>

"በሞት ሸለቆ ሳይታለፍ ታሪክ መቀየር አይቻልም" [ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጎንደር ላይ ያደረው  ሙሉ ንግግር]

     እዚህ የተሰበሰባችሁ ታላላቆቹም፣ ታናናሾቹም በመጀመሪያ እንኳን ለዚህ ዕለት አበቃችሁ፤ አበቃን፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት አስርታት የወልቃይትን ሕዝብ የማንነት፣ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲ እና የፖለቲካ ጥያቄ አደባባይ እንዲወጣ በተወለዳችሁበት አፈር ላይ ተተክላችሁ ለከፈላችሁት ውድ ዋጋ ጥልቅ አክብሮቴን ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላም ለሚመጡት ተጋፋጮች እናንተ መልካም ምሳ ናችሁ እና፡፡ እንደ ጋሽ ሲሳይ ታከለ እና ጎቤ መልኬ (ዋዋ) የመሳሰሉ ሰማዕታትን ታሪክ ለዝንተ ዓለም እንደሚዘክራችው አምናለሁ፡፡ በተጨማሪም፤ የጎንደር እናቶች የደርግ የቀይ ሽብር ጭፍጨፋ ያሳረፈባቸው መጥፎ ጠባሳ ሳይበግራቸው፤ ከአርባ ዓመታት በኋላ በጃን ተከል ዋርካ ሥር የተሰባሰቡ የሕዝባዊ እምቢተኝነት አራማጆችን፣ የውሃ ጥም ለማርካት ከእንስራዎቻቸው ቀድተው በማጠጣት አጋርነታቸውን ያስመሰከሩበትን ላቅ ያለ አብርክቶ እስር ቤት ሆኜ ስሰማ ያሳደረብኝን ሐሴት ቃላት አይገልጸውም፡፡ በትግሉ ተዋፅዎም የሴቶች ተሳትፎ አናሳ በሆነበት አውድ የእነዚህ እናቶችና በዕድሜ አቻዎቿ ዓርአያ መሆን የቻለችው ንግሥት ይርጋ ጀግንነትም ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው አይካድም፡፡ ጎንደርም ከመካከለኛው ዘመን የስልጣኔ እምብርትነት በዘለለ፣ የ21ኛው ክፍለ-ዘመን የፀረ-ጭቆና ብርሃን ፈልቃቂ ከተማ የመሆኗን ጉዳይ ባለፉት ሁለት ኣመታት ያየነው ሐቅ ይመሰክራል፡፡ በዚህ አጀንዳ ላይ ያለኝን አጭር አስተያየት ከማቅረቤ በፊት፤ ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ባለፉት አርባ ዓመታት በግፈኛው ሥርዓቶች ሕይወታቸው ላለፈ ወገኖቻችን የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንድናደርግ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡ …..አመሰግናለሁ፡፡
     ዛሬ በመላ ሀገሪቱ ለተከሰቱና ለመከሰትም እያንዣበቡ ላሉ ምስቅልቅሎሽና ግጭቶች አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ከደደቢት የተነሳው ዘውገኛ ብረት-ነካሽ የጠዋት ማንፌስቶ በግላጭ እንደሚነግረን “ነጻ የትግራይ ሪፐብሊክ”ን በመመስረት ቅዠት መለከፉን ነው፡፡ ግና፤ በወቅቱ ቅዠቱን ለማስፈጸም የሚችልባቸው “ደጋፊ-አቃፊ ሁኔታዎች” ስላልተሟሉ፣ ስልታዊ የአቋም ለውጥ አድርጎ፣ የትግሉን አጀንዳ በ“ብሔር-ጭቆና” ስም በመጥለፍ አያሌ ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ለምዕራባውያንና ለአረብ ሀገራት ጭምር በመስዋዕትነት አቅርቦ ለስልጣን በቅቷል፡፡ ወያኔ የነጻ መንግስት ጥያቄውን ለጊዜው መሳቢያ ውስጥ ቢከተውም፤ ለግንጠላ ያዘጋጀውን የበረሃ ካርታ ግን ከመተግበር ያገደው አንዳችም ኃይል አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት፣ ከጎንደር እና ከወሎ ግዛቶች የተነጠቁ በርካታ መሬቶችን “እወክለዋለሁ” ለሚለው ማሕበረ-ሰብ እንደ አንባሻ ሸንሽኖ ማከፋፈሉን ሁላችንም የምናውቀው ሐቅ ነው፡፡
  የሆነው ሆኖ፤ በሽፍታ-መራሹ ስብስብ የተጫረው “ወያኔያዊ አብዮት” ሁለት-ግቦችን በአምድነት የተሸከመ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ፤ ግዛት ማስፋፋትን ታሳቢ አድርጎ ባካሄደው ስር-ነቀል አብዮት የትግራይን ወሰን ተሻግሮ በጠብ-መንጃ ወርሮ በያዛቸው ግዛቶች ነባሩን ማሕበራዊ መዋቅር አፈራርሶ በአዲስ ተክቷል፤ የማሕበረሰቡን ርዕዮተ-ዓለማዊ ምልከታንም በአይነቱ አዲስ በሆነ ገዥ-ሃሳብ ቀይሯል፡፡ ሌሎች ስር-ነቀል እርምጃዎችንም ወስዷል፡፡ እነሆም በዚህ መልኩ ወደ መሬት ያወረደውን ደም-የጠገበ ፖሊሲን ነው የ“ታሪክ ማስረጃ” እያለ ረበ-የለሽ ሙግት አንስቶ የሚያነታርከን፡፡
   የሶሻል ሳይንስ ምሁራን ትንታኔ እንደሚያፍታታው “የዛሬ ፖለቲካ የነገ ታሪክ ነው”፡፡ በዚህ ሥነ-አመክንዮ መሰረትም፣ ትላንት የተጭበረበረ ፖለቲካ፣ ዛሬ ወደ ታሪክነት ሲቀየር የተጭበረበረ ከመሆን የሚያነጻው አንዳችም ተአምር አለመኖሩን እንረዳለን፡፡ ነገር ግን አበው “የሌባ አይነ ደረቅ…” እንዲሉ፤ ወያኔና የጥቅም ተጋሪዎቹ ይህንን የትላንት ብላሽ ፖለቲካ የአባቶቻቸው እውነተኛ ታሪክ አድርገው ከመውሠዳቸውም ባለፈ አካባቢው “የትግራይ ማህበረሰብ ይዞታ ነው” ለሚሉት ሙግት በማስረጃነት በማቅረብ እኛም አምነነን እንድንቀበል ለመጋት ሲዳዳቸው በትዝብት እየተመለከትን ነው፡፡  መላው ኢትዮጵዊ እውነቱን እንዳያውቅ የወያኔ ግርዶሽ የጨለማ ምርጊት ሆኖበታል፡፡ የመቀሌን ዩንቨርሲቲን የመሰለ ወገንተኛ ተቋምን አሁንም “የሸዋ የበላይነት ሊመጣ ነው” የሚሉ ትርኪሚርኪ ጥናቶችን (ምሁራን ) እያዘጋጀ ህዝባዊ ትግሉን ለማደናቀፍ እየሞከረ ነው፡፡ እዚህ ጋር መዘንጋት የሌለበት ቁምነገር የወልቃይትና አዋሳኝ መሬቶች በድህረ የካቲት አብዮት ለተነሱ የሽምቅ ተዋጊዎች ሁሉ ዋነኛ መፋለሚ መድረክ ሆኖ በመቆየቱ መረጃዎች በቃጠሎ፣ በዘረፋ በመበላሸት እና በመሳሰሉት መንገዶች የመጥፋት እድላቸው ሰፊ መሆኑን ለመገንዘብ የጥናት ሪፖርት መጠበቅ አያሻንም፡፡
   ስለዚህም በዘመናዊ ዓለም መሠል ግጭቶች በሚፈታበት ህዝበ ውሳኔ (የሪፈረንደም ጽንሰ ሀሳብ) የወልቃይትም ጉዳይ እንዲበየንበት መገፋፋት ካስነዋሪ የሕወሓት ቧልትነት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡
   ምናልባትም በጠመንጃ ክምችት እና በሰራዊት ብዛት የትኛውንም ህጋዊ ጥያቄ እየደፈቅን ለዘላቂው እንቆያለን የሚል መታበይ ከተጣባቸውም የታሪክ ድርሳናትን ጠንቅቀው እንዲያነቡ እንመክራለን፡፡ “ዓለምን ከእግሯ ጫማ በታች አሳድራታለሁ” እያለ መቄዶኒያን በሽለላ ሲያርዳት የነበረው ታላቁ እስክንድርም ወድቋል፡፡ ለጀግንነቱም ሆነ ለብልህነቱ ወደር ያልተገኘለት ናፖሊዮን ቦናፓርትም ተሸንፏል፡፡ አውሮፓን በብረት መዳፉ የጨበጠው አዶልፍ ሂትለርም የማታ ማታ የውርደትን ጽዋ ተጎንጭቷል፡፡ ክንደ ብርቱው መንግስቱ ኃይለማርያም ለአሳፋሪ ስደት ተዳርጓል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለውም የወያኔ መዘባበትና ዕብሪትም ከዚህ የተለየ ዕጣ ፈንታ ሊገጥመው አይችልም፡፡
   የወያኔ ሁለተኛው አብዮት ዕቅድ መዳረሻውን ምኒልክ ቤተመንግስት በማድረግ በተቀረው የሀገሪቱ አካባቢ የአዛዥ ናዛዥ ሚና እንዲኖረው  የሚያስችሉትን ሁለት መላዎችን ዘይዶ ያስፈፀመበትን እናገኛለን፡፡ የመጀመሪያው በመናኛ ሀሳብ ቡትቶ ፌዴራሊዝም ማንበር ሲሆን፤ ሁለተናው ደግሞ በሁሉም ክልሎች የአሻንጉሊት አስተዳደር መመስረትን ግቡ ያደረገ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉም ተሳክቶለታል፡፡ ቢሮክራሲውን፣ ኢኮኖሚውን፣ ሠራዊቱን፣ ደህንነቱን በስግብግብነትና በዓይን አውጣነት ጠቅልሎ ይዟል፤ ይህን ዕኩይ ሴራ ለማስፈፀምም መደላድል ይሆናሉ ተብለው ከተዋቀሩት ድርጅቶች መካከልም ብአዴን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ አብዛኛው የድርጅቱ አመራርም ከኤርትራና ትግራይ ቤተሰብ የተገኘ ቢሆንም የጎጃሜውን ገብሩ አስራትና የወለየውን ሳዕረ መኮንንን ፈለግ በመከተል ለወጣበት ማህበረሰብ ከመታመን ይልቅ ለደደቢት ፍሬዎች በመንገድ መሪነት አገልግሏል፡፡ እያገለገለም ነው፡፡ በወረራ የተያዙትን መሬቶች ጥንትም የትግራይ ለመሆናቸው ለሚቀርቡት የኑፋቄ ሐቲት በደቀ መዛሙርትነትም ተሰልፎ በሰሚ አልባ ጩኸት አደንቁሮናል፡፡ በግብረ-አበርነት በመሳተፍም የወልቃይትና የአካባቢው ነባሩ ማህበረሰብ የጅምላ ፍጅትና ሰንፋጭ ጭቆና እንዲፈፀምበት አድርጓል፡፡
  ለዚህም ነው ብአዴን በትጉሀን የህዝብ ልጆች ቁጥጥር ስር መዋል የምንለው፡፡ በነገራችን ላይ ዘግናኙ ጭፍጨፋ ልባችንን በሀዘን ቢሰብረውም ደመ ቁጡ ወጣቶች ትግሉን እንዲቀላቀሉ ገፊ ምክንያት በመሆኑ ደግሞ እንፅናናለን፡፡ ከሞላ ጎደልም እንደ ተድላ ባይሩ እና ዋቆ ቡቱ ሁሉ እነ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዴ፣ አታላይ ዛፌ፣ መብራቱ ጌታሁን እና መሰል ብርቱ ጓዶችን እየፈጠረ እንደሆነ በዓይናችን ተመልክተናል፡፡ እናንተ ዐውደ ብርሀንን የተጎናፀፋችሁ ጀግኖችን በጨለማው ላይ እንደምትሰለጥኑም አምናለሁ፡፡ በአናቱም በወልቃይት ጉዳይ እናንተ የመጨረሻዎቹታጋዮች ትሆኑ ዘንድ የፍትህና ዴሞክራሲ ወገን ሁሉ ከጎናችሁ እንዲቆም መወትወት አለባችሁ፡፡
   በጥቅሉ የወያኔና ደጋፊዎቹ ማንአህሎኝነት፣ መዘባነን፣ የፖለቲካ መሰሪነትን በጥልቅ ሀዘን ስናስተውል ኧረ ለመሆኑ በወልቃይት ጥያቄ ላይ ጉጅሌው ቡድን እንዲህ እንዲሳለቅ “ሊቼንሳ” የሰጠው ማነው? ስንል እንጠይቃለን፡፡ እዘህ ጋ ሳልጠቅስ የማላልፈው ከቀይ ሽብርም የከፋ ግፍ በአካባቢው ተወላጆች ላይ መፈፀሙ የማይስተባበል ዕውነታ ነው፡፡ በደርጉ ቀይ ሽብር ዘመን የጥቃት ዒላማ የፖለቲካ አቋምን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን የወልቃይት ግን ማንነትን ተንተርሶ የተፈፀመ የዘር ማፅዳት ወንጀል ነው፡፡
   በመጪዎቹ ጥቂት ወራትም ይህንን ጉዳይ በሠላማዊ መንገድ፣ በህጋዊ እና በቅንነት መፍታቱ በዜጎች ማህበራዊ ግንኙነትም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሊከሰት የሚችለውን ጽንፈኝነትና በጦር ሜዳ መሸናነፍ ላይ ማዘንበልን ይታደጋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ሂደቱ ያለ ግጭት እንዲያልቅ ሁሉም ኢትዮጵዊ ለማፍያውና አፋኙ ህወሃት የጎን ውጋት መሆን እንዳለበት ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ጊዜው የህግ እንጂ የውንብድና መሆኑ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት፡፡ በተቀረ ጥያቄውን በተለመደው መንገድ እወጣዋለሁ የሚለው ሕወሓታዊው ዕብሪት ለሕንድ እና ለፓኪስታን ዛሬም ድረስ እራስ ምታት የሆነችውን “የካሽሚር ግዛት” ክሰት እንዳደረገው ሁሉ፤ እዚሁ ዓይናችን “ጥቁሯን ካሽሚር” ማዋለዱ አይቀሬ መሆኑን ለመናገር የነብይነት ፀጋን አይጠይቅም፡፡ “ጭቆና ቀቢፀ ተስፋን ያስፋፋል” የሚሉ ጸሐፍትን ከግዙፉ የዓመድ ክምር ስር ፍም-ረመጥ የሚፈለቅቅ ሞት አይፈሬ ትውልድ ለመምጣቱ ምልክቶቹን እንዲያስተውሉ እመክራለሁ፡፡
      እናም በዋናነት ትግርኛ ተናጋሪውን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከግፉአን ጎን መቆም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተን እንናገራለን፡፡ ይህንን ጥያቄ ወደ አደባባይ ማምጣቱ የማህበረሰብን ሀልውና ያናጋል የሚለው ሙግትም ጊዜ ያለፈበት መድሀኒት ነው፤ የሚገድል እንጂ የማያሽር፡፡  የተማረው መደብም ምሁራዊ አይናፋርነቱን ገትቶ የመፍትሔ ሀሳቦችን ሊጠቁሙ የሚችሉ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚኖርበት እናሳስባለን፡፡ ልሂቃኑም የሕሊና ፍርድ ሊሰጡ ግድ ይላቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ብአዴን የተባለው የክልሉ አስተዳዳሪ “መልከ ሕወሓት” ጭምብሉን አውልቆ በመጣል የጥያቄው ባለቤት ሊሆን እንደሚገባው ነጋሪ መፈለግ የለበትም እንላለን፡፡
     በግልባጩ እንደ ከዚህ ቀደሙ በወያኔ ጥላ ስር እዝናናለሁ የሚል ከሆነ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፊል ክልሉን የነቀነቀው ህዝባዊ ቁጣ ክሽፈቱን አርሞ፣ ኃይሉን በብዙ እጥፍ አግዝፎ እየመጣ ነውና አንገቱን ለጊሎትን ማሽን ከማዘጋጀት ውጭ አማራጭ እንደማይኖረው ከወዲሁ አምኖ መቀበል አለበት፡፡   ስለሚን ቢሉ በእንዲህ አይነቱ የህዝብ ፍርድ የዘረፋና የጭቆና ሀሳብ አመንጪው ህወሃት ብቻ ሳይሆን፤ ተባባሪው ብአዴንም ከታዳኝነት አያመልጥምና ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ኦህዴድ ጓዶቹ የራሱን ህዝብ በምርኩዝነት ተጠቅሞ ጥያቄውን ከማስፈፀም ባሻገር ቅጥ ያጣውን አፈና፣ እስር፣ ግድያ፣ መሬትን ጨምሮ ሁለንተናዊ ንብረት ነጠቃን የማስቆም ሽራፊ ወኔ ካለው ያን ያህል አዳጋች እንደማይሆንበት የማህበረሰቡን መነቃቃት ጠቅሰን እናስገነዝባለን፡፡ በአናቱ የጭቆናውን ቀንበር የማላላት፣ የብዝበዛውን ሸክም የማቅለል፣ ፖለቲካዊ ኃላፊነቶቹን መዘንጋት የለበትም፡፡ ከዚህ በኋላ በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ መሞት-ካለመሞት፤ መታሰር-ካለመታሰር የሚኖርበት ግብር ሰብሳቢው፣ ሀብት አስተዳዳሪው፣ በስልጣን ተምነሽናሺው… ብአዴን ብቻ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡ ይህን ቃል ለዓመታት ብየዋለሁ፤ ዛሬም እናንተ ፊት ዕደግመዋለሁ፡-  በሞት ሸለቆ ሳይታለፍ ታሪክ መቀየር አይቻልም!!!

   ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic