>
5:09 pm - Thursday March 3, 0163

የመጨረሻዉና ቁርጠኛዉ ሰዓት (ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ) 

የመጨረሻዉና ቁርጠኛዉ ሰዓት

<< ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ሆኖ ኣለመገኘት ማለት ነዉ!!!>>

ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ 
የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም. ምፅዋ ከተማ ለተከማቸዉ አብዮታዊ ሠራዊትና አመራር ክፉ ቀን ነበረች። ሻቢያ ደግሞ እንደ ልደት ቀን ይቆጥረዋል። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ግዜ ምፅዋ ከተማን የረገጠዉ በዚች ዕለት ነዉና።
ሻቢያ በ1970 ዓ.ም ከጀበሃ ተዋጊዎች ጋር በመሆን አብዛኛዉን የኤርትራ ግዛት ተቆጣጥሮ ነበር።አስመራ ፤ ባሬንቱ፤ ምፅዋና ዓዲቀይህ ከተማ የነበሩትን የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምስሶ እነዚህን ከተሞች መቆጣጠር ግን አልቻለም። በመሆኑም የሃያ ስምንት ዓመታት ምኞቱን ሻቢያ በምፅዋ እዉን ያደረገበት ቀን የካቲት 9 ቀን 1982 ናት።
ጄኔራል ተሾመ ተሰማ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጠዋቱ 1.30 ሰዓት ላይ በምፅዋ ከተማ ርዕሰ ምድርዕ በተባለ አካባቢ በከባድ መሣሪያ በፈራረሱ ቤቶች ጥግ ሆነዉ የተወስኑ የጦር መኮንኖችን እና ባለሌላ ማዕረግተኞችን ሰብስብዉ ንግግር አደረጉ ።
<<ሻቢያ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ በእጅ ቦምብና በክላሽ በአሁኑ ሰዓት የከተማ ዉስጥ ዉግያ በማድረግ ላይ ነዉ። ሻቢያ የከባድ መሣሪያ ድብደባ አቁሞ በእግረኛ ብቻ ለመዋጋት አደስ ተዋጊ ኃይሉን በመኪና እያመላለሰ ዕዳጋ ከተማ ላይ እያከማቸ ነዉ። በአዲስ ጉልበት ተዋግቶ ምፅዋን ለመያዝ ቆርጦ ስለመነሳቱ ጥርጥር የለዉም። እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቼአለሁ ። ከጥር 30 ቀን 1982 እስከ ዛሬ የካቲት 9 ቀን 1982 የሞት ሽረት ትግል አድርጌያለሁ። የሻቢያን የጥፋት ዓላማ ለመግታት ያላደረኩት ጥረት የለም። ከዚህ በኋላ ግን የራስን ህይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ጸሐፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም። ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት ምቹ ሆኖ ኣለመገኘት ማለት ነዉ።
<<በዚች የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በርና ዓለም አቀፍ ወደብ በሆነችዉ በምፅዋ ከተማና በቀይ ባህር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ሆኛለሁ ። በእዉነት እኔ ዛሬ በሞት ብሸነፍም በታሪክና በመጪዉ የኢትዮጵያ ትዉልድ ፊት አልሸነፍም ። የአፄ ቴዎድሮስን እድል በማግኘቴም በጣም እኮራለሁ። እኔ አሁን የተዝጋጀሁለት ሞት ዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወtw ይሰጠኛል። በሻቢያ እንደ ጀኔራል ጥላሁን እና ጀኔራል ዓሊ ሐጂ ተማርኬ የሻቢያን መሪዎች ዓይን ማየት ግን የሞት ሞት ነዉ።
<< አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ወድቀዉ ከመዋረድ ሞትን መርጠዉ የራሳቸዉን ህይወት መቅድላ ላይ አጠፉ። እኔ ደግሞ በተራዬ ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት የተሰጠኝን የጀነራልነት ማዕረግ ሳላስደፍር ለመንግስትና ሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሰረት አቅሜ የፈቀደዉን ያህል ተዋግቼና አዋግቼ ሻቢያን አራግፌአለሁ። እንደ ጦር መሪም እንደ ተራ ተዋጊም ሁኜ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዤ ተፋልሜአለሁ። አሁን ግን ለመጨረሻዋ መስዋዕትነት ህይወቴን ለማጥፋት የቀሩኝ ጥቂት ደቂቃዎች ናቸዉ ።
<<ጎበዝ ስሙኝ ! ይህ የአደራ መልዕክቴ ነገ ለኢትዮጵያ ህዝብ ይደርስ ይሆናል። ምናልባት አምላክ ካለ ከእናንተ አንዱ መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ያደርስ ይሆናል ። ዛሬ ሻቢያ ምፅዋን ተቆጣጠርኩ በማለት የዓለምን መገናኛ ብዙሃን እንደሚያጨናንቅ ጥርጥር የለዉም ። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ሕዝቧ ትልቅ አደጋ ነዉ። በቀይ ባህር በራችን በኩል ብዙዉን ግዜ ወረራ ፈጽመዉብን በተደጋጋሚ ያሳፈርናቸዉና ፊት ለፊት ያልቻሉን ምዕራባዊያን ሀገሮችና አረቦች ዛሬ የሻቢያን ግዚያዊ ድል ሰምተዉ ይፈነጥዛሉ። ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነዉን ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየዉን የባህር በራችንን በመዝጋት እንዲሁም ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ባህር አይደለም በማለት በምድር ተወስነን እንድንቆይ ይደረግ ይሆናል ። ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነዉ።
<< ይሁን ! ምንም ማድረግ አልችልም። ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ወጭ ሆኗል። ከሙታን ዓለም መጥቼ ማረጋገጥ ባልችልም የፈለገ ግዜ ይጠይቅ እንጂ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር አልባ ሆኖ በኢምፔርያሊስቶችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ ተሸንፎና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም ። ይህ ከሆነማ የአፄ ዮሐንስ የቀይ ባህር ተጋድሎ እና የጀግናዉ ራስ አሉላ አባነጋ አጥንት እንዲሁም የእኔን ጨምሮ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት አጥንትና ደም የኢትዮጵያን ትዉልድ ሁሉ እስከዘላለሙ ይፋረዳል። እትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቂያና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በመሆኑም ጀግናዉ ሕዝቧ ሕዝባዊ የባህር በሩ በሻቢያ ተይዞና የጠላቶቹ መፈንጫ ሆኖ አይኖርም ። የፈለገ ግዜ ይቆይ እንጂ ሻቢያ ምፅዋን እንደያዛት ለዘለዓለም አይኖርም። ጊዜዉን ጠብቆ የኢትዮጵያ ጅግና ጠላቱን ደምስሶ ምፅዋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የፀና ነዉ።>> አሉና ትንፋሽ ዋጡ። ትንሽም ፋታ ወሰዱ።
የጀነራል ተሾመ ዓይን የቆሰለ ነብር ዓይን መስሏል። ከንፈራቸዉ በዉሃ ጥም ደርቆ ቅርፊት ይዟል። ፊታቸዉ በደረቅ ላብ ዥንጉርጉር ሆኗል። በተሰበሰበዉ አባል ዉስጥ በሰፈነዉ ፀጥታና ዝምታ መሀል << እናንተ አብዮታዊ መኮንኖችና ባለሌላ ማዕለግተኞች ስሙኝ ! አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ።>> አሉ ጀነራል ተሾመ ቆጣ ብለዉ።
<< አንድ ሰዉ ቤት ሲሰራ የሚሰራዉ ቤት በርና መስኮቶች አሉት። አንድ ሰዉ ደግሞ ሞt እንበል። m ቃብሩ በርና መስኮት የለዉም ። በርና መስኮቶች የሕይወት ምልክቶች ናችዉ። በመሆኑም ያለሀገር ነፃነትና ያለባህር በር ብልጽግና ስለሌለ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህር በር ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ አይደለም። ከሻቢያ ጀርባ ሆነዉ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ አይደለም የሚሉ ሀገሮችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸዉ የኢትዮጵያ ሞት ነዉ።
<< ይህ ምሳሌ ከገባችሁ የባህር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ግለሰብ የምትለየዉ በትንሹ ነዉ። ምክንያቱም የባህር ሃብት ከማጣቷም በላይ ምርቷን ወደ ዉጪ ለመላክ የግዴታ ወደብ ስለምትከራይ ለወደብ ክፍያ የምትከፍለዉ የገንዘብ ወጪ ዜጎቿን ያደኸያል። በአኳያዉ ጠላቶቿንና ባለመደቦችን ያበለፅጋል። ይህ ዕድል ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ቀይ ባህርን የኢትዮጵያ ትዉልድ ይፋረድ። ቀይ ባህር ለእኔ ዘለዓለማዊ ቤት እንዲሆን ወስኛለሁ። ደስተኛ እና እድለኛ ጀነራል ነኝ። እኔ ብሞት ታሪኬ አይሞትም። የእኔ ታሪክ በእያንዳንዱ እትዮጵያዊ ህሊና ዉስጥ እንደሚኖር አምናለሁ። ቻዉ ! ቻዉ! >> አሉና ጀነራል ተሾመ መኮንኖቹን ከሰበሰቡበት ቦታ ተፈናጥረዉ ወደ ቀይ ባህር ጠረፍ አመሩ ። የባሕሩ ጠረፍ ከስብሰባ ቦታዉ በግምት ከስልሳ ሜትር አይበልጥም። በፍጥነት ወደዚህ ባህር ጠረፍ ገሰገሱ ። ክላሺንኮቭ ጠመንጃቸዉን አቀባበሉና አዉቶማቲክ ላይ አድርገዉ በቀኝ እጃቸዉ ጨብጠዋል።
ከምፅዋ ወደብ በስተቀኝ ከሚገኘዉ ወታደራዊ ወደብና መደብር ላይ ሲደርሱም ለቀይ ባህር ዉሃ መገደቢያ በተሰ,ራ ግንብ ጠርዝ ላይ ጀርባቸዉን ወደ ቀይ ባህር ፊታቸዉን ወደ ምፅዋ ከተማ አድርገዉ ቆሙ። ቀጥለዉም በእጃቸዉ የነበረዉን ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ወደ ቀይ በህር ወረወሩት ። ከዚያም በወገባቸዉ ታጥቀዉት የነበረዉን ኮልት ሽጉጥ አወጡና የሽጉጡን አፈሙዝ በአፋቸዉ ጎርሰዉ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጥዋቱ 2.10 ሰዓት ሲሆን ቃታዉን ሳቡት ። የሽጉጥ ተኩስ ድምፅ እንደተሰማም ወደ ጀርባቸዉ በቀይ ባህር ዉኃ ላይ ወድቀዉ ሰጠሙ። ከጭንቅላታቸዉ የሚፈስ ደም በቀይ ባህር ላይ ቀልቶ ይታይ ነበር።
ወዲያዉ ይህን የጀነራል ተሾመን ሞት በምስክርነት ቆመዉ ከአዩት መካከል ከ 150 የማያንሱ የጦር መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች በሽጉጥ ፣ በእጅ ቦንብና በክላሽ ጠመንጃ ህይወታቸዉን አጠፉ። ከእነዚህም መካከል ሻለቃ ሮሬሳ ዳዲ በእጅ ቦንብ፣ ሻምበል ሸዋንታዬ አለሙ በማካሮቭ ሽጉጥ ፣ ሻምበል አዲሱ በማካሮቭ ሽጉጥ፣ ሻምበል ባሻ አማረ ናጂ በክላሽ፣ ሻምበል ወንደወሰን በሽጉጥ፣ ፶ አለቃ ፈቃዱ ቦጋለ በክለሽ ፣ ወታደር ሸንገረፍ በክላሽ ሕይወታቸዉን ያጠፉና በስም የሚታወሱ ናቸዉ። ሎሎችም በብዛት ራሳቸዉን ገድለዋል። በአጭር ደቂቃ ዉስጥ አካባቢዉ ሬሣ በሬሣ ሆነ።
ሌሎች ደግሞ ሻቢያን ገድዬ መሞት አለበኝ እያሉ ወደ ጠላት ወረዳ በመገስገስ ገድለዉ የሞቱም ነበሩ። ወደ ጠላት እየሮጡ በእጅ ቦምብ ታንክና ተሽከርካሪዎችን እያቃጠሉ ራሳቸዉን የገደሉ በሻቢያም የተገደሉ ጥቂት አልነበሩም።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ የ3ኛ ሜካናይዝድ ምክትል አዛዥ ከጀነራል ተሾመ ፣ ከሌሎች መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረግተኞች ሞት በኋላ የተረፉትን አሰባስበዉ የሻቢያን ከበባ ሰብሮ ለመዉጣት ሞከሩ ። የ፶ አለቃ ታደስን እና ከ300 ያላነሱ አብዮታዊ ሠራዊት አባላትን በቀጥታ በመምራት ከምፅዋ ከተማ ዋናዉን የመኪና መንገድ ይዘዉ አዋጉ። ዉግያዉ ከባድ እልቂት ያስከተለ ነበር ። ሻቢያን እያባረሩ እየገደሉ ሻቢያም የአብዮታዊ ሠራዊት አባላትን እያባረረና እየገደለ የእጅ በእጅ ዉግያ ጭምር ተደረገ። የኮሎኔል በላይ ሠራዊት በዚህ መራራ ፍልሚያዉ ከምፅዋ አለም አቀፍ ወደብ በግምት ሁለት ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘዉ በረዶ ፋብሪካ ወይም ጡዋለት ወደተባለችዉ የምፅዋ ክፍለ ከተማ የ70 ደቂቃ ዉግያ በማድረግ ሻቢያን ሰብሮ በማለፍ ቀይ ባህር ሆቴል አካባቢ ደረሰ። ግማሹ ኃይልም ቀይ ባህር ሆቴልን ያዘ።
ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ የተከማቸዉ የሻቢያ ኃይል በጣም ብዙ ስለነበር የሠራዊቱ ሙከራ ተገታ። ሻቢያን ሰብሮ ወደ ዕዳጋ ከተማ ለመሻገር አልቻለም ። በዚህም ሁለተኛዉ ትራጀዲ ተከሰተ።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለብስዉ ከቀይ ባህር ሆቴል በረንዳ ላይ በአንዲት ጥልፍልፍ የቃጫ ወንበር ላይ ተቀምጠዉ አጠገባቸዉ ለነበሩት ጥቂት አባላት መልዕክት ያስተላልፋሉ። << ጀግና ቢሞት በእልፍ አእላፍ ጀግና ይተካል። የእኔ ታሪክ ለትዉልድ ይቀራል። ታሪክ ይናገር እንጂ እኔ ብዙ አልናገርም። >> የምትል መልዕክት ነች። መልዕክታቸዉን እንደጨረሱ ፊታቸዉን ወደ ምፅዋ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስትያን አዙረዉ አማተቡና የከላሽንኮቭ ጠመንጃቸዉን አፈሙዝ ጎርሰዉ ቃታዉን ሳቡት። ለጥቂት ሰኮንዶች አዉቶማቲክ የክላሽንኮቭ ድምፅ አስተጋባና ፀጥታ ሆነ።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ክላሽንኮቭ ጠመንጃቸዉን እንደያዙ ወንበሩን ተደግፈዉ ተዝለፍልፈዋል። የለበሱት የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በላያቸዉ ላይ ደምቆ ይታያል። ይህን ትዕይንት ሻቢያ ፎቶግራፍ አንስቶታል። በቪድዮ ካሜራም ቀርፆታል። የወታደራዊ ሸሚዝና ሱሪያቸዉን ኪስ ሻቢያ ሲበረብርም ከንጹህ ወረቀት በስተቀር ምንም አላገኙም። አንድ የሻቢያ ተዋጊ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ለብሰዉ የተሰዉትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላያቸዉ ገፈፈና ክብሪት ጭሮ አቃጠለዉ። የኮሎኔልን አስክሬን ከወንበር ገፍትሮ በመጣልም በደም የተጨማለቀዉን ወንበር በአንድ እጁ ወደላይ አነሳዉ። ይህ ድርጊትም ጋብ ያለዉን ተኩስ በመጠኑም ቀሰቀሰዉ። ከአንድ አቅጣጫ የተተኮሰች ጥይት ያን የሻቢያ አባል ከነወንበሩ ጣለችዉ።
እኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት አባላት እኒህን የመሰሉ አኩሪ ጀግኖች ወንድሞቻችንን ምንግዜም ቢሆን እያሰብናቸዉና አብረን የሞትንለትን ዓላማ ሳንዘነጋ ኢያስታወስን እንኖራለን። ያሁሉ መስዋዕትነት እንደ ከንቱ ተቆጥሮ ዛሬ ሁሉን ያጣን ሆነን እየኖርን ነዉ!!!
የጅግናዉ ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ቁርጠኛዉ ሰዓት
ከ ( አይ ምፅዋ , በታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ ) መፅሐፍ
ከገፅ 187 ጀምሮ
Filed in: Amharic