>

ፍቅርና ይቅርታ መንገድ ትውልድ ስህተቱን እሚያክምበትን በር ይከፍታል (ከነአን ፋሌቅ)

ኦቦ በቀለ ገርባን ተከትሎ የተነሳውን የሰሞኑ ዘውጌኛ ውዝግብ አይቶ ስጋት ያልገባው ያገሬ ሰው ካለ አንድም ይህን ዘመን በህልፈቱ ያመለጠ ሙታን አልያም ይሄን እብድ አለም በውልደቱ ያልተቀላቀለ ፅንስ መሆን አለበት።ያንድነታችን ፀሃይ የጠለቀች በመሰለን አስፈሪ ሰኣት ከኦሮሚያ ማህፀን የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ተስፋ እሚቀጥል ሰው ወደ አደባባዩ ወጥቶ ባየን ማግስት፣የኢትዮጵያን ስምና ባንዲራ ሽሽት ጥግ ጥጉን እሚደበቅ ሽፍታ ስናይ <የእናት ሆድ ዥንጉርጉርነት>ን እንታዘባለን።ሰውነትህ ሞቶ ሲቀበር ያገሬ እንግዳ ብሎ እግርህን ሊያጥብ የመጣን ያገርህን ሰው እንስራ በካልቾ ትነርታለህ።
ሰውየው የሄዱበትን ሃገረ አሜሪካ ቡጢና ጥይት ተቀብለው በመራር ትግል አገር ካረጉት ያለፈው ክፍለ ዘመን ሰዎች አንዱ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው።ማርቲንን አሜሪካኖቹ ከነ አብርሃም ሊንከን እና ቤንጃሚን ፍራንክሊን ጋር <ዘ ፋውንዲንግ ፋዘር> እያሉ ይጠሩታል።በቤቴ ግድግዳ ከኔልሰን ማንዴላ ጎን ተለጥፎ በማየው የነሉተር የዛኔው የተቃውሞ ሰልፍ ፊት መስመር ላይ፣ማርቲን ብዙ ግፍ ካደረሱበት ነጮች ጋር እጁን አቆላልፎ አሜሪካን በሃይል የቀየረውን የእኩልነት ትግል ሲመራ ይታያል።ቀለምን ተከትሎ ሲደርስ ለነበረው በደል መቆምና፣ሰዎች ሁሉ <ኢሪስፔክቲቭ ኦፍ ዜር ከለር> በፍትህ ለሚኖሩበት ስርኣት ምስረታ ከጎኑ ቁም እንጂ ቆዳህ ቢጫ ሆነ ግራጫ፣ዘርህ ካፍሪካ ይመዘዝ ካንታርቲካ ለዛ ዘመን ጥቁሩ ሰው ሉተር ግዱ አልነበረም።እኔን ካላመንክ በወቅቱ ከሃገራችን ሄደው ትግሉን ካደራጁት ሰዎች አንዱ የነበሩትን ፕሮፌሰር እንድርያስን ጠይቃቸው።
ማርቲን በጥበብና በአካታችነት በሄደበት መንገድ ጫፍ ባርባ አመቱ ዋዜማ የጄምስ ሬይ ጥይት ገሎታል።ከእውነትና ፍትህ የወገነው ትግል ግን የኋላ ኋላ ሌላውን ጥቁር ሰው ባራክ ኦባማን በዋይት ሃውስ ወምበር ላይ አስቀምጧል።ኦባማ ሉተርን <ኤ ፐርማነንት ኢንስፓይሬሽን> ብሎ ሲያሞግሰው ከሰማህ ስኬቱ የማን መራር ትግል ፍሬ መሆኑን ስለሚያውቅ እንደሆነ ይግባህ።
ማርቲን በትግሉ ውስጥ ፍቅር ፍትህና አንድነት ዘራ።የልጅ ልጆቹ ሃገርን ለመምራት ክብር ሲበቁ፣የገዳዮቹ ትውልዶች የሟችን ዘር በፈቃዳቸው በዋይት ሃውስ ሾመው የአያቶቻቸውን ሃጥያት አስተሰረዩላቸው።የፍቅርና ይቅርታ መንገድ ትውልድ ስህተቱን እሚያክምበትን በር ይከፍታል።ሉተር በገንዛ እራሱ ላይ በደረሰበት መከራ ምሬት ዘመኑን በሚጋሩ ግፈኞች ላይ ቂምን ሳይተው አለፈ።የዛሬ ያገራቸን ሰው መቶ አመት ያለፈው የጥላቻ ድርሳን ደርሶ፣ከመቶ አመት በኋላ የመጣ ትውልድን ሃጥያት አሸክሞ፣ለቀጣይ መቶ አመት እሚተርፍ ጥላቻ ይዘራል። ካባቶቹ እማይሻል ትውልድ ባይፈጠርስ?
እንደ ታላቅ መሪ ከሚታዩ የዘመናችን ዘውጌ የተቃውሞ ሃይሎች የኋላ ኪስ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ በሰዎች ህሊና ውስጥ ይኖራሉ ብላችሁ እማትገምቱት ብዙ ህመምተኛ ሃሳብ አለ።እርቅና በቀልን ከዘመረው ከነ ማንዴላ እና ሙጋቤ ትግልና ካመጣው ውጤት ጥቂት እንኳን እማይማር ሰው ፖለቲካህን ከመራው ሰው እንዳይወጣበት በተረገመ አገር ስለመኖርህ መጠርጠር አለብህ።
እርቀኛው ጥቁር ሰው በይቅርታና ምህርት ፖለቲካ መሪ በምርጫ እሚቀየርበት፣አህጉሯን በኢኮኖሚ እምትመራ አገርን ለልጆቹ አወረሰ።ዛሬም ድረስ ካልዳኑ ቁስሎቿ ጋርም ሆና ቢሆን ጆ በርግ አቀበቱን በፍትህና ዲሞክራሲ እምትሻገር አገር ነች።ዛሬ ላይ እነ ትራምፕ <የዝንጀሮ አህጉር> እያሉ እንዲጠሩን የዝንጀሮን ስርኣት በገነቡት በነሙጋቤ አገር የሆነውን ያየነው ነው።
ባገራችን ሰማይ ስር ግን አገሩን ሁሉ ያንተ እናርገው ስትለው ከፊኒፊኔ ሊያስወጣህ ቀን ለሚጠብቅ <ፖለቲከኛ> ዛሬም ይጨበጨባል።አንተ ግን ከጋራህ የሰፋ ሙሉ ሜዳ ሸሽቶ ኩሽናው ውስጥ እንዳትመጣ የሚያደርግ ስርኣትን ለማንበር <በሚታገል> <መሪ> እንዴት ያለ ተስፋ ያድርብሃል?እኩል እያዋጣህ አብረህ በምትኖርባት አገር ዋና ከተማ እሱ በሚናገረው ቋንቋ መሲህነት አዱኛና በረከቱ ለኔና ዘምዶቼ ይቅደም እሚል <አፓርታይድ አሳቢ> ዘመንህን ሲጋራው እንዴት አታዝን!
ከሰዎቹ የኋላ ኪስ እንደምን ያለ <ሸሌ ካርታ> እንደተያዘ ሳያስቡት ጎንበስ ባሉበት አጋጣሚ ሁሉ አይተናል።ከኔ ዘር ወዲያ ላሳር ባዮቹ ዘውጌዎች <ፖቴንሻሊ> የዚች መከረኛ አገር ተረኛ መቅሰፍቶች ናቸው።ያገሬ ሰው ካገሩ ወጥቶ በሰው ሃገር ከሰው ሁሉ እኩል ሆኖ በሚኖርበት ስልጡን ጊዜ አግላይ ዘውጌነት ከ<አቡሃይ ፈሴ> ያጠረ ድኩም ሃሳብ ነው።ሰዎቻችን ሺህ አመታትን ሲወድቅ ሲነሳ፣ሲለማ ሲጠፋ ከኖረው የአለም ታሪክ ላይ ሠይፍ ባነሳ ላይ ይፍጠንም ይዘግይ ሠይፍ ሳይነሳ እንደማይቀር ቢረዱት አስተዋዮች እንላቸዋለን።ግራውን ሲመቱት ቀኙን እሚሰጥ የዋህ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ ብቻ ነው ያለው።ዘውጌ ብለህ ሰይፍ ስትመዝ ሌላ ዘውጌ የኔስ ዘውግ ብሎ ጦር ይመዝብሃል።በሰፈሩት ቁና መሰፈር ጊዜ አይሽሬ የዚህ አለም አይቀሬ ህግ ነው።መስታወት ቤት ውስጥ እሚኖሩ ወንድማማቾች እንደ ሞኝ ድንጋይ እንደማይወራወሩ እሚነግረን የዛሬው ሰዋችን ማርቲን ሉተር ነው።
“We must learn to live together as brothers or perish together as fools.” እያለ!
በተረፈ ዛሬ በምትዘራው ጥላቻ አጨብጫቢው እሚከብህ፣ቂምን በሚያተርፉ የነገ ልጆችህ እምባ አናት ላይ ነው።ሩቅ አይተህ ቂምን ሽረህ የተሻለ ነገን እማታወርስ ፖለቲከኛ ካደባባይ ገለል በል።አልያም በፍትህ ድንኳን ስር አብሮ ከመኖር ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው በሚገባው የነገ ትውልድ ስምህ ሲረክስ ይኖራል።የተሻለ ተስፈኛ አየር መንፈሱ ደሞ አይቀሬ ነው።ምንም ቢዘገይ ትውልድ እየተማረ መሄዱ አይቀሬ ነዋ።አሸናፊው ማን እንደሆነ ደግሞ እንግሊዛውያንን ጠይቃቸው።<<መጨረሻ ላይ የሳቀው>> እንደሆነ ፈገግ ብለው ይነግሩሃል።
በል ሰላም ሰንብት!
Filed in: Amharic