ኢትዮጵያም እንዳትፈርስ አማራም እንደይጠፋ ከተፈለገ ሁሉም ወገን መራራውን እንክብል ለመዋጥ መዘጋጀት አለበት!!!
ይህንን አጭር አስተያየት እንድሰጥ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉ አማራዎች ብዙ ህይወትና ንብረት ከወደመ በሁዋል ወደ መጡበት ቦታ እንደሚመለሱና ቤትም እንደሚሰራላቸው የሚገልፅ ዜና በመስማቴ ነው። ይህ ተግባር አንድን ነገር በተመሳሳይ መንገድ በተደጋጋሚ እየሰሩ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው የሚለውን አባባል ያስታውሰኛል።
ይህንን ሃሳቤን ብዙ ሰዎች እንደማይወዱትና እስከዛሬ እያስታመምን የተሸከምናቸውን ወደ መፍትሄ የማይወስዱ ሃሳቦችን እንደመጋፋት አድርገው እንደሚወስዱት እገምታለሁ። ነገር ግን መፍትሔ የማያመጣን ሃሳብ በሽፍንፍን ተሸክሞ ከመኖር ይልቅ መራራውን ሃቅ ተጋፍጦ መፍትሄ ወደሚያመጣ ሃሳብ መግባት አለብን የሚል እምነት አለኝ።
እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በአማራ ሕዝብ ላይ ህገ መንግስታዊ ሽፋን አግኝቶ “የነበረውን የተዛባ ግንኙነት ለማረም” በሚል እየተፈፀመ ያለውን ግፍ ከብዙ በጥቂቱ ለመጥቀስ፦
፨ በጋምቤላ ደገኞች በሚል በመንግስት ባልሥልጣናት በተሰጠ ትዕዛዝ ሲገደሉና ሲፈናቀሉ፣
፨ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ቦታዎችና በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገደሉ ሲሳደዱና በግፍ ስለተገደሉት ሰዎች ማንም ተጠያቂ ሳይሆን እንደመፍትሔ በህይወት ለተረፉት ስለወደመባቸው ንብረት ምንም ሳይባል ቤት ተሰርቶላችኋል ተመልሳችሁ ግቡ እየተባለ፤
፨ በደበብ በመንግስት ባለሥልጣን በተሰጠ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሲገደሉና ሲፈናቀሉ፣
፨ በቤኔሻንጉል ሰሞኑን ከተፈናቀሉት በተጨማሪ በተመሳሳይ መንገድ የመንግሥት አካላት በሚሰጡት ትዕዛዝ አማራዎች ሲገደሉ ንብረታቸው ሲወድምና ሲሳደዱ ማየት የተለመደ ተግባር ነው።
ይህ በአማራ ህዝብ ላይ የተፈፀመው ግፍ በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ምደባ መስፈርት መሰረት በGenocide, Ethinic Cleansing, Crime against Humanity or Act of Fascisim የትኛው ላይ እንደሚያርፍ እርግጠኛ መሆን ባልችልም በእኔ እይታ ግን Genocide በሚለው የወንጀል ምድብ ውስጥ ያርፋል ብዬ አምናለሁ።
እንዲህ ዓይነት ወንጀል የተፈፀመበት ሕዝብ ደግሞ ይዋል ይደር እንጅ ራሱን ወደመከላከል እርምጃ መሄዱ የማይቀር የተፈጥሮ ግዴታ በመሆኑ ዛሬ አንድ ወገን ሲያጠቃ ሌላኛው ወገን ተመጣጣኝ እርምጃ ባለመውሰዱ ሥርዓቱ የቆመና የሚሰራ ሊያስመስለው ይችላል። ነገር ግን ከላይ እንደገለፅኩት የተገፋ መገፋትን ለዘለዓለሙ ሊሸክም ስለማይችል ይህን ስርዓት የቆመ ያስመሰለው ነገር ሁሉ የተገፋው ወገን ተፈጥሮዊ የመከላከል መብቱን መጠቀም ሲጀምር እየፈራረሰ መሄዱ አይቀርም።
ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ አንዱን ጭቁዋኝ ሌላውን ተጨቁዋኝ የሚያደርግ ህገ መንግስት ይዛ መቀጠል እንደማትችል ከበቂ በላይ የሆኑ ግልፅ ማሳያዎች አሉ። ከላይ በአማራ ህዝብ ላይ ህገ መንግስታዊ ሽፋን ተሰጥቶት ከሚፈፀመው ግፍ በተጨማሪ የጎሳ አስተዳደሩ የወለዳቸው አስተሳሰቦች በአፋርና በኢሳ፣ በጌዲዮና በጉጅ ኦሮሞ ፣በሶማሌና በኦሮሞ መካከል በተፈጠረ ግጭትና በኮንሶና በቁጫ የራስ አስተዳደር ጥያቄ ምክንያት የጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት ውድመት የችግሩን አሳሳቢነት ግልፅ ማሳያዎች ናቸው። በመሆኑም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ሁለት ግልፅ ያሉ አማራጮች ፊት ለፊታችን ተደቅነዋል። አንደኛውና ጠቃሚው አማራጭ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዜግነታቸው የሚኮሩበትና በየትኛውም አካባቢ አንዱ መጤ ሌላው ባላገር የማይሆንበት በዜግነት ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስት መመስረት ነው። ሁለተኛው አማራጭ አሁን ያለው ህገ መንግስት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚያመቻች በመሆኑና ምልክቶችም በግልፅ እየታዩ ስለሆነ ከኢትዮጵያ መፍረስ የሚጠቀም አለ ብየ ባላምንም እውነታውን መሸሽ ስለማይቻል በመከፋፈሉና በመበታተኑ ሂደት ብዙ ደም መፋሰስ ሳያስከትል መለያየቱን መፈፀም የሚያስችል ዘዴ ፈልጎ ሁሉም ድርሻ ድርሻውን ይዞ ፍችው በጊዜ እንዲፈፀም የሚቻለውን ማድረግ ነው። ከእነዚህ ውጭ ሌላ ምርጫ ያለ አይመስለኝም። የኢትዮጵያ መፍረስ የሚያሳስበን ሁሉ ይህ ‘ሌላው ለማስደሰት ከአማራ ቀንስ የሚለው ሂሳብ አወራራጅና ከፋፋይ’ ህገ መንግስት በመሰረቱ እንዲቀየርና በዜግነት ላይ በተመሰረተ ህገ መንግስት እንዲተካ ትግላችንን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሔ ነው።