ይህ አስደንጋጭ ክስተት መረን የለቀቀውን የሕወሃት/ኢሕአዴግ ፋሺስታዊ መንግስት የግዛት መሰረቱን ያናጋ፣ የገዥዎችን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ፥ የስርአቱ ቁንጮዎች ሳይወዱ በግድ ፈጣን የማደናገሪያ ምላሽ ለመስጠት ተገደዱ፥ በተሃድሶ ስም የተነሳባቸውን የለውጥ ትኩሳት ለማስታገስ ብዙ ድንጋይ ፈነቀሉ።
ይህ ነበር እንግዲህ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የለውጥ ንፋስ ያመጣው፥
አንድ አጋጣሚ በመጠበቅ አንገቱን አቀርቅሮ ያደፈጠው የኦሮሞ ወጣት ቄሮ ጣና ኬኛ ኦሮሞ የኛ በሚል የአንድነት ማዕበል እየቀዘፈ ከመሃል ሸዋ እስከ ወለጋ ተጠራርቶ ጣናን ዘይሮ በውቧ ባህርዳር የአማራ ዋና ከተማ ተዝናንቶ ቁሰለኛውን ጎንደር በፍቅር እስትንፋስ ጠግኖ፥ ወጣትነት መልካም ነው ያለምንም አደራዳሪ ከአንተ በፊት እኔን ያርገኝ በሚል ቃል ዲዳን ታሪካቸውን አድሰው ተመለሱ።
የጣንን ጉብኝት ተከትሎ፥ ወጣቱ የኦሮሞ ፖለቲከኛ፥ ክልሉን ቄሮ በሚል ምትሃታዊ ስም አደራጅቶ፥ ቲም ለማን አስመርቶ፥ አብይን በቀኝ አዲሱን በእግራ አሰልፎ አቶ ለማ መገርሳ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው በሚል አማላይ ቃል ታጅቦ እንደ ሀምሌ ዝናብ ሳያጉረመርም በገዱ ግዛት በአማራ አደባባዮች ላይ ድንገት ተከሰተ። ወያኔዎች ሱሪያቸው መላላት ጀመረ፥ የአማራ እና የኦሮሞ ትብብር ሽብር ለቀቀባቸው።
በቲም ለማ መገርሳ እና በገዱ አንዳርጋቸው ቡድን መደጋገፍ የወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ቁንጮዎች ዓይናቸው ደም ለበሰ፥ ህዝብ አምርሯልና የፈየደው ነገር የለም እንጂ በሚስጥርም ሆነ በይፋም ሹም ሽር ለማድረግ ሞከሩ።
ከዚህ በፊት ሲጠሩት የያዘውን ሁሉ ይጥል የነበረው ገዱ አንዳርጋቸው ያልተገመተ ጽናት አሳየ፥ በእስራት ማስፈራሪያም ሆነ በስራ ቅያሬ ከቦታው ንቅንቅ የማይል ጀግና ወጣው፥ የሰጡትን የአምባሳደርነት ሹመት ስራየን አልጨረስኩም አልቀበልም አላቸው።
ብዙም ሳይቆይ ለግዛቷ የመበታተን፣ ለህዝቧ የመጠፋፋት አደጋ ለገጠማት አገራችን ኢትዮጵያ ይታደጋል ያሉትን የፖለቲካ ሃኪም ዶክተር አብይ አህመድን ከኋላ ሸሽገው፥ አንደበተ ርቱዕ ጀግና የሆነውን የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ለማ መገርሳን አስመርቶ፥ የአማራው ክልል አስተዳዳሪ ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለውጡን በፊታውራሪነት እየመራው መሆኑ ግልጽ ሆነ።
የሃይል ሚዛኑን ላለማስነጠቅ ወያኔ ተፍጨረጨረች ግን አልሆነም፥ ቄሮ መሃል አዲስ አበባ መግባቱን አራት ኪሎ ቤተመንግስት ወረድ ብሎ በመሌኒየም አዳራሽ በወጣቱ የኦሮሞ አቀንቃኝ ዜማ አይናቸው እስኪፈጥ ድረስ ትለቃለህ ትሰዳለህ በሚል ፉከራ ለወያኔ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፥
ቲም ለማ እና ቲም ገዱ አዲስ አበባ ተጠርተው በኢቲቪ ማብራሪያ እንዲሰጡ፥ ጥርስ የሌለው ውሻ ሆኖ ቀረ እንጂ ለማስፈራራት ተሞከረ፥ አቶ አዲሱ የኦሮምያ ሙሁራን ይዞ፥ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የአማራ ሙሁራን ጋር ተደጋግፈው የወያኔውን አፈቀላጤ አፉን አስያዙትና በሚዲያ ዙሪያ ድል ተመዘገበ፥ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በጭንቅላቱ ላብ እያጠመቀው መንዜነቱን በእልህ አስመሰከረ፥ እሰይ መክት አማራ ተባለ።
ሳይታሰብ ሊውጧቸው ነው ሲባል ለማና አብይ ከቲም ገዱ ጋር ተመሳጥረው ወያኔን ሸበለሉትና፥ ዶክተር አብይ ሹመት ነው ምርጫ ነው በሚባል የሚያሻማ ቃል ጠቅላይ ሚኒስቲር ሆኖ ቁጭ አለና ነገራት ሁሉ በወያኔ ላይ ድንገት ተገለባበጡ።
የወያኔ ጉጅሊዎች አቦይ ስብሃትና አባይ ዲቃሎቻቸውን ይዘው ከፖለቲካው ጨዋታ ውጭ ሊሆኑ ስንዝር ቀርቷቸዋል፥ በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ ባህርዳር ላይ አይተውት የማያውቁት ውርደት ገጥሟቸው ለጌታቸው አሰፋ ስሞታ ሊናገሩ ወደ አዲስ አበባ መሄዳቸው ተሰምቷል።
ከዚያ በኋላ እየተከሰተ ያለው ነገር ቅጽበታዊ ነው፥ ትግሉ በይፋ ተጀመረ፥ የጥሎ ማለፍ ጨዋታው አገር ውስጥ ገባ፥ ታዋቂ ነን የሚሉ ድርጅቶች የጫጉላ ጊዜያቸው አለፈ፥በተለይ በውጭ የሚገኙት በሆነ ባልሆነው ሰበር ዜና ማስወራት ቀረና የሚያራግበው ሰው ቀነሰ፥ እውነቱ ግን ተቃዋሚው የሚያደርገውን ትግል አቁሞ ሳይሆን አገር ውስጥ በሚደረገው ግብግብ ቀልቡ ስለ ተያዘና ስራውን ወደዛ ስላደረገ ብቻ ነው።
ታዲያ እሄን ከውስጥ የተጀመረ የለውጥ ሂደት ተከትሎ ትግል ቀዘቀዘ፥ ለውጡ ተፋዘዘ፥ የሚሉ አንዳንድ ወገኖች በምናይበት ጊዜ፥ እነዚህ ሰዎች አንድም እኛ ያላማሰልነው ወጥ አይወጥወጥ በሚል የእኔነት አባዜ ተለክፈዋል፥ ወይም የፖለቲካን ሀ. ሁ…. አልተገነዘቡም በሚል እሄን ለማለት ተገደድን።
ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው፥ ፖለቲካ ሰጥቶ የመቀበል ተክህኖ የሚጠይቅ ጨዋታ ነው፥ የፖለቲካ ጉዞ እንደ ሁኔታው የትግል ስትራቴጅ እያወጣህ የምታስኬደው ፈጣን ነገር እንጂ እንደ ኃይማኖት አንድ ቦታ ግትር ብለህ ቆመህ የምትጠብቅበት የቁልቁለት መንገድ አይደለም ይላሉ ሙያውን ያጠኑ ሰዎች።
ነገር ሳላበዛ በምሳሌ ላስረዳና ላብቃ፥
አንዳንድ ጊዜ ዲል ያለ ሰርግ ተደግሶላቸው ያገቡ ሴቶች፥ በተለያየ ምክንያት መውለድ ላይ ይዘገያሉ፥ ታዲያ በትዳር ህይወታቸው የሚናገሩት አዲስ ነገር ገና ስላላፈሩ፥ ሰዎች በተዳሩ ቁጥር ስለራሳቸው ሰርግና ምላሽ እያሰቡ፥ ሌላውም ስለ እነርሱ ሙሽርነት ብቻ እንዲያወራ ይፈልጋሉ፥ እንዲያውም የእነርሱ ስም ካልተጠራማ ሰርግ በእኛ ጊዜ ቀረ አይነት ወሬ ይዘው የአዲሶቹን ሰርገኞች ፌስታና ድግስ በማናናቅና፥ ሙሽሮችን በማሸማቀቅ ተጽዕኖ ለመፍጠር ይሞክራሉ።
ሰሞኑን በተቃዋሚው ጎራ እየተሰማ ያለው ትግሉ ቀዘቀዘ የለውጥ ሂደቱ ተፋዘዘ ማለት ከዚህ የተለየ አይደለም። በተለይም ድምጻቸው ጎልቶ ይሰማላቸው በነበሩ የውጭ ሚዲያዎችና ዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ተዘውትሮ ይነሳል።
ሲጀመር ትግል ይቁም ያለ ማንም ሰው የለም፥ በዚህም ሆነ በዚያ ያሉ ሰዎች ይቁም ቢሉም የህዝብ ጥያቄ እስካልተመለሰ ድረስ፥ የትግል ስልቱ ይቀያየራል እንጂ ጨርሶ ሊቆም አይችልም።
አሁንም ትግሉ ከዳር አገር ወደ መሃል አገር ገባ እንጂ አልቆመም፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም በላይ እየታገለ ነው።
ታላቋ ሮም በአንድ ቀን አልተገነባችም፥ የሺህ ማይል መንገድ በአንድ ይጀመራል እንደምሉት
እንዲያ በዳዴ የጀመሩት ትግል ዛሬ ላይ ደርሷል፥ የዶክተር አብይ መንግስት ፈተናውን በአሸናፊነት ይወጣል ወይስ ይወድቃል በሂደት የሚታይ ነገር ነው።
እኛ ግን ለኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እየተመኘን የአማራን ህዝብ እናደራጃለን፥ ትግላችን እንቀጥላለን።
ቲም ገዱ አንዳርጋቸው የቲም ለማን ድል በወያኔ ኢሕአዴግ ላይ እንዲደግም በማንኛውም መልኩ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረገውን የለውጥ ጉዞ እያበረታታን ለስር ነቀል ለውጥ እንታገል። ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል፥
አማራ ሆይ መክት!
ኢትዮጵያችን ለዘላለም ትኑር።