>

የጋሼ ሌንጮ ነገር (ፋሲል የኔ አለም)

 ኦዴግ ከአርበኞች ግንቦት7 ጋር ጥምረት ፈጠረ። ከዚያም ተፋታና ከሌላው ጋር መወዳጀትን መረጠ። በፖለቲካ ታሪክ ካየነው የኦዴግ ውሳኔ አስገራሚ አይደለም። ጋብቻ፣ ፍች ወይም አብሮ መኖር በፖለቲካ ውስጥ የነበረ፣ ያለና የሚኖር   ነው። ምናልባት በኦዴግ ዜና የተገረሙ ሰዎች ካሉ፣ በፖለቲካ ውስጥ አስገራሚ የሚባል ነገር እንደሌለ የዘነጉ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።  ፖለቲካ “ ጥቅምን አስልቶ የሚደረግ ጨዋታ” ነው። ጥቅሙ ለግል ወይም ለብዙሃኑ ሊሆነ ይችላል። በዚህ መነጽር ካየነው  የኦዴግ አገር ቤት መግባትም አስገራሚ ዜና ሊሆን አይችልም። ኦዴግ በውሳኔው ስላገኘው ትርፍና ኪሳራ ራሳቸው መሪዎቹ እንዲያሰሉት ልተወውና ምን ይጎዳል በሚለው ላይ አንድ ነገር ልበል።
አሜሪካ ሰሞኑን ከኢራን ጋር የነበራትን ስምምነት በመጣሷ “ከሃዲ” ተብላለች።  በሃቅ እንፍረድ ከተባለ ከአሜሪካ ይልቅ ኢራን  ለቃሏ ታማኝ ሆና ተገኝታለች።  አሜሪካ እምነት (ማተብ) የሚባለውን ነገር አጥታለች። ፖለቲካ የጥቅም ጨዋታ ቢሆንም፣ ተዓማኒነት( trustworthiness) ጥቅምን በዘላቂነት ለማስከበር ወሳኝ ነው። ኦዴግም እንደ  አሜሪካ  ተዓማኒነቱን አጥቷል። ኢህአዴግም ሆኑ ተቃዋሚዎች ሌንጮን  አምነው አብረው ለመስራት መቻላቸውን እጠራጠራለሁ። በእኛ አገር ፖለቲካ ለቃልህ ታማኝ ሆነህ ካልተገኘህ  አለቀልህ። የእኛ ሰው ባለማተብ ነው፤  ፖለቲካውም ላይ ያሰርከው ማተብ እንዳልተበጠሰ ማየት ይፈልጋል።
 አርበኞች ግንቦት7 ኦዴግን አስጠግቶ እንስራ በማለቱ ምን አገኘ? ምንስ ተጎዳ? እሱን ለድርጅቱ አመራሮች ልተወውና ትረፉ ላይ አንድ ነገር ልበል። አርበኞች ግንቦት7 እንደ ኦዴግ አይነቶችን እምነት የማይጣልባቸውን ድርጅቶች እንኳ ለአገር አንድነት ሲባል  አቅፎ ለመጓዝ የማይቸግረው ድርጅት መሆኑን አስመስክሯል። ኦዴግ   ለዲሞክራሲና ለአገር አንድነት የሚታገለውን ድርጅት “አላማህን ወድጀዋለሁና አብሬህ ልስራ” ቢል “ተወዳጁ” ድርጅት “እምቢ” ማለት ይቻለዋል? አይመስለኝም። እንዲህ ካለማ ከራሱ አላማ ጋር ተጋጨ ማለት ነው።  እንዲህ የከረረ አቋም ያላቸውን ድርጅቶች ከማለዘቢያ መንገዶች አንዱ አቅርቦ ማናገር ነው። ዛሬ  ዶ/ር አብይ እየተጠቀመበት ያለው ስልት ማለት ነው።  እኔ የሚኒልክ ስልት እለዋለሁ። የሚፋጁትን እያቀረቡ ማቀዝቀዝ።
 “በአንድ መስመር ተሰልፌአለሁ እና አብሬ ልስራ” ብሎ የመጣውን ድርጅት አግ7 ቶች “ዞር በል”  ቢሉት  ኖሮ፣  ይጠብቃቸው የነበረው ውግዘት ቀላል አይሆንም ነበር። ወያኔም አርበኞች ግንቦት7ትን በዘረኝነት ለመፈረጅ ጥሩ ሰበብ ያገኝ ነበር።  አላማህን ደግፎ የሚመጣውን ሁሉ ወደ  ቤትህ  ልታስገባው ትችላለህ፣ ከሳሎን እንዳያልፍ ማድረግ ግን ያንተ ፋንታ ነው። ። እሱ የሚያየው ቤትህ መግባቱን  እንጅ ሳሎን ውስጥ መቀመጡን አይደለም።  አንተ ሳሎንክን በማሳየትህ ጥሩ ገጽታ ስለምትገነባ ታተርፋለህ እንጅ አትከስርም።  “ለምን ጓዳህን አላሳየኸውም” ብሎ የሚተችህ የለም። ቤትህ ገብቶ ቢጋበዝ እንኳን ወጪው ኢምንት ነው። እሱ ካንተ ቤት ገብቶ ከበላ በሁዋላ ላንተ ጠላት አድሮ አንተን ቢተችህም የከሰረው እሱ እንጅ አንተ አይደለህም።
Filed in: Amharic