>

አምስት የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጡረታ እንዲያርፉ ተደረገ - የጠ/ምኒስትር ጽ/ቤት

ባሕርዳር፡ግንቦት 7 /2010 ዓ/ም(አብመድ) አገራችን እያካሄደች ያለችው ሪፎርም የተሳካ እንዲሆን የማድረጉ ሥራ እንዲሁም ለሕዝቡ የልማትና ለውጥ ፍላጎት ተገቢ ምላሽ የመስጠቱ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያግዙ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እያካሄዱት ያለው የካቢኔ ለውጥ ይገኝበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በአዳዲስ ኃላፊዎች እንዲመሩ በማድረግ ላይም ይገኛሉ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም በጡረታ እንዲያርፉ እየተደረገ ነው፡፡
በዚህም መሰረት በጡረታ እንዲያርፉ የተደረጉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ክቡር አቶ ስብሐት ነጋ/አቦይ ስብሐት/፣ ክቡር ዶ/ር ካሱ እላላ ከፖለሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል፣ ክቡር አቶ በለጠ ታፈረ ከተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም፣ ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት ፕሮጀክት፣ ክቡር አቶ ታደሰ ኃይሌ ከንግድና ኢንዱስትሪ የፖሊሲ ዕቅድ አፈጻጸምና ክትትል፣ እና ክቡር አቶ መኮንን ማን ያዘዋል ከፖሊሲ ምርምር ማዕከል ሲሆኑ በቀጣይም ረዥም ጊዜ በመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ እንዲያርፉ የማድረጉ ሥራ ይቀጥላል፡፡
 የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት
Filed in: Amharic