: “ሐብት”የአስተዋይነት የክብር መለኪያ አድርጋ አትመለከተም :: መንትያ የሞያ አጋሯና አብሮ አደግ ማለት ይቻላል ::  ዝነኛው ደራሲ አዘጋጅና ተዋናይ ተክሌ ደስታ አለም ፀሀይ ” ከሞያዋ በተጨማሪ በብዙ ነገሮችና በግል ህይወቷ እጅግ የምታስደንቅ ነች  ይላል :: እኔ እድሉን አግኝቼ በቅርብ አውቃታለሁ :: አለም !! አንዳንድ ሰብዕናቸውን ለትንንሽ ጥቅም የሸጡ ሞያተኞች ስታይ ትፀየፋቸዋለች ::ተክሌ  በማናቸውም የታሪክ ዘምን ብንኖርም ለአንድት ቁራሽ እንጀራ ብለን ሌላ ሰው ከመሆን ይልቅ እራስን ሆኖ ቀና ብሎ መሄድን እመርጣለሁ ትላለች :: ሌላው እጅግ የሚገርመኝ ችሎታዋ ! ብዙ ሰዎች ይህንን  አንድ ቀን አደርጋለሁ በሚለው የማይዳሰስ ተስፋ እያለሙ ይኖራሉ :: ለአለም ፀሐይ ወዳጆ እንዲህ አይነቱ ተስፋ እሷ ጋር  አይሰራም :: ለአለም እያንዳንዷ ቀን ዋጋ አላት ::  እያንዳንዷ ቀን  ለሷ የመጨረሻ ቀን ናት ማለት ይቻላል ::  ትናንት የነበረውን ሳይሆን ዛሬ ! መሆን ያለበትን የመወሰን ብቃት አላት :: አለም ” አደርገው አለሁ  “ብላ  ከተነሳች ማንም አያቆማትም :: ደግሞም ታደርገዋለች :: ይህን፣ስልህ ግን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ነው ማለት ሳይሆን ከአረም አበባን መርጣ የተፈጥሮ ውበትን ለማየት ስለምትፈልግ  ለትክክለኛ ምርጫዋ  ብዙ ዋጋ ትከፍልበታለች ::   የምትከፍለውን ዋጋ ግን እራሷን ቤተሰቦቿን ሁሉ እንደሚጎዳባት እያወቀች ክብሯንና ታሪኳን ጠብቃ የምትኖር ብርቱ ሰው ናት ” በማለት አጫውቶኛል
አለም ፀሐይ ወዳጆ የሞያ አጋሬ ብቻ ሳትሆን እህቴ ናት የሚለው ታላቁ የቲያትር ተዋናይና አዘጋጅ !  ደበበ እሸቱ  በበኩሉ ፣አለም ፀሐይ ወዳጆን እንዲህ ይገልፃታል
”  አለም የሰው ፍቅር ያላት፣ ከራስዋ አስቀድማ ለሰው የምትጨነቅ፤ ማንም፤ ሰው በመሆኑ ብቻ ከበሬታ የምትቸር ልዩ ተፈጥሮ ያላት ናት።
ዓለምን በአንድ ሙያ አለያም እንደማንኛዋም ሴት አድርጌ ለማሰብ እቸገራለሁ ምክንያቱም ዓለም ማለት የልጆች ፍቅር የጥበብ ፍቅር የሃገር ፍቅር የሰው ፍቅር የተፈጥሮ ፍቅር ያላት ብቻ ሳትሆን ለሁሉም በአዋጅና መመርያ የተሰጣት ይመስል የምትጨነቅና ጥብቅና የምትቆም በመሆንዋ ነው።
ዓለም ማንም ሲቸገርና ሲከፋ ከምታይ እራስዋን ለሰው ችግርና መከፋት ሃላፊነት ወስዳ ያን ሳታሳካ እንቅልፍ እረፍት ብሎ ነገር የማይኖራት፤ ስው ታመመ ጠያቂ አጣ ተቸገረ ከተባለ ለራስዋና ለቤተሰብ ማሰብዋን እርግፍ አርጋ ትታ ያንን ችግርና መከፋት ለማቅለል ቅድሚያ የምትሰጥ ፍጡር ናት።
በሀገረ አሜሪካ ኑሮን ማሸነፍ ምጥ በሆነበት ዓለም የጣይቱ ማእከልን ለተሰደደው ወገንዋ መገናኛ መሰባሰብያ እንዲሆን ብላ ከዜሮ ተነስታ ስትመሰርት ከራስዋ በቀር ይዘልቃል ያለ አልነበረም። ዓለም ግን የነካችው ሁሉ ፍሬው ያማረ እንደሚሆን ታውቃለችና ጠንክራ፣ ጉልበትዋን ንብረትዋን ቤተሰብዋን እሱዋነትዋን ለወጠነችው የጣይቱ ማእከል በማድረግ ማመን በሚያስቸግር መልኩ አሁን ያለበት ደረጃ መድረሱ ለኔ ከጅምሩ አንስቶ አብሪያት ስለነበርኩ የሚይስገርም ስኬት ነው። አስራ ምናምን ዓመታት ደንቃራውን እንቅፋቱን አርቲ በርቲ አሉባልታውን ሁሉ ድል አድራጊ ሆና ዘልቃለች።
ማንም ችግር የገጠመው ሰው ተቸገርኩ ሲል መፍቻ ቁልፍ ሆና የምትነሳው ዓለም፣ ችግሩን ከሰማች አንስቶ በቅድሚያ እነማን ጋ እንደምትደውል ቅደም ተከተል ስለአላት ግንባር ቀደም ሆነው የተመዘገቡት ዘንድ ስትደውል ሳትነግራቸው እነሰው አስቀድመው ከሠላምታ በፊት “እሺ ስንት ነው?” በማለት ነው ጥሪውን የሚቀበሉት እና የችግሩ ችግርነት ማቆም ይጀምራል። ዓለም ነቻ ሴትዮዋ!
ይቀጥላል
Filed in: Amharic